Komentar baru

Advertisement

ይሠለቻል ወይ???

Eriyot Alemu
Jan 23, 2023
Last Updated 2023-08-21T21:35:32Z
Advertisement

ተፈጥሮ አትጠገብም። ተፈጥሮ አትሰለችም። ሰው የሰራው ሁሉ ወቅቱን ጠብቆ ይሰለቻል፡፡ እምዬ ተፈጥሮ ግን ሁሌም እያደር አዲስ ነች፡፡ ብንገልጣት ብንገልጣት ብንገልጣት እኛ እናልቃለን እንጂ እሷ እዛው ነች፡፡ ለዚህ ምሳሌ ይሆነን ዘንድ፣ የዮሐንስ አድማሱን "ይሰለቻል ወይ?" የሚለውን ግጥሙን እንውሰድ፡፡ ግጥሙን ሳስበው በግሌ... ታ ህሳስ 16 ፣ 12 ሰአት ከሩብ አካባቢ፣ ማርታ ከምትባል ቀንበጥ ልጅ ጋር፣ የገብስ ማሳ ውስጥ ጋደም ብለን፣ጨዋኛውን ወግ ወጉን ስንጫወት ይሰማኛል፡፡



"እንደ ገብሱ ዛላ የኔ አለም ፀጉሯ ተጎንጉኖ" የሚለው የኤፍሬም ታምሩ ዘፈን በባትሪ በሚሰራ ራዲዮ ተከፍቶ አጠገቤ ቁጭ ያለም ይመስለኛል፡፡ ይህ በገሃዱ አለም የተከሰተ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን የሆነ ያህል የሆነ ያህል ይሰማኛል፡፡ ማርታም በእውኑ አለም የለችም፡፡ እንዲሁ ጣቴ ላይ የምትከሰት ምናብ ነች፡፡ አስቡትማ በዛ ነፋሻማ አየር ማርታ ጉልበቴ ላይ ጋደም ብላ... ከገብሱ ዛላ ኮርጄ ፀጉሯን ጉንጉን እየሰራኋት ወ ሬአችንን ስንቀድ። የፈጣሪ ያለህ!!! አሁን ይሄ ይሰለቻል? ወደ ግጥሙ እንሂድማ፡፡


ይሰለቻል ወይ?

ቀስተ ደመናው፣ 

በኅብሩ አሸብርቆ ጎበብ ጎንበስ ብሎ፣ 

ባድማስ በሰማዩ ሰፍኖበት ተንጣሎ፣ 

—————————>ይሰለቻል ወይ?

መስኩ፣

የልምላሜ ምሥጢር በልምላሜ ሰልቶ፣ 

አምሮ ተሰንግሎ በተፈጥሮ ጠርቶ፣ 

————————->ይሰለቻል ወይ?

የመፀው ምሽቱ፣

አብራጃው ሲነፍስ የኅዳር የጥቅምት የትሣሥ አየር፣ 

ጨረቃ አጸድላ ተወርዋሪ ኮከብ ሲነጉድ ሲበር፣ 

——————-———>ይሰለቻል ወይ?

በክንድ ላይ ሁና፣

ብላ ዘንጠፍ ዘና፣ 

ሶባ ቀዘባዋ የሚያፈቅሯት ልጅ፣ 

ፍቅር ሲፈነድቅ ሲሰራ ሲያበጅ፣

ይሰለቻል ወይ?

የውበት የፍቅር የሐሴት ሲሳይ፡፡

 

"አያምርም?" ይላል አንዷለም ደጀኔ አንድ የፈርኒቸር ማስታወቂያ ላይ... "ግጥሙ አያምርም?" በአንዷለም ድምፀት እንጠይቅማ። የእውነት ያምራል፡፡ ማርታ ካለች ደግሞ የትም አይሰለችም፡፡

ከማሳ ወተን ወደ በረሃው ስንሄድ ደግሞ በዕውቀቱ ስዩምን እናገኘዋለን፡፡ "የምድረ በዳ በረከት" ይሰኛል ግጥሙ፡፡ ቀጥታ እንግባበት፡፡


አንዲት ብርጭቆ ወይን፥ 

አንዲት ጤፍ እንጀራ÷ አንዲት አሪፍ ቅኔ 

እነዚህ ባሉበት÷ በምድረበዳ ላይ÷ ቁጭ ካልሽ ከጎኔ 

ሌላው ምን ይሰራል 

ምድረበዳው ሁሉ÷ ዓደይ ለብሶ ያድራል፡፡

 

"ይሄስ አያምርም?" ይሄንንም በአንዷለም ደጀኔ ድምፅ... ስለ እውነት ያምራል፡፡ በተለያየ ምክንያት ወይን የማንጠጣ ብርጭቆውን በጁስ መቀየር እንችላለን፡፡ ውሃም ቢሆን ዋናው ማርታ ትኑር እንጂ ችግር የለውም፡፡እሱባለው ይታየው የሺ "ብቻ አንቺ ኑሪ እንጂ የትም ይመቸኛል የትም..." ብሎ መዝፈኑ እኮ ለሌላ አይደለም፡፡ ጆኒ ታፈሰ ከሳምቮድ ጋር ሆኖ የዘፈነውን "ውቤ ከረሜላ" የሚለውን ዘፈንማ ይሄን ጠናከር ማረግ ፈልጎ እኮ ነው፡፡ ጆኒ በዛ ወፍራም ድምጡ ይዘፍነዋል...


"ውቤ ከረሜላ

ቤላ ከረሜላ

አንቺ ካለሽ ልዩ ነው 

የጎደለው ሙሉ ነው 

አቀበቱ ሜዳ ነው 

የራቀውም ቅርብ ነው

አንቺ ካለሽ ምሽቱ 

ይጨምራል ውበቱ 

ይደምቃሉ ከዋክብቱ 

ያልፍለታል ለሊቱ

ውቤ ከረሜላ

ቤላ ከረሜላ

 

እውነት እውነት አሁን ይሄ ይሰለቻል ወይ???????

iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

1 comment:

  1. አይሰለችም ሪታ በተለይ የማርታ ሃሃሃሃ ማርታ ተደጋግማ እረ እቺ ማርታ ከቶ ማነች እያልን ነበር ተመልሶልናል። ምንም የሚያምርበት እኮ ነው ትላለች እትየ ሰላም አምነናል ሐቅ ነው።

    ReplyDelete

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement