Komentar baru

Advertisement

Book of My mother

Eriyot Alemu
Feb 15, 2024
Last Updated 2024-02-24T00:00:19Z
Advertisement


ብዙ ቦታ ጠጥቼ የትም አድሬ አውቃለሁ፡፡ የጓደኛዬ ጓደኛው ጓደኛ ቤት ማደሬ ግን ዛሬም ድረስ የሚገርመኝ ነገር ነው፡፡ ሐሙስ ቀን ይመስለኛል አመሻሽ ላይ ኦሪጅናሌው ጓደኛዬ ደወለ፡፡ በድሉ ህንጻ አጠገብ የነበረው ካንቫስ ስደርስ ጓደኛዬ ካንድ ፀጉረ ልውጥ ጋር ተቀምጧል፡፡ ሰላምታ ሰጥቼ ተቀላቀልኩ፡፡ ከትንሽ ብርጭቆ እና መላመድ በኋላ ቤቱን መገምገም ነበረብኝ፡፡ ብቻዬን ግን አልነበርኩም፡፡


ቤቱ ሁሉ ነገሩ ሙሉ ቢሆንም እኔና የጓደኛዬ ጓደኛ ግን አንድ ነገር አልተመቸንም፤ ቤቱ ለኛ አጫጫስ በፍፁም የሚመች ቤት አልነበረም፡፡ ቤት ቀየርን፡፡


ከዚ በኋላ አስፈላጊ ስላልነበር ኦሪጀናሌው ጓደኛዬ ቤቱ በጊዜ መግባት ስለነበረበትም ተሰናብቶን ሄደ፡፡ ከአዲሱ ጓደኛዬ ጋር ሐትሪክ እየተሳሳቅን ስንገባ ላየን አብሮ አደግ ጓደኛማቾች ነው የምንመስለው::


የሆድ የሆዳችንን እየተጨዋወትን እየጠጣን እያለ የአዲሱ ጓደኛዬ ስልክ በመሃል ጠራ፡፡ ወጣ ብሎ አናግሮ መጣና ኢቦኒ ጓደኛው ጋር ብንሄድ ምን እንደሚሰማኝ ጠየቀኝ፡፡ ብርጭቆው ይኑር እንጂ ሁሉም ጓደኛ ነው በሚለው ህግ መሰረት ተመርቼ፣ ደስታ እንደሚሰማኝ በደስታ ገለፅኩለት፡፡ ተያይዘን ወደ ኢቦኒ፡፡ አንድ ነገር እርግጠኛ ሆኛለሁ፣ ኢቦኒ ረግጬ ቤት አድሬ አላውቅም፡፡


ከቢራ ወደ ድራፍት ከድራፍት ወደ ሜንት በሰላም ተሸጋገርን፡፡ ሁለተኛው አዲሱ ጓደኛዬ ደሞ ረሃ የሆነ ሰው ሆኖ አገኘሁት፡፡ በርግጥ ሰዓቱም የፈንጠዝያ ቢሆንም ልጁ ግን የእውነት ምርጥ ልጅ ነበር፡፡


የመጀመሪያው አዲሱ ጓደኛዬ የቺክ ጥሪ ደርሶት ይመስለኛል ተሰናብቶን ሄደ፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ሁለተኛው አዲሱ ጓደኛ ከሱ ኦሪጅናሌ ጓደኛ ጋር የምንተዋወቀው በዛች ቀን ብቻ መሆኑን መንፈስ አልገለጸለትም ነበር፡፡ ብቻ ከዚም ጋር ስንጠጣ ስንጠጣ ከልባችን ተዋወቅን ሃሃሃሃ ከኢቦኒ ወተን እሱ ሰፈር አቅራቢያ አንድ ሁለት ስንል ላየን ዘወትር ስንደጋግመው የኖርረው ጉዳይ እንጂ የዛን ቀን ብቻ አይመስለውም፡፡


ጠጣነው ጠጣነውና ዘጠኝ ሰዓት ሲል እየተማረ እንደሆነና ነገ ፈተና እንዳለው አረዳኝ፡፡ የራሴ እንደዚህ አይነት ለሊቶች ብዙ አሳልፌያልሁ፤ አንዳች ተሰምቶኝ አያውቅም ነበር፡፡ ለምን እንደሆነ ባይገባኝም በሱ ጉዳይ ግን ራሴን በጣም ወቀስኩ፡፡ ቀጥታ ወደ ቤቱ እንድናመራ ግፊት አረኩ፡፡


የክስተት ቀን ነውና ሌላ ያልጠበኩት ነገርም ተከሰተ፡፡ ቤቱ እናት አባት እህቱ የሚኖሩበት ቤት ነው፡፡ እህቱ በዛ በለሊት ተነስታ በር ከፍታ ስታስገባን፣ የመጨረሻ ተሸማቅቄ እያለ ከወንድሟ ጋር በኃይለኛው ሲሳሳቁ ደሞ ተመለከትኩ፡፡ ወደኔ መጣችና "ማነው ስምህ?" አለቺኝ፡፡ ነገርኳት፡፡ እየሳቀች፣ አባቷ ካገኙኝ ጸጉሬን ላጭተው እንደሚያባርሩኝና በጠዋት ላጥ ማለት እንዳለብኝ ነገረቺኝ፡፡ ሳቋ ቢያረጋጋም ውስጤ ግን ተረበሿል፡፡ ወደ ማደሪያችን ስናመራ በሹክሹክታ ስሜን ጠርታ ደና እደር አለቺኝ፡፡ እየሳቀች ነበር፡፡


ወንድሟ አልጋ እንደነካ ሙክክ ብሎ ተኛ፡፡ እኔ እንደዛች ሰዓት በአዕምሮዬ እጅግ ብዙ ነገር በአንዴ ሲመጣ አላስታውስም፡፡ ወዲያው ለብዙ አመታት ተኝቼው የማላውቀውን ዓይነት እንቅልፍ ወሰደኝ፡፡ ስነሳ ነው የታወቀኝ፤ ማራቶን ሩጥ ብባል እንኳ የመሮጥ አቅም የነበረኝ ይመስለኛል።  የሶስት ሰዓት የሚሆን እንቅልፍ ነው የተኛሁት ግን በሱስ ከተነከርኩ ጊዜ ጀምሮ እንደዚህ የማረፍ ስሜት ሲሰማኝ አላስታውስም። 


አዲሱን ጓደኛዬን ቀስቅሼ ስሰናበተው "ቻዎ ኤፍሬም ትንሽ ልተኛ!" ሲለኝ እየሳኩ ስወጣ እህቱ በር ላይ ቆማለች፡፡ ሳቄ ከፊቴ እንዳልጠፋ የታወቀኝ "ምን አሳቀህ?" ስትለኝ ነው፡፡ ቻዎ ኤፍሬም ስላለኝ ነው ስላት ፈገግ አለች፡፡


ጥበቃዋ ምን ፍራቻ እንደሆነ ስለገባኝ ፈጠን ፈጠን ብዬ ወደ በሩ አመራሁ፡፡ ከልቤ አመስግኛት ወንድሟ ፈተና አለብኝ ሲል እንደሰማሁ እና ሰዓት እንዳያልፍበት ነግሪያት ስሄድ "ቻዎ ኤፍሬም" አለቺኝ፡፡ ዞሬ ሳያት እየሳቀች "ቻዎ….. ስምህን አቀዋለሁ" አለቺኝና ገባች፡፡


በመሪ የገባሁብት መንገድ ያለ መሪ ቢያስቸግረኝም እንደምንም አስፋልት ዳር ወጥቼ የሜክሲኮ ታክሲ ያዝኩ፡፡ ሌላ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት አዳር ሳድር በጠዋት ቤቴ ሄጄ እንቅልፌን፣ ወይ ካቆመበት እቀጥለው፣ ወይ እንደ አዲስ እጀምረው ነበር፡፡ ያን ቀን ግን ቁርስ በልቼ ቀጥታ ወደ ወመዘክር ላይብረሪ አመራሁ፡፡


ወመዘክር እንደደረስኩ ቀኑ ይፈቅዳል ብዬ ባሰብኩት ሊትሬቸር መደርደሪያ ጋር ቆምኩ፡፡ አንድ መጽሃፍ አይኔ ገባ፡፡ book of my mother ይላል፡፡ ከቨሩ ሳበኝ የገጽ ብዛቱን አየሁ (124 ነበር)፡፡ ትንሽ መግቢያውን ቆሜ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ደራሲው በ73 አመቱ ድንገት በማስተር ፒስ በሆነ ሌላ ስራው ድንገት ፌመስ እንደሆነ ስረዳ መጽሃፉን ለማንበብ ደረጃውን መውጣት ጀመርኩ፡፡ ኦድ የሆነ ነገር በጣም ነው ደስ የሚለኝ፡፡


ሁለት አንቀጽ እንዳነበብኩ ነው መጽሃፍ ቅዱስ የማንበብ አይነት ስሜት የተሰማኝ፡፡ የጽሁፉ ዘዬ፣ ውበት፣ ፍሰት እጅግ ገራሚ ነው፡፡ ከርዕሱ ጀምሮ መጽሃፍ ቅዱሳዊ አጻጻፍ ስሜት ይጭራለ፡፡ ታድያ ብዙም ሳልቆይ ነው ከደራሲው ፀፀት ጋር መፋጠጥ የጀመርኩት፡፡ ሙሉ መጽሃፉ እናቱን ካጣ ከጊዜያት በኋላ ወደ ኋላ ተመልሶ ነገሮችን በፀፀት የሚመለከት ሰው ታሪክ ነው፡፡


ስለ ፀፀት ከዚ በፊት ባውቅም፣ እንደዚህ ግን ስጋ ለብሶ ተከስቶ አይቼው አላውቅም፡፡ እናቴ በህይወት እያለች የደራሲው ስሜት እንዲህ ተጋኖ ሲሰማኝ፣ እናቱን አጥቶ ለሚያነበው ሰው ነው ገና ሳስበው የሰቀጠጠኝ፡፡ መጽሃፉን እስካጋምሰው ድረስ ቀና አላልኩም ነበር፡፡ ከዕንባዬም ጋር ከባድ ትግል ውስጥ ነበርኩ፡፡


ቀላል የሚባሉ ነገሮች በደራሲው ፀፀት ውስጥ ምን ያህል ትርጉማቸው ላቅ ያለ መሆኑን እየተረዳው ነው፡፡ በፊት በፊት የእናትን ውለታ መመለስ ሲባል፣ በአመዛኙ በቁስ ዙሪያ ብቻ የሚሽከረከር ይመስለኝ ነበር፡፡ ለካ የእናትን ስሜት መረዳት ከቁስም የላቀ ነበር፡፡


ደራሲው ቀላል የሚመስሉ ነገሮች አልፎ ሲያስባቸው የእግር እሳት ሆነውበት ተጋብቶብኝም ሳይ በጣም ነው የደነገጥኩት፡፡ ለምሳሌ እናቱ በእግዜር እንደማያምን እያወቀች ቤተስኪያን ሂድ እያለች ስትመክረው የነበረውን ጽሁፍ ሳይ ከራሴም ጋር እያዛመድኩ ነበር የምደነግጠው፡፡ በወቅቱ እኔም ኢአማኒ ብሆንም እናቴ የሱን አይነት ምክር ትመክረኝ ነበር፡፡ ግብረ ምላሼ ግን ልክ አልነበረም፡፡ የተግባሩ ይቅርና የቃሉ ነው ልክ ያልነበረው፡፡


እናቱ ይሁዲ በመሆኗ ሃይማኖታዊ አመለካከቷ ከኛ ባህል ጋር ስልሚተሳሰር ብዙ ስሜቶቹ በቀላሉ ይጋቡ ነበር፡፡ ካላጋነንኩ በፍቅር ስለ ፍቅር ከተጻፉ እንደዚህ ጥልቅ ነገር አንበቤ አላውቅም፡፡ ከመጽሃፉ አጋማሽ በኋላ ያለሁበትን ሁሉ ረስቻለሁ፡፡ ዕንባዬ እንደዛ ሲወርድ አስሬ በአፍንጫዬ ዙሪያ እየደረስኩ ብመለስም ስለማንም ግድ አልሰጠኝም፡፡


የደራሲው የግሉ ፀፀት አለንጋ ሆኖ እየገረፈኝ ሳለ መጽሃፉ ማሳረጊያ ላይ "እናንት እናቶቻችሁ በህይወት ያሉላችሁ ፍጡሮች..." እያለ በኔ የደረሰው አይድረስባችሁ ዓይነት ነገር የሚመስል… ማስተዋልን ይመክራል፡፡ መጽሃፉን እዛ ድረስ አንብቦ ለመጣ ሰው፣ የደራሲው የመጨረሻ ግሳፄ አጥንቱ ድረስ ዘልቆ ይሰማዋል፡፡


መጽሃፉን ጨርሼ እንደተነሳው ምድርና ሰማዩ ነው የተቀላቀለብኝ፡፡ በፍጥነት የተጠቀምኩበትን ጠረጴዛ ለመያዝ አልቻልኩም፡፡ ጭንቅላቴ 'ጓ' ሲል ብቻ ነው የሰማሁት፡፡ ደግነቱ ፀጉር ስለነበረኝ ጭንቅላቴ ብዙ አልተሰማውም፡፡ አሁን ግን ያን አወዳደቅ ሳስበው ወደ ራሴ የመለሰኝ አወዳደቅ ይመስልኛል፡፡ ላይብረሪው ጢም ማለቱንም ያኔ ነው ያወኩት፡፡ የማውቀው ሰው ስፈልግ አንድ ሶስት አየሁ፣ በኋላ አብረን እንስቃለን ብዬ ምንም እንዳልተፈጠረ ተረጋግቼ ከላይብረሪው ወጣሁ፡፡


አጫሽ ከነበርኩበት ጊዜ አንስቶ አጫሽ እንደነበርኩ የረሳሁበት ብቸኛ አጋጣሚ ነው፡፡ 'እንዴ አጭስ እንጂ' ብዬው ነው ራሴን ወደማጨሻ ስፍራ የወሰድኩት፡፡ መጽሃፉ የሰጠኝ ሌላ ነገር ቢኖር እናትን ሆኖ ማሰብን ነው፡፡ እናቴን ሆኜ ራሴን ሱሰኛ አርጌ ሳስበው ማመን ነው የከበደኝ፡፡ እናት አፍንጫዋ ስር ልጇ ሱሰኛ ሆኖ ማሰብ ይሰቀጥጣል፡፡ ያውም ከልቧ የምትተማመንበት ልጇ፡፡ በሱስ ዙሪያ ምንም ብላኝ ስለማታውቅ ስሜቷን ለሰከንድ አስቤው አላውቅም ነበር (ወይም ውስጤ ማሰብ አይፈልግም ነበር)፡፡ ALbert Cohen የተባለ ሰው ግን ሁሉ ነገሬን ቀየረው፡፡


ታክሲ ይዤ ወደ ቤት ሳመራ እውነት ለማውራት እናቴን በህይወት የማገኛት አልመሰለኝም ነበር ፡፡ በሆዴ እንዲህ እያልኩ ነበር "አንተ እናቴ ሁሌ የምትለምንህ አምላክ ካለህ እናቴንም ጠብቅልኝ፣ ፀሎቷንም ስማት!"፡፡ ሁሌ ራሷን በመቁጠሪያ እየገረፈች 'ታሪክ ቀይር ታሪክ ቀይር ታሪክ ቀይር….!' ስትል እሰማት ነበር፡፡ በሃሳቤ ታይቶኝ ታከሲ ውስጥ "አሜን" ስል ድመፄ ካፌ ወጥቶ ነበር፡፡


ቤት ስደርስ እናቴ በረንዳ ላይ ቁጭ ብላ ወደ በር እያየች ነበር፡፡ Oh Maman ይላል Albert Cohen አሳዘንቺኝ፡፡ ገና ስታየኝ ፊቷ ላይ እፎይታ አንብቢያለሁ፡፡ ተነስታ ወደ ውስጥ ስትገባ ይሄን ብቻ ነው ያለቺኝ…."እሪዮት ጭራሽ ሰው ያስባል ብሎ ማሰቡንም ተውከው" .... ውጪ አድሪያለሁ ብዬ አለመደወሌ ሁላ ትዝ ያለኝ ያኔ ነው፡፡ የእማዬ ግን በጥንቃቄ የተሞላ ንግግሯ ይሄ ብቻ ነው፡፡ ጫን አርጋ የመናገር ብዙም ልምዱ ባይኖራትም ጫን ብትለኝ ይብስበታል ብላ ስለምታስብ በጭራሽ አታደርገውም፡፡


የተነሳቺው ምግብ ልትሰጠኝ እንደሆነ ስለገባኝ ምሳ በልቻለሁ እቃ ልወስድ ነው የመጣሁት ብዬ ቀበጣጥሬ ተመልሼ ወደ ጫት ቤቴ አመራሁ፡፡ ውጪ ካደርኩ፣ 6 ሰዓት ሲል ጫት ቤት እንደምገኝ የሚያውቀው ወዳጄ ሰዓቱን ገፍቼ ስለተከሰትኩ "ጫት የተውክ ሁሉ ነው የመሰለኝ" ብሎ በቀልድ ተቀበለኝ፡፡ እስክመረቅን ሌላ ሌላ ጉዳይ ላይ ቆየሁና ስመረቅን "ሱስ ብተው ምን የማረግ ይምስልሃል?" ብዬ ጠየኩት፡፡ "ሲጀምር አንተ ሱስ አትተውም፡፡ ብትተው ግን ካገር ወተህ ዶክተር ኢንጂነር ተብለህ….." ምናምን ሲለኝ "በኤሌክትሪካል…" ብዬ ስጮህ ለራሴም የነገርኩት ነገር ነበረኝ፡፡


ስርዓት ማለት አባቴ ነው በቤታችን፡፡ በህጻንነቴ ባጣውም ህጎቹ ግን አሁንም ድረስ ትዝ ይሉኛል፡፡ ብዙ ነገር በዓይኖቹ ነበር የሚነግረን፡፡ ይሄን ፍራቻ ሱስ ከጀመርኩ ጊዜ አንስቶ ለ10 አመታት የአባቴን ፎቶ ቀና ብዬ አይቼው አላውቅም ነበር፡፡ ዓይኖቹን እጅግ እፈራቸው ነበር፡፡ ለወዳጄ ቀኑ ነውና ይሄንና የመሳሰሉትን ነገሮች ነግሬው.. ሱስ ብተው መጀመሪያ የማረገውን ነገረኩት፡፡ "ከእናቴ የነጠኩትን የልጅነት አመታት አጠገቧ ሆኜ እመልስላታለሁ" ስለው... 'ሚጣ ትሙት ሪታ ሱስ ልትተው ትችላለህ' አለኝ፡፡ ይሄን ወዳጄ አስገድጄው ቢሆንም ቅሉ በሱስ ምስቅልቅል ብዬ ስዳክር 'ሱስ ልተው ነው' ስል ያመነኝ ሁለተኛ ሰው ሆኖ ተቆጥሮ ነበር፡፡ እድሜ ልኬን የማረሳቸው ሁለት ሰዎች አሉ፡፡ ካገኘሁዋቸው አመታት የሆኑኝ ሁለት ሰዎች…ደጋግሜ ደጋግሜ ያመሰገንኳቸው ሁለት ሰዎች አሉኝ፡፡ በጭለማው ዘመንህ ብርሃንህን ማየት የሚችሉ ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ እነዛ ሁለት ሰዎችም እንዲሁ ናቸው። 


አንተ የሚጣ አባት ይኸው ባልኩህ ልክ አመታት ሰፍሬ፣ ቃሌን ሳልሸራርፍ መጠበቄን ላሳይህ እነሆ ተከስቻለሁ፡፡ 'ከዛስ?' ብለኸኝ ነበር አይደል?.... "ህይወቴን እንደ አዲስ እፅፈዋለሁ!" ብዬህ ነበር፡፡ ምን ያህል ቃሌን በመጠበቅ እንደምደሰት ታውቃለህ መቼም… መኖር የሚሰማኝ ቃሌን ስኖረው ነው እልህ አይደል?…. ያ ነው የሚሆነውም፡፡ በፍጹም እንደምታምነኝ ስለማውቅና የምትጠብቀውን ስለማውቅ ነው ይሄን ማለቴ፡፡ እስከዛው ባለህበት ግን ተመስገንልኝ፡፡ ቃሌን ለምሰጠውም ለምረከበውም ልቤ ትልቅ ቦታ አለው፡፡


ማስታወሻ:- ሱስ መተው ከጀመርኩበት አንድ መውደቅ መነሳት ከነበረው አንድ አመት ጋር፣ ሱስ የተውኩበት ጊዜ ወደ 10 አመት እየተጠጋ ነው፡፡ ሱስ ለመተው ብዙ ምክንያት ቢኖረኝም፣ እናቴ ቁጥር አንዷና ትልቁ ስዕሏ እሷ ብትሆንም፣ ሱስ የተውኩት ግን ... ለራሴና ለራሴ ብቻ ብዬ ነው... ስል አስረግጬ ነው፡፡ በሱስ ዙሪያ የሚከታተሉኝ ሰዎች ያልሆነ ብዥታ እንዳይኖራቸው ስለምፈልግ ነው አፅንዖት መስጠቴ፡፡ ሱስ የሚተውበት ብዙ ምክንያት ቢኖርም የሚተወው ግን ለራስና ለራስ ሲባል ብቻ ነው፡፡ ይሄ መቼም መዘንጋት የለብትም፡፡


መጽሃፉን ማንበብ ለምትፈልጉ እነሆ ፒዲኤፉ Book of My Mother


iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

2 comments:

  1. እሪዮት ላስቸግርህ ይሄን መፅሃፍ በፒዲኤፍ ማግኘት እችላለሁ? እኔ ፈልጌ ፈልጌ ስላጣሁት ነው። አመሰግናለው።

    ReplyDelete
    Replies
    1. ይኸው ከላይ አድርጌልሃለሁ። ለሌላ ጊዜህ ደግሞ የትኛውንም መጽሃፍ ስትፈልግ Z-library የሚለውን ተጠቀም። በአለማችን እጅግ ትልቁ የመፅሃፍ ስብስብ ያለበት ዌብሳይት ነው። ፈልገህ የምታጣው ከ1 ፐርሰንት በታች ቢሆን ነው። ውድ ውድ ከሆኑ አካዳሚክ መጽሃፍት ጋር በተያያዘ ይመስለኛል መነሻው FBI እየተከታተለ ይዘጋዋል። እነሱም ሌላ አማራጭ ይጠቀማሉ። አሁን በዚህ ወር እየሰራ ያለ አድራሻ ልስጥህ https://z-library.se/ ሂድና ተመዝገበህ በመጽሃፍት ዋኝ። ይሄም ከተዘጋ መነሻህን z-library አድርግና ኃሰሳ ውጣ ወይም ኢሜይል አድርግልኝ። ካለው እተባበርሃለሁ። z-library alternative ተብለው የምታያቸው ከሞላ ጎደል ፌኮች ናቸው። የምትፈልገውን አታገኝባቸውም። እንግዲህ ከFBI አይን ይሰውራቸው እያልኩ አጠቃልላለሁ። አመሰግናለሁ።

      Delete

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement