Komentar baru

Advertisement

ስለ ሱስ መሰረታዊ ነገሮች በሙሉ!

Eriyot Alemu
Mar 3, 2023
Last Updated 2023-08-06T20:08:33Z
Advertisement

ክፍል አንድ



<<ከአንድ ሱስ ስትፋታ ያን ሱስ የምትተውበት ምክንያት ላይ ብቻ ካተኮርክ ይቆይ እንጂ ወደዛ ሱስ መመለስህ አይቀርም>>

ይሄን የምለው ብዙ መውደቅ መነሳትን ካሳለፈው ልምዴ ተነስቼ ነው፡፡ ምሳሌ እንይ...

ለሚወዳቸው ሰዎች ብሎ ሱስ ተውኩ የሚል ሰው... እወዳቸዋለሁ ያላቸው ሰዎች ትንሽ ጓ ገጭ ካሳዩት ጭንቅላቱ መጀመሪያ የሚያስበው ሱሱን መልሶ መጀመር ነው፡፡ ከዛ በኋላ ያለው ነገር እንደ ሰውዬው ቢወሰንም ቅሉ፡፡


ለጤናው ብሎ ሱስ የተወ ሰው ጤናው ሲሻሻል መጀመሪያ የሚያስበው... ከበፊቱ በተለየ ሁኔታ ጤናውን ሳይጎዳ ሱሱን መጠቀም ነው፡፡ ከዛ ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ ጤናውን ዘጭ ሲያደርግ ራሱን ያገኘዋል፡፡

ምን እያልኩ ነው? ስለፈራን ሱስ አንተውም፡፡ እንደዛ ቢሆን ኖሮ <ቶባኮ ሲሪየስሊ ዳሜጅ ኸልዝ> የምትለው ኒያላ ፓኬት ላይ ያለችው ማስጠንቀቂያ ብቻዋን አልአጫሽ ታደርገን ነበር፡፡ መጎዳታችንን ማወቃችን ከሱስ አያድነንም፡፡ ከሱስ የሚያድነንም ዘላቂው መፍትሄም ያን ሱስ ለምን እንደምናደርገው በትክክል ማወቃችን ብቻ ነው፡፡ ያንን ማወቃችን ሱስ ለመተው ብቻ ሳይሆን ትቶም እስከመጨረሻው ለመኖር ዋነኛው መንገድ ነው፡፡ የብዙሃኑ ችግር ሱስ መተዉ ብቻ አይደለም መልሶ መጀመሩ ነው፡፡


እዚጋ ይሄን የሚያሳይ ልክ ያልሆነ ግን በድግግሞሽ እውነት የሚመስል አባባል እንይ << ሱሰኛ ያርፋል እንጂ አያቆምም>> ... ይህ አባባል የብዙዎችን ወደ ሱስ መመለስ ቢያሳይም እውነት ግን አይደለም፡፡ እውነት ካደረግነው እናምነዋለን ፤ ካመነው ደግሞ መቼም ሱስ አንተውም፡፡ በራሴ ልምድ ሳወራ ይሄ አባባል ብዙ ተጫውቶብኝ አልፏል፡፡ ከዚ አባባል የዳንኩት መጀመሪያ የፈጠረው ሰውዬ ደነዝ መሆኑን ያወኩኝ ጊዜ ነው፡፡ ከዚ አባባል የዳንኩት ይሄን አባባል ሲያስተጋቡ የኖሩት አባባሉን በሚገባ ሳይረዱ የሚያስተጋቡ መሆናቸውን ያወኩ ጊዜ ነው፡፡ ዕውቀት ነፃ ያወጣል፡፡ ይሄ አባባል ያልሞከሩ ተሸናፊዎች አባባል ነው፡፡ አሸናፊ ደግሞ የተሸናፊዎችን አባባል አይሸከምም፡፡ መንገዳችን የሚቀየረው ልክ ያልሆነ እምነታችን ሲቀየር ነው፡፡


ሌላውን ሱስ እንተውና ይቺን ሚጢጢዋን ፌስቡክ እንይ... ያው ብዙ ሰው በአንድም በሌላም የሆነ ልምድ ይኖረዋልና ነው ፌስቡክን መጠቀሜ፡፡

ልብ ብላችሁ ከሆነ ለአንድ ለሁለት ወር ፌስቡክ የተዉ ሰዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የሆነ ነገራቸው ሲለወጥ ታስተውላላችሁ፡፡ አትኩሮት ከሰጣችሁ መልካቸው ራሱ ለውጥ ይኖረዋል፡፡ የእንቅልፍ ሰዓታቸው ስለተስተካከለ ይሆናል ብለን እንለፈው፡፡ ሌላም ሌላም ለውጥ ይኖራቸዋል፡፡

ታዲያ ለውጣቸውን በሚገባ ከተረዱ በኋላ ሮጠው ወደ ፌስቡክ ይመለሳሉ፡፡ ለምን? ቀድሞ ፌስቡክ ከሚጠቀሙበት ምክንያት አንዱ ራስን ማሳየት ስለነበረ። እዚጋ ፌስቡክ የተዉበትን ምክንያት ከጊዜ በኋላ ረስተውታል ማለት ነው፡፡ ችግሩ ከስሩ አልተፈታም ማለት ነው።


አጠቃላይ ስለ ሱስ ባህሪ እናውራ


ብዙ ጊዜ ጓደኞቼ በሱሰኞች መሃል ያለውን ልዩነት በኔ መረዳት ልክ እንዳስረዳቸው ይጠይቁኛል፡፡ ምሳሌ ጥሩ ነውና በምሳሌ እናውራ።




የሱስ ህይወት ማለት መነሻ እንጂ መድረሻ በሌለው የባህር ላይ ጉዞ ይመሰላል፡፡ ከቀን አንድ ጀምሮ ተጓዡ በትንሽ በትንሹ የሚሰምጥበት የባህር ላይ ጉዞ፡፡ አብዛኛው ተጓዥ ለተወሰኑ ጊዜያት መስመጡን አያስተውልም፡፡ የእያንዳንዱ ሰው የመስመጥ ሁኔታ እንደ አጓጓዙ፣ እንደ ኑሮው፣ እንደ አመለካከቱ፣ እንደ የገንዘብ አቅሙ ይለያያል፡፡


እስኪ ተጓዦችን ጥቂት እንከፋፍላቸው...


1) አንዳንድ ተጓዦች መስመጣቸውን ሳያውቁት (ሳያማርሩት)... እስከ መጨረሻ ጀምበራቸው መጥለቂያ ድረስ ሊጓዙ ይችላሉ፡፡ ዙሪያቸው ግን መስመጣቸውን በሚገባ ያውቅላቸዋል፡፡ ሆኖም አማረሩትም አላማረሩትም በመስመጥ የሚጠቀም የለምና ጉዳቱ ያገኛቸዋል፡፡

2) አንዳንዶች ተጓዦች ደግሞ ከጉዞው ትንሽ ፈቀቅ እንዳሉ እየሰመጡ መሆናቸውን በሚገባ ልብ ይላሉ፡፡ ሆኖም የበለጠ ላለመስመጥ ትግል አያረጉም፡፡ ሆኖም እየሰመጡ መሆናቸውን በማወቃቸው ብቻ ከመጀመሪያዎቹ የበለጠ ስለሚንፈራገጡ፣ የበለጠ የሚሰምጡ ናቸው፡፡

3)ሶስተኛዎቹ ተጓዦች በጉዟቸው እየሰመጡ እንዳሉ አውቀው ወደ የብሱ ለመመለስ የሚያስቡም ናቸው፡፡ እነዚህ የመዳን ተስፋ ያላቸው ቢሆኑም ከመጀመሪያዎቹ ሁለቱ በእጅጉ የሚጎዱት ናቸው፡፡ የበለጠ ስለሚታገሉ የበለጠ ይሰምጣሉ፡፡ ወደፊትም ወደኋላም ጉዞው የባህር ነው፡፡ ሆኖም የነዚህ ጉዞ ወደ የብስ ስለሆነ ቢሰቃዩም መድረሻ ተስፋ አላቸው፡፡ ታግለው ወደሚያውቁት የብስ ሊመለሱ ይችላሉ፡፡ 


ማህበረሰቡ ግን በሚገባ የማይረዳው ሶስተኞቹን ነው፡፡ ራሳቸውን የጣሉ፣ ዙሪያቸውን ያልተረዱ አድርጎ ይስላቸዋል፡፡ በተሻለ ግን አለምን የሚረዱ ናቸው አብዛኞቹ፡፡ እስቲ በሱስ ህይወቱ እጅግ ዝብርቅርቅ ያለ ሰው ትላንቱን ለማየት ሞክሩ፡፡ የሆነ የሚናገረው ነገር አለ፡፡ የበለጠ የሚታገሉ የበለጠ ይሰምጣሉ ነው ነገሩ፡፡ የበለጠ የሚታገሉ የበለጠ አለምን ይረዳሉ ነውም ነገሩ፡፡ እንቀጥል...


ሱስ የጀመርንበት ቀን አንድ ጀምሮ ሁለት ማንነት ይፈጠራል....


<<የትኛውንም ሱስ የምንጠቀመው ሱስ የሚያሲዝ ንጥረ ነገር ስላለው ነው>> ይህ ዋነኛው ነገር ቢሆንም የሱሰኛን ህይወት ከቀን አንድ ጀምረን እንየው፡፡

የትኛውም ሱሰኛ ሱስ ከጀመረባት ከቀን አንድ ጀምሮ ሁለት ሰው መሆን ይጀምራል፡፡ 

1) ከሱስ በፊት የነበረው ሰው (የድሮው ማንነት እንበለው እንዲመቸን) እና 

2) ልክ ሱሱን ሲጠቀመው የሚፈጠር አዲስ ማንነት (አዲሱ ማንነት እንበለው እንዲመቸን)




ልክ ሱስ ሲጀመር መላው እኛነታችንን የሚቆጣጠረው አዲሱ ማንነት ነው፡፡ የትኛውም ሱስ ሲጀመር የዶፓሚን ለውጥ ስለሚኖር ደስ የሚለው ስሜት ስላለ... የድሮው ማንነት አፉን ዘግቶ ይቀመጣል፡፡ አዲሱ ማንነት ያለ ከልካይ ለእያንዳንዱ የሱስ እንቅስቃሴያችን ትርጕም መስጠት ይጀምራል፡፡ የሱሱን ጥቅሞች በማስረዳት ይጀምራል፡፡



~> ሱስ ደስታ ይሰጣል

~> ሱስ ድፈረት ይሰጣል

~> ሱስ ማህበራዊ ህይወትን ያቀላጥፋል

~> ሱስ ጉልበት ይሠጣል

–> ሱስ ትኩረት ለመሰብሰብ ይረዳል በየቀኑ እነዚህን የመሰሰሉ ነገሮች ለድሮው ማንነት እያስረገጠ ይነግረዋል፡፡ መጀመሪያ ሰሞን እነዚህ ከላይ ያሉ ነገሮች ያሉ ያሉ ስለሚመስሉ የድሮው ማንነት እያጨበጨበ ነው የሚቀበለው፡፡ ከዛ ህይወቱን ለአዲሱ ማንነት አሳልፎ ሰጥቶ ለረዥም ጊዜ ጥልቅ እንቅልፍ ይተኛል፡፡


የሁለቱ ማንነቶች መሰረታዊ ልዩነት


አዲሱ ማንነት ለመኖር የግድ ሱሱ ያስፈልገዋል፡፡ ያንን ለማግኘት ደግሞ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ያለ ሱሱ መኖር አይችልም፤ ይሞታል፡፡ በዚህ የተነሳ ከድሮው ማን ነት የተሻለ ያስባል፡፡

የድሮው ማንነት ግን ለመኖር የሚያስፈልገው ምግብ እና ውሃ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ደግሞ እንደ ሱስ ብዙ ስለማያለፉ በልምድ በአዲሱ ማንነት ይበለጣል፡፡ በዚህ የተነሳ የድሮው ማንነት ለአዲሱ ማንነት ባሪያ ነው፡፡ የተባለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ አዲሱ ማንነት ስለ ሱስ አስፈላጊነት የሚያስፈልገውን ሁሉ ካስረዳው በኋላ በተራው ጥልቅ እንቅልፍ ይተኛል።



ከአመታት በኋላ


ከብዙ ጊዜያት በኋላ የድሮው ማንነት መሰላቸት ይጀምራል፡፡ ይሄ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ስለ ሱስ ጥቅም የተነገረው እና ያመነው ነገር በሙሉ ከጊዜ በኋላ ልክ አለመሆኑን ይረዳል፡፡ ለምሳሌ ሱስ ማህበራዊ ህይወትን ያቀላጥፋል የሚለው እምነቱ ተሸርሽሮ ተሸርሽሮ አልቆ... ሱሰኛው ማህበራዊ ህይወቱ የተመሰቃቀለ ሰው ሆኖ ራሱን ያገኘዋል፡፡ ሱስ ድፍረት ይሰጣል የሚለው እምነቱ መንምኖ መንምኖ... ሱስ ሱሰኛውን የአለም ፈሪ እንዳደረገው ይረዳል፡፡ የትኛውንም ነገር ለማድረግ ከመወሰን በፊት ሱስን መፈለግ የፍርሃት ጥግ ነው፡፡ ሱሰኛው ህይወቱ በስጋትና ፍራቻ መከበቡን በሚገባ ይረዳዋል፡፡ ስልክ ለማውራት እንኳ ማጨስ (መጠጣት) መፈለግ የፍርሃትን ጥግ ነው የሚያሳየው፡፡ እና አሁን የድሮው ማንነት መጠየቅ ይጀምራል፡፡



እዚህ ሰዓት ላይ ጥልቅ እንቅልፍ ተኝቶ የነበረው አዲሱ ማንነት ይነቃል፡፡ ስማርት ስለሆነም መከራከሪያዎቹን ይቀይራል፡፡ << ጥያቄህ ተገቢና ትክክል ነው፡፡ ሱስ ጎጂ ነገር ነው፡፡ ለመተው ግን ጊዜው አሁን አይደለም... ያ ጊዜ ሲመጣ ትተዋለህ!>> የሚል ማደንዘዣ ይወጋውና ወደ ቀደመ ጥልቅ እንቅልፉ ይመለሳል፡፡



አዲሱ ማንነት የድሮውን ማንነት በደንብ ያውቀዋል፡፡ ደካማ እና ጠንካራ ጎኑን በሚገባ በልቶታል፡፡ የድሮው ማንነቱም ከአዲሱ ማንነት ጋር በሃሳብ በመስማማቱ ደስ እያለው የተባለውን ያምናል፡፡ <<ያ ቀን ሲመጣ እተዋለው>> ብሎ የቀደመ ኑሮውን ይገፋል፡፡ ሱሰኛውን መመገቡን ይቀጥላል፡፡ አዲሱ ስማርት የሆነው ማንነት ግን ያ ቀን በራሱ መቼም እንደማይመጣ ያውቀዋል፡፡ ያ ቀን ራስህ ድንገት አሁን የምትፈጥረው ብቻ ነው፡፡ ስፔሲፊክ ሆኖ ሚስት ሳገባ እተዋለው ያለ... ልጅ ስወልድ ብሎ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ አለም የምክንያት ደሃ አይደለችም፡፡ ምክንያቶች አያልቁም፡፡




ከሌላ አመታት በኋላ...


ይሄ ይሄድና ይሄድና የድሮው ማንነት አቅሙን ሁሉ ጨርሶ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ ከዚ በኋላ ያለው ምርጫ ሱስ መተው ብቻ እንደሆነ ያምናል፡፡ አሁንም አዲሱ ማንነት ያለ የሌለ ኃይሉን ሰብስቦ ይነሳል፡፡ ከማንም ቀድሞ ለድሮው ማንነት አለመቻሉን የሚነግረው እሱ ነው፡፡ በደንብ ስለሚያውቀው... ሱስ መተው የማይችልበትን ምክንያት አንድ በአንድ ያስረዳዋል፡፡ ያለ ሱስ መኖርን እጅግ አስፈሪ እንደሆነ አርጎ ይስልለታል፡፡ ያለ ሱስ ከመኖር በሱስ መሞት እንደሚሻል ጭምር ለማሳመን ይጥራል፡፡



ይህ ነው የብዙ ሰዎች አዲስ ወሳኝ የህይወት ምዕራፍ መጀመሪያ፡፡ ብዙዎች ባለማወቅ እዚህ ጋር እጅ ይሰጣሉ፡፡ ጥቂቶች ቆራጦች ግን ሲያስቡት ሌላ ከባድ የሚመስል፣ ሲገቡበት ግን ቀላል የሆነ ትግል ውስጥ ይገባሉ፡፡ ጥቂት ዘዴዎችን ቀድሞ በማጥናት ብቻ የምናሸንፈው ዓይነት ትግል ነው፡፡



አዲሱን ማንነት እዚጋ እናሰናብተዋለን፡፡ ከዚ በኋላ እሱን የሚሰማ ጭራሹኑ ያበደ ሰው ነው፡፡ አሁን የድሮው ማንነት ብቻውን እናግኘውና ምን ማድረግ እንዳለበት እናንሳ፡፡


ክፍል ሁለት



ድሮ በጣም ድሮ ነው… የጥርስ ሕክምና ሳይኖር በፊት የእንግሊዟ ንግስት ኤልሳቤጥ አንደኛ፣ ጥርሷን በጠና ታመመች። ያው እንደምታውቁት የጥርስ ህመም እጅግ ከባድ እንደሆነ የተክለሃይማኖት ከፍተኛ ክሊኒክ ማስታወቂያ ጨርሶታል። <<እም—ምም የጥርስ ህመም>> እያለ በሚያስገመግም የማስታወቂያ ድምፅ ህመሙን ቁልጭ አርጎ በዓይነ ህሊና እንድንመለከተው አድርጎናል። እናም ወደ እቴጌዋ ስንመለስ መላው የእንግሊዝ ህዝብም ከንግስቲቱ ጋር አብሯት ታመመ። ለሊት ለሊት ሲያሯሩጣት አብሯት የሚሮጠው ቁጥር እልፍ ስለነበር ታሪክ ይሄን ያህል ብሎ እንቅጩን ባይናገርም ወፈ ሰማይ ህዝብ መሆኑን ግን መስክሮ አልፏል ሃሃሃሃ 


በስተመጨረሻ ንግስቲቱ ህመሟ እጅግ ሲፀና እንደ ተራ ሰው ጥርሷን ለመነቀል ወሰነች። (ድሮ ተራ ሰው ነው ጥርሱን የሚነቀለው)። የኛ ነገስታቶች ግን ጥርሳቸውን ሲታመሙ አጠፋሪስ ይታጠኑ እንደነበር አንድ አዛውንት ሲያወሩ የሰማው መስሎኛል። እስቲ ጊዜ ካላችሁ አጣርታችሁ ትነግሩኛላችሁ። ወደ ኤላሳቤት ስንሄድ… ጥርሱን ያመመው ማንኛውም ሰው ጥርሱን መነቀል እንደሚፈራው ኤልሲም  ፈራች። በዚ ጊዜ አንድ ትልቅ በለንደን ከተማ የተከበሩ ሰው… ወደ ንግስቲቱ እየገሰገሱ መጡ። ማንነታቸው አስፈላጊ ስላልሆነ ነው የተዘለለው።

እንደ ተለመደውም ንግስት ሆይ ሺ አመት ይንገሱ ብለው አደገደጉና፣ ብዙ ተራ ሰዎች ጥርሳቸውን ሲነቀሉ እንዳዩና ጥርስ መነቀል ተራ ኢምንት ነገር እንደሆነ ተናግረው…  ያወሩትም እውነት መሆኑን ለማሳየት ፊለፊቷ ራሳቸው መነቀል እንደሚችሉ ያብራራሉ። ኤልሲም ያለ ምንም ይሉኝታ "እስቲ ያሳዩኝ" ብላ አዛውንቱን ፊቷ እንዲቀመጡ በንግስትኛ ትወስናለች…  ያው በፒንሳ ይሆናል ብለን እናስባለን በዛ ጊዜ ፒንሳ ከነበረ…  ካልሆነም በሆነ ብረት ነው የሚሆነው… ብቻ አዛውንቱ ጥርሳቸውን ነክሰው፣ ጥርሳቸውን ተነቅለው ለንግስቲቱ ያላቸውን ክብር፣ ፍቅር ወዘተርፈ አሳዩ። ከዛ በኋላ ኤልሲ የምትወደውን ቆሎ በነፃነት መቆርጠም ጀመረች። እንግዲህ እንዲህ ነው ኤልሳ ቆሎ የተጀመረው ሃሃሃሃ  ወደጉዳያችን እንሂድ… 


ሱስ አንዴ መተው ያሰበ ሰው፣ ራሱን ጥርሱ እንደተነቃነቀበት ሰው ይቁጠረው። "የተነቃነቀ ጥርስ ካልወለቀ ጤና አይሰጥም" እንዲል ብሂሉ… አንዴ መተው የፈለገ ሰው ሁነኛ መዳኛው ማስነቀሉ ብቻ ነው።  ያለበለዚያ ትርፉ ከራሱ ጋር ሲጠዛጠዝ መኖሩ ነው። ይሄን የጥርስ ጉዳይ ያነሳሁት ሱስ ለሚተውም ሰው ጥሩ ምሳሌ ስለሆነ ጭምር ነው። 


አንድ ሱስ ለመተው የሚታገል ሰው እፎይታውን የሚያገኘው… ልክ ጥርስ ታማሚ ጥርሱን ሲነቀል እፎይ እንደሚል… ሱሰኛውም እፎይ የሚለው ሱሱን ሙሉ በሙሉ ሲተው ብቻ ነው። "አጠቃቀሜን መቀነስ፣ ራሴን መቆጣጠር" እያለ የሚያስብ ካለ <<ሞክረህ ሞክረህ እስክትነቃ ድረስ መልካም የመጃጃል ዘመን>> ከማለት ውጪ ምንም አይባልም። ሱስ <መቀነስ> የሚባል ምርጫ የለውም። ያለው ምርጫ ሙሉ በሙሉ መተው ብቻ ነው። ለምን? የእለቱ አጀንዳችን አይደለም። 


እዚህ ድረስ ከተግባባን…  አንድ ሱሰኛ ሱስ መተው ሲያስብ ቀጥሎ የሚገጥመውን ደግሞ በሚገባ ማወቅ እንዳለበት እናወራለን። ቀድሞ ያወቁት ነገር ከብዙ አደጋ ያድናልና። ጥርሱን ታማሚው በጥርሱ መነቀል እፎይ ቢልም ድዱ ሙሉ በሙሉ እስኪያገግም ራሱን መንከባከብ አለበት። ከመጀመሪያ ትንንጥ ነገሮች ሊጀምር ይችላል… ምራቅ አለመትፋት ሊሆን ይችላል… ትኩስ ነገር አለመጠጣት ሊሆን ይችላል። የታዘዘለትን መዳኒት በአግባቡ ጨርሶ መውስድ ሊሆን ይችላል። ከንፋስ መከላከል ሊሆን ይችላል። ጊዜው እስኪያልፍለት ምላሱንና ድዱን አፋቅሮ መቆየትም ሊሆን ይችላል። ምላስ እና ድድ ያላቸውን ፍቅር ጥርሱን የተነቀለ ብቻ ነው የሚያውቀው… በሚገባ መዳኑን ለማወቅ ምላስ አስሬ ነው ድድን የሚቀምሰው ሃሃሃሃ  ድድ የሚገጥምብበት የራሱ ጊዜ አለው፤ ሁሌ እንደዛ ሆኖ አይኖርም ነው ዋነኛው ነጥብ።


አንድ ሱሰኛም ሱስ ሲተው እፎይ ቢልም፣ እንደ ድዱ ትንሽ ጊዜ የሚያስታምማቸው ነገሮችን ሊያውቃቸው ይገባል። ለምሳሌ መደበር፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ትኩረት ያለ መሰብሰብ ችግር፣ መዝለፍለፍ፣ ራስ ምታት፣ ድባቴ፣ ቁጡ መሆን እነዚህ ቀላል የሚባሉ እንደ ድድ ህመም ያሉ ነገሮቹ ሲሆኑ………  ከወር በኋላ የሆድ ህመም፣ የልብ ምት መቀነስ፣ ጭንቅላት ውስጥ የመጨፍገግ ስሜት ሊኖርም ላይኖርም ይችላል። እንደየ ሰዉ ቢለያይም የትኛውም ሰው ግን የሆኑ ቀላል ችግሮችን አያጣም። ብዙ ሰው ሱስ ይተውና እነዚህን መሰል ችግሮች ሲገጥሙት፣ አላፊ መሆናቸውን ባለመረዳቱ ሮጦ ወደ ሱሱ ይመለሳል። እሱም በሚገባ አውቆት፣ ቤቶቹንም በሚገባ አሳውቆ የሚገባበት ግን ይሄ አያሳስበውም፤ ሁሉም አላፊ መሆነቸውን ያውቃልና። ቀድሞም ተዘጋጅቶ ስለሚጠብቃቸው እሱ ላይ ያላቸው ጉልበት አናሳ ነው፤ ሰውነቱ ሰልጥኖ ጠብቋቸዋልና። 


ቤቶቹ ሲባል ብዙ ሰው በሱስ ጉዳይ ግልፅ እንዳልሆነ ይታወቃል። ሱሰኛ ስንሆንና ከቤት ውጪ የምንጠቃቀም ሲሆን ቤተሰብ የሚያውቅ አይመስለንም። ሆኖም የሱሰኛ ኑሮ ግመል ሰርቆ አጎንብሶ ነውና፤ ባንድም በሌላም ያስታውቃል። ቤቶቻችን ስለሚወዱን ላያስጨንቁን ፈልገው ቀጥታ ወሬውን ላያወሩን ይችላሉ። ግን ማወቃቸውን አትጠራጠሩ።


እናም ጊዜው አስገድዶን ስለ ሱሳችን አውርተነው ለማናውቀው የቤተሰብ አባል "ሱስ ልተው ነው የተወሰነ እገዛህ ያስፈልገኛል!" የሚለውን በቃል መናገር እጅግ ብዙ ነገር ነው የሚያቀለው። ይህን ለማድረግ ትንሽ ብቻ ነው ድፍረት የሚፈልገው። በተለይ በልዩ ሁኔታ የምንፈራውን ሰው ቢሆን… በለው! የመጨረሻ ምርጥ ነገር ነው የሚሆነው። አንደኛ አዕምሮአችን "ቤተሰቦቼ ቢያውቁ ምን ይሰማቸዋል?" ከሚል አላስፈላጊ ጭንቀት ያርፋል። ኦልረዲ እኮ ቤተሰብ ያውቅ ነበር። ይሄ ሸክም አዕምሮ ሲቀለው፣ በዛው ትርፍ ኢነርጂም ይኖረዋል። ሁለተኛ ቤተሰቡ ደግሞ፣ አጥቼዋለው ያለውን ልጁን በድጋሚ ያገኘ ስለሚመስለውና ተስፋም ስለተቀበለ፣ ለልጁ የሚሰጠው ፍቅር የተለየ ይሆናል። ከሱስ ስትፋታ ከሚያስፈልጉ ወሳኝ ነገሮች ውስጥ ደግሞ ብዙ ፍቅርና ብዙ ውሃ ይጠቀሳሉ። ሌላው ለቤቶቹ ማሳወቁ አንዱ ጥቅሙ…  ቀድሞ ይገጥመኛል ያላቸው ችግር ስለሆነ ሲገጥመው የሚያዩት፣ ተጨንቀው ስለማያስጨንቁት ከባድ ጫና ያቀሉለታል። ባልደረባ ቢሆን "አቦ ቃም አትፍዘዝብን!……… ቃምበት ቃምበት… መታ መታ" እያለ ነው እሳት የሚያቀጣጥለው። እነዚህን ላልተወሰነ ጊዜ አርባ ክንድ መራቅ ነው ሃሃሃሃ  


ከልምድ ሲወራ… ሱሰኛ የሆነ ሰው፣ ሱስ የሚተዉ ሰዎችን አበረታቶ አያውቅም! የሚያበረታታም አይመስለኝም። የአንዱ መተው ለሌላኛው ራሱን እንዲወቅስ ያደረገው ስለሚመስለው፣ የቻለውን ታግሎ  በሱስ ውስጥ ማቆየትን ይመርጣል። ይሄ ጥሬ ሐቅ ነው። የትም ሃገር የሚሆን። ስለዚህ ይሄን ቀድሞ ያወቀ ሰው፣ የሱስ የመተው ሃሳቡን ሱስ ውስጥ ላለ ሰው ማካፈል የለበትም። አሳማኝ ምክንያት ፈጥሮ መለየቱ አዋጭ መንገድ ነው። 


"ሱስ ልተው ነው" ብሎ ሌሎች ሱሰኛ ወዳጆቹን ከተለየ ራሱ ላይ ነው ፈተና የሚያዘንበው። ባልተለመደ ሁኔታ ጎትጉቶ ሊጋብዘው ደጁ የሚሰለፍ ሲበዛ ሊመለከት ይችላል። የአንድን ሰው ልምድ እዚ ጋር ስጠቅስ… ያ አንድ ሰው ስድስት ወር ጫት ሲተው ሁሉም ባልደረቦቹ የሚያውቁት ጫት ቤት መቀየሩን ብቻ ነበር። አንድም ሰው ጫት እየተወ እንደነበር አያውቅም። ከስድስት ወሩ በኋላ እንዳዲስ ልተው ነው ብሎ አውርቶ ያየውን ፈተና እሱ እና እሱ ብቻ ነው የሚያውቁት። ስለዚህ ለሁሉ ነገር መላ ያስፈልጋል። ሌላው ደግሞ የራሱ የሚለውን፣ የሚስማማውን መላ ይፍጠር ማለት ነው። በተለይ ለጫት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት እስከ ስድስት ወር ድረስ ሴንሴቲቭ ናቸው። እዚጋ መያዝ ያለብን ነጥብ ሱስ ውስጥ ያለ ሰው፣ ሌላ ሰው ሲተው… የሚፈትነው መጥፎ ሰው ሆኖ አይደለም። እንደዛ እንዳትረዱብኝ። እኛም ብንሆን ቦታው ላይ ብንሆን የምናደርገው ነው። "አንኮሽየስሊ" የሚደረግ ነገር ነው። ከጥሩነት ከክፉነት ጋር አይያያዝም። 


ታድያሳ ጉዳያችንን ገፋ ስናደርገው "ዘፈንን ዘፈን ያነሳዋል" ቢሉም ባይሉም አቀናባሪዎች… 

እሱባለው ይታየው የሺ፣ የህንድ ሙዚቃ የሚመስል ክሊፕ ያለው፣ <ሲከፋሽ አልወድም> የሚል ዘፈን አለው… እዛ ውስጥም ይሄ አለ

"የማልደራደርባቸው መሃል መሃል

የምወድሽ የኔን የኔን ያሃል ያሃል"

የመጀመሪያውን ስንኝ ይዘን እንቀጥል… 

ከሱስ ስንፋታ "የማልደራደርባቸው መሃል መሃል…" ብለን ለሰውም ለራሳችንም የምንዘፍናቸው ጉዳዮች ሊኖሩ ግድ ይሉናል። ዝምብዬ እንደምሳሌ፣ እንደ ነገሩ 5 ላንሳ… ሌላው ደግሞ የራሱን ያዘጋጃል።


1) እምቢኝ ማለት መልመድ! ይሉኝታ ማቆም! 

አዲሱ የህይወት መስመር ትንሽ መንሸራተት ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል አውቆ፣ ከአዲሱ ህይወት ጋር የማይሄድን ነገር ያለምንም ይሉኝታ እምቢኝ እያሉ ዙሪያን ማስለመድ መጀመር! 

(እኔ አልጠጣም! እኔ አልቅምም! እኔ አላጤስም…  ወዘተርፈ ደጋግመው እያሉ፣ ለራስም ለሰዎችም እምቢኝን ማስረገጥ!)

2) እንቅልፍ! 

በዚኛው አዲስ ህይወት፣ ሱስ እንደተዉ ሰሞን ትንሽ ጊዜ ቢያስቸግርም፣ ቆይቶ እንቅልፍ ስርዓት ይስተካከላልና… ከዛ በኋላ የሚመጣውን (ቢያንስ አንድ አመት)… በቀን የ7 እና የ8 ሰአት እንቅልፍ ወሳኝ ነው። በምንም ሁኔታ በእንቅልፍህ አለመደራደር!

3) ጉልበት! 

አንዳንዴ የምግብ ሰው ባንሆን እንኳ ቡሌ ወሳኝ ነገር ነው። መምረጡ በራሱ ጊዜ የምንማረው ነገር ቢሆንም፣ የተፈጨ ቀይ ስጋ ወሳኝ ስንቅ ነው–ለብዙዎች። እዚጋ ኑሮአችንን ግምት ውስጥ ያስገባ ነገርም ማሰብ አለብን። በምንም አይነት ሁኔታ እንሁን ግን ምግብ ሳይበሉ መንቀሳቀስ ግን ፈንጅ ወረዳን እንደመርገጥ ይቆጠራል።

4) ተፈጥሮ ውስጥ መዝለቅ! 

ሱስ ውስጥ ስንቆይ አንደኛው መጥፎ ጎን ራሳችን ብዙ አይሰማንም። ራሳችንን ፊል አናደርገውም። ጠንከር ሳረገው እየኖርን እንደሆነ አይታወቀንም። እና ከሱስ ስንወጣ ያን መጥፎ ስሜት ከውስጣችን አውጥተን ህይወት እንደአዲስ እንድትሰማን… ተፈጥሮ ውስጥ መዝለቅ አለብን። ሳር ላይ ተኝተን ቁጫጮች ይሂዱብን… እንዴት ደስ እንደሚል ሲያዩት ነው የሚታውቀው። በግድግዳ ታጥሮ ቂጡን ደፍኖ ሲቅም ለነበረ ሰው ትንሽዬ ኩሬ በብዙ ታስቦርቀዋለችና። ያውም የት ነበርኩ ግን እስከዛሬ? እያለ… 

5) ፊልም፣ ሙዚቃ፣ መፅሃፍ…!

ሙዳችን የሆነውን ራሳችን መምረጥ… ቦክስ አሎሎ ምርኩዝ ዝላይ ካስደሰተን የት እንዳሉ የምናውቀው እኛው ነንና ያሉበትን ፍለጋ እዛው መባጠስ ነው…… የሚያዝናናን፣ ሙያም ሊያረጉት የሚፈልጉትን ነገር መምረጥ የባለቤቱ ፈንታ ነው!


ከላይ ያሉትን እንደመነሻ መያዝ በትንሹ ስህተት ላለመስራት ይጠቅማል።


ከሱስ ከተፋታን በኋላ ደግሞ እስክንረሳው ድረስ ትግሉ የየቀን መሆኑን መረሳት የለበትም። አንዱን ቀን ካሸነፍነው በኋላ ነው ነገ ነገን እየወለደ ዓመት የሚሞላው። ስለዚህ ለዚህ የየቀን ትግል በቂ ጉልበትና በቂ እንቅልፍ አስፈላጊ ናቸው። ተዳክመን የተገኘን ቀን ውስዋሱ ከባድ ነው። እናም ጥሩ ጉልበት በጥሩ እንቅልፍ ሰንቀን ቀኑን ስንጀምረው… ምን ሆኜ ነበር ድሮ ብለን በበፊት ቀኖቻችን ላይ ራሱ ሙድ እንደ መያዝ ይዳዳናል። ያኔ ውስዋሱ በዜሮ ተባዢ ነው። 


ከላይ እንግዲህ ለጉልበት የሚሆን ስንቅ ምን እንደሆኑ ከተረዳን ዘንዳ  ለአዕምሮ ደግሞ ስለሚሆኑ መፅሃፍት እናውራ። ሶስት እጅግ ቀሽት ቀሽት በሆኑ ሰዎች የተፃፉ መፅሃፍት አሉ። በመጀመሪያ ግን እነዚህን ሰዎች የመረጥኩበትን ምክንያት እንጨዋወት… ለብዙ ጊዜያት አብረውን ስለሚቆዩ፣ ሞቅ አርገን በደንብ እንቀበላቸው። ጭብጫቦ ጭብጫቦ ሃሃሃሃ ምክንያቱ ይኸውና… 


1) ፍፁም ኦሪጅናል ናቸው።

2) ስለሚያወሩት ነገር ጠንቅቀው ያውቃሉ።

3) እየመከሩ አልያም እየሰበኩ አያዝጉም… ነጥብ ነጥቡን ነው ጨዋታቸው።

4) ከራሳችን ከውስጣችን ጋር ቀጥታ ያገናኙናል። 


ትንሽ እንዳነበብናቸው የኛ የብቻችን ችግር የመሰለን ጉዳይ፣ የሁሉም በኛ መስመር ያለፉ ሰዎች አልያም የሚያልፉ ሰዎች ችግር መሆኑን ስንረዳ፣ነገሩ ትንሽ ይቀለናልና… በአንዳች የመነሳሳት ሃይልም እንሞላለን (ትንሽ ላካብድ ብዬ ነው )


★ ፩) martin nikolaus {empowering your sober self}


ይህ ሰው ከዚህ በፊት አንድ ቦታ ላይ እንደፃፍኩት… አንድን ሱስ ውስጥ ያለን ሰው ሁለት ያደርገዋል። ሶበር የሆነውን (ከሱስ በኋላ የምትጀምረውን አዲስ ሰው) እና ሱሰኛ የነበረው ሰው። የሱ መንገድ፣ ከሱስ በኋላ ያለህን ህይወት ስታጎለብተው ሱሰኛ የነበረው አንተነትህ እየሞተ ይመጣል የሚል ነው። እኔ ትንሽ ከሱ የምለየው ሱሰኛውን እንዳይነሳ አርገን ከመጀመሪያውም መግደል እንችላለን ብዬ ስለማምን ነው። ሌላ ጊዜ በዚ ርዕስ አረሳስተና ስናወራ፣ በሰፊው እናየዋለን። የዚን ሰው መፅሃፍ እስከ ምዕራፍ አራት ካነበብነው ለጊዜው በቂ ነው። ሌላው ለጊዜው ወይንም ለመጀመር ያህል አይመለከተንም። ጊዜ በብዙ ያለው ይግባበት፣ ዕውቀት አይጎልምና!

ፒዲኤፉ ይኸው empowering your sober self


★ ፪) allen carr {easy way to stop smoking, The easy way to control alcohol}


አለማችን ላይ በሱስ ዙሪያ እንደሱ እጅግ ብዙ ተፅዕኖ የፈጠረ ሰው አለ ብዬ አላስብም። የሚሊየኖችን ህይወት የቀየረ ግለሰብ ነው። እኔ ስጀምር ሱስ የተውኩት በራሴ መንገድ ነው። አምስት ወር ካለፈኝ በኋላ ነው ይሄን ሰው መጀመሪያ ያወኩት። እውነት እውነት እላችኋለሁ ቀድሜ ባውቀው ኖሮ ድሮ ብዙ መውደቅ መነሳት ሳይኖርብኝ ሱስ እተው ነበር። ዘግይቼ ስላወኩት ቆጭቶኛል። ላለፉት 7 አመታት በሱስ ዙሪያ የተፃፉ አያሌ ፅሁፎችን አይቻለሁ… እንደዚህ ሰው በብዙ ቦታ ግንባር ቀደም ሆኖ የሚጠቀስ ሰው አልገጠመኝም። ከላይ ቁጥር አንድ ላይ ያነሳሁት መፅሃፍ ፀሃፊ እንኳ መፅሃፉ ላይ በክብር ያነሳዋል። ከታች ቁጥር ሶስት ላይ የምጠቅሰውም ጭምር በክብር ያነሳዋል። የሱስን ሳይኮ ጥጥት አድርጎ የጨረሰ እንግሊዛዊ ነው። 

ፒዲኤፉም ይኸው easy way to stop smoking

                          easy way to stop drinking


★ ፫) Joel spitzer {never take another puff}


ይህ ሰው ደግሞ በራሱ መንገድ… የማጨስበት ናቸው ብለህ የደረደርካቸውን ምክንያቶች በዜሮ ያባዛልሃል። ከዛ አንተም ለምንድነው የማጨሰው ትላለህ። ሲጋራ ትተህ ቆይተህ፣ ሰው ነህና ሊያጋጥም ስለሚችል… አንድ ትንሿ የሲጋራ ፓፍ እንዴት ቀድሞ የነበርክበት ቦታ ላይ እንደምትመልስህ ያሳይሃል። ቆይቶ ኔቨር ቴኩ ጋር ይዞህ ይሰምጣል። 

ፒዲኤፉ ይኸው never take another puff


በቅደም ተከተላቸው መጨምጨም ግዴታ ባይሆንም አሪፍ ነው ባይ ነኝ።… የምንፈርሽ ከሆነም በሃይለኛው ፈርሸን እንጨምጭማቸው! አንድ መፅሃፍ በራሱ ሙሉ ላይሆንልን ስለሚችል፣ እነዚህ ሶስቱ ግን በእርግጠኝነት ክፍተትን በሚገባ የሚሞሉ ይመስለኛል። በሁሉም አቅጣጭ ለዛሬም ለነገም የሚሆኑ መፅሃፍት ናቸው። እኔን እንድተው ባይረዱኝም ትቼ እንድቆይ መንገድ ስለጠረጉልኝ በዛው እያመሰገንኳቸውም ነው። ውለታ እየመለስኩም  ነው። እናንት መፅሃፎች ክበሩልኝ!!!


ሁለተኛው ሰውዬ Allen Carr እንደውም (አንብበን እስክንጨርስ ድረስ የምናደርገውን ነገር እንድንቀጥለው) ሁሉ ይገፋፋናል። የምትጠጣ ከሆነ አንብበህ እስክትጨርስ ጠጣ ይልሃል። የምታጨስም ከሆነ እንደዛው። በማንበብ እንደሚተውም ደረቱን ነፍቶ ያወራል። እመኑኝ እውነቱን ነው። 


አንድ ነገር ላይ ሳሰምርበት ስለ ሱስ ካልገባን አልገባንም ነው። ስለ አንዱ ሱስ ገባን ማለት ደግሞ ስለ ሁሉም ሱስ ገባን ማለት ነው። አንዱን ሱስ ብቻ መተው ቻልን ማለት… ሌላው ሁሉ ሱስ እንዴት እንደሚተው ተገለፀልን ማለት ነው። የሱሳ ሱሶች ስማቸው እና አንዳንድ ከፍታቸው ቢለያይም፣ አሰራራቸው ግን አንድ አይነት ነው። በአንዱ ስንነቃ ሌላው እዳው ገብስ ነው።


iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

12 comments:

  1. እስካሁን ሳላውቅህ የትነበርኩ? once again life make sense to me የብቻዬ አልነበረም ጉዜዬ ለካ እናቴ አንድ ቀን ታመሰግንሃለች! mark my word buddy!!!!!

    ReplyDelete
  2. የሱስን ህይወት በባህር ላይ ጉዞ የመሰልክበትን መንገድ ካየሁ በዋላ ህይወቴ እንደ በፊቱ አይደለም። ቢያንስ በሳምንት ሶስቴ ይሄን አነብና እበረታለሁ። ያሰብኩት ከሆነልኝ ለውለታህ ክፍያ ባለህበት እመጣለሁ። ጨምሮ ጨማምሮ በረከቱን ይሰጥልኝ። ክፉ አይንካህ። ያሰብከው ሁሉ ይሁንልህ።

    ReplyDelete
    Replies
    1. ምንም አያስፈልግም ቡራ። ይሄ የፃፍከው ከክፍያ በላይ ነው ለኔ። የእውነት ከልቤ ከውስጡ ነው ደስታ ሲሰማኝ የታወቀኝ። ጓዴ ከርቀት ፏ ብለህ አይቼህ ትዳሩ ነው ብዬ አስቤ ነበር። ለካ ይሄም ተጨምሮ ነው። በሁለቱም እግዜር ይመስገን ብያለሁ ላንተ። ደስታህ ደስታዬ ነው። እንዲህ ስላስደሰትከኝም ሌላም ደስታ ይጨምርልህ። ስልክህ ጠፍቶኛል ደውልልኝ። ሌላ ሰው ነው የሆንከው ስለ እውነት። በራስህ ኩራ ቡራ ገጠምኩ ሃሃሃ ደውልልኝ።

      Delete
  3. From your favorite movies 'smashed' is my real story!!! መጥፎ ሰዎች ሆነው አይደለም ግን ግን አርባ ክንድ መራቅነው is my turning point. 1 year 2 months and 14 days sober now. and i am missing my poor charlie badly. what do you think? በርግጥ የኔ ህይወት ነው ካጀንዳውም የራቀ ነው ግን say something please.....

    ReplyDelete
    Replies
    1. ውድ ኬኢ ማለቴ ኬኤች አጀማመሬ ነገር አለው ሃሃሃሃ ነገሮችን ገጣጥሞ የተሰወረው ላይ መድረስ ዕጣ ክፍሌ መሰለኝ። ረግጫለሁ ማለቴ አረጋግጫለሁ ሃሃሃሃ

      ወደ ጉዳዩ ስገባ.... ያንቺ አይነት ሰው እንዳለ ማሰቡ ብቻ የሚሰጠኝን ኢነርጂ ብታስቢው ይጋባብሽ ነበር። ወደ ፊልማችን ስመጣ ደግሞ በፊት ለራሴ ፍጆታ ነበር ያየሁት። ውዴታዬም የመጣው ከራስ ፍላጎት በመነጨ ነበር። ካየሁትም በጣም ቆይቻለሁ። ካንቺ አስተያየት በኋላ ግን መልሼ ማየት ነበረብኝ። ጊዜ ተርፎኝ አይደለም። ጉዳይሽ ምን ያህል ሲሪየስ እንደሆነ ስለተረዳው ነው። ስለዚህ የአሁኑ መነፅሬ ከድሮው በእጅጉ ይለያል ማለት ነው። ያንቺንም አይን ጨምሬ፣ ሁለት ሆኜ ነው ያየሁት።

      እንዳልሽው ከፃፍኩት ርዕስ የማይገናኝ አይደለም። ግጥም አርጎ ሙሉ በሙሉ ይገናኛል። ትሁት ለመሆን አስባ ነው ብዬ ዘልዬዋለሁ። ከሱስ ህይወት የተፋታች፣ ሁለተኛ አመቷን የጀመረች፣ ስንጣቅ የገባው ትዳር ያላት፣ ኢትዮጵያዊት ሴት አድርጌ ጫናዎችሽን በሙሉ በሃሳብ ቀንበሬ ተሸክሜ አይቼልሻለሁ።

      ጫናሽ አንድ ብቸኛ ጥቅም አለው። ስለ ቻርሊሽ ባሰብሽው ላይ በእጅጉ ይጠቅምሻል። በነገርሽ ላይ በህይወቴ ለሰዎች ፈፅሞ አስተያየት በማልሰጥበት ጉዳይ ነው የፈተንሺኝ። ቀዳዳ ስለከፈትሽልኝ ግን ወደ ገደለው ልግባ። ወደ ቻርሊ ተመለሺ። ያንቺን ህይወት ከፊልም ጋር ማመሳሰል ነውር ቢሆንም አንቺ ከኬት የምትለዪው መጀመሪያውኑም ቻርሊን ትወጂው ስለነበር ነው። እሷ አትወደውም ነበር አላልኩምም። ያንቺ በባዶ ያለመጠጥ ማለቴ ነው። ልዩነቱ ይገባሻል ብዬ አስባለሁ።

      መጠንቀቅ አለብሽ የምለውን ግን ላስምርበት። ፈፅሞ ቻርሊ በምንም ሁኔታ ውስዋስ ውስጥ እንዳይከትሽ አስጠንቅቂው። የትም ቦታ ላይ። አንቺም በጭራሽ ወደ አንቺ ህይወት እንዲመጣ ልትመክሪው እንዳታስቢ። በምንም አይነት ሁኔታ። ሃሳቡ ከሱ ከመጣ ግን ቢችል በራሱ መንገድ ሲታገል በፍቅር ደግፊው። እሱም እንደሚወድሽ ስለማስብ ወደ አንቺ መንገድ በራሱ ሰአት እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ።

      በአስተያየትሽ እንዳነሳሽው አርባ ክንድ መራቁ ፍቱንነቱ ገብቶሻል። ግን አንድ ነገር ዘለሻል። ላልተወሰነ ጊዜ ብያለሁ... ሁሌ ተርቆ አይቻልም። በዚ ርዕስ 40 ገፅ ብፅፍ ያለምክንያት የማስገባት አንዲት መስመር አትኖርም። ለጊዜው የምትሪቂያቸው ኋላ መልሰሽ የምትቀርቢያቸው እንደ ራስ የሆኑ ሰዎች ጥቂት ቢሆኑም ሁሌም አሉ። ቻርሊሽ ደግሞ ከዛም በላይ ነው።

      አይተሽዋል ብዬ አስባለሁ When a man loves a woman ፊልም ከስማሽድ ዘነፍ ያለ መንገድ አለው። ቦታ ቀይረሽ የሚደመር ደምረሽ የሚቀነስ ቀንሰሽ አስቢው። አንቺ ከባዱን ጊዜ አልፈሺዋል አሁን ለራስሽ ሚሞሪውን ልትጋብዢው እንደሆነ ቀድመሽ ካሰብሽበት በእጅጉ ይቀልሻል። ፈፅሞ ግን .... ኔቨር ቴክ አናዘር ሲጵ ምናምን የምትባይ ሴት እንዳልሆንሽ አውቃለሁ። ቻርሊ በጣም በጣም በጣም እድለኛ ነው። ማሳረጊያዬ በኩራት ተመለሺለት ነው።

      ቃል ማስገባት ከቻልኩ.... ቀጣዩ ከቻርሊ ጋር የሚመጣውን ህይወትሽን ፃፊው። ከሁለቱ ፊልሞች ውጪ የሆነ ብዙ ሰው የሚያስተምር ሰበዞች ይኖሩታል። ህይወትሽን ፊልም ማረግ የጀመርሺው አንቺ ነሽ ሃሃሃሃ

      በጣም ኮስተር ስላልኩ ስለታወቀኝ ፈታ ብዬ ልውጣ... ፊልሙ ታሪኬ ነው ስትይ ሞይስት ኬኩንም ይጭምራል ወይ? ሃሃሃሃሃ ሳየው ቆርጬ ባወጣው ደስ ባለኝ። ደሞ አሁንም ኬኩን አይደለም ሃሃሃሃ

      ውድ ኬት ብቻሽን መሆን ይብቃሽ። መልካሙ ሁሉ እንዲገጥማቹ እመኛለሁ። ኢሜይል ብታረጊልኝ ደስታዬ ነበር። ይሄን ሳልልሽ ኢሜይል ብልሽ ትደነብሪያለሽ ብዬ እንጂ ጉዳዩስ የውስጥ ነበር። አሁን ቤተሰብ ስለሆንን ስላወኩሽም ፈታ ብለሽ ነይ። በዚ ርዕስ 24 7 ይመቸኛል። ችግሩ ኢንተርኔት ለረዣጅም ጊዜያት ስለምፎርሽ ነው
      ሃሃሃሃ

      Delete
  4. አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ ጭራሽ ሱስ ውስጥ ይገባል ብለህ የማታስበው ሰው በጣም ሱሰኛ መሆኑን ብጣቅ ምን ይሰማሃል?

    ReplyDelete
    Replies
    1. ይቅርታ ስለዘገየሁ… ደጋግሜ እንዳልኩት በየመሃሉ ኢንተርኔት ስለምፎርሽ ነው። ጉዳዩን በዚህ ስጀምር “ሱስ መቼም አይጀምርም እንዲሁም ሱስ መቼም አይተውም የምለው አንድም ሰው የለኝም” የትኛውም ሰው በተለያየ አጋጣሚ ሱስ ውስጥ ሊገባም ሊወጣም ይችላል። ስለዚህ በማንም ሰው ጉዳይ አልገረምም፤ አልደነቅም።

      ገንዘባችን ላይ ይሄ ሰፍሯል “ላምጭው እንዲከፈል ሕግ ያስገድዳል”… እናም ጥያቄው የአንተ/የአንቺ መሆኑን ወስጄ ቀጣዩን ልል ወደድኩ። ባይሆንም መመለሱ ችግር እንደሌለው እሙን ነው።

      አንድ ሰው “ሱስ ውስጥ መቼም እገባለሁ ብዬ አላስብም ነበር” ብሎ ካሰበ፣ ለራሱ የሚሰጠው ግምት የተጋነነ ነው ማለት ነው። ያ በራሱ ችግር ባይሆንም ሱስ ጋር ሲመጣ ግን ጥንቃቄ ይፈልጋል።

      ሱስ ላይ ስሰራ ሁለት አይነት ሰዎች ትንሽ ሲቸገሩ አያለሁ
      1. እንዴት እኔ ሱስ ውስጥ እገባለሁ? የሚሉና
      2. እኔ እኮ ሱሰኛ አይደለሁም የሚሉ

      የመጀመሪያዎቹ “እኔ እኮ ራሴን መቆጣጠር የምችል ሰው ነበርኩ” ብለው የሚያስቡ ሲሆን ሁለተኛዎቹ ደግሞ “እኔ አሁንም ራሴን እቆጣጠራለሁ” ብለው የሚያምኑ ናቸው። ሁለቱም ያልገባቸው ነገር ሱስ መቆጣጠር የሚባል ምርጫ የሌለው መሆኑን ነው። ሱስ ይቆጣጠርሃል እንጂ መቼም አትቆጣጠረውም።

      ስለዚህ እዚህ ጋር ቆም ማለት ተገቢ ነው። ሱስ ውስጥ መግባት እንደ ስህተት ከተቆጠረ ማንም ሰው ስህተት ሊሰራ ይችላል ማለት ነው። አንተን የተለየ የሚያደርግ ምንም አይነት አመክንዮ የለም። ስህተትን በራስ መቀበል በሱስ የመዳን መጀመሪያ ነው። ደግሜ ልንገርህ ማንም ስህትት ይሰራል አንተም ልዩ ሰው አይደለህም።

      ሱሰኛ መሆን ብርቅ አይደለም። በሆነ አጋጣሚ ሱስ ውስጥ ገብተሃል። ዋናው ነገር መውጣት መቻልህ ብቻ ነው። ስለዚህ እኔ እንደዚ እኔ እንደዛ ከሚል እንቶፈንቶ ውጣና “እኔ ሱሰኛ ነኝ ግን መውጣት እፈልጋለሁ” ወደሚለው ሃሳብ ና…. ምን ያህል መንገድህን እንደሚያቀልልህና ምን ያህል እፎይታ እንደሚሰጥህ አስረግጬ ስለማውቅ ነው ጫን ብዬ የተናገርኩት።

      ደጋግመህ አስበው/አስቢው መሃል ላይ አንተ በሚለው የቀጠልኩት አንተ/ አንቺ ማለቱ ሰልችቶኝ ነው። ብል ይሻል ነበር መሰለኝ ሃሃሃ አመሰግናለሁ። ለየትኛውም ጥያቄ ወ ምላሽ አፀፋዬ ፈጣን ነው ልል ነበር… እንደ ኢንትርኔት አጠቃቀሜ ነው በሚለው አሻሽዬዋለሁ ሃሃሃሃ

      Delete
  5. እንዳንጠጣ ቢፈልግ ኢየሱስ የወይን ጠጁን አይቀይረውም ነበር። እንኳን አለቀ ይቅርባቹ ይለን ነበር። ስለዚህ እንጠጣለን። ድሮ ጠጡ ወደኔ እስክትመጡ ተብሏል እያልክ አልነበር የምታጠጣን? ሪታ ጉስታቮ ሃይ ሃይ ሃይ

    ReplyDelete
    Replies
    1. ሃይ ሃይ ሃይ ለአንተም። ከጉስቶቭ ውጪ ሁለት ሰዎች ጉስታቮ ይሉኛል። አንደኛው የሰጠኸውን አስተያየት ሊሰጥ አይችልም። ስለዚህ ቀዮ ነው ብዬ ልቀጥል። እኔም አንተም ደማቅ ጥቁር መሆንህን ብናቅም ቅሉ ሃሃሃ

      ይገርምሃል የፌስቡክ የመጀመሪያ ፖስቴ ከተደረደረ የድራፍት ጠርሙስ ጋር “ጠጡ ወደኔ እስክትመጡ” የሚል ነበር። አየህ የእብደቱን መጀመሪያ…. ሲብስብኝ ነው የራሴን የግል ፎቶ እየቀያየርኩ የመንገደኛ አስተያየት መጠባበቅ የጀመርኩት… ድኜ ሳስበው ገርሞኝ ነው ሃሃሃሃ

      አንተ ግን “የምታጠጣን” ብለህ ያከልክበት…. እየጋበዝከን ማለት ፈልገህ ነወይ ወይ ወይ ወይ? ወይስ ጣፋጭ የጥቅስ ዘለላ ነው የምትጋብዘን ልትለኝ ፈልገህ ነወይ ወይ ወይ ወይ? ወይንስ የአቻ ግፊት ሲሉ ሰምተህ፣ እኔን አቻየው ገፊ እናንተን ደግሞ አቻየው ተገፊ ማረግህ ነወይ ወይ ወይ ወይ? መልስ የለም መልስ የለም አለ ገጣሚ ሃሃሃሃ

      ወደ ቁምነገሩ እንለፍ……
      ምሳሌ ጥሩ ነውና በምሳሌ እንማማር። እንደምታውቀው እኔ አሁን ላይ ፈፅሞ መጠጥ አልጠጣም። የመጠጥን አስቀያሚነትም ጠንቅቄ አውቃለሁ። ለማንም ሰው ምንም አይነት ጥቅም እንደሌለውም ጭምር። ምኞቴ ጠጪ ሁሉ መጠጥ ትቶ፣ ባለመጠጣት የሚገኘውን ደስታ፣ ፌሽታ፣ ፈንጠዝያ ሲጎናፀፈው ማየት ነበር። ሆኖም ሆኖም ማለት ጥሩ አንድንም ሰው አትጠጣ ይቅርብህ ብዬ አላውቅምም አልልምም። እጅግ የምወዳቸው የማከብራቸው ሰዎችን፣ ስቃያቸውን ባየው እንኳ ፈፅሞ ተዉ አትጠጡ ስል መቼም አታገኘኝም። ግን እርዳታ የጠየቁኝ ጊዜ ምላሼ ከብርሃን ይፈጥናል። የምችለውን ሁሉ ሙሉ ኃይሌን እሰጣለሁ። ቀድሞ እርዳታውን የጠየቀኝን ሰው ከዛ በኋላ “አትጠጣ ተው…” የማለት ሙሉ ስልጣን አለኝ። የሱስ መተው ሕግ የሚሰራበት ሁነኛ መንገድ ይሄ ስለሆነ ነው።

      በጣም ሳስገርምህ… አንድ ሰው ራበኝ ብሎ ቢጠይቀኝ እና ሌላ ሰው ደግሞ ተወስውሻለሁ የመጠጥ ስጠኝ ቢለኝ፣ ፈጥኖ እጄ የሚዘረጋው ለባለመጠጡ ነው። መቅደም ያለበትን በመኖር ስለማውቀው። ይሄን ሰው ችላ ማለት ኃጢያት ሁሉ ነው የሚመስለኝ። እንዳላጋነንኩ አንተ የምትረዳ ይመስለኛል። ታዲያ ይሄን ማረጌ ሰዎች እንዲጠጡ እፈልጋለሁ ማለት ይመስልሃልን? ጠጡ ማለቴስ የቱጋር አለ? እያስተዋልክ ቆይ።

      ወደ ክርስቶስ ስመጣልህ… የታደመበት ሰርግ ላይ ችግራቸው የሚታየው ሁለት ነው። አንድ ደጋሾቹ መጠጥ ጨርሰው ሊዋረዱ ነው። ሁለት ታዳሚዎቹ መጠጥ ጀምረው ተወስውሰው ሊያቆሙ ነው። አዲስ የሚመጣም ሊኖር ይችላል። እናም ክርስቶስን እንኳን (እናቱ) እርዳታውን ጠይቃው አይደለም እንዲሁ ሊያደርገው የሚገባውን ነገር ነው ያደረገው። ፀረ መጠጥ አቋም ያለኝ እኔ ቦታው ላይ ብሆን፣ በሰውኛ ወጥቼ ብዙ ሳጥን ቢራ ገዝቼ እመለስ ነበር። (ያኔ ቢራ የለም ብለህ ሃሳብ እንዳትሰነጥቅ)። አየህ ወዳጄ እኔ ተራው ኢምንቱ እዚህ ግባ የማልባል ሰው የሰዎች ስሜት እንዲህ ካስጨነቀኝና ከተረዳው ክርስቶስ መድኃኔአለም እንዴት የሰው ስሜት ያስጨንቀው??? ያን ማድረጉ ሰዎች ይጠጡ ማለቱስ ይመስልሃልን? መልሱን ላንተ ትቼዋለሁ።

      መውጫ፡-መልስ የሰጠሁህ ስለመጠጣት አለመጠጣትህ አይደለም ስለ ምክንያትህ እንጂ። ብዙ ሰው የምክንያቱ እስረኛ ነው። አንዳንዶች ቁንፅል ከነሱጋር የማይገናኝ አንድ ጥቅስ ይመዙና መጠጥን ሃይማኖታዊ ሊያረጉት ይሞክራሉ። ደሃ ድህነቱን ይረሳ ዘንድ ይጠጣ ተብሏል ይሉሃል። ከዚህ ጥቅስ በላይ ከፍ ስትል ስለመጠጥ አስከፊነት ተፅፏል። ድህነትንም መቀየር እንደሚገባ ጭምር…. ስለዚህ እኔ ግን እልሃለሁ “ድሃ ድህነቱን ይረታ ዘንድ ጠንክሮ ይስራ”

      በስልክ ቢሆን እየሳኩ እነግርህ ነበር ይሄ የምኮሳተርበት ግዛቴ ነውና አፉ በለኝ። አመሰግናለሁ። ደግመህ ግን እንዲህ አይነት ርዕስ አታንሳብኝ። አለማዊ ሰው ነኝና ወደማይገባኝ ቦታ እንድሄድ አታስገድደኝ። በድጋሚ አመሰግናለሁ።

      Delete
  6. ፍሮም ፈርታይል ማይንድ ኦፍ ኢንጂነር እርዮት አለሙ የፈለቁ ሁለት ጥቅሶች…. ሱሰኛ እና አክሲዮን ሻጭ ለመጨረሻ ጊዜ ማለት ያበዛል…. መጠጥ እና ፕሮግራሚንግ ቆይተው ሲመለሱባቸው እንዳዲስ ያደናግራሉ…. ሁለቱንም ኖሬዋለው። ይገርምሃል ስንቱን ሳጥን ገልብጬ ቤቴ የምገባ ሰው በ7 ቢራ ተምበጫበጭቁ እና አሁን ደግሞ ብርድልብስ ውስጥ ሆኜ ያንተን ፅሁፍ እያነበብኩ ራሴን አገኘሁት። ምን ትለኛለህ ፕሮፌሰር? ያክብሮቴን ነው።

    ReplyDelete
    Replies
    1. ሃሃሃ አንተ ነባር ኗሪ ፊነርባቼ ትመስለኛለህ። ፊነርባቼ የኛ ባች ማለት ነው ሃሃሃ ከፃፍከው ተነስቼ ስሜትህንና ያለህበትን ሁኔታ ያገኘሁት ይመስለኛል። ግን ግላዊ ጉዳዮች የሚኖሩት እና ረዥም መልስ የሚፈልግ ስለሆነ እዚህ ተዘሏል።

      ከአባባሎቼ ስነሳ በቅርበት ልታውቀኝ የምትችል ሰው እንደሆንክ እገምታለሁ። ስልኬ ይኖረዋል ብዬም አስባለሁ። ይህ ከሆነ ልትደውል በምትችልበት ሙድ ላይ ስትሆን ደውልልኝ። በባዶ ስሜቱን አውቀዋለሁ። ይህ ካልሆነ እዚሁ ኮንታክት ውስጥ ገብተህ ኢሜይል አርግልኝ። አንተን በሚመችህ እና ምቾት በሚሰጥህ ሁኔታ ለመመለስ ዝግጁ ነኝ።

      የመጠጡን ግን ለምን ቆይተው ሲመለሱበት እንደሚያደናግር የደረስኩበትን ልንገርህ።

      ሲጀመር መጠጥ ፖይዝን ነው። የመጀመሪያው ቀን ከሰውነታችን ጋር ሲገናኝ፣ ሰውነታችን “ተጠንቀቅ ልክ ያልሆነ ነገር እየተከናወነ ነው” የሚል ምላሽ ይሰጣል። በማስመለስ፣ በራስምታት፣ በምሬቱ ብቻ በሆነ ነገር ማስጠንቀቂያውን ይሰጣል። አሁን ገልባጭ የምትለው የትኛውም ሰው ስለቆየ ቢረሳውም ሲጀምር መጠጥ ተጎራብጦታል። የኔ የመጀመሪያ ሳምንቴ መዘፍፊያዊ ነበር በኋላ እሱ እኮ በርሜልም ቢጠጣ… ሊሉኝ ሃሃሃሃ

      መርዝም በትንሽ በትንሹ ከተላመዱት አይገልም እንደሚሉት ነው። መጠጥም አንድ ሁለት እየተባለ ነው 10 20 የሚደረሰው። “ጭንቅላት እና ወረቀት የያዙትን አይለቁም” እንዲሉ አበው ባይሉም ቅሉ ሃሃሃ፣ በመጠጥ ህይወትህ የመጨረሻ ጊዜ የጠጣኧውን ጭንቅላትህ መዝግቦ ይቀመጣል። በተቃራኒው ደግሞ ሰውነትህ መጠጥ ስተተው ሁሉን እንዳልተፈጠረ አድርጎ መርሳት ይጀመራል።

      ቆይተህ ስትጀምር ታድያ ሰውነትህ እንደመርዙ በትንሽ በትንሹ መላመድ ሲኖርበት… ጭንቅላትህ ደግሞ ቀድሞ የሚያውቀው ቁጥር ጋር መቀመጥ ይፈልጋል። እና ቆይተህ ስትመለስ ጭንቅላትህ 10 ቢራ እንደምትችል ይነግርሃል ሰውነትህ ደግሞ አልችልም ብሎ እዬዬ ይላል። የሁለቱ ግጭት የአንተን የድሮ ሙድ ስለሚያጠፋው ስካርህ ቅጥ ያጣል። መጠኑ ከበዛ የሚሞት ሁሉ ሊኖር ይችላል። እናም የተንበጫበጨከው ለዛ ነው።

      ዋናው ጥያቄ ግን ቆይቶ መመለሱ ለምን አስፈለገ ነው? ያልተፈታ ችግር ነበር ማለት ነው። ለዚህ እኮ ነው ከላይ ብትፈልግ በስልክ ብትፈልግ በኢሜይል አንድ ሁለት እያልን እንጨዋወት የምልህ። ጨዋታውን ነው ደሞ አንድ ሁለት እያልን የምንቆጥረው ሃሃሃ

      ብረትን መቀጥቀጥ እንደጋለ ነው ስለመዘግየቴ ይቅርታ። ምክንያቴንም ታውቃለህ ብዬ አስባለሁ። አግዬ ስለምቀጠቅጥህ ችግር የለውም ሃሃሃ። አለሁ አለሁ ለማለት ነው። በሚመችህ ሁሉ ይመቸኛል። ከተመቸህ በሃላል ከተመቸህ በአኖኒመስ ፃፃ የለውም። ከሰላምታ ጋር!!!

      Delete

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement