Komentar baru

Advertisement

የቱሉ ፎርሳን ደራሲ እኔ እንደምገምተው…

Eriyot Alemu
Jan 23, 2023
Last Updated 2023-08-21T18:47:56Z
Advertisement

ከዚህ በፊት የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች የቱሉ ፎርሳን ደራሲ ግምት ሲያስቀምጡ አይቻለሁ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ሰርቅ ዳንኤል፣ ጃርሶ እና ዳዊ ኢብራሂም ከፊት የሚገኙት ናቸው፡፡ የኔ ግምት ሰለሞን ለማ ነው መላምቴም እንደሚከተለው ነው፡፡




፩) የደራሲው ድምፅ


አንድን ደራሲ ደጋግመህ ስታነበው አዕምሮህ ውስጥ የሚፈጠረው ድምፅ ማለት ነው፡፡ የአዳም፣ የበዓሉ በቀላሉ ይለይልኛል፡፡ የአዳም እንደውም የተለየ ከለር ያለው ሁሉ ይመስለኛል፡፡ የሰለሞን ለማም እንዲሁ የራሱ ድምፅ አለው፡፡ አንድ ቀን ከተለያየ ስራዎቹ ጋር አብራቹ ብትውሉ የሚሰማቹ ይመስለኛል፡፡ ስራዎቹም ይሆን ያህል የበዙም አይደሉም።

  • የእግር እሳት ለብቻው ያሳተመው የአጭር ልብወለዶች ስብስብ ነው።
  • እነሆ፣ ጉዞው፣ አባደፋርና ሌሎችም ታሪኮች ከተለያዩ ደራሲያን ጋር በህብረት የወጡለት የአጫጭር ልብወለዶቹ መገኛ ናቸው፡፡

በመፅሄት የወጡለትና በሞስኮቭኛ የተተረጎሙለት 2 ስራዎችም አሉት።


፪) አጀማመሩ


የሰለሞን ለማ አጀማመር ይለያል ብቻ ሳይሆን እጅግም ደስ የሚል ቅለት ያለው ነው ማለት እንችላለን፡፡ ከመሃል ነው የሚጀምረው.... አብረኸው ረዥም ሰዓት ቁጭ ብለህ ቆይተህ ድንገት ጨዋታውን እንደሚጀምር ዓይነት ሰው ይሰማል፡፡ሁሉም አፉን ከፍቶ የሚያዳምጠው አይነት ጨዋታ አዋቂ ሰው ወሬ ጅማሬ ነ ው አጀማመሩ፡፡ አልሰማህም ለማለት አቅም የሚያሳጣ ዓይነትነገር፡፡


ምሳሌ እንይ

እነሆ ላይ “ሚጢ ሚጢዬ" የሚል ስራው ሲጀመር.....


ይች የጋሸ ከበደ ልጅ ትንሿ በጣም ደስ ትለኛለች፤ ትገርመኛለች፡፡ ሁለት ዓመት ቢሆናት ነው:: ሚጢጢ ነው ስሟ ፡፡ እናትና አባቷ ፥ እኛም ጐረቤቶች ፧ ሚ ጢጢ ፧ ነው እምንላት ፡፡ ደሞ ‘ሚጢ ፥ ሚጢዬ' እ ንላታለን ስናቆላምጣት ፡፡ በዛች ኮልታፋ አፏ ስትናገር ትንንሽ ምራቆች እየተቆራረጡ ይረጫሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ፧ ባለማንጠልጠያ ይሆኑና አፏ ላይ ታስረው በማንጠልጠያቸው ቁልቁል ይወርዱና አገጯን ተንተርሰው ይወዛወዛሉ ። እኔ ደሞ ደስ እሚለኝ ይኸ ነው፡፡ ልጅን “ለሀጩ ፤ ምኑ" ማለት አልወድም ፡፡ ብቻ ሚጢየ ስትናገር እምትናገረው ቃል ሳይሆን ቃሉን እንዴት እንደምትናገረ ው ነው ደስ እሚለኝ ፡፡ ታዲያ የሁለት ዓመት ልጅ ምን ቁም ነገር ይናገር ብየ ላዳምጥ።

 

ጥጉ የአራዳ ልጅ የእግር እሳት ውስጥ


ይገርመኛል! አንዳንዱ በመለኪያም ይሁን በጠርሙስ አራት አምስት ይጠጣና ከሞቅታ ዐልፎ ብዙ ብዙ ያናግረዋል ፡፡ ጥጉ ያራዳ ልጅ ግን ይች ቅምም አትለው ፡፡ እሱ እቴ ! ስምንተኛውን ሲያስቀዳ ነው መጠጣት ጀመርኩ የሚለው። በጠርሙስም ይሁን በመለኪያ ዐሥርን ካላለፈ ሰውም ቀና ብሎ አያይ። ዐሥራ አምስትን እንደተዳፋ ዘፋኝም ፥ ጋባዥም ፡ ጀግናም ፡ ፎካሪም ፥ ሥራ ወዳድም ፧ ቆጣቢም ሁሉንም መሆን ይጀምራል ፡፡ አየ ጥጉ ! ታዲያ መለኪያውን እንደ ጨበጠ ድንገት ብድግ ይላል ከመቀመጫው።ከዚያማ ጐርደድ ፧ ጎርደድ ይላል፧ ዙሪያ ገባውን እየተመለከተ ፡ ጠጪው ሁሉ አፍጦ ይመለከተዋል ፡፡ እሱ ምን ዕዳው ፡፡ እሚያውቁት « ሸጋው ወንደላጤ ፡ ጥጉ ያራዳ ልጅ» ይሉታል ። ደስ ይለዋል ፡፡

 

የገብሩ መዘዝ የእግር እሳት ውስጥ


አራዳ ገበያ እንደ ዛሬው ሳይሻሻል ትርኪ ምርኪ የበዛበት ሰዉም ፥ ፍየሉም በጕም አህያዉም የሚርመሰመስበት ሥርዓት የለሽ ጕልት በነበረበት ጊዜ ቃሪያና ሽንኩርት መቸርቸር የጀመረችው ሀዋ ዛሬም እዚያው አራዳ ቸርቻሪ ናት ፡፡

 

እ ን ኮ ዬ


ከእንጦጦ እየተምዘገዘገ እሚመጣው ሽንጣም አውቶቡስ ባልቴቷን ለጥቂት ሳታቸውና መንገዱን አሳብሮ መልሶ እንደዚያው ሲምዘገዘግ የተመለከተው ሁሉ ድንግጥ ብሎ ቀረ ፡፡ የስድስት ኪሎን ሐውልት ተጠምዝዞ ተዐይኔ እስኪርቅ ድረስ ተከተልኩት ፡ እየተምዘገዘገ ወረደ ። በጣም ተናደድኩኝ ፡፡ ሴትዮዋን እኮ ጨፍልቋቸው ዐርፎ ነበር እሳቸውስ ዳር ዳሩን አይሔዱም ። ደሞ መልሼ ተናደድኩ ፡፡ ዘወር ስል የተረፉት ባልቴት ከጐኔ ድንግጥ ፍዝዝ ብለው ቆመዋል ። 

 

ባሻ ገላጋይ


ሲጥል ያደረው የክረምት ዝናብ ፥ የእነ ባሻ ገላጋይን መንደር አጨቅይቶት መተላለፊያ ጠፍቷል ፡፡ በእንዲህ ያለው ቀን ደግሞ ባሻ ገላጋይ ከመኝታቸውም መነሣት ደስ አይላቸው :: ግን ሥራ ነውና ተነሡ :: ዝናቡ ሌሊቱን አልቆ ኖሮ ጧቱን ብን ብን እያለ የሰፈር ውሪዎችን በየቤታቸው አሸሎአቸዋል ። ባሻ ገላጋይ ልብሳቸውንና ጉልበታቸው ድረስ የሚለጠጠውን ካ ልሲያቸውን አጥልቀው የሱሪያቸውን ጫፍ ጠቅልለው እውስጡ ከተው ሁለት ጊዜ ወደ ላይ እንጣጥ እ ንጣጥ ብለው ቁልቁል ተመለከቱ፡፡ ጫማቸው ፥ ካል ሲያቸው ፥ ሱሪያቸው በመልክ በመልኩ ሆኗል ። ነጩን ረዥም ጢማቸውን በቀኝ እጃቸው ሁለት ጊዜ ዠምገጉት፡፡ ብዛቱም ርዝመቱም ያው ትናንት እንደነበረው ነው :: 

 

ጉዞው ላይ

ደብዳቤው


ለተወዳጁዋ እህቴ ለወይዘሪት ብስራት ፡፡ አይቸሽ ድንገተኛው ፍቅርሽ የዘወትር ሰቀቀን ሆኖብኛል። በፍቅርሽ ወጥመድ ውስጥ ገብቼ በጕምዥት ካራ መተፍተፍ ከጀመርኩ ውዬ አድሬአለሁ ፡፡ ዳሌሽ ጣ ቶችሽ ፥ ፀጉርሽ አንገትሽ ብዬ ውበትሽን ለማድነቅ አልሞክርም ፡፡ ቃላት አጥረውኝ በጅምር ከምተወው አለመሞከሩን መርጫለሁ ፡፡ ፈጣሪ ብዙ ሰዎችን መሥራት የሚችልበትን ጊዜ በአንቺ ላይ አጥፍቶአል ፡፡ ተጨንቆ ተጠቦ የሠራሽ በመሆንሽ ኩራት ይሰማሽ። አንቺን በማፍቀሬ እኔም ኩራት ይሰማኛል ። በዓ ይኖችሽ ግርፍታ ከተገረፍኩ ወዲህ  ዋኝቼ ከማልወጣው የፍቅር ባሕር ውስጥ ገብቻለሁ። ከአንቺና አንቺን ከወደደው ከእኔ ሰውነት በቀር ሌላ ማየት አስ ጠልቶኛል ፡፡ የምበላው አይስማማኝም የሰዎች ወሬ አይጥመኝም ፡፡ ምን አለፋሽ ዘመድ የሌለው እብድ ሆኘልሻለሁ ፡፡ ይህ ሁሉ አንቺን በማፍቀሬ አንቺን በመውደዴ ነው። ብስራት ፍቅረኛዬ እንድትሆኝ መርጨሻለሁ። እንደማትጨክኝብኝ አውቃለሁ :: በእኔ መጨከን ያን ተጨንቆ ተጠቦ የሠራሽን አምላክ ማስቀየም ነው፡፡ ዓይኖችሽ ብዙ በማንበብ እንዲቀሉ አልፈልግም ፡፡ መልስሽም አጭር ቢሆን ደስ ይለኛል ።ቁርጥ ያለ " እሺ ወይም እምቢ " ይኸን ያልኩሽ ያንቺን መልስ ማንበብ ይሰለቸኛል ብየ አይደለም ፡ ብዙ በመጻፍ እኒያ አለንጋ ጣቶችሽ እንዲዶለድሙ አልፈልግምና ነው። በተስፋ መልስሽን እጠብቃለሁ።ሰላምና ጤና ከአንቺ ጋር ይሁን ፡፡ 

የፍቅርሽ ምርኮኛ 

ህዳር 21 ቀን 1950 ዓ.ም

 

ጉዞው ላይ 

ጎራው


ጦር ሜዳ ውሎ አያውቅም ብቻ ስለጦር ሜዳ ሲወራ ብዙ ጊዜ ሰምቷል ፡፡  በአምስቱ የወረራ ዘመን ዱር ቤቴ ብለው ቅጠል ለብሰው ጢሻ ለጢሻ ተጉዘው መግቢያ መውጫ ሲያሳጡት ጠላትን ሲያርበብዱት እሚሉ ወሬ ከሰማ አፉን ከፍቶ ሲያዳምጥ ይውላል ፡፡ ሆኖም ደነቀው አገር ያወቀው ዘመድ ወዳጅ እሚወደው ታታሪ ገበሬ ነው ፡፡ የአድዋ ድል ሲከበር የነፃነት ቀን ሲታወስ እሱም ያ ያላየው ያ ያልዋለበት ጦር ሜዳ ትውስ ይለውና ነሸጥ ያደርገዋል። ወደ ኋላ ተመልሶ በወሬ የሰማውን ጀግንነትና ቀኛማች ደጀኔም ያጫወቱትን ታሪክ እያደነቀ ይገረማል። በላይ ዘለቀ ሲባል ስምቷል ፡፡ ከበላይ ጋር ጦር ሜዳ ከዋለ ሰው እኩል ስለ በላይ ያወራል ፡፡ እናቱ የወሬወሬ “ የተወለድከው ደጃች በላይ በተያዙ በአምስተኛ ው ዓመት ነው ሲሉት'' “ ምነው ሳይያዙ ቀደም ብለሽ ወልደሽኝ በነበር" ብሎ ይጸጸታል ፡፡ ታዲያ ያ ሲተረክ እሚያስፈዝዘው የጦር ሜዳ ወሬ ወሬ ሁኖ አልቀረም ፡፡ እናት ሀገር ጀግኖች ልጆቹዋን የምትፈልግበት ለብዙ ልጆቹዋ ጥሪ የምታደርግበት ወቅት መጣለት – “ጀግኖች ልጆች ያላት ሀገር ተደፍራ አትቀርም” ብሎ ሁሉም በያለበት ሲነሳ  በደነቀው ደም ውስጥ የሚፈላው ጀግንነትም አብሮ ተቀሰቀሰ ፡፡ የአባቱ ጓደኛ ቀኛማች ደጀኔ ያ ሚያጫውቱት ሁሉ ቅርብና እሚጨበጥ መስሎ ታየው

 

ቱሉ ፎርሳን ደሞ እዚጋ እናምጣው…


ቱሉ ፎርሳን ማን የማያውቅ አለ? እናንተ አታውቁትም እንዴ ? ቱሉ ይሄ ማካሮኒ ፋብሪካ ውስጥ የሚሠራው እኮ ነው ፡፡ኦ ቱሉን ማን የማያውቅ አለ? 

 

ቱሉ ሠላሳ ዓመቱ ነው፡፡ወይም ወደዚያ ግድም ነው፡፡ እና ቱሉ ቁመቱ ረጅም ነው። የቱሉ እጆች ትላልቅ ናቸው፡፡የቱሉ ክንዶች ጠንካሮች ናቸው፡፡የቱሉ መዳፎች ሸካራ ናቸው፡፡ ቱሉ ከማካሮኒ ፓስታና ፓስቲኒ ፋብሪካ ውስጥ ወፍጮ ክፍል ነው የሚሠራው፡፡ ወፍጮ ክፍል ስድስት ዓመት ሠርቷል፡፡ የፋብሪካው ባለቤት ሙሴ ጋሌብ ናቸው፡፡ ጌታ ጋሌብ እዚች ሃገር (ይቺው የኛይቱ የምንላት) ሲገቡ ቤሳቤስቲን አልያዙም ።እዚህ ከገቡ በኋላ ነው ይህንን ሁሉ ያፈሩት፣ ያንን ሁሉ ቪላ ሠርተው የሚያከራዩት፣ያንን ሁሉ ሱቅ የከፈቱት፡፡ ጌታ ጋሌብ የናጠጡ ዲታ ናቸው፡፡አቤት ሠራተኛ ሲፈራቸው፡፡ጌታ ጋሌብ ሽማግሌ ናቸው፡፡አጭር መላጣ ባርኔጣ የማይለያቸው አማርኛ አቀላጥፈው የሚያውቁ ዕድላም ሰው ናቸው፡፡ ስለ አበሻ ሲናገሩ < < አበሻ ሥራ አይወድም፡፡አበሻ ሠነፍነ ው ለዚህ ነው ሃብታም የማይሆነው -- እንደኔ>> ይላሉ። 

 


፫) የገፀባህሪያት ምርጫው


አብዛኛው ምርጫው ወይ ዝቅተኛው መደብ አልያም ሰራተኛው መደብ ነው፡፡

እንደውም የእግር እሳት መፅሃፉ ውስጥ “ድብብቆሽ” ላይ ያለችው አረጋሽ፣ ቱሉ ፎርሳ ላይ ያለው ማህበር ለመቋቋሙ ጥንስስ ከሚጥሉት ወገን ነች፡፡


፬) የድርሰቱ ባህሪ


አብዛኛው ስራው የሚያሳዝን ሃሳቦች የሚነሱበት ነው፡፡ እንደውም የእግር እሳት ሙሉ መፅሃፉ በሞት የተለወሰ ነው ማለት ይቻላል። በዚህ አጋጣሚ ሰለሞን ለማ የሰዎች የሞት ምክንያት እና ራሱ ሞት በብዛት የሚያስደንቀው ሰው ይመስለኛል፡፡

እና ስራው ሃዘን ቢበዛውም እያንዳንዱ ውስጥ በሚገርም ሁኔታ ፈገግታ ወይም ሳቅ አለ፡፡ የሚያሳዝን ነገር ሲነግርህ ፈገግ ብለህም የምትሰማው ሰው የተለየነት ይጠይቃል፡፡ ሰለሞን ለማ እንደዛ ነው፡፡

ቱሉ ፎርሳም ያ መንፈስ አለው፡፡


፭) አጨራረሱ


አጨራረሱ ሰቅጣጭ የሚባል ነው፡፡ ወይም በጣም አስቂኝ፡፡ ቱሉ ፎርሳም ሊያልቅበት ያለበት መንገድ የተለመደው የሰለሞንን መንገድ ነበር፡፡ የህፃኑ ሁኔታ ፍፃሜው ሞት ነበር፡፡ ግን የሰራተኛው ማህበር ጉዳይ ስለበለጠበት ይመስለኛል ህፃኑ ሊተርፍ ችሏል፡፡ ትንሽ ደመደምኩ መሰለኝ......


፮) ልኬት መጠኑ


ሁሉም የሰለሞን ስራ ቅልብጭ ያለ ነው፡፡ ደጋግመው ሲያነቡት መጠኑን መገመት ይቻላል፡፡


፯) አንዳንድ ገለፃዎቹ


እድሜ፣ አረማመድ አይነት ሲገልፅ ከቱሉ ፎርሳ ጋር የሚሄድ ብዙ አይቻለሁ፡፡ እሱ እቴ ዓይነት የአገላለፅ ድግግሞሹም ጭምር፡፡ የደራሲው ድምፅ እና አገላለፅ ተያያዥነትም አላቸው፡፡


ይህ እንግዲህ የኔ ግምት ነው፡፡ ግምት ደግሞ መላምት ነው፡፡ ላይሆንም ይችላል የሚል ነገር አለው ውስጡ፡፡እንዲህ ከሆነ ደግሞ ታዲያ እሺ ማነው? የሚል ጥያቄን ይወልዳል ። እኔ ደግሞ መላምቴን ማስቀመጥ ወድጃለሁና አደረግሁት፡፡ 


ይሄን የምታነቡ ሰዎች እድሉ ካላችሁ ስለ ሰለሞን ለማ የተፃፈ ነገር ሁሉ ብታጋሩኝ ስል ከታላቅ ትህትና ጋር እጠይቃለሁ፡፡ እንዲሁም ፎቶግራፉን አይ ዘንድ ብታስችሉኝ ደስታዬ እጥፍ ድርብ ነው፡፡

በዚህ ርዕስ ዙሪያ ለማንኛውም አስተያየት ጆሮዬ የቆመ ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡


በመጨረሻ ግን እነሆ የተሰኘ የደራሲያን ማህበር ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳተመው፣ የተለያዩ ደራሲያን ውጤት የሆነ የአጭር ልብወለድ ስብስብ ውስጥ የተካተተውን “ሚጢ ሚ ጢዬ” የተሰኘውን የሰለሞን ለማ ስራ ጋብዤ ነው የማሳርገው፡፡ አቤት ይሄን ስራ ስወደው.... አቤት ውበቱ፣ ቅለቱ፣ ስሜቱ ብዙ ብዙ ነገሩ ሲበዛ ይደንቀኛል፡፡ ይማርከኛል።

እነሆ ብያለሁ 


                                                                ‘ሚጢ ሚጢዬ’


ይች የጋሸ ከበደ ልጅ ትንሿ በጣም ደስ ትለኛለች፤ ትገርመኛለች ፡፡ ሁለት ዓመት ቢሆናት ነው ፡፡ ሚጢጢ ነው ስሟ ፡፡ እናትና አባቷ፧ እኛም ጐረቤቶች ፡ ሚጢጢ ፥ ነው እምንላ ት ፡፡ ደሞ “ሚጢ ፥ ሚጢዬ” እንላታለን ስናቆላምጣት ፡፡ በዛች ኮልታፋ አፏ ስትናገር ትንንሽ ምራቆች እየተቆራረጡ ይረጫሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ፡ ባለማንጠልጠያ ይሆኑና አፍ ላይ ታስረው በማንጠልጠያቸው ቁል ቁል ይወርዱና አገጯን ተን ተርሰው ይወዛወዛሉ ። እኔ ደሞ ደስ እሚለኝ ይኸ ነው፡፡ ልጅን “ለሀጩ ፤ ምኑ” ማለት አልወድም ፡፡ ብቻ ሚጢየ ስትናገር እምትናገረው ቃል ሳይሆን ቃሉን እንዴት እንደምትናገረው ነው ደስ እሚለኝ ፡፡ ታዲያ የሁለት ዓመት ልጅ ምን ቁምነገር ይናገር ብየ ላዳምጥ ፡፡


ሚጢዬ ጭቃም ስታቦካ ፥ ዐፈርም ስታቦካ ፥ ዐመድም ስትቀባ ፥ ሣርም ላይ ስትንከባለል ሳገኛት ሳልስማት አላልፍም ፡፡ ልስማት አስቤ ቁጭ ካለችበት ወይ ከተጋደመችበት ሳነሳት፥ በግድ ነው፡፡ የያዘቸውን ነገር በቀላሉ አትለቅም ፡፡ ቁርስ፧ ምሳ፥ እራት በቡጢ ነው እምትበላው ፡፡ ጋሸ ከበደም ሲደክም ውሎ ሲደክም ያመሽና ራሱን ስቶ ቤት ይገባል ፡፡ ታዲያ እየፎከረ ይተኛል እንጂ ፥ ‘ሚጢ በላች ወይ ፧ ታጠበች ወይ?' እሚሉ ጣጣ አያውቅ ም ፡፡ እሱ እቴ ! እናቷም ልጅ እስከ አፍንጫቸው ድረስ ስላላቸው ነው መሰል የት ሔደች ? ምን በላች ? አለቀሰች? ሣቀች ከቁብም አይጥፉአት ፡፡ ይገርመኛል! የድሃ ሀብቱም በሽታውም ልጁ ነው እሚባል ለካ እውነት፥ እውነት አለው ::


ሚጢዬ በሌሊት ትነሣለች :: አሁን ልጅ ተንጠራርቶ ዐይኑን አሻሽቶ ተገላብጦ አይደለም እሚነሣው ! እሷ እንደሱ አታረግም ፡፡ ጅምላስቲክ እሚሠሩ ሰዎች ቁጭ በሉ ሲሏቸ ው ቶሎ ንስት አደል እሚሉ! እሷም ልክ እንዲሁ ናት ፡፡ ዘጠኝና ስምንት ሰዓት ተኝታ እምትነሣ አትመስልም ፡፡ ሰው ተደብቃ ቆይታ ሰውዬው ሲሔድላት ሌላ መደበቂያ ፍለጋ እምትሸሽ ነው እምትመስለው ፡፡ ራቁቷን ትነሣለች ፡፡ አይ ሰውነቷ ደስ ስትል ፡፡ የዶሮ ያህል እኮ አትከብድም ፡፡ አጥንቶቿ ፈጠው ፈጠው ፥ ሰውነቷ ዐመድ የተቀባ መስሎ ያች የአንድ ቀን ዝናም ችፍ ያደረጋት ሣር እምትመስል ጸጉሯ ተያይዛ ተያይዛ ፡፡ እኔ ደስ ትለኛለች ፡፡ እናትና አባቷ እኮ ገና አፍላው እንቅልፍ ላይ ናቸው፡፡ሰማይና መሬቱ በል ደና ዋል ተባብሎ ሳይሰነባበት ለማኝ ምን ሳይል ነው እሚባል ያን ጊዜ ብድግ ትልና አብረዋት እሚተኙትን ወንድምና እኅቶቿን ረጋግጣ ፈትለክ ትላ ለች ፧ ራቁቷን ፡ ወደ ትንሿ ሳሎን ፧ መቸስ ሳሎን ከተባለች፡፡


ጋሸ ከበደ የበሩን መቀርቀሪያ ወፍራም ዕንጨት በበሩ ግራና ቀኝ ባሉት የቦንዳ ቀለበቶች ውስጥ ያሳልፍና አሻሮ መቁሊያም ልብስ ማጠቢያም ፥ የውሃ ማጠራቀሚያም አንዳንድ ቀንም የገላ መታጠቢያ የሆነውን ትልቅ ብረት ምጣድ አስደግፎት ይተኛል ፧ ሌባ ቢመጣ ሲንቋቋ ሊነሣ ፡፡

ውሸቱን እኮ ነው ፤ እንኳን የብረት ምጣድ ኳኳቴ የመድፍ ጩኸትም እኮ አይቀሰቅሰው! እንኳን ዕቃውን እሱንም ተሸክመውት ቢሔዱ እኮ አይነቃ ፡፡ እንዳው ሌባዉ በሩን ሲገፋ ብረት ምጣዱ ወድቆ ሲንኳኳበት ራሱ ደንግጦ ይሔድ እንደሁ እንጂ ፥ ጋሼ ከቤ አቅበታለሁ ፡፡ከተኛ ንቅንቅም አይል ፡፡ እንዴ ስንት ዓመት! አብረን ኖረን ይኸ ደሞ ይጥፋኝ ፡፡


ታዲያ ሚጢዬ ትነሣና ያንን ብረት ምጣድ በእግሯ ገፍታ ትጥለዋለች ፡፡ ዘሎ ፧ ዘሎ ፧ ዘሎ ፥ ጮሆ ጮሆ ፥ ዝም ይላ ል ፡፡ አንዱን መዝጊያ ከፈተች ማለት ነው ፡፡ ሮጥ ትልና ጋሼ ከቤ በዳንቴል የተሸፈነች ሬዲዮኑን እሚያስቀምጥባትን አጣና ተራ የተሠራች ትንሽ ጠረጴዛ እየገፋች ታመጣለች ፡፡ ከብረት ምጣዱ ቦታ ላይ ቁጭ፡፡ ከዛ ትግል ትጀምራለች ፥ ጠረጴዛዋ ላይ ለመውጣት ፡፡ ብላ ብላ ትወጣለች ፡፡ ተዚያ ወፍራም ዕንጨት ጋር ትታገላለች ፡፡ ወደ አንዱ ወገን ባለ ኃይሏ ትገፋዋለች ፡፡ ትገፋለች ፤ ትገፋለች ። ድክም ይላታል ፡፡ ጠረጴዛው ላይ ቁጭ ትልና ደሞ ትነሣለች ፡፡ ትገፋለች ፤ ትገፋለች ። ያ ግንድ ወደ አንዱ ቀለበት ይበልጥ እ የገባ ከሌላው እየወጣ ይሔዳል ፡፡ ደስ ይላታል ፡፡ ትገፋለች ፤ ትገፋለች ፡፡ ኋላ ራሱ ይንኳኳና ይወድቅላታል ፡፡


“ኦ" ትልና ሁለት ሦስት ጊዜ ትዘላለች ፥ የደስ ደስ ፡፡ ይህን ሁሉ ስታደርግ አንድ ሰው ንቅንቅ አይልም ፡፡ ጭራሽ ያንኮራፋል ፡፡ አዬ ሚጢዬ ! እስቲ ብቻዋን ! ትወርዳለች ተጠረጴዛዋ ላይ ፡፡ እየገፋች ከነበረችበት ቦታ ትመልሳታለች ፡፡ አሁን ትልቁ ደስታዋ ነው ፡፡ ቶሎ ትልና በሩን ከፍታ ወደ ውጭ ፡፡ በቁሟ ሽንቷን ትለቀዋለች ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ዐፈሩ ይመጣባታል ፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ትንሽ ኩሬ ይሠራላታል ፡፡ ትንሹ ኩሬ ሲሠራላት አቤት ደስታዋ !


“ አናና አናና " እያለች ትዘላለች ወደ ላይ ኩሬ ኩሬውን እየተመለከተች ፡፡ ኩሬዉ ዐልፎ ዐልፎ ዐረፋ ይኖረዋል ፡፡ አቤት ደስ ሲላት ! መጀመሪያ በዚያች በዐረፋዋ ትጫወታለች ፡፡ በጣቷ ጠንቆል ስታደርጋት ትጠፋላታለች ፡፡ ደሞ ውስጥ ውስጡን ትሔድና ሌላ ቦታ ብቅ ትልባታለች ፡፡ ያችንም ጠንቆል ታደርግና ታጠፋታለች፡፡ ሁሉም ሲጠፋላት ዐፈር ለመዛቅ ትሔዳለች ፡፡ የእኛ ሰፈር ደግሞ በዐፈርና በጭቃ አ ይታማ አደል ! ወደ አንዱ ወገን ትሔድና ዛቅ አድርጋ ታመጣለች ፡፡ ከዚያ ማቡካት ፡፡ እንግዲህ እናቷ ሊጥ ሲያቦኩ አይታም እንደሁ እንጃ ታዲያ አቤት ጭምልቅልቅ ትላለች ፡፡ እኔ እሚገርመኝ ብርዱን እንዴት እንደምትችለው ! 


እኔ እንግዲህ በሌሊት አደል እምነሣው ፧ ሠራተኛ ከየቤቱ ለማምጣት ፡፡ አሥመራ ያለው ወንድሜ የላከልኝን ባለጐፈር ጃኬት ሚስቴ ባለሙያ ናት—የሠራችልኝን ሹራብ ፥ የፈተለችልኝን ጋቢ ደራርቤ ነው እምወጣው ፡፡እንዳው የሹራብና የሚስት ነገር ከተነሣ እንዴ ያለኝ ሹራብ እኮ ቀላል አይደለም ፡፡ እኔ ፋብሪካ ወረስኩ እንጂ ሚስት አገባሁ ማለት አይገባኝም ፡፡ ታዲያ ይኸን ሁሉ ደራርቤ ስወጣ ብርዱን አልችለውም ፡፡ “ልጅና ፊት አይበርደውም " እሚባለው እኮ ውነት ነው :: እኔን እንዳው እርግፍግፍ ነው እሚያረገኝ ፡፡ የልጅ ሰውነት ይችለዋል ልበል? አየ ሚጢየ!


ሁልየም ቢሆን ልክ በ12 ሰዓት ጣጣየን ጨርሼ ከቤት እወጣለሁ፡፡ ሰኞም ልውጣ ማክሰኞ ገና ቤቴን ከፈት እንዳደረግሁ እማየው መጀመሪያ— ነፍሱን ይማረውና የዕድራችን ጥሩምባ ነፊ የነበረውን የጋሸ መርጊያን ውሻ ነው ፡፡ ጋሸ መርጊያ ይኸው እንግዲህ ጠላት ከወጣ ጀምሮ ጡሩምባ ነፊ ነበር፡፡ ጥሊያን ጥሏት የሔደ የባንዲራ መስቀያና ማውረጃ ጡሩምባ ከየት እንደሁ አላቅም ይወርሳል ፡፡ ለመዳትና የኀዘን ጡሩምባ ነፊ ሆነ ፡፡ይኸን እንኳ አልደረስኩበትም ፡፡ ያች ጡሩምባ አርጅታ እምቢ ብትለው እሷን ይጥልና የዕድር ጡሩምባ ነፊ ሆነ ፡፡ ታዲያ ዕድሜ ልኩን ጡሩምባ እንደ ነፋ አርጅቶ ሞተ፡፡ ውሻውም እኮ አርጅቷል ፡፡ ውይ ደግሞ የውሻ እርጅና ሲያስታውቅ እቴ ፡፡ ታዲያ ያ ውሻ እያሳዘነኝ ተምበላው አቀማምሰዋለሁ ፡፡ የወደቀውን አመጣና እሰጠዋለሁ ፡፡ያችን ውለታ አርጐ ቤቴን መጠበቁ ነው ፡፡ ሁለተኛ እማየው ሚጢዬን ነው ጭቃዋን ስታቦካ ፡፡ እራቁቷን እንዳው ዕርቃነ ሥጋዋን ፡፡


ሳያት አንጀቴ እርግፍ እርግፍ ይላል ፡፡ እሷም ስታየኝ እኮ አያስችላት ፡፡

“አናና አናና!” እያለች ትዘላለች ፥ ወደ እኔ እየተመ ለከተች

“ ሚጢየ " እላታለሁ ፡፡

“ አናና አናና!” ትዘላለች ፡፡ አንጀቴ እርግፍግፍ ፡፡ ወይኔ ልጅ እንኳ የለኝ ፧ ልጅ ምን አስወደደኝ ፡፡ ኧረ ልክ ነው ልጅማ ቢኖረኝ አልወዳትም ነበር ፡፡ እንኳን አልኖረኝ ፨ የራሷ እናት አሉ አይደል ልጅ የሞላቸው ፡፡ አያስችለኝ አደል ቀረብ እላታለሁ ፡፡

“ አናና አናና!" መዝለል ብቻ ፡፡ አይጣል እኮ ነው ልጅ ሲወድ ፡፡ በጣም ነው እምትወደኝ ፡፡ ትኩር ብየ ስመለከታት ፧ ጭቃ ብቻ ። ፊቷን ኩላ ኩላ በቃ ደንበኛ አይጥ ፡፡ ሰውነቷ በሙሉ ጭቃ ፡፡ በእውነት በጣም እበሽቃለሁ ፡፡


“ሚጢየ በይ ነይ እማማ ፡፡”

“አናና አናና!”

“ዐይኔ እያየ ዝም ብየሽ አልሔድም ፡፡”

“አናና አናና!"

እቅፍ አረግና ጋቢየን ልብስ አረጋታለሁ ፡፡ ሰውነቴ ላይ ጥብቅ አረግና ሽፍንፍን አረጋታለሁ ፥ እንዲሞቃት፡፡ ታዲያ በጣም ይገርማችሁአል እንዲህ ሳደርጋት ነው እሚበርዳት ፡፡ ያንቀጠቅጣታል ፡፡ እኔ አንጀቴ አይችል፡፡


“ሚጢየ በረደሽ?"

“ቢቢ ቢቢ ፡ "

“እህ መኪና ትፈልጊያለሽ? በመኪና ልውሰድሽ?”

“አቢቢቢቢ።”

“አይዞሽ እወስድሻለሁ!"


“አናና አናና!” አንዳንድ ጊዜ ተመሥሪያ ቤት መኪና ይዤ ስመጣ እዚያው እመንደር ውስጥ አለ አይደለም ! አንሸራሽራታለሁ ፡፡ የመኪና ነገር ሞቷ ነው ፡፡ ቢቢ ማላቷ በመኪና ውሰደኝ እኮ ነው ፡፡ ታዲያ እንደዚያው እቅፍ አረጋትና ሚጢየ የከፈተችውን በር እቆረቁራለሁ ፡፡ አይሰሙኝም፤ ትንሽ ጨመር አረጋለሁ ድምፁን፡

“ማነው?”

“የሚጢ እናት ነዎት !"

“አዎ!”

“በሞትኩት ፥ ምነው በጧቱ ጋሸ አበራ?"

“ኧረ ሚጢየ እኮ ራቁቷን ውጭ ነች፤ እባካችሁ አስ ገቧት ብርድ ይገላታል ።”

“ይች እርኩስ ፥ የማን አባቷ ጦስ ልትሆን ነው? እባክሁ አስገቡልኝ ጋሸ አበራ ?"


እቅፍ እንዳረግሁአት እቤት ውስጥ አስገባና በሩን መለስ አድርጌባት እሮጣለሁ ወደ ሥራየ ፡፡ ታዲያ ብዙም አልራመድ ፡፡ ስታለቅስ ይሰማኛል፡፡ “ለምን በሌሊት ወጣሽ ?" ብለው እናቷ በኩርኩም በጥፊ ይመቷታል ፡፡ ውይ ያልተወለደ አንጀት እሚሉት ይሻል የለም እንዴ እባካችሁ ፡፡ አፍልሰው አፍልሰው ይተዋታል ፡፡ ታለቃቅስና መልሳ ወደዚያቹ ጭቃዋ ! የዚህን ጊዜ እሚያስገባት ጋሼ ከቤ ነው ፡፡ እጅዋን ጨ በጥ ያረጋታል ፡፡ ቀና ትልና ታየዋለች ፡፡ጐንበስ ይላል እንደ መንበርከክ “አናና አና አናና!" ትዘላለች ፤ ትዘላለች ፡፡ እንግዲህ አባቷ መጥቶ የለ ! በእሷ ቤት ሊታቀፋት ይመስላታል ፡፡ ታፋዋን በቁንጥጫ ለምዝጎ ለምዝጎ ለምዝጎ ይተዋታል ፡፡ 

ገፍትሮ ወደ ቤት ያስገባታል ፡፡


“የት አባሽ ደጅ ሆንሽ? ይችን ፈልገሽ አይደለም በሌ ሊቱ እሚያንቀዠቅዥሽ” ይላሉ እናቷ ከውስጥ ሆነው፡፡


ኤዲያ ? አንዴ ማልቀስ ከጀመረች አታቆምም ፡፡ ዜማዋን እየቀያየረች ስታለቅስ ትውላለች ፡፡ ደሞ ትንሽ ትጫወትና፥ “እሰይ አቆመች” ሲባል ትጀምራለች ፡፡ ደሞ ማረፍ ፥ ማልቀስ ፥ እሷን እሚያስቆም በሰፈሩ እሚያልፍ መኪና ብቻ ነው ፡፡ ገና ከሩቅ ድምፁን ስትሰማ ለቅሶዋን ታቆማለች ፡፡ ቀረብ እያለ ሲመጣ እየዘለለች ፥

“አናና አናና አናናና ፡ አናና !" ፌሽታ ይሆናል፡፡ ልክ በእሷ ፊት ለፊት ሲያልፍ ደግሞ ፡፡

“ኦ…” ትልና በሣቅ ትሞታለች ፡፡ አይ ሚጢየ ! ደስ ትለኛለች ፤ ትገርመኛለች ፡፡ ምስኪን !


አንዳንድ ቤት ያውም እኮ ምን የመሰለ እንኳን ብርድ ጥይት እማያስገባ ምንጣፍ እያለ ፥ ሚጢን እምታህል ልጅ ካልሲ ሳታረግ ፥ ጫማ ሳትደርብ በእግሯ ከሔደች አቤት የሚደርሳት ማስጠንቀቂያና ማቁለጭለጫ !


“ጫማ ሳታደርጊ በእግርሽ ከሔድሽ" ትባላለች ፡፡ “ኢሂ ኢ ኢሂ" ትላለች ፡፡ እንግዲህ ኩልትፍትፍ እያለች እሚያስጠነቅቃት ሰው አፏን እንደሷ ለማጣፈጥ እየሞካከረው ጠበብ ፥ ሞጥ ሞጥ ጠመም እያደረገ ፥

“ብሽክሊት አይገዛልሽም?"

“ኢሂ — ኢ – ኢሂ፡”

“ደሞ በቢቢ አትሔጅም?"

“ኢሂ – ኢ ኢሂ፡፡”

“ደሞ ቪዲዮ አይከፈትልሽም?"

“ኢሂ - ኢ - ኢሂ ፡፡”

“ደሞ ሶደሬ ተነ ፒፒ ጋር አትሔጂም?"

“ኢሂ ኢ ኢሂ ፡፡ ”

“ጫማሽን ታደርጊያለሽ አይደለም?"

“ኢሂ ኢ – ኢሂ " እቅፍ ያደርግና እያባበለ ካልሷንም ፡ ጫማዋንም ያረግላታል ፡፡ እኔ እንደ ሚጢ ደስ እምትል ልጅ ደስ ይለኛል ፡፡ እንደ ሚጢ እምታሳዝን ግን ደስ አይለኝም ።እንዲህ ተሆነ አልወልድም።


ሰኞ ዕለት ተረኛ ስላልነበርኩ ፥ በ10 ሰዓት ከሥራ ወጥቼ ወደ ቤቴ ነበር የሔድኩት ፡፡ በዐሥር ሰዓት የገባሁ ዕለት በገዛ ቤቴ እንግዳ እሆናለሁ ፡፡ ሚስቴ እምታረገኝን ነው እምታጣው ፡፡

“ቡና ይፈላልህ?” — “እሽ”

“በቅቤ አድርጌ ትንሽ ቂጣ ልስጥህን” – “እሽ”

“ለእግርህ ውሃ ይሞቅልህ ?” – “እሽ”

“ለራትህ ፖስታ ይሠራልህ?” – “እሽ፡፡”


አቤት ! ደግሞ አምሽቼ ስገባ :—

“ምነው ያመሽህበት አላሳድር አሉህ?" — ዝም 

“ለአንተ ቤት ከፋች የተቀጠረ እኮ የለም!” —ዝም “ሰው እንዴት እንደ ጅብ ሲሔድ ያድራል!”—ዝም “ወይ ሌላ ቤት ታለህ ንገረኝ?” —ዝም


ራቴን ምኔን አልልም ፡፡ ጥቅልል ብየ እተኛለሁ ፡፡ በጊዜ ስገባ እኔም አፍራለሁ ፡፡ እንዳው እኮ እማይቀርብልኝ ነገር የለም ፡፡ ታዲያ ሰኞ ዕለት በጊዜ ገባሁና መጀመሪያ ቂጣየን በቅቤ ግምጥ ፥ ቀጥሎ ለእግሬ ውሃ ፡፡ እሱን ያዝኩና በረንዳየ ላይ ቁጭ ፡፡ ከሩቁ ሚጢየን አየኋት ፡፡ እሷም አየችኝ ፡፡


“ሚጢየ እንደምን ዋልሽ ?"

“አ — ና — ና — አ — ና — ና !"

“እየተጫወትሽ ነው?"

ዝም አለችኝ ፡፡ ጐንበስ አለችና አንድ ነገር ትኩር ብላ ማየት ጀመረች ፡፡ እኔም እግሬን ማሸት ጀመርኩ፡፡ ኣቤት ሞቅ ባለ ውሃ ፧ ልትጠልቅ የምትሰናዳ ጀምበር ብርሃንን እያዩ ሲታጠቡ ደስ ሲል!


ሚጢየ ብድግ ቁጢጥ ትላለች ፡፡ እጅዋን ሰንዘር ታረግና ደሞ መለስ ታረጋለች ፡፡ ደሞ ሮጥ ትልና ቆም ፡፡ አንድ ነገር እንደሚጨብጥ እጅዋን ሰንዘር ታረግና ደሞ መለስ፡፡ ያ እምትይዘው ነገር ያመልጣታል ፡፡ ተከትላ ሩጫ አንድ ሣር ላይ ሲያርፍ ትሮጥና እጅዋን ትዘረጋለች ፡፡ ይነሣና ይበርባታል ፡፡ ድክም አላት ፡፡ ስታሳዝን ! ምን እያረገች ነው አልኩና መታጠቤን ትቸ እመለከታት ገባሁ፡፡ እንደ ሄሊኮፕተር እየተንደቀደቀ እሚሔድ በራሪ ነገር ነው እምትከተል፡፡ ሁለቱም ድብብቆሽ እሚጫወቱ ይመስላሉ፡፡ አየሁህ— አላየሁህ የድብብቆሽ ጨዋታ፡፡ ያዝኩህ ስትለው ያመልጣታል ፡፡ ትከተልና ያዝኩት ስትል ይበርባታል ፡፡ ዙሪያውን አዞ ራት ፡፡ እንደ መብሸቅ አለችና ሩጫዋን ፈጠን አረገችው። ያ በራሪ ነገር “አትይዥኝ፥ አትደርሺብኝ ፥ ሚጢ ሚጢጢ — አንቺ ሰነፍ” እሚል ይመስል በኩራት በራሷ ላይ አንዣበበባት ፡ እንደ መደንገጥ ብላ እጆቿን እራሷ ላይ ደፍታ አቀርቅራ ዝም አለች ፡፡ ወይ እንዳው እስኪ በገዛ እጅዋ ፡፡ አንዣበበ አንዣበበና በፊት ለፊቷ ሒዶ ቁጭ አለ ፡፡


እሷም ባቅሟ መሸወዷ እኮ ነው ፤ አፏን በቀኝ እጅዋ መዳፍ ሽፍን አደረገችው ፡፡ ድምፅ ሰምቶ እንዳይሔድባት ቀስ እያለች መራመድ ጀመረች ፡፡ ቶሎ አለችና ድፍት አለች ፡፡ ተነሥቶ በላይዋ ላይ አንዣበበባት ፡፡ በሸቀች አንጋጣ ተመለከተችው ፡፡ ጢዝ – ዝ – ዝ ቀለደባት ፡፡ ብሽቅ አለችና ለቅሶዋን ልታቆም ነው !


“ሚጢየ አይዞሽ!" ቀጠለች ለቅሶዋን ፡፡


“ተይው በቃ እኔ እይዝልሻለሁ ፡፡” አሁንም አንጋጣ ለቅሶዋን ፡፡ ያ በራሪ ነገር ዝም ብሎ ጢዝዝ – እሷ እየተመለከተችው ለቅሶ ፡፡


“የት ነው እኔ እይዝልሻለሁ፤ ይኸ ቆሻሻ የት አባቱ አይዞሽ ! " በጣቷ ወደ በራሪው ነገር እያመለከተችኝ

“አ — አ — አ” አለች ፡፡ ንዴቷን እንድወጣላት ፡፡


“አይዞሽ!” አልኩአት ፡ ተነሣች፤ ብይዝላት ደስ ባለኝ ፡፡ እግሬን እያደረቅሁ ሆኖ እንጂ ፡፡ አንዣበበ አንዣበበና ጠፋት ፡፡ እሰይ አልኩ፤ እሷም ዝም አለች ፡፡


አይ የልጅ ነገር ደሞ የእኔን ዶሮ ማባረር ጀመረች ፡፡ ዶሮዋስ እንደ በራሪው አልቀለደችባትም ፡፡ ታባርራትና ስትደርስባት በእግሯ ገፋ ታደርጋታለች ፡፡ ዶሮዋ ትንሽ ጩኸት አሰምታ ትሸሻለች ፡ ደሞ ታባርራታለች ፡፡ ትደርስባትና በእግሯ ትገፋታለች :: ዶሮዋ “ኧረ እባክሽ" እያለች ትሸሻለች ፡፡ ሚጢየ ድክም አላትና ቆመች ፡፡ ዶሮዋ ትክዝ ብላ ቆመችና የብስጭት ነው መሰል ኩሷን ከሰከሰችና ጠፋች :: ሚጢየ ሮጠች በርከክ አለች ዶሮዋ ጥላው የሔደቸውን ቁልቁል እያየች


“አንቺ ሚጠየ አትነሽም ፡፡”

“አ – ና — ና !"

“ተነሽ ቆሻሻ ነው ከሱ ላይ ።"

“አ — ና — ና — ና — ና!" ጣቷን አሾለችና ወደ ኩሱ ዘረጋችው ፡፡ ዘንቈል አ ረገችና ወደ አፏ ዘረጋችው :: “ኤጭ” አልኩና ሩጫዬን ቀጠልሁ ወደ እሷ — ለጥቂት። 

iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

2 comments:

  1. እኔ ሙሉጌታ ጉደታ እንደሆነ ነው ምጠረጥረው።

    ReplyDelete
    Replies
    1. በመጀመሪያ ምስጋናዬንም ደስታዬንም ልግለፅልህ። የፃፍከው አጭር ቢሆንም ከፃፍከው በላይ አጭሩን አርዝሜ ማሰብ እችላለሁ። የሚያስደስተኝ አስተያየት ነው ይሄ። ወደ ብሎጌ ስመጣ ሁሌም እንዲህ አይነት አስተያየቶች እጠብቅ ነበር። ዛሬ ሆኖልኛልና እግዜር ይስጥልኝ።

      ወደ ጥርጣሬህ ስመጣ በኮመንት ላይመች እንደሚችል ብረዳም ትንሽ መነሻ ሃሳቦችህን ብታካፍለኝ ደስ ይለኝ ነበር። ሙሉጌታን ስታነሳው ለኔ አንተ ሁለተኛ ሰው ነህ። ከዚ በፊት አንድ ወዳጄ እንዲሁ ሙሉጌታን ጠርጥሮ አንድ ምክንያቱን ነግሮኝ ነበር። ከሙሉጌታ የግል ባህሪ ተነስቶ ነው። እንደሰራው ስራ ብዛት ብዙ ያልተወራለት ሰው የመሆኑ ምክንያት ለዝና ብዙም አለመሆኑ ነው። ይሄ ደግሞ ቋሚ ባህሪ ስለሆነ ቱሉፎርሳን ሳይታወቅ ፅፎት ነው፤ ነው መላምቱ።

      ሰዎች መላምታቸውን ካየሁ በኋላ የግምታቸውን ሰው እንዳዲስ አጠናዋለሁ። ጊዜው የቆየ ቢሆንም እኔ ደግሞ የቱሉፎርሳ ደራሲ ሙሉጌታ ጉደታ ሊሆን አይችልም የምልበት ሶስት ምክንያት ያልኩትን የማስታውሰውን ልንገርህ።

      1. ቱሉ ፎርሳ ሲፃፍ ሙሉጌታ ተማሪ ነበር። ልጅም ነበር። ነገሮችን በእድሜ ባልሰፍርም ልምድ ግን ትርጉም እንዳለው እረዳለሁ። እናም የሰራተኛ ማህበሩን ህይወት በምናብ ወይም በሰማው ወይም ባነበበው(እንደዚህ የተፃፈ ካለ) ሊያመጣው ይችላል ብዬ አልገምትም።
      2. ጥቂት የማይባሉ ስራዎቹ ውስጥ ስለሰራተኛው መደብ ያለውን ስሜት በሚገባ ተገንዝቢያለሁ። ፖለቲካ እንዳይሆንና በዘመኑ ስለነበረው ስርአት የነበረው አመለካከት ይገባኛል። ይሄ የግል አረዳዴ ነው። በደፈናው ግን በዚህ ምክንያት የቱሉፎርሳ አይነት መነፅር ይኖረዋል ብዬ አልገምትም። ይሄን ምክንያቴን ከዚህ በላይ ስለማላብራራው ዝለለው ሃሃሃሃ
      3. ሙሉጌታ ጉደታ በዲያሎግ በደንብ የማውራት ዝንባሌውም ከቱሉፎርሳ ጋር እጅግ ስምም እንዳይሆን ያረገኛል።

      ወዳጄ ግን የቆየ ምክንያቴን ነው የነገርኩህ። አንተ ደግሞ ምክንያቶችህን ኢሜይል ብታደርግልኝ እኔ እንደወረደ መልሼ እዚህ አመጣዋለሁ። ይሄ የሚያዝናና ቼዝ ጨዋታ ይመስለኛል። ሃሳቤንም በሚገባ እገርባለሁ። ካልተቸገርክ በኮመንት መስጫው ላይ ብትፅፈውም ደስታዬ ወደር የለውም።

      ብቻ እግዜር ያክብርልኝ። ያንተ አይነት ሰው አስተያየት እኔና ፖስቴ ሁሌ እንናፍቃለን። በሚገባቸው ልክ ያልታዩ ሰዎችን የሚያዩ ነፍሶች የታደሉ ናቸው። ሙሉጌታን እዚህ እኔ ገፅ ላይ እንዲሰፍር በማድረግህም ጭምር በጣም ነው የማመሰግነው። አንተንም በድጋሚ አመስግኛለሁ።

      Delete

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement