Advertisement
….. ታውቃለህ? ቀኑን ሁሉ አስታውሰዋለሁ፡፡ አርብ ለት ከትምህርት ቤት እየወጣን እያለ ከሩቅ “እየሩስ" ብሎ ጠራኝ፡፡ ዘካሪያስ መሆኑን ሳውቅ ገርሞኝ ቆምኩኝ፡፡ ምስኪኑ፣ ከትምህርት ውጪ ምንም የማያውቀው ዘካሪያስ፣ ደሞ ስለ ትምህርት ምን ሊለኝ ነው ብዬ ጠበኩት፡፡ ረዥም ሰዓት አየኝ አየኝና ….. “እየሩሳሌም ምድር ላይ ካሉ ሴቶች በሙሉ አንቺ ቆንጆዋ ሴት ነሽ እጅግ በጣም አፈቅርሻለሁ" አለኝና ዕንባው ዱብ ዱብ አለ፡፡ በወቅቱ ምን እንደተሰማኝ አላውቅም፡፡ ደስታ፣ ሐፍረት፣ ሐሴት፣ መሸማቀቅ .... I don't know ድብልቅልቅ እንዳለብኝ ግን አስታውሳለሁ፡፡
16 አመቴ ነበር፡፡ ዘካሪያስን ግን አመንኩት፡፡ ምድር ላይ ካሉ ሴቶች በሙሉ ቆንጆዋ ሴት ነኝ ብዬ አመንኩ፡፡ ከዛ በኋላ ብዙ ዘካሪያሶች እየመጡ ይሄንኑ እንደሚነግሩኝ ከልቤ ተማመንኩ፡፡ ዘካሪያስን ጀማሪው ብቻ አድርጌ ወሰድኩት፡፡ …… ታውቃለህ?ከዛ በኋላ ድፍን 16 አመት ሆነኝ.... ቆንጆ ነሽም እጅግ በጣም አፈቅርሻለሁ ያለኝም አንድ ሰው የለም፡፡ ያሳፍራል ይሄ? እኔንጃ… ዘካሪያስን ግን ጀማሪም ጨራሽም ይሆናል ብዬ በፍፁም አልገመትኩም ነበር፡፡
.... አንተ አጣበከኝ እኮ… አንተ ልቀቀኝ...
ዘካሪያስ ግን ብዙ ተመላልሶ ቆንጆ መሆኔን ይነግረኝ ነበር፡፡ ምን ያረጋል በሌላ ዘካሪያስ ስላላረጋገጥኩ አላመንኩም፡፡ ልቤ አብዝቶ ሌላ ዘካሪያሶች ይጠብቅ ነበር፡፡ እሱ ግን ሳይሰለች 8 አመት ሙሉ ለምኖኛል፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ምን አለኝ መሰለህ? ... “እየሩስ የምረሳሽ አይመስለኝም፡፡ ከዚ በኋላ ግን ያፍቅረኛል ብለሽ እንዳታስቢ ቆርጦልኛል" .... አሁን ይሄ ምን ማለት ነው? ... አይ ዘኪ…
.... አንተ ጡቴን! ….ያመዋል እንዴ? እንደውም ልቀቀኝ… ፊትህን እያየሁ ነው የማወራው…
ሁለት ልጆች አሉት፡፡ ሳሮን እና ዳዊት ይባላሉ፡፡ አልዋሽህ? .... ሴት ልጁን እየሩሳሌም የሚላት ይመስለኝ ነበር፡፡ ጅል ነኝ ኣ? ሚስቱ ግን ስሟ እየሩሳሌም ነው… ሲሳይ ይሙት! ...
…እቀፈኛ!…
በርግጥ እኔም ዘካሪያስ የሚባል ስም ያስደነግጠኛል፡፡ አንዴ አንድ ታካሚ በድንገተኛ መጥቶ ስሙ ዘካሪያስ መሆኑን ሳውቅ የኔው ዘኪ መስሎኝ ውሃ ሆኜልህ ነበር፡፡ የኔው አልኩ እንዴ? ሃ ሃ .... አልዋሽህ? ቀለል ያለ ህመም ታሞ እኔ ባከምኩት ብዬ ተመኝቼ ሁሉ አውቃለሁ፡፡ እሱ ግን ጉንፋን እንኳ አያውቀውም::
ከአንድም ሁለት ጓደኞቼ ያፈቅሩት ነበር፡፡ አንዷ እንደውም ፈጣጣ ስለነበረች ነግራኛለች፡፡ አንዷን ግን እንዲሁ አውቅባት ነበር፡፡ ሁለቱም እኮ ብዙ አፍቃሪ ነበራቸው፡፡ ግን እንደኔ መፈቀር ይፈልጋሉ፡፡ “የዘካሪያስ አይነት አፍቃሪ…" የሚሉት ነገር ነበራቸው፡፡ ብዙ ሰው የሚያስበው እኔ እሱን የማላፈቅረው አርጎ ነው፡፡ ከሱ ቢብስ እንጂ ፍቅሬ ከሱ አያንስም፡፡ ሲሳይ ይሙት! ... ግን...
.... ኧረ ማኩረፍህ እንዳይሆን ብቻ? ተው ድራማ አትስራ በጣም ነው የማውቅህ እኮ! እንካ እሺ ሳመኝ.. ሃ ሃ ሃ ከምኔው ማኩረፍህ ተረሳ? ድራማ ተው በግልፅነትህ ቀጥል…
አንዴ ለምንድነው እንደሌሎች ጄሪ የማትለኝ ስለው “ጄሪ የአይጥ ስም ነው ደሞ ጄሪ ከእየሩስ ይልቅ ለጄሪካን ይቀርባል" ብሎኝ ሳቀ፡፡ ጥርሱ ሲያምር ቆንጆ እኮ ነው ደግሞ፡፡
8 አመት ሙሉ አልወድህምም እወድሃለሁምም አላልኩትም፡፡ ዝምብዬ ሰምቼ እሸኘዋለሁ፡፡ ውስጤ ሌላ ዘካሪያሶች ይጠብቅ ነበር፡፡ “ምድር ላይ ካሉ ሴቶች በሙሉ አንቺ ቆንጆዋ ሴት ነሽ" እንዲሉኝ እፈልግ ነበር፡፡ ማመን እፈልግ ነበር፡፡ እሱ ግን ያሳዝነኝ ነበር፡፡ አንጀቴን ይበላኝ ነበር፡፡ አለቅስ ነበር ሁሌ… ጎበዝ እንጂ ቆንጆ ያለኝ ከሱ ውጪ ማንም የለም… አለቅስ ነበር...
.... ና በናትህ እንደቅድሙ ጭመቀኝ… አዎ! እንደሱ… ወይኔ እየሩሳሌም…
ላስገርምህ? ሚስቱ ዶክተርም ነች፡፡ ሲሳይ ይሙት! ... አያስቅም ይሄ?
....ጀርባዬን እንዳሁኑ ሳመኝ ....
ለመጀመሪያ ጊዜ ከሴት ጋር ያየሁት ጊዜ እንዴት እንደተቃጠልኩ ብታይ… ልጅቷን ብቦጫጭራት ሁሉ ተመኝቼ ነበር።
.... እንዴ አንተ ቧጨርከኝ እኮ! ...ያመዋል እንዴ? ....
እንዴት ግን 8 አመት ሙሉ እጅግ በጣም አፈቅርሻለሁ ያለ ሰው፤ ያላንቺ ህይወቴ ባዶ ነው፤ ያላንቺ መኖር ትርጉም አይሰጠኝም የሚለኝ ሰው… አልዋሽህ? እኔን ካላገኘ ራሱን ያጠፋ ይሆን እያልኩ ውስጥ ውስጡን ሳስብ፣ ድንገት መጥቶ “… ከዚ በኋላ ግን ያፈቅረኛል ብለሽ እንዳታስቢ" ብሎኝ እልም ይላል፡፡ ይሄ እብደት አይደለም?
... ዙር አትየኝ! እያለቀስኩ መስሎህ ነው ኣ? አይደለም አላለቅስም… ባለቅስም ግን ይገባኛል ግን አላለቅስም…
አንዴ የመጀመሪያ ልጁን ሳሮንን ከወለደ በኋላ ላግኝህ አልኩት፡፡ ለመንኩት፣ ሰገድኩለት ብል ይቀለኛል፡፡ በመጨረሻ ሰው የሚበዛበት ፐብሊክ ቦታ ሊያገኘኝ ተስማማ፡፡ በተፈጥሮው እኮ እንዲህ አይነት ቦታ ይጨነቀዋል፡፡ ብቻውን ሰው የሌለበት ነበር ማግኘት የፈለኩት… ግን ምርጫ አልነበረኝም ተስማማው…
.... ቁጭ ማለትህ ነው… እሺ እንደተመቸህ…
ተገናኝተን ትንሽ ቁጭ እንዳልን ቀጥታ ለምን እንደፈለኩት ጠየቀኝ፡፡ እያመነታው ለምንድነው ቆንጆ ሳልሆን ቆንጆ ነሽ እያልክ የምትሸነግለኝ አልኩት፡፡ ፈገግ አለ፡፡ አሁን ድረስ ፈገግታው አይረሳኝም፡፡ “ችግር እንዳለብሽ አውቅ ነበር" ብሎ ፈገግታውን ቀጠለው፡፡ በጣም ነው የደነገጥኩት፡፡ ብቸኛ ቆንጆ ነሽ የሚለኝ ሰው… ችግር እንዳለብሽ… ሲለኝ እንዴት አልደነግጥ? … አልዋሽህ? ቆንጆ ነሽ ብሎ እንዲያስታውሰኝ ነበር ያገኘሁት፡፡ ቀጠለና ምን አለኝ መሰለህ?…
“ብዙ ጊዜ ሰዎች 'እየሩስ እኮ ጭንቅላቷ ፓፓ ምናምን' ሲሉ ሰቃይ መሆንሽን ብቻ አይተው እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ እኔ ግን ጭንቅላትሽን ማሰቡን እጠራጠራለሁ..." ከመደንገጥ እንዴት ወደ ማልቀስ እንደተሸጋገርኩ አላወኩም፡፡ የቆጡን አወርድ ብላ የበብቷን ጣለች ማለት ይሄኔ ነው፡፡ አስበው እስኪ? እሱ ብቻ ይነግረኛል ብዬ የማስበውን ቁንጅናዬን ለማረጋገጥ መጥቼ፣ ብዙዎች የሚነግሩኝን ጉብዝናዬንም ስቀማ? ዕንባዬን አይቶ ወይ ያባብለኛል ወይ እንውጣ ይለኛል ብዬ ብጠብቅም ምንም አልመሰለውም፡፡ ቀጠለ….
“ይቅርታ ይሄን በማለቴ… ይሄን ማሰብ ካልቻልሽ ጎበዝ ነሽ ብዬ ማሰብ ይከብደኛል፡፡ እየሩሳሌም ሲሳይ በጣም ቆንጆ ነሽ፡፡ እንደውም አሁን ጨምረሻል፡፡ ግን ከትምህትር ውጪ አርቀሽ የማታስቢ ደነዝ ነበርሽ…" ቢሰድበኝም ፈገግታዬ አልቀነሰም ነበር፡፡ የዝናብ ፀሃይ ማለት ነው ፈገግታዬ።
“… ጉብዝናሽ እሾህ አጥርሽ ነበር፡፡ የኔ ጓደኞች እንኳ ከጉብዝናሽ ውጪ ስለ መልክሽ ሁሌ ያወሩ ነበር፡፡ ራሷን ሳትጠብቅ እንዲህ ያማረች ራሷን ብትጠብቅማ ምን ልትሆን ነው ይሉ ሁሉ ነበር፡፡ ግን ሁሉም ሰው እንደሚፈራሽ ይፈሩሽ ነበር፡፡ ሴት ልጅ ጎበዝ ተማሪ ስትሆን ወንዶች ይፈሯታል፡፡ አንቺን ደሞ አስቢው… ያን የሚያካክል ውጤት እያመጣሽ፣ ደብተርሽ ስር ተወሽቀሽ እያደርሽ ማን ደፍሮ ያናግርሽ? አንዴ ጓደኛዬ ብሩክ ምን እንዳለኝ ታውቂያለሽ? … 'ጄሪ ገና ስጠጋት ውስጤ የማስበውን ታውቃለች ብዬ ስለማስብ እንጂ ስለፍቅርህ ጥልቀት አስረዳልህ ነበር' አየሽ እንዴት እንደሚያስቡሽ? ... አንቺ ደሞ ከትምህርት ውጪ ስለማታስቢ ይሄን ይሄን ማሰብ አትችይም…. በራስሽ ስለማትተማመኚና ከትምህትርት ውጪ ምንም የሌለሽ ስለሚመስልሽ ትምህርትሽን ብቻ ሙጥኝ አልሽ፡፡ እሱ ችግር ባይሆንም ሙሉ ሆነሽ ጎዶሎ ሆነሽ ኖርሽ፡፡ ቆንጆስ ባትሆኚ ቆይ ምንድነው ችግሩ? ... "
“... ሌላው ሲበዛ ዝምተኛ ነበርሽ፡፡ እኔ ራሱ ወሬ የለመድኩት ባንቺ ነው፡፡ አንቺ ጋር መጥቼ እኔው አውርቼ እኔው ራሴን አዳምጬው እሄዳለሁ፡፡ እየሩስ ከባድ ችግር ነበረብሽ፡፡ ይኸውልሽ እንዲህ አይነት ቦታ የቀጠርኩሽ ባለትዳር ሆኜ ጉራንጉር ውስጥ ከሴት ጋር መታየት ስለማልፈልግ ነው፡፡ ሚስቴ ብታምነኝም እኔ ግን መታየት አልፈልግም፡፡ (ጄሪን) በጣም ነው የምወዳት፡፡ ብዙ ዋጋ ከፍላልኛለች፡፡ ቅድም ስታለቅሺ ዝም ያልኩሽ የሚጠቅምሽ መስሎኝ ነው፡፡ እውነቱ ይሻልሻል፡፡"
ከዛ በኋላ ዝምብዬ ሳየው ነበር፡፡ ረጅም ጊዜ፡፡ ግራ እንደገባው አይቼ ነበር፡፡ የሞት ሞቴን ... ይሄን ታድያ ለምንድነው ቀድመህ ያልነገርከኝ… አልኩት፡፡ እንደቅድሙ ፈገግ አለ፡፡ ደሞ ሊሰድበኝ ነው ብዬ ፈገግ አልኩ፡፡ ግን አልፈራሁም ነበር።
“እየሩስ ሳትጠይቂኝ የምነግረሽ ፍቅሬን ብቻ ነበር፡፡ ሳትጠይቂኝ ምን ብዬ ልንገርሽ?" ፈገግታው አልጠፋም ነበር፡፡ እኔም ተረጋጋው፡፡ ቆንጆ ነኝ ግን? አልኩት ለመጨረሻ ጊዜ ...
“ሌላ ሰው ቢነግርሽ አይሻልሽም?" አለኝና ሳቀ፡፡
.... ናልኝ ናቲ .... ና በከንፈርህ ንገረኝ ... ና በቃ ከዚ ወዲህ ስለ ዘካሪያስ አልነግርህም .... ና ሳመኝ! ... ና እንደውም እኔ ልሳምህ... ናቲዬ.... ናቲ ....