Komentar baru

Advertisement

የተማሪ አበሳና የአናሎጉ ጊዜያችን ትዝታ

Eriyot Alemu
Jan 21, 2023
Last Updated 2023-08-21T21:38:38Z
Advertisement

በኛ ተማሪነት ጊዜ የነበሩት ባንኮች ጥቂቶች ነበሩ። ኤቲአኤም ምናምን ጭራሽ አይታሰብም። ሁሉም ነገር አናሎግ ነበር። አንዳንዴ የተላከልን ብር በእግሩ የሚመጣ ነው የሚመስለው። አስቸኳዩ ራሱ ይዘገይ ነበር። ወላጅ ደግሞ በአብዛኛው የሚጠቀመው ንግድ ባንክን ስለነበር መጀመሪያ አካባቢ ብዙሃኑ የንግድ ባንክ ተጠቃሚ ነበር። በዚህም በሌላም ምክንያት ባንኩ ያለልክ ይጨናነቅ ነበር። ትንሽ ቆይተን ነው ሁኔታውን ስንባንን ሌሎች ባንኮችም እንዳሉ የተገለፀልን። 


ሌላው እንደሚታወቀው የክፍለሃገር ዩንቨርሲቲ ደግሞ በአብዛኛው መገኛው ከከተማ ወጣ ያለ ቦታ ላይ ነው። እኛም የነበርንበት ዩንቨርሲቲ ከከተማ ራቀ ባይባልም ባንክ ለመሄድ ግን የግድ ታክሲ ያስጠቅም ነበር። 


ንግድ ባንክ በነበርንበት ከተማ ሁለት ቅርንጫፍ ቢኖረውም ብዙሃኑ ተማሪ የሚጠቀመው ለከተማው መሃል ያለውን ነው። ሁለተኛው ቅርንጫፍ ከነመኖሩም የሚያውቁት ጥቂት ሀገር አሳሽ ተማሪዎች ናቸው።


እና በወቅቱ ብር የተላከለት ሰው፣ ንግድ ባንክ እንደደረሰ መጀመሪያ የሚያደርገው ነገር፣ ንግድ ባንኩ በር ላይ ያለውን ቦርድ መመልከት ነው። ቦርዱ ላይ ስሙ ካለ ብር ተልኮለታል። ከሌለ ደግሞ አልተላከለትም ማለት ነው። ያን ያህል አናሎግ ነው። እዛ ቦርድ ላይ የሚለጠፈው ተማሪ ብዛት ደግሞ የትየለሌ ስለነበር ስም መፈለጉ በራሱ አሰልቺ ነበር። በብዙ ደክሞ ስሙን ያገኘ ቁጥሩን ይዞ እያፏጨ ወደ ውስጥ ይገባል። ባያፏጭም ችግር የለውም። ቦርዱ ላይ ስሙ ሳይኖር ልዩ ሁኔታ አለኝ የሚል ለመጨቃጨቅ ወደ ውስጥ መግባት ይችላል። ብዙ ጊዜ ግን ሰሚ ግን አያገኝም።


እናም አንዴ አንድ ወዳጃችን ምሳ ሰዓት አካባቢ እየበረረ መጣና … “ባንክ ልሄድ ነው መሳፈሪያ ስጡኝ” አለን። ሶስት ነበርን፣ ተሽቀዳድመን የደርሶ መልስ ሁለት ሁለት ብር አወጣን። በንክ ለሚሄድ ሰው መዘግየት ጡር አለው። ዳር ተቀምጬ የነበርኩት እኔ ነኝ ዘለለኝና መሃል ከነበረው ሁለት ብሩን ተቀበለ። አሁን ድረስ የመዘለል ስሜቱ ውስጥ እግሬ ድረስ ዘልቆ ይሰማኛል። ሆኖም ምንም ክፉኛ ሐዘኑ ቢጠልቀኝም… ባንክ በሚሄድ ሰው ቅር አይሰኙምና… ሆድ ካገር ይሰፋልና… ሆድን አስፍቶ መጠበቅ ግድ ነውና… ሲመለስ ምሳ ይጋብዘናልና… ብድርም ሊገኝ ይችላልና እያልኩ እያልኩ ተፅናናሁ።


በምን መስፈርት እንደሆነ ባልገባን ሁኔታ ከወሰደው ሁለት ብሩንመ‍እ አገላብጦ አየና፣ አንዷን ብር በሁለት ጣቱ አንጠልጥሎ ለባለ ብሩ “ያዘው ይጠቅመሃል” … ብሎ መልሶ እየበጠረ፣ እያፏጨ ጥሎን ሄደ። በዓይናችንም ሸኘነው። “በቸር ተመለስ በቸር..” ብለንም አንጎራጎርን። ሲመጣ የምንበላውንም ጥብስ እያለምን ነበር።


ጢቅ ጢቅ እያለ ነው ሰዓቱ… ብንጠብቀው አይመጣም። ብንጠብቀው አይመጣም። ልክ ሰዓቱ ካፌው መዘጊያ መድረሱን ሲያመለክት… ያለ የሌለ ኃይላችንን ተጠቅመን፣ ካፌ ደረስንና የደረስንበትን ጥርግራጊ አሽተን ተመለስን። ባለባንኩን የበላው ጅብ ግን እንኳን ሊጮህ ቀርቶ እኛንም አስበልቶን ነበር።


ስምንት ተኩል አካባቢ አንድ ገፁ ጠየም ጠቆርም ያለ፣ ያረገው ቲሸርት በውሃ የተነከረ፣ ሲሄድ ወሽከፍ ወሽከፍ የሚል ሰው ፊለፊታችን ቆመ። መጀመሪያ አለየነውም ነበር። አየን አየንና ምንም ሳይናገር አልጋው ላይ ዝርግፍ አለ። ራሱ ባለባንኩ ነው። እኔና ሌላው ባለዳር ተያይተን ሳቅን። የመሃሉ ብሩን ስለተበላ ክፉኛ ደንዝዟል።


ባለባንኩ ከኮማው እስኪነቃ በንቃት መጠባበቅ ያዝን። በሆዳችን ሲወጣ ስላቅራራብን… “የታባቱ የጁን ነው ያገኘው”… “ምናለ መጨረሻውን ሳያውቅ ባያቅራራውስ” … እያልንም ነበር።


ታድያ በእንቅልፍ ልቡ እንበለው አልያም በድካም ልቡ … “እስቲ አለምገና በሚል ስም እይልኝ” ሲል ሶስታችንም ሳቅን። ስሙ አለማየሁ እኮ ነው…. አጅሬ ለካ በአለማየሁ አጥቶ በአለምገናም አስፈልጎ ነው የመጣው። እንግዲህ ስሙን ውጪ ቦርድ ላይ አጥቶ ውስጥ ገብቶም ተጨቃጭቋል ማለትም ነው።


ሆዳችን ቦጭ ቦጭ እያለለት ቅዠቱን ቀጠለው… “አክስቴ እቤት እቤት አለምገና ስለምትለኝ እኮ ነው… ምናለ ብታይልኝ” አለ ጭንቅላቱን ከትራሱ ጋር እያሸ። ምስኪን እዛ ባንክ በመስታወት ቀዳዳ የተለማመደውን ነው እዚህ በትራስ የሚደግመው። ትግሉን ያየ ትራሱን በስቶ የሚገባ ነው የሚመስለው። ታገለ ታገለና በጀርባው ለጥ ብሎ ተዘረጋ። ትንሽ ፋታ ወስዶ እጁን ዘረገና “እሺ አንድ ብር መመለሻ ስጠኝ… መመለሻም የለኝም” ሲል አሳዝኖን ሲወጣ እየተቀናጣ የመለሰውን አንድ ብር አስጨብጠነው እኛ ቡና ልንጠጣ ወጣን።




“አለም ሳይሰለጥን ጊዜው ሳይሻሻል

የሰራነው ሁሉ እንዴት ይረሳሻል…”


የሚለው የጋሽ መሃሙድ ሙዚቃ ካፌው ውስጥ እየተንቆረቆረ ነው። እኛም ጃን ጥላ ስር ሆነን ጨዋታችንን ጀመርን።


iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

Leave Your Comment

Post a Comment

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement