Advertisement
ዝምብዬ ሳስበው ሳስበው ግን "ትመጫለሽ ብዬ..." የሚለው የሕዝብ መንቶ ግጥም ሲጀምር ብዙ ሰው ቀድሞ የሚያስበው "ሳይ ማዶ ሳይ ማዶ"ን ብቻ ይመስለኛል፡፡
ገብረክርስቶስ ደስታም “ቀረሽ እንደዋዛ" ግጥሙ ላይ ተጠቅሞታል፡፡
"ትመጫለሽ ብዬ ሳይ ማዶ ሳይ ማዶ
የልጅነት ዓይኔ ሟሟ እንደ በረዶ"
ግን ሌላም አንጀትን የሚያላውሱ ትመጫለሽ ብዬዎች አሉንኮ።
ትመጫለሽ ብዬ በሬን ባልዘጋው
ከፍቶት አድሯል ብሎ ማን ጠየቀኝ ሰው
(ሕብረ ቃሉን አውጡ ሃሃሃ)
ትመጫለሽ ብዬ ከማዶው በላይ
አንገቴ ረዘመ ቆሜ አንቺን ሳይ ሳይ
ትመጫለሽ ብዬ አሻግሬ ሳይ
አንቺ ልጅ ማለፊያ መንገድ አጣሽ ወይ
ትመጫለሽ ብዬ መንገዱን አላምነው
የሚመላለሰው ሌላው ሌላው ሰው ነው
ትመጫለሽ ብዬ ነጠላ ስቋጭ
ምን ትጠቀሚያለሽ አንገቴ ቢቀጭ
የመጨረሻውን የገጠመው ሰውዬ ሴቶች አንዴ እንኳ በስህተት "ትመጣለህ ብዬ…" ሲሉ ባለመስማቱ… ራሱ በቁጭት ነጠላውን እየቋጨ ገብቶበት ይመስለኛል ሃሃሃሃ በናትሽ ምጪለት አንገቱ ከሚቀጭ ሃሃሃሃ (የመቋጨት ልምድ ያላችሁ ግን ይህ ከላይ ያለው ቋጪ በትክክል ምን ማለት እንደፈለገ ብትነግሩኝ አይከፋኝም፡፡ ባትነግሩኝም አይከፋኝም)
በዚህ አጋጣሚ ግን አያቹ ሴቶች ምን ያህል ጠባቂ እንዳልሆኑ ... ቀጥታ እንደ መሰሉ ፋንታሁን "ወይ ልምጣ ወይ ምጣ" ብለው ነው የሚዘፍኑት።
ተያይዞም አንድ ግርም የሚለኝ የቅብብሎሽ ዘፈን አለ፡፡ እትዬ ሒሩት እና ጋሽ መሃሙድ ናቸው የሚዘፍኑት። ለመሃሙድ ጋሽ ማለቴ ካልቀረ ነው ለሒሩትዬ እትዬ የጨመርኩት እንጂ… እቤት እቤት ልክ እንደ ቡዙዬ እሷንም ሒሩትዬ ነው የምላት ሃሃሃ
እሷ…
"ተው ዘገየህ አንተ ሰው ዘገየህ ተው ዘገየህ አንተ ሰው ዘገየህ
እመጣለሁ ብለህ ልቤን እያጋየህ ተው ዘገየህ አንተ ሰው ዘገየህ" ትለዋለች።
እመጣለሁ ስላላት ነው የምጠብቀው እንጂ ከላይ እንዳሉት እንደ ሞላ ወንዶች፣ ዝምብላ በመላምት 'ትመጣለህ ብዬ' እያለች አትጠብቀውም። ወንዶች ከዚ ብዙ ሊቀስሙ ይገባል ባይ ነኝ፡፡ እንደውም ወንዶች ግልፁን ሊነገራቸው ይገባል። በመላምት ሰው አጠብቁ። ተመከሩ ብያለሁ… በኋላ እንደኔ ጣፋጭ ጣፋጭ የምክር ዘለላውን የሚያካፍላቹ አታገኙም ሃሃሃሃ
በመላምት ሰው የምጠብቁ መጨረሻችሁ የደበበ ሰይፉ “ጠብቄሽ ነበረ" ግጥም ነው የሚሆነው
ጠብቄሽ ነበረ
መንፈሴን አንጽቼ
ገላዬን አጥርቼ
አበባ አሳብቤ
አዱኛ ሰብስቤ
ጠብቄሽ ነበረ፤
ብትቀሪ ጊዜ፣
መንፈሴን አሳደፍኩ
ገላዬን አጎደፍኩ
አበባው ደረቀ
አዱኛው አለቀ፤
ብትቀሪ ጊዜ፣
የጣልኩብሽ ተስፋ
እኔን ይዞኝ ጠፋ።
ተመከሩ ብያለሁ ተመከሩ ሃሃሃ
ታድያ ጋሽ መሃሙድም… ኮራ ጀነን ብሎ…
"ና ካልሺኝ አልቀርም የኔ አለም ና ካልሺኝ አልቀርም የኔ አለም
ስላንቺስ የማልሆነው የለም" ይላታል፡፡ እንዲህ ነው ወንድ ልጅ መሆን ያለበት፡፡ አሞቱ ኮስተር ያለ ወንድ እወዳለሁ ሃሃሃሃ ዝም ብለው ና ሳይባሉ የሚሄዱ ነፈዞች ያበሽቁኛል ሃሃሃሃሃ ሆኖም መጀመሪያ "እመጣለሁ" ብሎ ያላት እሱ ሆኖ "ና ካልሺኝ አልቀርም" እርስ በእርሱ ቢወሳሰብም፣ ዋናው ፍቅሩና የሁለቱ መግባባት ነው ብለን እናልፈዋለን፡፡ በፍቅራቹ መሃል ነፋስ አይግባ ብሎ መመረቅ እንጂ እንዲህ ስር መግባትም አያስፈልግም ሃሃሃሃ
ግን ግን ጨዋታው ጨዋታ ነውና "ትመጫለሽ ብዬ" ትንሽ ዘወር ተደርጎ በሚካኤል በላይነህ "ትመጪ እንደው እያልኩ" ተብሎ የተዘፈነው ዘፈን… በትመጫለሽ ዘርፍ የሚስተካከለው ያለ አይመስለኝም፡፡ "ትዝታም አይደለም ተስፋ ነው ቅኝቱ" የሚለው አንጓ ምን አይነት መንፈስ የሆነ አገላለፅ ነው ያስብለኛል ሁሌም ሳስበው ሳስበው፡፡ ይሄ ዘፈን ቀን ቀን እየገፋ፣ ዕድሜዬ እየታለበ ስንቴ እንደሰማሁት ስንቴ እንደገረመኝ… እኔና ጆሮዬ ነን የምናውቀው። ዝም ብዬ ባልፈው ጆሮዬ ይታዘበኛል ብዬ ነው እንጂ ዛሬ በማካበድ ሙድ ላይ አልነበርኩም ሃሃሃሃ
ሌላው በማሳዘን፣ አንጀት በመብላት፣ በቅላፄ የሚከተለው የባህታ ገብረህይወት “አሁንም እዛው ነኝ" የሚል ዘፈን ነው….
“ምናልባት ብትመጪ እንዳይጠፋሽ ቤቴ
አሁንም እዛው ነኝ የፍቅር እመቤቴ
ጊዜን መስሏል ብለሽ ሃሳብሽ እንዳይጠም
እንኳንስ ፀባዬ ልቤም አልተለወጠም
እስቲ መጥተሽ ራርተሽ ናላሽ ይታዘበኝ
በእድሜ ካልሆነ በሌላው እዛው ነኝ፡፡"
አስቡት መጥታ እንዳታጣው ከሰውነት ወደ ዛፍነት ሲቀየር… በዜማ የማታውቁት ይኧው ስሙትና ልባችሁ ቅልጥ፣ እዝን፣ ኩርምት ይበል ለሱ....
የወንዶችን ጠባቂነትን በግጥም እናሳርገው ...
ኑረዲን ኢሳ… “ሰው እንዴት በሁለት መስመር እንደዚህ ልቦለድ ይፅፋል?” የሚያስብለኝ ግጥም አለው፡፡ ባሰብኩት ቁጥር ግርም ድንቅ ጥልቅ የሚለኝ ግጥም ነው፡፡
“ምን ያህል ሆኖ ነው ምን ያህል ስንት ዕድሜ
ሳር የበቀለብኝ ስጠብቅሽ ቆሜ"
ሴቶች “ትመጣለህ ብዬ.." አይሉም ብዬ እንዳልምል ይቺ አስቱካ “የኔ ቆንጆ” ዘፈኗ ላይ ቀጣዩን ትሰነቅራለች…
ትመጣለህ ብዬ ድንጋዩን ስለቅም
እንደወጣህ ቀረህ ያንተን ሆድ አላውቅም
እዚሁ ዘፈኗ ላይ ታድያ ቀደም ብላ… “አትምጣ ግርሻ ትሆንብኛለህ.." ስለምትለው... ልጁን ይመጣል ብላ ድንጋይ የምትለቅመው ልትፈነክተው ነው ወይ? አያስብልም ትላላችሁን? ሃሃሃሃ
በመቀጠል ደሞ "አልመጣም!" ስለሚሉቱ ስለምንማማር እስከዛው.. "አልመጣም ቀረሁኝ —ሸጌ— አልመጣም ቀረሁኝ ካንቺ የተሻለ— ሸጌ— እዚህ አገኘሁኝ" የሚለውን ብትፈልጉ በተሾመ ምትኩ ብትፈልጉ በኃይለየሱስ ግርማ ብትፈልጉ በስለሺ ደምሴ የተሰሩትን እንደምርጫቹ እያዳመጣቹ ቆዩኝ...
ተዋ እሪ! በመላምት አትጠብቁ ብለህ ትመክራለህ አይደል? እኔ አለው አይደል ያለሁበት ሀገር እንደማትመጣ እያወኩ አንተ ያለህበት እንደማልመጣ እያወኩ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆኜ …. ትመጣለህ ብዬ ….. ውጪ ውጪውን የማይ ምስኪን! ደሞ ሰሞኑን የሆነ አስተያየት ተሰቶክ ያጠፋዋል አያጠፋውም ስል አጥፍተከዋል… አቦ ተይአ በለኝ ናፍቆኛል። ሁሌም መልካሙን!
ReplyDeleteፈንዱሼ ሌላ ጊዜ አቦ ተያ የምለው ጭንቀቴን ነው ዛሬ ግን ምን ያህል እንደምትረጂኝ ስለማውቅ አቦ ተይአ የምልሽ በረፍት ስሜት ነው። ሜሪዬ በዚ ጉዳይ ሌላ ምንም አልበልሽ!!!!!!!!!!!!!
Deleteአስተያየቱን ካየሺውማ ላብራራው ሃሃሃሃ የአስተያየቱ አጠሪራ "ከአንዲት ፍሬ ልጅ ጋር ሲኒማ ቤት አየሁህ ተው አግባ" ነው የሚለው። ኡዝባኪስታንኛው ከአንዳንድ ፍሬ ልጆች ጋር ከምትንዘላዘል ለምን አታገባም ነው። እኔም እስማማለሁ።
ሲጀምር ግን ልጅቷ ሶስተኛ ድግሪዋን በመስራት ላይ ያለች እጩ ዶክተር ነች። እንደኔ እድሜዋን አተመስልም። ሲቀጥል ግንኙነታችን ትምህርታዊ ነው። ወንድምና እህት ይሰለቻል ብዬ ነው ሃሃሃ ሲሰልስ ሰው እንደፈለገ ያስበኝ እንጂ ህይወቴን አላብራራም ስለምል፣ እንደ አስተያየት ሰጪዋ አተራማሽ አርገው የሚያስቡኝ አሉ። እኔን ጭምቱን ሃሃሃሃ በጣም ጭምትም የሚያረጉኝ ደሞም አሉ። ከቶ እኔ ማነኝ ሃሃሃሃ
ሜሪዬ እኔ ለትዳር ያለኝን እጅግ ቀና አመለካከት አታውቂምን? መንዘላዘልንም በዛው ልክ እጠየፋለሁ። ወንደላጤ መሆን ማለት ትዳርን መጥላት፣ መንዘላዘል መምረጥ ለሚመስለው ሁሉ አስረድቼ አልችለውም ብዬ ነው። ገና በካላንደር አቆጣጠር 40 ሳንገባ ንዝንዙ በዛብኝ። በዛ ላይ ከእግዜር ጋር ተከራክሬ ያስመለስኩት 10 አመት አለኝ። አስቢው እንዴት አንድ ፍሬ ልጅ መሆኔን ሃሃሃሃሃ ሜሪ አንቺ ሆነሺብኝ ነው እንዲህ ያብራራሁት ማርያምን!!!!!!!!!