Komentar baru

Advertisement

ያቺ ሁሉ ነገሯ የሚበላው ልጅ!!!

Eriyot Alemu
Oct 9, 2024
Last Updated 2024-10-13T11:38:28Z
Advertisement

 


"እስቲ ዛሬ ሲሪየስ ሙድ ሲሪየስ ሙድ ለምን አንጫወትም? ለምን ታሪክህን አትነግረኝም?" አለችው ጥፍሯን እየበላች፡፡ ድሮ ድሮ 'ጥፍረ መጥምጥ' የሚባል ነገር ነበር፡፡ አሁን ይኑር አይኑር የሚታወቅ ነገር ባይኖርም፣ ሲቲያና ግን ጥፍረ መጥምጥ አይደለችም፡፡ ሲያልፍም አይነካካት፡፡ ጥፍሯ ሁሌም ቢበላም እጅግ በጣም ያምራል፡፡ እጇም ጭምር፡፡ አረ ራሷም ጭምር (ራሷ የተባለው ከአንገቷ በላይ ያለው ራስ ቅሏ ሳይሆን ሙሉ ራሷ ታምራለች ለማለት ነው፡፡) እንደውም አንዳንድ ክፉ ገላጮች ውበት ሲገልፁ "እከሊት እኮ ሁሉ ነገሯ ይበላል" እንደሚሉት፣ በእከሊት ቦታ ላይ ሲቲያና የሚለውን ስም ማስገባት በቂ ነው፡፡ ሲቲያና ሁሉ ነገሯ ይበላል፡፡


ሲቲያና እጅግ ውብ ሴት ናት፡፡ምናልባት ሁሉ ነገሯ ስለሚበላም ይሆናል በዚ ሰሞን ጥፍሯን መብላት የጀመረችው፡፡ ያለ ልማዷ፡፡ 


"የሚነገር ታሪክ አለኝ ብለሽ ነው?" አላት የውሸቱን በጎረነነ ድምፁ፡፡ እሱ እኮ አለሌ ቀጫጫ ነው፣ ድምፁ ግን እጅግ ወፍራም ነው፡፡ የሰውነት ውፍረትን እና የድምፅ ውፍረትን የግድ ለሚያያይዙ ድንዙዞች ወንዲራድ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ለነገሩ ይሄ ወንዲራድ የሚሉት ልጅ ብዙ ነገሩ ከሚመስለው በተቃራኒ የቆመ ነው:: 


"ሁሉም ሰው የሚነገር ታሪክ አለው፡፡ ሁ—ሉ—ም ሰ—ው!" አለች፡፡ ሁሉንም ቃላት እየረጋገጠቻቸው፡፡ ቃላት ግን መሬት ናቸው ሲረገጡም "ዝም አይነቅዝም" ይላሉ በቃላትኛ፡፡ እንደውም ሲረገጡ ይጠብቃሉ መሰለኝ፡፡ ወይ ቃላት!!!


የጎረሰውን እሳት ለጣቱ አቀበለው፡፡ ብዙ ጊዜ ሲጃራውን አፉ ላይ ያቆየዋል፡፡ ያለበለዚያ የሚያሰማው አይመስለውም፡፡ እንደዛም ሆኖ ጭስ አያባክንም፡፡ በአፉ ይዞ ጭስ በትቦ እንደሚያስተላልፍ ነገር ጭስ የማይባክንበት ብቸኛ ሰው ሳይሆን አይቀርም ወንዲራድ፡፡ ያኔ ጀማሪ አጫሽ እያለ ግን "ጭሱ ቦለለለለለለለለ,,,,,..." እያለ እየዘፈነ ነበር የሚያጨሰው፡፡ ያኔ ለቄንጥ በሚያጨስ ዘመን፣ ከ 10 አመት በፊት፡፡ አሁን የሚያጨሰው "አጫሽ" ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ያው ሱሰኛ ላለማለት ነው፡፡ ስም ለማሳመር ታህል፡፡ ጊዜው ግን እንዴት ነው የሚነካው?....



ሲጋራ የተሰካበት አፍ አፉን እያየችው ነው፡፡ እሱም ቢሆን ተርዚና የወጠረ ጉንጭ ጉንጯን እያየ ነው፡፡ ቺኮች ሲቅሙ ደስ አይለውም፡፡ ተርዚና ወጥረው ሲያያቸው፣ ፊታቸው እንደዛ ሆኖ እንደሚቀር እየተሰማው ይሁን፣ወይንም ተርዚና ወጥረው ሲያወሩ ምራቃቸው አብሮ ስለሚያመልጣቸው ይሁን፣ ወይንም በውል በማያቀው ምክንያት ቺኮች ሲቅሙ ይደብሩታል፡፡ ምንም ራሱ እልል ያለ ቃማቴ ቢሆንም ቅሉ፡፡ 



ግን ማለት ጥሩ ነው የሲቲያና ግን ይለይበታል፡፡ ተርዚና ወጥራ ስታምር ያያት ብቸኛ ሴቱ እሷ ብቻ ነች፡፡ ስለሚወዳት ብቻ አይደለም፣ ተርዚናም ወጥራ ስለምታምር ነው።


"እሺ ካልሽ.." አለና ትንሽ አንጠራራ ወይንም እንደ ማፈር ነገር ሰራራው...


"እኔ ወንዲራድ ከአቶ ማሞ እና ከወይዘሪት ሰላም በ1985 አመተ ምህረት ልዩ ስሙ ሳይሆን ኖርማን ስሙ ካሳንቺስ የሚባል ሰፈር ተወለድኩ፡፡ ከነቃጭሌ… 'በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ' እንዳይሉ ብቻ አበው፡፡" ሳቁን ለቀቀው፡፡ አብራው ሳቀች፡፡ ተርዚና ወጥራም ስትስቅ እጅግ ታምራለች፡፡ አጃኢብ ነው የሷ ነገር፡፡


ድንገት ከሳቁ አባራና ኮስተር ሲል፣ ከልቡ እንዳልሆነ ቢገባትም "ምነው?" አለችው በሆዷ የታቀፈችውን ትራስ እያስተካከለች፡፡ "ያው ደንባራ መሆኔ ግልጥ ሆኖ ሳለ… ከቃጭሉ ጋር አገናኝቼ ራሴን በቅሎ ማለቴ ፀፅቶኝ ነው፡፡ በሌላ እንዳያዩብኝ እቴጌ" የምሩን በሚመስል ሁኔታ በሃሳብ ሩቅ የነጎደ መሰለ፡፡ እሷ ሳቋን ካቆመችበት ቀጠለችው፡፡ 


"አረኸ አላይብህም ጌታው! አንተ እንደውም እንኳን በቅሎ ልትሆን ቀርቶ፣ መቼ በቅሎ ታቅና ነው?... አስቱካ 

'በፈረስ ይምጣልኝ በሚለሰልሰው

መቼ በቅሎ ያቃል እንደሱ ያለ ሰው' ያለችው ለአንተ አይደል እንዴ???" 


"በለው እቴጌይቱ በርግጥ የተናገርሽው ነገር ሐቅ ነው፡፡ ሆኖም ከፈረስና ከበቅሎ የትኛው የበለጠ መለስለሱን እንዴት እንዳንቺ ያለ በዘመነ ቆርቆሮ ተወልዶ፣ በቆርቆሮ ውስጥ ለኖረ ሰው መገለጡ እፁብ የሚያሰኝ ነው፡፡ ብቻ እፁብ ነው፣ ድንቅ ነው፣ ግሩም ነው" 

የታቀፈውን ትራስ ወረወረና ወደጎን ተስቦ አቀፋትና...


"ሳስበው ሳስበው ሲቲያናዬ… በዘመነ ጋማ ከብት የኖረ የሆነ መንፈስ እንዳለሽ ይሰማኛል፡፡ በጣም እንደምትገርሚኝ ግን ታውቂያለሽ???" አላትና ጉንጯን በስሱ ሳመው፡፡ ቆነጠራት ነው የሚባለው፡፡ እንዳታልቅበት። 


                                    ******* 


ሀገሬ ውስጥ ሩቅ ሀገር የሚባል ቦታ ነው ያለሁት፡፡ ከአዲስ አበባ ብዙ ኪሎሜትሮች ርቄ ተጉዣለሁ፡፡ ስሜ ተቀይሯል፡፡ መልኬም ተለውጧል፡፡ ሰው ንቅሳቱን ተሟሙቶ በሚያጠፋበት በዚህ ዘመን… የገጠር ንቅሳት ላዩ ላይ ያሰራ ብቸኛ ሰው ሳልሆን አልቀርም፡፡ የሚያውቁኝ ቢኖሩ እንኳ እሷን ትመስላለች እንጂ እሷ ነች አይሉኝም፡፡ ተሰብሬያለሁ፡፡


ብቻዬን የምሆንበት ብዙ ጊዜ የለኝም፡፡ ግን ጥቂት ጊዜ እንኳ ሳገኝ … “እንዲህ ለመሆኔ ተጠያቂው ማነው?" ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ መልስ ግን አግኝቼ አላውቅም፡፡



ከከፈለኝ ጋር ሁሌ እሄዳለሁ፡፡ መጀመሪያ ሰሞን እመርጥ ነበር፡፡ በኋላ ሲገባኝ ህይወቱ ለካ ምርጫ የሚባል ነገር የለውም፡፡ በደብዛዛ መብራቶች ውስጥ ሆኜ ትላንት በንደዚህ ዓይነት መብራቶች ውስጥ ሆኜ ያሳለፍኳተውን የተደሰትኩባቸው የሚመስሉ ቀኖቼን አስባለሁ፡፡ ግን ደስታዬ ብዙ አይቆይም፡፡ ዛሬ እንደዚህ መቀመቅ ውስጥ የከተተኝ አንድም የዚህ ደብዛዛ መብራት መርገም መሆኑን ሳስብ ወደ መደብዘዜ እመለሳለሁ፡፡


ብዙ ጊዜ መሞት እፈልግና ያቺ ብዙ ዋጋ ከፍላ አንቀባራ ያሳደገቺኝ በሽተኛዋ እናቴ ትዝ ትለኝና ሃሳቤን እተወዋለሁ፡፡ በርግጥ አልሞትኩም፣ ለመሞትም እየሰራሁ አይደለም ማለት አልችልም፡፡ ሰውነቴ በድን ነው፡፡ ዓይኔ ተሰላችቷል አያይም፡፡ ጆሮዬም ደንቁሯል፡፡ እጆቼ ስሜት አልባ ናቸው፡፡ መልኬ ብቻውን ግን እኔን ለማኖር ይታገላል፡፡


“አማርኛሽ እኮ ጥርት ያለ ነው፡፡" ይሉኛል ንቅሳቴ ግራ ሲያጋባቸው፡፡ “አዲስአባ ሰው ቤት ተቀጥሬ ብዙ ስለሰራው ነው" እላቸዋለሁ፡፡ ያኔ ጥያቄ ያቆማሉ፡፡ "አክስቴ አጎቴ ቤት ስለኖርኩኝ ነው..." እያልኩ ሞክሬው ነበር፡፡ ግን ይሄ ቀጣይ ጥያቄው ብዙ ነው፡፡ ጥያቄ ደሞ አልወድም፡፡


ወንድ ሆኖ ከኔ ጋር ሊጋድም ለሚመጣ ለማንም ሰው አዝኜ አላውቅም፡፡ ሰለሞን ግን ያሳዝነኛል፡፡ ስሙ አይመስለኝም፡፡ ደሞ ሁሉም ቤት ውስጥ ያሉ ሴቶች ከሱ ጋር መሆን ይፈልጋሉ፡፡ ገንዘብ ስላለው፣ ጨዋታ አዋቂ ስለሆነ አይደለም፡፡ ሴት የሚጋብዘው አጠገቡ ሰው እንዲኖር ስለሚፈልግ ብቻ ነው፡፡ ከዛም አብዝቶ ስለሚጠጣ ይዟት የገባትን ሴት ምንም ሳያረጋት ይነጋል፡፡


እንጨት ቤት ውስጥ ነው የሚሰራው፡፡ የፈለገ ቢጠጣ ግን ስለራሱ ብዙ አያወራም፡፡ ቀንም ማታም ኮፍያ እና መነፅር ያረጋል፡፡ የሆነ የሚደብቀው የሚደበቀውም ነገር እንዳለ ይገባኛል፡፡


ከአራት ቀን በፊት የJohnny Cashን 'hurt' የሚል ሙዚቃ በኤርፎን እያዳመጠ ነበር፡፡ ቤቱ ውስጥ መብራት የለም አብሬው ነበርኩ፡፡ ኤርፎኑን ከጆሮው ላይ ወስጄ ወደራሴ ሳረገው ምንም አላለኝም፡፡ "ይሄ ዘፈን እዚም ተከትሎኝ መጣ" እያልኩ በሃሳብ ጋልቤ… ሳላውቀው አብሬ እየዘፈንኩ ዕንባዬ ወረደ። ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ “አንድ ነገር ልንገርሽ? ንቅሳትሽ ፌክ ነው፡፡" አለኝ፡፡ ተስፈንጥሬ ተነሳሁ፡፡ እጄን ስቦ ሲያስቀምጠኝም ደንዝዤ ነበር፡፡ ሰው አየን አላየንምን ልብ አላልኩም፡፡ “እኔም እንዳንቺ ስደተኛ ነኝ፡፡ ስጨርሺ ነይ" ብሎኝ ያለ ሰዓቱ ወደ ክፍሉ ሄደ፡፡ አልዘገየውም ተከተልኩት፡፡


አጭር ታሪኩ ይሄ ነበር፡፡ የዩንቨርስቲ አንደኛ አመት ተማሪ እንደነበር ነው ሱስ የጀመረው፡፡ ሶስተኛ አመቱ ላይ ተባረረ፡፡ ግን ወደ ቤቱ አልሄደም፡፡ እዛው ቆይቶ ጊዜው ሲደረስ ተመርቄያለሁ ብሎ ቤቱ ሄደ፡፡ ከዛ ስራ አግኝቻለሁ ብሎ ደግሞ አሁን ያለንበት አገር መጣ፡፡


“አብሪያችሁ ሆኜ ወሲብ የማልፈፅመው መጠጡ አድክሞኝ አይደለም፡፡ መጠጥ እችላለሁ፡፡ ለጉልበት ስራ ግን አዲስ ነኝ፡፡ በፊት ትልቁ ሸከሜ እስኪሪብቶ ነበር፡፡ እዚህ ስራ የጀመርኩት ግን በቀን ስራ ነው፡፡ ሰውነቴን ማዘዝ እስኪያቅተኝ ይደክመኛል፡፡ አየሽ ሰውነቴ በስራ አልዳበረም፡፡ ገና ነው፡፡ አሁንም ደክሞኛል ከፈለግሽ ሂጂ" ብሎ ተኛ፡፡ በሙሉ ሰውነቴ አቅፌው ልተኛ ፈልጌ ነበር፡፡ ለሊቱን ሙሉ ሳለቅስ አደርኩ፡፡


ከዛ ቀን በኋላ ቤታችን አልመጣም፡፡ ለምንም ነገር ግድ የማይሰጠኝ ሴት ለሰለሞን እጅ ሰጠሁ፡፡ ፍቅር አይደለም፡፡ ግን አዘንኩለት፡፡ አሁንም ፍቅር አይደለም፡፡ በር በሩን እያየሁ ስራ እያበላሸው ብዙ ጠበኩት፡፡ አንዳንዴ ራሴን እወቅሳለሁ፡፡ ታሪኩን ስለነገረኝ ተፀፅቶ የጠፋ ይመስለኛል፡፡ "መሳ የሚመስለውን ታሪኬን ብነግረው ኖሮ ይፅናና ይሆን ነበር?" እላለሁ፡፡


ቢመጣ እንኳ መንገሬን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ብቻ ይምጣ ያኔ እወስናለሁ፡፡ ግን ምን ሆኖ ይሆን? የወጣውም በጠዋት ነበር፡፡ አሁን ድረስ ኩርምት ብሎ የተኛው አተኛኝ በአይኔ ይመጣና በዓይኔ ዕንባ ይሞላል፡፡ በሙሉ ሰውነቴ አቅፌው ልተኛ ፈልጌ ነበር፡፡

iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

Leave Your Comment

Post a Comment

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement