Komentar baru

Advertisement

ክንፉ ጊዜ … “I believe I can fly” Mode!

Eriyot Alemu
Apr 29, 2024
Last Updated 2024-04-30T01:49:08Z
Advertisement


ክንፉ ጊዜ የምለው ሱስ በተውን የመጀመሪያው እና ሁለተኛው ዓመት ላይ ያለውን ጊዜ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ይሄንን ወቅት በሚገባ (ማወቅ በሚገባን ልክ አለማወቅ) ዋጋ እንደሚያስከፍል መነገር ስላለበት ነው ክንፉ ጊዜን ማንሳቴ፡፡


በሱስ ስንቆይ ብዙ ጊዜ ትግል ውስጥ ነበርን፡፡ እናም ራሳችንም ከሰውም የሰማናቸው ነገሮች በሙሉ አለመቻላችንን ነው ሲነግሩን የቆዩት፡፡ ከሁሉ በላይ ጎልቶ የሚሰማው ደሞ እኛው ለራሳችን የምንነግረው የነበረው “ሱስ መተው አትችልም" የሚለው ድምፅ ነው፡፡ ዙሪያችንም ሱስ መተው ከባድ እንደሆነ ያስባልም ያብራራልም፡፡


በዚህ መሃል ሱስ የሚተው ሰው ያንን ያለመቻል ስሜት ስለሆነ ሰብሮ የሚወጣው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ላይ እጅግ የታላቅነት ስሜት ይሰማዋል፡፡ ተአምረኛ ሰው እንደሆነ ጭምር ራሱን ይቆጥራል፡፡ መጠኑ ይለያይ እንጂ ዙሪያውም ያንን ሱስ የተው ሰው የሚያይበት ዓይን ፍፁም የተለየ ይሆናል፡፡ ያንን ሱስ የተወ ሰው የማይቻል የቻለ፣ ማክጋይቨር (ምንተስኖት ሁሉን ቻይ) አድርጎ ያስበዋል፡፡


ይሄንን ጊዜ ከክንፉ ጊዜ የተለየ የሚገልፅ ስያሜ ስላጣሁለት ነው፡፡ ብረር ብረር የሚለውን ስሜት ሌላ ምንም ልለው አልችልም፡፡ እዚህ ጊዜ ላይ ያለ ሰው ክንፍ እንዳለው ሁሉ ሊሰማው ይችላል፡፡ ሁሉም ሰው መቻሉን እንዲያውቅለት ይመኛል፡፡ ሱስ ትቶ የተመለሰ ታላቅ ሰው መሆኑን ሲያወራ በታላቅ ኩራት ነው፡፡ ታክሲ ውስጥ ድንገት ጨዋታ ቢጀምር ለማያውቀው ሰው ሱስ ትቶ የተመለሰ መሆኑን በጨዋታ መሃል ሳይነግረው አይወርድም፡፡ ሁሉም ፍጡር፣ ኃያል ሰው መሆኑን እንዲረዳለት ይፈልጋል፡፡


ወሬው ሁሉ ስለ ሱስ ነው፡፡ ኢነርጂው የሚገርም ነው፡፡ ሱሰኞችን በሙሉ ከሱስ ማውጣት ይመኛል፡፡ (የዚ ጊዜ እጅግ ቀና ነገሩም ይሄ ነው)፡፡ ሌላው ስሜትም ቀና አይደለም አላልኩም፡፡ ልብ የሚል ሰው ካለ፣ ሱስ የተዉ ሰዎች የመጀመሪያው ሁለት አመታት ውስጥ ነው ከሱስ ማገገሚያ ማዕከላት እንኳ እስከማቋቋም ሲደርሱ የሚታዩት፡፡ ይሄ እጅግ ደስ የሚል ነገር ነው፡፡


ግን ይሄ ወቅት ቀላል የማይባል ጥንቃቄ እንደሚፈልግ መታወቅ አለበት፡፡ እዛ ወቅት ላይ ስለነበርኩ ስሜቱንም ሂደቱንም በሚገባ አስታውሰዋለሁ፡፡ እዚህ ወቅት ላይ እያለሁ አንድ በሱስ ዙሪያ የሚሰራ ሰው፣ እዛ ወቅት ላይ ስለሚፈጠር “የታላቅነት ስሜት" የሆነች አንዲት አንቀፅ ፅፎ ነበር፡፡ በወቅቱ ተቃውሜው ነበር፡፡ ያ የታላቅነት ስሜት ዘላቂ፣ ብዙ አመታት አብሮን የሚቆይ ይመስለኝ ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር ያን የፃፈው ሰውዬ በሱስ ዙሪያ ከ30 አመታት በላይ የሰራ ሰው ነው፡፡ እኔ ደግሞ በክንፉ ጊዜ ምርቃና ላይ ስለነበርኩ የጉዳዩን ጠቃሚነት ቦታ አልሰጠሁትም ነበር፡፡


ሰው ማወቅ ያለበትን ጉዳዮች ቀድሞ ማወቁ ባይጠቅመው እንኳ አይጎዳውም፡፡ በሱስ ጉዳይ ከመጣን ቀድሞ ማወቅ ግዴታ ሁሉ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሱስ ከተተወ ከሁለተኛው አመት በዋላ (አመቱ ሊያጥርም ሊረዝምም ይችላል) ነገሮች ቀስ በቀስ በፊት ወደነበሩበት ይመለሳሉ፡፡ ኖርማል ሰው መሆን እንጀምራለን፡፡ እናም ክንፍ እንዳለው ሲሰማው የነበረ ሰው ቀድሞ ካላወቀው ድንገት ክንፉን እንዳጣ ሰው ሊደነግጥ ይችላል፡፡


ሱስ ስንተው ሊገጥሙን የሚችሉ ነገሮችን በእጅጉ እንደጠቀመን ሁሉ ይሄንንም ጊዜ ቀድሞ ማወቁ ከሚፈጠረው የስሜት መዋዠቅ ቀድሞ ያድነናል፡፡ ዋናው ነገር ክንፉ ጊዜ ወሰን እንዳለው መረዳታችን ነው፡፡


ህይወት ለሁሉም ሰው እኩል ነች፡፡ የሁሉም ሰው ህይወት አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው የሚታገለው የየራሱ የህይወት ትግል አለው፡፡ ያን ትግል ታግሎ ማሸነፍ የሁሉም ኗሪ ግዴታው ነው፡፡ እኛም ሱስ የተውን ሰዎች የተለየን አይደለንም፡፡ የህይወት ከፍ ዝቅ ሁሌም ስላለ እንደማንኛውም ሰው ህይወትን ለመጋፈጥ መዘጋጀት ነው ያለብን፡፡ ከክንፉ ጊዜ የሚመለስ ሰው ራሱን ከሌላው እኩል ለማየት መዘጋጀት አለበት፡፡ ሱስ ውስጥ ስለነበርክ ብላ ህይወት ለማንም ሰው የተለየ “ፌቨር” አትሰራም፡፡ እንደሌላው ታገለው ነው መልሷ፡፡


ይህ ወቅት ጥቂት እንዳለፈ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ወደ ቀደመው ሱሳቸው ለመመለስ ፈተናዎችን ሰበብ የሚያረጉት ለዛ ነው፡፡ ኖርማል ሰው መሆናቸውን ካለመቀበል የተነሳ ይጎዳሉ፡፡ ስለዚህ ቀድሞ ማወቁ እዚጋ ነው ጥቅሙ፡፡ ለምሳሌ ሐዘን፣ ስራ ማጣት፣ ከሰው ጋር ፀብ ሲገጥማቸው ሌላው ኗሪ ሁሉ እነዚህ ነገሮች እንደሚገጥሙት አውቀው ያን መቋቋም ብቻ ነው መዳኛቸው፡፡ እንጂ እኔ ሱስ የተውኩ ስለነበርኩ እነዚህ ነገሮች ሊገጥሙኝ አይገባም ብሎ ማሰብ ከምናልፍበት መንገድ ካለማወቅ የሚፈጠር ስህተት ነው፡፡


ብዙ ጊዜ የሰው ሁሉ ችግር ለራስ የሚሰጥ ግምት ነው፡፡ እናም ክንፉ ጊዜ ላይ የቆየ ሰው ሁሉን እንደሚችል ሲያስብ ስለቆየ ቀጣይ ህይወቱ ትንሽ ጎርበጥ ሊልበት ይችላል፡፡ እችላለሁ ብሎ ማሰብ በራሱ ክፋት የለውም፡፡ ሱስ መተውም ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ግን ሱስ መተው ስለቻልን የአለምን ችግሮች ሁሉ በቀላሉ እንደምንፈታ ማሰባችን ነው ችግሩ፡፡ ስለዚህ ችግሩ ከምን እንደመጣ እያወቀን ስለሆነ ህይወትን እንደ አዲስ መቀበል መለማመድ ይኖርብናል ማለት ነው፡፡ ክንፉ ጊዜ በአጭሩ ሲጠቀለልም ይሄን ይመስላል፡፡ ሰው ድንገት ክንፉን እንዳጣው ከሚሰማው ቀስ ብሎ መደሽደሹ ጠቃሚ ስለሆነ ነው ይሄ ፅሁፍ የተፃፈው፡፡


ክንፉ ጊዜ ላይ ያለ ሰው ይሄን ሲያነብ ውስጡ የሚያስቀረው ነገር አለ፡፡ አሁን በክንፉ ጊዜ ምርቃና ስላለ ላይታየው ቢችል እንኳ የተጣለ መሰረት አለ፡፡ ዋናው ነገር ደሞ ለወደፊቱ ስንቅ መያዙ ላይ ነው፡፡ የዚህ ፅሁፍ አላማም ያ ነው:: የፀሃፊውም ምኞት በሱስ ዙሪያ ያለች እያንዳንዷን ቀዳዳ እየደፈኑ መሄድ ላይ ነው።



iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

Leave Your Comment

Post a Comment

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement