Advertisement
ድሮ ገና ለማጅ ጠጪዎች እያለን… እንደማንኛውም ለማጅ ጠጪ የለሊቱ አጠጣታችን ካርታ አልነበረውም፡፡ ዕለቱ ፒያሳ ላይ ተጀምሮ በቦሌ አርጎ ካሳንቺስ ሊጠናቀቅ ይችላል፡፡ማንም ምንም አያውቅም፡፡ እና በዚ ጊዜ እጅግ አሰልቺውና አስቀያ ሚው ነገር ሰአት እላፊ ላይ ተዛዝሎ አልጋ መፈለጉ ነበር። መጀመሪያ አልጋ ይዞ መጠጣት የሚመጣው ሲኒየር ሲኮን ነው፡፡
ታድያ ከእለታት በአንዱ ቀን ሰንጋ ተራ የተጀመረው ምሽታችን መጨረሻውን ፒያሳ ሰራተኛ ሰፈር አረገ፡፡ ከለሊቱ 10 ሰዓት ሆኗል ሲበዛ ተዳክመናል፡፡ ከጣይቱ ጀምረን እስከ ሚጢጢ ሆቴሎች አልጋ ብንፈልግ ብንፈልግ ወፍ የለም፡፡ ድንገት ራሳችንን ሰራተኛ ሰፈር ውስጥ <<አልጋ ነው? አልጋ ነው? ...>> በሚሉ ሰዎች ድምፅ ተከበን አገኘነው፡፡ ሶስታችንም እንተያይ እና እንሄዳለን፡፡ አሁንም <<አልጋ ነው? >> የሚል ድምፅ ይሰማል፡፡ ህፃናት፣ወንዶች፣ ሴቶች፣ ትልልቅ አዛውንቶች ጭምር አሉ፡፡
አንዲት ለምድር ለሰማይ የከበዱ፣ የጥጥ ፍልቃቂ የመሰሉ አዛውንት ጋር ስንደርስ ቆምን፡፡ <<አልጋ ነው? >> አሉን ፈገግ ብለው ... እኩል ነው <<አዎ>> ያልነው፡፡ <<ኑ ተከተሉኝ!>> አሉንና ፊት ፊት መሄድ ጀመሩ፡፡ ላጥ ላጥ እያልን ሶስት አራት ቅያስ አልፈን ቤታቸው ደረስን፡፡ አንዲት ክፍል ነች በመጋረጃ ለሁለት ተከፍላለች፡፡ ለእኛ አልጋውን ለቀው እሳቸው መሬት ትንሽ ፍራሽ ላይ ተኙ፡፡ ሃሳቤ ሐዘን መተረክ ስላልሆነ የስሜቱን ጉዳይ እንዝለለው፡፡ ሁሉም የየራሱ ሐዘን ስለሚበቃው ሐዘን ለማጋራት ቁጥብ ነኝ፡፡
በሚገርም ሁኔታ አሁን ድረስ የሚገርመኝ... ትንሽ ከማይባ ሉ ሆቴሎች በተሻለ ሁኔታ አንሶላውም አልጋ ልብሱም በጣም ንፁህ ነበር፡፡ ሶስታችንም አልገመትንም፡፡ ምናልባት የሚኖሩበት ቤትም ስለሆነ አፀዳዱ ከሆቴሎቹ ለብለብ የተሻለ ሳያረገው አልቀረም፡፡ ሁለቱም ጋደኞቼ ቤታቸው ያሉ ይመስል ጧ ብለው ተኙ፡፡ ስፎግር ነው ሙክክ ብለው ስለሰከሩ ነው ጧ አባባላቸው፡፡ የቤቱ ባለቤት እንዳልተኛው ሲያውቁ ዝምብለው ትዝታቸውን ያወሩልኝ ነበር። የማስታው ሰው ልጄን ትመስላለህ ብለው እንደ ጀመሩልኝ ብቻ ነው፡፡ እህ እህ እያልኩ ትንሽ ለማዳመጥ ታግዬ እኔም ወደማይቀ ረው እንቅልፌ ተጠራሁ፡፡
በማግስቱ በዓል ነበር፡፡ ሃይለኛ ብርሃን ቤቱን ሞልቶታል፡፡ በመጋረጃው ስር አልጋው ጠርዝ ድረስ ቄጠማ ይታየኛል፡፡ ውጪ የጀመረ የቢላ መሳል ድምፅ ወደኛ እየተጠጋ መጣ፡፡ በግምት ሶስት ሰአት አካባቢ ይሆናል፡፡ሁለቱም ጓደኞቼ ነቅተዋል፡፡ መሃል ያለው ጓደኛዬ እጅቅ ዝቅ ባለ ድምፅ <<ምንድነው? >> አለኝ... ድምፄን አርቄ <<እየሳለ ነው!>> ስል ዳር ያለው <<ምንድነው የሚስለው?>> ሲለኝ አናደደኝ... <<ስዕል ልበልህ ገጣጣ>> ስለው... መሃል ያለው ቡፍ ብ ሎ ሳቀ፡፡
በእጁ × ምልክት የሰራ በግራ እጁ መጋረጃውን ገልጦ፣ በቀኙ ደግሞ የተደራረቡ ሁለት ቢላዎች የያዘ ወጣት ነው፡፡ እንደ ብርቅዬ፣ እንደ ልዩ ነገር ሲያየን ሲያየን ቆይቶ፣ ድንገ ት <<እማዬ... ምንድናቸው?>> የሚል ድምፅ ሲያወጣ የደነገጥኩትን ድንጋጤ እኔና የ መደንገጥ አምላክ ብቻ ነን የምናውቀው፡፡ <<እማዬ በቃ ተይ ብልሽ እምቢ አልሽ አይደል?... ተነስ ምናባቱ ያፈጣል ደሞ!>> አለና ቢላውን መሳል ጀመረ፡፡
ብርሃን እንዲህ አይፈጥንም በጥግ ዳር ላይ የነበረው ጓደኛችን፣ ሁለታችን ላይ ተገላብብጦ መሬት ወርዶ ታዛዥነቱን አስመሰከረ፡፡ እኛም ያው ነበርን። <<ቀጥ ብለህ ዞረህ ሳታይ ውጣ!>> አለ በቆራጥ ድምፅ፡፡ሶስታችንንም በአንድ ጨምቆን ነው አንተ ያለን።
ተከታትለን እንደወጣን ከፊት ያለው እግሬ አውጪኝ አቀጠነው... ሩጫ ተላላፊ ነገር ነው መሰለኝ እኛም ተከተልነው፡፡ ሶስት ቅያስ እስክናልፍ ድረስ ዞረን አላየንም፡፡ ከዛ በቀረችን ትንፋሽ የምንችለውን ያህል ስቀን እንቅልፋችንን ካቆምንበት ለመቀጠል ቄራ የሚኖር የማይጠጣ ጓደኛችን ጋር አቀጠንነው፡፡
በጣም ስለምናስቸግረው መሰለኝ፣ ከቀብር እንደሚመለስ ሰው በሩ ላይ በባሊ ውሃና ጆግ አዘጋጅቶልናል፡፡ አንድ አንድ ሙሉ ጆግ ውሃ መጠጣታችንን ካረጋገጠ በኋላ ነው ወዷ ቤቱ የሚያስገባን፡፡ <<በኋላ አመመኝ ብትልና እዚህ ስተተፋ ብታድር አንተን ይዤ አልንቆራረጥም!>> ሲል የሆነ የማላውቃት አክስቴን ነበር የሚመስለኝ፡፡
እሱ ጋር ተኝተን ስንነሳ ግን ሁሌም ሰላም ነበረን። ሲጠጣ ያመሸ ብዙ ውሃ ጠጥቶ መተኛቱ... በማግስቱ ሰላም ያለው አነሳስ መነሳቱን... ጠጥቶ ሳያውቅ እንዴት አወቀው እል ነበር—ሁሌ፡፡ ምናልባት በበፊት ህይወቱ ገልባጭ ይሆን ይሆናል፡፡ "ማን ያውቃል?" እንዲሉ አብዬ መንግስቱ "ማን ያውቃል ?" ብቻ እንዲህ እንዲያ ያሉ ብዙ ለሊቶቻችን አልፈዋል፡፡
ነገ ለልጆቼ ከተሳለ ቢላ ያመለጥኩ ሰው ነኝ ብዬ ከመተረኬ በፊት ለናንተ ቅምሻውን ላስጎንጫቹ ብዬ ነው ሃሃሃሃ ይህ በአዲስ አበባ ምሽቶች በለሊት አከናውነናቸው ጠዋት ከማንተነፍሳቸው ጉዳዮቻችን መሃል አንዱ ነው... የዚህ አይነት ብዙ እልፍ ለሊቶች አልፈዋል፡፡ ሲያልፉ ያስቁ ይሆና ል፡፡ በቦታው ግን እጅግ ያሳቁነበር፡፡