Advertisement
ንስሮች ልክ አርባ አመት ሲሞላቸው ብዙ ነገራቸው ይጃጃል፡፡ መንቁራቸው ይገረጅፋል፣ ጥፍራቸው በእርጅና ብዛት ይዶለዱማል፣ ክንፎቻቸው እጅግ ወፍረውና ተደራርበው ሸክምም ይሆኑባቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ሁለት ምርጫ አላቸው፡፡ ከነችግራቸው እየኖሩ ሞትን መጠባበቅ አልያም የሚከፈለውን ዋጋ ከፍለው ራሳቸውን ማደስ፡፡ በግል ምርጫቸው ደግሞ ማንም ጣልቃ አይገባም፡፡
እምቢኝ እጅ አልሰጥም፣ እስከ መጨረሻው እታገላለው፣ ታግዬም አሸንፋለው ያለ ንስር እንዲህ ያደርጋል…
በመጀመሪያ ብቻውን የተራራ ጫፍ ላይ ይወጣል፡፡ [ልብ አርጉ የመዳን መጀመሪያ ብቻ መሆን መጀመር ነው] .. ቀጥሎ መንቁሩን ከአለት ጋር አጋጭቶ አሮጌውን ያስወግዳል፡፡ ከዛም ይታገሳል [ጊዜ የማዳኛ የራሱ የሆነ ጊዜ አለው፤ ስለቸኮልንም ምንም የሚሆን ነገር የለም] በምትኩም አዲስ መንቁር ይወጣለታል፡፡
አዲስ ነገር ሁሌም አዲስ ጥቅም አለው፡፡ በአዲሱ መንቁሩ ደግሞ አሮጌውን ጥፍሩን ፈንቅሎ ያስወግዳል፡፡ ከዛም ይታገሳል… በምትኩ አዲስ ይወጥማለታል፡፡
ቀጥሎም በአዲሱ ጥፍሩ ያረጁና የተደራረቡ ክንፎቹን ይነቃቅላል፡፡ ከዛም ይታገሳል… በስተመጨረሻ ዋነኛ መንቀሳቀሻው ክንፉም አዲስ ይሆንለታል፡፡[ ይህ ሁሉ የሚሆነውም የራሱ በሆነ ጊዜ ነው… ስለቸኮለ ልጁ ያለ ጊዜው ጥርስ የሚያወጣለት አባት የለም… ትግስት የመንገዱ አካልም ግዴታም ነው!]
ይህ አስቸጋሪ፣ አስጨናቂ፣ እልህ አስጨራሽ ትግል የሚፈጀው አምስት ወራትን ብቻ ነው፡፡ ሽልማቱ ግን ለቀጣይ 30 አመታት እንደ አዲስ መብረር ነው፡፡ ሽልማቱ ልጅነትን ወጣትነትን መልሶ ማግኘት ነው፡፡ ሽልማቱ ከውድቀት በኋላ መልሰው ሲነሱ የሚጎናፀፉትን፣ወድቀው የማያውቁ ሰዎች ያላጣጣሙትን ደስታ ማጣጣም ነው፡፡ ምክንያቱም ወድቀው የተነሱ የትም የሌለ ጣፋጭ የደስታ ማንፀሪያ አላቸውና!!! ሽልማቱ በየቀኑ ይሄን እያሰቡ ፌሽታ እያረጉ መኖር ነው፡፡
ይሄ ተረትም ሆነ እውነት ብዙዎችን የሚያነሳሳ ታሪክ ነው፡፡ አዎ ብዙዎች ተረትም የተፈጥሮ ነገርም ኢንስፖየር ያደርጋቸዋል፡፡
ዋናው ነገር ለጥቂት ጊዜ ከሰው ተለይቶ ከተራራው ጫፍ ላይ መውጣት ነው፡፡ የውስጥን ድምፅ ማዳመጥ ነው፡፡ መቼም ሁላችንም ካንድ በላይ ያረጁ ነገሮች ታቅፈን የምንኖር ፍጡሮች ነን፡፡ የትኛው መንቁራችን፣ የትኛው ጥፍራችን፣ የትኛው ክንፋችን እንደሆነ መለየት የኛ ፈንታ ነው፡፡ ከዛ የመጀመሪያዋን ከባድ ነገር ማለፍ… ከዛ ሽልማቱ አይነገርም፡፡ ደሞ በህይወት የኛ የሆነ ነገር ሁሉ ይከፈልበታል፡፡ አልጋ በአልጋ የተባለ ነገር ያለው ፍራሽ ተራ ብቻ ነው፡፡ ለፍተው ያገኙትም ዘላቂ ደስታን ይሰጣል።
እንደ ምሳሌ የአንድን ሰው ህይወት እናቅርብ፡፡ ከተራራው ጫፍ ወጣና አሰበ፡፡ መንቁሩን ለየው፣ ጫቱ ነበር፡፡ ከጫቱ ተፋታና ታገሰ፡፡ ከዛም ጥፍሩን አየ፣ መጠጡ ነበር፡፡ በጫት አልባ ህይወቱ መጠጡን መፋታት ብዙም ከባድ አልነበረም፡፡ የመጨረሻውና ክንፉ ሲጋራው ነበር፡፡ በጫትና መጠጥ አልባ ህይወቱ፣ ሲጋራም ብዙም ከባድ አልነበረም፡፡
ሁሉም ግን የራሳቸው ጊዜና የራሳቸው ዘዴ ይፈልጉ ነበር፡፡ ከዛም ድጋሚ ለመብረር ትንሽ መታገስ ነበረበት፡፡ ስድስት ወር አልያም አመት የሚከፈል መስዋትነት ለቀጣይ አያሌ አመታት "እንደ አሞራ ክንፍ አውጥቼ ልብረራ" ብሎ የሚያዘፍን ከሆነ አይቆጠርም፡፡ አንድ አመት ለብዙ አመት ኢምንት ነው፡፡ ግን የመንገዱ መጀመሪያም ነው፣ ተራራውን መውጣት፡፡ አንድ አመትን ለብዙ አመታት መሰዋት፡፡
ቅድሚያ የምንሰጠውን ማወቅ የመንገዱ መጀመሪያ ነው… ሁሉም ነገሮች ከኛ አይበልጡም፡፡ ነገ ይደርሳሉ፡፡ ያውም ከአይናችን ጉድፋችን ወጥቶ አጥርተን በምናይበት ዘመን፣ ዛሬ የምንተዋቸው ነገሮች ነገ ቁጭ ብለው ስለሚጠብቁን፣ ነገ በብዙ ነው የምናተርፈው፡፡ ቅድሚያ የምንሰጠውን ማወቃችን ለሌላውም ተራፊ ያደርገናል ......... እኛ ብዥታ ውስጥ ሆነን የምናወራው፣ አጥርተው የሚያወሩትን ስለሚያሰናክል፣ ዝምታችንን እንደ መልካምነትም መውሰድ እንችላለን፡፡ ፖለቲካውም፣ ወሬውም፣ ዜናውም ነገ ራሳቸውንና አጫዋቾቻቸውን ቀይረው ይኖራሉ፡፡ የእውነት ጥሪያችንም ከሆኑ ነገ ይደርሳሉ፡፡ ቅድሚያ ግን እኛ ከተራራው ጫፍ እንውጣ!!!
እንዲህ እንዲያ እያለ ነው መንገዱ የሚጀምረው!
እርዮት አለም እጅግ አመሰግናለሁ። ላፍህ መስሎኝ ነበር እሺ ያልከኝ። ለካንም ከልበህ ነበርና በፍጥነትህ አወኩ።
ReplyDeleteታዴ ከ8 ወይ ከ7 አመት በፊት ነበር የፃፍኩት። እውነት ለመናገር ረስቼው ነበር። አንተ ልብ ውስጥ ከቀረማ ሌላም ቦታ አያጣም ብዬ ነው። ወቅቱን ኩልል አርጎ ነው ያስታወሰኝ። መጨረሻ ያልኩትን ለራሴ ደጋግሜ የምለው የነበረውን ነው። ብቻ እግዜር ይስጥህ ብዙ ኋላ ደርሼ መጣሁ። እሺ ካልኩ ግን እሺ ነው እምቢ ለማለት ስለማላመነታ እሺዬ ሁሌም የምር ነው።
Delete