Komentar baru

Advertisement

ትውስታ ዘ መልመጃ!

Eriyot Alemu
Mar 24, 2024
Last Updated 2024-04-30T01:49:20Z
Advertisement


 ''ድሮ የመልመጃ ጥያቄ ትሰጠን ነበር አሁን ትተሃል…'' የሚል ቅልብጭ ያለ ደስ የሚል አስተያየት ደረሰኝ፡፡ ለአስተያየት መስጫ ኮሮጆዬ ያለኝን ክብር ለማሳየት ያህል ... አስተያየቱን ተቀብዬ የምንባብ ጥያቄ አዘጋጅቻለሁ፡፡


ምንባቡን በጥንቃቄ እና በማስተዋል ካነበብን በኋላ መጨረሻ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች በአግባቡ እንመልሳለን፡፡ ለዚህ መልመጃ የተሰጠው ሰዓት 30 ደቂቃ ብቻ ነው፡፡ ዳይ ጀምሩ!!!


*** የሰፈራችን አዛውንት ጋር ደርሶ መልስ ***


አንድ የሰፋራችን ፍሪክ አዛውንት ጋር ምክር እንዲለግሱኝ ወደ ቤታቸው ገሰገስኩ፡፡ ተጠግቼም እንዲህ አልኳቸው፡፡ "አባቴ! ትዳር ተቋም ነው የሚሉ ሰዎች፣ ከትዳር በፊት በሚገባ ተጠናኑ ይሉናል፡፡ እርሶ እንደሚያውቁት ደግሞ በቃና ዘገሊላም እንደተመሰጠረው… የሰው ልጅ በባህሪው መጀመሪያ አካባቢ ሲቀርበን መልካሙን ወይን ጠጅ ያቀርብልናል… ትንሽ ቆየት ብሎ ደግሞ መናኛውን። እናም በፍቅር ግንኙነት ውስጥ መልካሙን ያቀረብን ሁሉ… ትዳር ውስጥ ስንገባ መናኛውን ላለማቅረባችን ምን ዋስትና አለን? መጠናናትስ እንዴት ያለቸው ነች? እንዴትስ ነው የምትገለፀውስ? እባክዎ አባቴ ቢጨንቀኝ ነው!" ስላቸው


"ከልምዴ ላርግልህ… በቲቪ ከማየው?" አሉኝ ስልካቸው ላይ እንዳቀረቀሩ፡፡


"ሜኑ ያለው ምክር ደስ ይለኛል አባቴ! በቲቪ ከሚያዩት ያድርጉልኝ"


"የህንድ ፖርላማ አባል ሲያወራ የሰማሁት ነው፡፡ ወደፊት ለብዙ ሺ ሰዓታት ራት ለመብላት አብራህ ቁጭ የምትል ሴትን ለመፈተን፣ የማይመጣ ባቡር የሚጠበቅበት ቦታ ይዘሃት ሂድ፡፡ ትንሽ እንደቆየች መነጫነጭ ከጀመረች ተስፈኛ ሰው እንዳልሆነች ታውቃለህ፡፡ በመቀጠል አንተ ትነጫነጭና ግብረ ምላሿን ትለካለህ፡፡ የመልስ ምቷን ማለት ነው፡፡ መልሶ ማጥቃቷን ማለት ነው፡፡ ያንተ መነጫነጭ የማይቀይራት፣ የማያበሳጫት ከሆነ በእውነቱ ትግስተኛም ተስፈኛም ነች ማለት ነው… ተስፈኛነቷን፣ ንጭንጯን በዚህ ታጠናና ቁጡ መሆኗን አለመሆኗን ለማወቅ ደግሞ ረዥም ርቀት የሚጓዝ አውቶቡስ ውስጥ ይዘሃት ትገባና.... " አቋረጥኳቸው፡፡


"አባቴ በቃ ስለ ቁጣዋ ሌላ ጊዜ ይነግሩኛል… ይሄን በልቦናዬ ያሳድርብኝ" ብዬ ስነሳ… "አየህ ልጄ አንተ ራሱ ትግስትህ ስሱ ነው… ሰውን ከመፈተንህ በፊት እኔ ማነኝ በል!" ሲሉኝ "ይሄን ያለውስ የቡሩንዲ ፓርላማ አባል ነው ወይ?.. " ልላቸው ብዬ ተውኩትና አመስግኜ ተነሳሁ፡፡ በዚህም አጋጣሚ ማለት የምፈልገውን ፊለፊት የማልል፣ እንዲሁ አመስጋኝ ሰው መሆኔ ተገለጠለኝ፡፡ "አሻሽል" አልኩት ራሴን፡፡ "እሺ" አለኝ ራሴ፡፡ በዚህም አጋጣሚ ታዝዥ ሰው መሆኔ ተገለጠልኝ፡፡


ከዛ በኋላ እንደ ጅል ሰው የተባልኩትን ቃል በቃል ለመተግበር… የማይመጣ ባቡር የማገኝበትን ቦታ ማሰስ ጀመርኩ፡፡ በጆሮዬ የባህሩ ቃኜ ዘፈን ኩልል እያለ ይወርዳል፡፡ 

"የገበታሽ ራት አይነትም አልበዛው 

ያው ተስፋሽ ነው እንጂ ፊቴን የሚያወዛው" 

በቃ በባቡር ጣቢያው ጋር ከፈተንኳት በኋላ፣ ተስፈኛ ከሆነች ይሄን ዘፈን እጋብዛታለሁ አልኩ ለራሴ፡፡



በስተመጨረሻ ለፍቼ ለፍቼ አንድ ባቡር ጣቢያ አገኘሁ፡፡ ባቡር የሚያልፍበት፣ ግን የማይቆምበት ቦታ ነው፡፡ እሷ ሳታውቅ እዚህ በሚስጥር አምጥቼ እፈትናታለሁ አልኩኝ ለራሴ፡፡ ቦታው ላይ እንዳይጠፋብኝ ምልክት አድርጌበት ልጅቷን ደግሞ ልፈልጋት ተነሳሁ፡፡ እሷን ደሞ የት አገኛት ይሆንን?


አሁንም የቅድሙ አባት ዘንድ ሄጄ የኔ የሆነችን ሴት እንዴት እንደምለያት፣ የት እንደማገኛት ይመክሩኝ ዘንድ ምክር ልጠይቃቸው ጉዞ ጀመርኩኝ፡፡


*** ተፈፀመ ***


[ ይቺ አጭሬ ልቦለድ መታሰቢያነቷ:- self help መፅሃፍት በብዛት ለሚያነቡ ትሁንልኝ፡፡ ካልናቋት የውሃ አጣጫቸውን ለመገምገም ትረዳቸዋለች፡፡ ]


[ ምስጋና፦ ይቺን አጭሬ ልቦለድ በማዘጋጅበት ሰዓት ጎኔ ላልነበራቹ ሁሉ፡፡ ጎኔ ባለመኖር ቀልቤን ሰብስቤ እንድጨርሳት ስለረዳቹኝ ከልብ አመሰግናለሁ]


ወደ ጥያቄዎቹ እንሂድ… ከ100 የሚያዝ ነው፡፡ እያንዳንዱ አንጓ 25 25 ነጥብ ይዟል፡፡ መልካም ዕድል!


1) እውነት ሃሰት በሉ በልቦለዱ ውስጥ የተላለፈው ዋነኛ መልህክት "ቅድሚያ መስጠት ላለብን ቅድሚያ እንስጥ! … ብዙዎቻችን ሁለተኛ በሚመጣ ጉዳይ ራሳችንን አድክመን፣ ዋናውና መጀመሪያ መሆን የነበረበትን ጉዳይ ጉልበታችንን ጨርሰን እንጠብቀዋለን" የሚል ሊሆን ይችላል፡፡


2) ምርጫ


የአዛውንቱ ስህተት የሆነውን መርጣቹ አክብቡ፡፡

ሀ) ስልካቸው ላይ ማቀርቀራቸው

ለ) ግንኙነትን የአንድ ሰው ብቻ አድርገው ማሰባቸው፡፡ አንዱ ወሳኝ ሌላኛው ውሳኔ የሚካሄድበት አድርገው ማሰባቸው እና ፍቅር የሁለት ሰው የጋራ ውሳኔ የሚተላለፍበት መድረክ መሆኑን መዘንጋታቸው፡፡

ሐ) ከልምዴ ላርግልህ በቲቪ ከማየው ማለታቸው

መ) አዛውንቱ ተሳሳቱ እንዴ?


3) ዳሽ ሙላ!


የአዛውንቱ ስም ——————ነው፡፡


4) ደረቅ ጥያቄ


ፀሃፊው አጀማመሩና አጨራረሱን አይተን ምን አይነት የአፃፃፍ ስታይል ተከተለ እንላለን?


አዛምድ በመቅረቱ ከባድ ይቅርታ እየጠየኩኝ ሌላ ጊዜ ግን እንደማካትት ከወዲሁ ቃል እየገባሁኝ ነው፡፡ እስከዛው ዘመድ ከዘመዱ አህያ ካመዱ ጋር ይዛመዱልኝ ስል በትህትና ነው፡፡


የናንተው ....

iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

Leave Your Comment

Post a Comment

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement