Komentar baru

Advertisement

አዳም ረታ፣ ራሚሱ እና ኑረዲን

Eriyot Alemu
Jan 22, 2023
Last Updated 2023-08-06T23:24:59Z
Advertisement

ከአንዲት ንባብ ወዳጅ ልጅ ጋር እያወራን “ከአዳም ረታ ስራዎች (አፍ) በጣም ያስጠላኛል” አለቺኝ። ያስጠላኛል ከባድ ስሜት ነው። ምክንያቷን ቶሎ ማወቅ ፈልጌያለሁ።



በርግጥ አፍ በግሌ አዳም ረታ ከስራዎቹ ሁሉ የቸኮለበት ነው ብዬ ባምንም የሚጠላ ስራ ግን በፍፁም እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ እንደውም ከሱ የወጣትነት የነ ጂሚ ዘመን ወዷ እኛ ወጣትነት የቀረበበት የተለየ ስራው ነው፡፡ ችኮላ ያልኳት አንድም እዚህ ውስጥ ብትገኝም ቅሉ፡፡ ከዚ በፊት በዚህ ጉዳይ ረዥም አብርቼ ፅፌ ስለነበር እዚህ እንለፈው፡፡


“ለምንድነው የሚያስጠላሽ?” ቀጠልኩ.... 


“ሃይማኖት በጣም ይሳደባል፡፡” አለቺኝ ቆፍጠን ብላ፡፡ 


“አሃ ራሚሱ ነዋ... እሱ እኮ ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን ሁሉ ነገር ነው የሚሳደበው፣ ሁሉ ነገርም ነው የሚያስጠላውም፡፡ የራሚሱ ስሪቱ እንጿዛ ስለሆነ ነው”


“እና እሱ የአዳም ውጤት አይዷለም?'' 


“በጭራሽ!.... አዳም ከብዙሃኑ ደራሲዎቻችን የሚለይበትን ተጨማሪ ነገር ልንገርሽ፡፡ አዳም እጅግ እጅግ ብዙ ስራዎቹ ላይ ፈፅሞ በገፀባህሪዎቹ ላይ አድሮ አቋሙን አያንፀባርቅም፡፡ ገፀባህሪያቱ በራሳቸው ሙሉ ሆነው የሚቆሙ ናቸው፡፡ ይሄ በጣም ለስራው ያለውን ጥንቃቄና የተለየ ችሎታውም የሚንፀባረቅበት ነገሩ ነው፡፡ ገፀባህሪያቱም ራሳቸውን ለመሆን ፍፁም ነፃ ናቸው.....


“… ለምሳሌ ራሚሱ ኢአማኒ፣ ሱሰኛ (በልዩ ሁኔታ የተለየ ቃማቴ ነው).... በሱ ልክ ስለ ጫት የሚያውቅ ገፀባህሪይ (ሰውም ጭምር) ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ በመፅሃፍት መደርደርያ ውስጥ መስሎ ያስቀመጣቸውን የተለያዩ የጫት ማውጫዎች ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ራሚሱ ሁሉ ነገር ነው የሚያስጠላው፡፡ ሰው የተባለው ፍጡር፣ የሰው ነገሮች ሁሉ፡፡ ማንበብ እንደሚወድ ይገባሽና.... መጽሃፍን ካሳተመው ይልቅ ያቃጠለው ፀደቀ ሲል ታገኚዋለሽ.... የተለየ ስነልቦና ያለው ምስኪን ሰው ነው፡፡ ስትረጂው አትናደጂበትም ታዝኚለታለሽ እንጂ.... ሌላ ጊዜ በሱ መስመር ግን የተለየ ስብዕና ያለው የአዳም ገፀባህሪይ አሳይሻለው፡፡'' አልኳትና ወሬያችንን ጨረስን።



እነሆም ጊዜ ፈቅዶ ልናወራው ነው፡፡ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ የሚለው የአዳም መፅሃፍ ውስጥ “ፍትፍትና ደጀሰላም" የሚል ስራ አለ፡፡ እዛ ውስጥ ደግሞ ኑረዲን የተባለ ገፀባህሪ አለ፡፡ የኔ ምርጥ ኑሬ........ አንጀቴ ድረስ ዘልቆ የሚሰማኝ ኑሬ..... ከጢቦ ቀጥሎ መንገድ አስታክኬ ሁሌ የማስበው ኑሬ....


ኑረዲን የሁለተኛ ደረጃ መምህር ነው፡፡ ኑረዲን ሰካራም፣ አጫሽ ሱሰኛ ነው፡፡ ኑረዲን ኢአማኒ ነው፡፡ ከራሚሱ ግን በብዙ የሚለይ ስብዕና አለው፡፡ ድክመቱን ያውቃል ጥንካሬውን ያውቃል፡፡ ራሱን ሳያታልል ራሱን በሚገባ ይፈትሻል፡፡


መፅሃፏ ውስጥ ኑረዲንን መተዋወቅ የምንጀምረው ከብዙ ዓመታት በኋላ ውይይት ታክሲ ውስጥ ከሚገናኘው፣ ሞገስ ከተባለ የልጅነት ጓደኛው ጋር “ቡና እንጠጣ" ተባብለው ምግብ ቤት ውስጥ ሲገቡ ነው፡፡


ከዛ ድርሰቱ ውስጥ ተራኪው ኑረዲን ስለሆነ... ስለ ራሱ ግለሂሱን በመስጠት ነው የሚጀምረው… (ከዚህ በታችም እስከመጨረሻው ተራኪው ኑረዲን መሆኑን እንዳትረሱብኝ)


ምግብ ቤቱ ውስጥ አስተናጋጅ ሴቶች የሉ ም፡፡ (የቀበሌ ምግብ ቤቶችና ድራፍት ቤቶ ች የሚያደርጉት ለዚያ ማዘጋጀት ነው) ከጎ ረምሳነቴ ጀምሮ ሴት ያሌለበት ቡና ቤት እ ንደማልወድ ያውቃል፡፡ እንደ እሱ ቤት ሠር ቼ፣(በወሬ እንደሰማሁት) ትዳር ይዤ (ይኼ ንንም በወሬ እንደሰማሁት)፣ በጎለመሰ ቂ ጤ ሞቅ ያለ ቤት ውስጥእንዳላርፍ ያደረገ ኝም ከዚህ ጋር የተያያዘው ብኩንነቴ እንደሆነ ያውቃል፡፡

“እንደተባባልነው ቡና አላዘዝንም:: ከዚህ ጓደኛዬ ጋር አንዷን ጎጆ ለሁለት ይዘ ን ቢራ እንዲመጣልን ጠየቅን፡፡”


ብሎ ይቀጥላል፡፡


እዚህ ጋር ከላይ ባለው “እንደተባባልነው ቡና አላዘዝንም” በምትለው አገላለፁ የተሰላቸ ጠጪ መሆኑን በስሱ መረዳት እንጀምራለን ማለት ነው፡፡


ከዛ ከቢራው ጋር ሲጨዋወቱ አንድ ከኢአማኒ ከማይጠበቅ ከሚመስል አቋሙ ጋር እንገናኛለን... እንዲህ ይላል፡፡


“ለእኔ.....አየህ ሐጢያተኛ ነኝ እኔ። ብዙ ሐጢያት ሰርቼአለሁ፡፡ ለእኔ ቤተክርስቲያን ስለ እግዚአብሔር የምትማርበት ቦታ ብቻ ሳይሆን ሰዎች በተቻላቸው አቅም፣ ከሆነላቸው _ አንዱ ለ አንዱ ለመተሳሰብ አጋጣሚ የሚያገኙበት ቦታም ይመስለኛል፡፡ በልጅነቴ ደብረዘይት ሚሽን እሄድ ነበር...ትዝ ይልሃል? ከእኔ የተሻለ _ ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች አጋጥመውኛል»

 

ኑረዲን በሞገስ አይን ሙስሊም ነው፡፡ በስሙ ምክንያት ይመስለኛል፡፡ ኑረዲን ግን ኢአማኒ ነው፡፡ በሁለቱም መንገድ ቢሆን አማኞችን የሚያይበት ዓይኑ ይህ ነው፡፡ በሁለቱ ጓደኛሞች መሃል ያለውን ውይይት ፖለቲካውን ትተን ስናየው ኑረዲን ለሃቅ የቆመ፣ የሌሎች መብት ግድ የሚሰጠው ሰው መሆኑን እንረዳለን፡፡ የሰዎችን ሃይማኖት እንኳን ሊራገም ቀርቶ ሽንጡን ገተሮ ሲከራከር የምናገኘው ሰው ነው፡፡ እንዲህም አይነት ኢአማኒ አለ፡፡ እንዲህም አይነት ኢአማኒ ስሎልናል አዳም ረታ፡፡ ራሚሱን ደግሞ እዚጋ አምጥቶ ማሰብ ነው፡፡


ቡና እንጠጣ ተብሎ የተጀመረውን ምሽት “አምስተኛ ቢራ ገባን፡፡ ሚስቱን ተረበ" ብሎ ይቀጥለዋል፡፡ የተሰላቸ ጠጪ ነው እንግዲህ እንዲህ ቢራ እየቆጠረ ነገር የሚያስበው፡ የአዳምን ጠንቃቃነት ልብ የሚል ልብ ይበል፡፡ ምንም ነገር ያለምክንያት አይመጣም፡፡


ይቀጥልና ቀጣዩን ይተርካል፡፡


«ታዲያስ….ቢራ ትጨምራለህ?» አልኩት «አንድ ለመንገድ» ሽማግሌውን ጠራቸውና ስለቢራ መጨመር ሲያነሳ፡

«ልጆቼ ሰዓት መድረሱ ስለሆነ ልንዘጋ ነው አሉን።

«እዚህ ቅርብ ቡና ቤት አለ ሳትወደው አትቀርም፡፡ እዚያ አንዳንድ ብለን እንገባለን። ያው ወንደላጤ ነህ፤ ቆንጆ ልጅ አለች አስተዋውቅሃለሁ» አለኝ::

እንዴት ነው ሸሌ የሚያስተዋውቀኝ? ሁለታችንም ከጎጆው ተከታትለን ወጣን።

 

ቀጥሎ አብሮት ስላለው ጓደኛው ሲያወራ… 


ጎበጥ ብሎ ያጨሳል...ሲናገር እንኳን ዓይኖቹን ከመሬት ብዙ አይነቀልም ነበር:: በማጤስና በመጠጣት ድርጊቶቹ የወንጀለኛነት ስሜት እየተሰማው መደበቁ ይሆናል፡፡ (ቤተሰቦቹን የሚያውቁ _ ሰዎች፣ ሲጠጣና ሲያጤስ እንዲያዩት አይፈልግም ነበር) 

 

ይህ ስሜት ራሱ ስለሚሰማውም ጭምር ነው ሰው ላይም ሊፈልገው የሚችለው፡፡


የመጠጡ መዝጊያ ንግግራቸው ይሄ ነው....


“እንቅልፌ መጥቶብኛል ታውቃለህ» አለኝ፡፡ ተደብሬአለሁ' እንደማለት፡

«ግድ የለም ጥቂት ስንጠጣበት ይጠፋል፡፡ ሲጀምር እንደዚያ ነው» አልኩት

በረቂቁ ፈገግ አለ፡፡ ፈገግታው ከከናፍሮቹ ሳይጠፋ ሲጋራ አስገባ። ቢራ ባሕር ላይ ውድቄ አመሸሁ...

 

ከላይ ኑረዲን ሃቀኛ፣ ራሱን የሚተች፣ የሰለቸው ጠጪ ነው ብያለሁ፡፡ አሁን ደሞ እንዲህ አይነቱ ሰው ነው ሱስ የመተው ተስፋው ብዙ የሆነው ብዬ ልቀጥል፡፡


ቢራ ባሕር ላይ ወድቆ ያመሸበትን ምሽት ጠዋቱን እንዲህ ይገልፀዋል....


ብዙ ጊዜ እንዲህ ሰክሬ ስነቃ.....የጉልበቴን መድከምና የኪሴን መራቆት እያማረርኩና እያዛጋሁ፣ መስኮት ከፍቼ አልጋዬ ውስጥ ተመልሼ እደበቃለሁ፡፡ ከላይ እስከ ታች ሕይወቴ፣ ኑሮዬ ያስጠላኛል፡፡ እስከ ተሰራበት የጡቡ ማዕከል ድረስ ባሕርዬ ይቀፈኛል። ወጣትነቴ በስካርና ማንነታቸውን በማላውቃቸው የሜዳ ላይ ፌርማታ ሴቶች ታልቦ ረዥም ዕድሜ ሳልኖር እንደማልፍ ይሰማኛል፡፡ ታዲያ አልጋዬ ላይ ተጋድሜ በደከሙ ዓይኖቼ ሳይ...እዚያው ያልታጠቡ ጌሾ ጌሾ የሚሸቱ ሁለት ቆሻሻ አንሶላዎቼ መሃል ሕይወቴ እንደምትከስም ያለጥርጣሬ አምናለሁ። ግን በዚህ የመሸነፍ ስሜት ሳትገዛ አንድ ምኞት ሕሊናዬ ውስጥ ተንሳፋ ትቀራለች። ብሞት፣ አልጋዬ ላይ ይሁን፣ ወይ የሆነ ባዕድ አልጋ ላይ ብቻ መስኰት ተከፍቶልኝ እንድሞት....ተከፍቶልኝ ብቻ ሳይሆን በተከፈተው መስኰት የጠራ ሰማያዊ ሰማይ እያየሁ ብሞት:: 

ይሔ አሟሟት ምቾት ይመስለኛል....

 

ጠጪ ሆኖ ይህ ስሜት ያልጎበኘው ሰው ካለ በውነት በሱ ሰው በእጅጉ እገረማለሁ ለማለት እገደዳለሁ፡፡ 


አሁን መስከረም የምትባለውን ገፀባህሪ ደግሞ መተዋወቅ እንዳለብን ይሰማኛል፡፡ መስከረምን ራሱ ኑረዲን ያስተዋውቀን…..


ለመስከረም የእንግሊዘኛ አስተማሪዋ ነበርኩ፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት። እዚህ አየር ጤና የተባለ አዲስ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ለመጀመሪያ ቀን ማስተማሪያ ክፍል ስገባ፣ አንደኛው ረድፍ ሁለተኛው መስመር ላይ ተቀምጣ ጎንዋ ከምትቀመጥ ሃና ከምትባል ጓኛዋ ጋር እየተጎሻሸመች ስትሳሳቅ አየኋት። ታዲያ አርባ አምስት ደቂቃ ሙሉ ሳስተምር አይኖቼ እሷ ላይ ሲያርፉ(ፊቷን አገጯ ላይ አስደግፋ፣ የናፈቃትን ነገር የምታሰላስል የመሰለች ልጅ) ቆዩ። ከሌሎች ሴቶች ተለይታ ነፍሴ ውስጥ ገባች። የጠጪ አለም ግን የፈሳሽ አለም ነው፡፡ ተምኔታችን ይሄ ነው፡፡ የዓለም ጠጣሮች በሙሉ ከዕለታት አንድ ቀን ጂንና ቢራ ሆነው የሚፈሱ ይመስለናል፡፡ ማስተማሬን እንደጨረስኩ.....በቀጥታ የምሄደው ከምንም የበለጠ በፍቅር ወደማስበው መጠጥ ቤት ነበር፡፡ አልፎ አልፎ ግን የመስከረም የጠራ ቀን ጠይም ፊት ትዝ ይለኛል፡፡ በስካሬ ነፍዤ ዞሮብኝ ዘወርዋራ ስራመድ ...... በሠላም አንዲት የምወዳትንና የምትወደኝን ልጅ አግብቼ ትዳር መስርቼ ሳልጠጣ መኖር ሳስብ…..መስከረም ትዝ ትለኛለች፡፡ በዓለም ላይ ልኑር አልኑር የማታውቀውን ልጅ። 

 

ከዕለታት አንድ ቀን አውቶቡስ ስትጠብቅ አገኘኋት፡፡ በስነስርአት ሰላም አልኳት፡፡ ማታ ነበር አስራ ሁለት ሰዓት _ አካባቢ። ያ ሰአት ክንፍ አብቅዬ..... በላዬ የረገፈውን የቾክ አቧራ እያቦነንኩ እንደ አባያ ዕውር ጳልቃን ወደ ቪኖ ሐይቅ የምበርበት...ስትቁነጠነጥ ነበር...ሰላምታዬን እንዳሰፋው... ወሬ እንድጀምር…… እንድንጣበስ........ሁኔታዋ ገብቶኝ ነበር። ግን ጳልቃን ነበርኩ…የተሳሳተ ደጀሰላም የሚያርፍ፡፡ ምንም ሳልላት ተለያየን።

 

በዛን ሰሞን የሜክሲኮው ቤት ስለራቀኝና ስላልተመቸኝ ቤት እፈልግ ስለነበር በመሪ በመሪ የሚያከራይ አግኝቼ ሰዎች አንድ አሮጊት ጋ ወሰዱኝ፡፡ በሁለተኛው ቀን እቃዬን አስገብቼ ሲጋራ ለማጨስ በረንዳ ላይ ብቅ ስል... አየኋት። _ መስከረምን አየኋት፡፡ ምን የሚሉት ግጥምጥም ነው? ለራሴ እስኪታወቀኝ ደነገጥኩ፡፡

 

«ሠላም ቲቸር» አለች ተረጋግታ

 

ታዲያ ዕጣ መሰለኝ፡፡ ካየኋቸው ሴቶች ሁሉ ለምን መስከረም ብቻ ህተሟን ተወች? ስለምንስ አዙሮ አዙሮ ቤቷ አመጣኝ? ይኼ ያስፈራኝ ነበር። አልኮል አቡዞኝ የምጎትታቸው መልከመልካም ባዕድ ሴቶች ላይ ስተነፍስ ይሄም እየታሰበኝ......(ራሴ ፈጥሬ ያመንኩበት የትንሽነት ምክንያት ይሆን? ንፅሕናዋ እየተጫነኝ በወንጀለኛነት ስሜት ገጠመኙን እያደመቅሁት ይሆን?) ገንዘቡ አልቆ የጋባዦቼም ገንዘብ አልቆ ብሮክ' ሆኜ....አንድ ሳምንት-- ሁልጊዜም አንድ ሳምንት...ቤቴ ዘግቼ ስውል የሚያደቡ እጆቻችን፤ በተዘረጋ መፅሐፍ ላይ፣ በቀለም ስብከቶቼ አንጓ መሃል በፍርሃት ተነካኩ። ግን በየመሃሉ ተደጋጋሚ ሰካራምነቴ ይመጣና የንኪኪያችን ትዝታ ይሰወራል…..ቀኑን ግን በፍቅር እያሰብኳት ንክኪያችን የምትደገምበትን ጊዜ እየናፈቅሁ፡፡

 

እናትዬዋ(እማማ የመጀመሪያ ቀን ታዛቢነታቸውን ዘንግተው አስተማሪዋ እንደ ነበርኩ ሲያውቁ ለሙያዬ አክብሮት፣ ለሰካራምነቴ ሐዘንና ቁጭት ያሳዩ ጀመር፡፡

 

መስከረምን እንዲህ ከተቀበልናት፡፡ በመሃል ስለ ራሱ ጠጪነት የሚያስበውን እና የወደፊት ሱስ ለመተው የሚመኘውን ህልሙን ብቻ አስተውላችሁ እለፉልኝ ብቻ ነው የምላችሁ፡፡


ጠጥቶ ወዳደረበት ቀን ስንመለስ...ያን ቀን ተኝቶ ነግቶ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ሲል ከእንቅልፈ‍ኡ የቀሰቀሰችው መስከረም ነች፡፡ ቀጥሎ ይሄን ያወራሉ…..


«እማማ አለቀሰች በአንተ ነገር»

 

«ምን? ለምን?» አልኩ ሱሪ እየለበስኩ ወደ ሳሎን እየገባሁ፡፡ (ቤቴ ሁለት ክፍል ናት። ጓዳና ሳሎን) ቀጠልኩና፡ “መስከሬን ላስቆመው አልቻልኩም፡፡ የዘር በሽታ መሰለኝ» እየተነጫነጭኩ ካሉኝ ሶስት የእንጨት ወንበሮች ደህናውን መርጬ ስቤ ተቀመጥኩ፡፡

 

«ማቆም ከተፈለገ ይቻላል» አለች አጠገቤ ቆማ እንደሚያሳዝን ፍጡር ወደ ታች እያየችኝ፡፡ ከረዥም ሴት ጋር ለምን መዋደድ ጀመርኩ አልኩ ለራሴ፡፡ በፍቅር አምኜ አላውቅም፡፡ ፍቅር ለእኔ በወሬ ጀምሮ አልጋ ላይ የሚያልቅ ነው:: ቃሉ ራሱ የሚቀፍ ነገር _ አለው። ፍቅር ቃሉ ከመፋቅ ከመፋፋቅ ጋር ይቀራረባል:: ለምን ልፋቅ? ይህቺ መስከረም የተባለች ልጅ እኔ ቆሻሻውን ከእንቅልፌ የምትቀሰቅሰኝ ለምንድነው? ለምንድነው እናትና ልጅ ልብሴን እየተቀባበሉ የሚያጥቡት? ከእኔ ምን ይፈልጋሉ? እኔስ ራሴ ከእሷ መሸሽና መራቅ የከበደኝ ለምንድነው?

 

መሃል ላይ ሌላ ቡዙ ወሬ ካወሩ በኋላ ወሬያቸው ይሄ ይሆናል…


«ልንገርህ ኑረዲን..ማምሸትህን መጠጣትህን ብታቆም እዚህ አብሬህ እንደማመሽ። ራትህን እሰራልሀለሁ:: ቡና አፈላልሀለሁ» ወጥ የነካ አመልካች ጣቷን ታችኛው ከንፈሬ ላይ አስቀምጣ፣ በትንሹ ጫን አለችውና ለቀቀችው፡፡ ጥርሶቼና ከንፈሬ ሲጋጩ በትንሹ ቦጭ የሚል ድምፅ ወጣ፡፡

 የምመልሰው ጠፋኝ። ወደ ፍርፍሩ እጄን ሰደድኩ።

«ከዛሬ ጀምሮ አልጠጣም» አልኩ በብስጭት / «ውነት?» አለች የድምፅዋን ከፍታ አውርዳ

“አስባለሁ፡፡ ሁልጊዜ አስባለሁ”

“በከፊል ዕፍረት ትሪውንና ድግሷን እያየሁ ልታፅናናኝ ፀጉሬን በቀስታ ዳበሰችኝ። ፍርፍር ያለማቋሻ ዘግኜ ጐረስኩ። እያላመጥኩ ደረቷን ተደገፍኩ፡፡ ልቧ ሲመታ ይሰማኛል፡፡ ሳላምጥ ድምመታው ይጠፋል፡፡ ማላመጥ ሳቆም ይሰማል።

 

ከዛም ብዙ ብዙ ያወሩና እንደተደገፋት እንቅልፍ ይወሰወደዋል፡፡ ይህ የሆነው በዕለተ እሁድ ነው፡፡ መጠጥ መተው መሞከር እንዳለበት ወሰነ። በአንዴ ግን አደገኛ አይኮንም፡፡ ይቀጥላል፡፡


ሰኞ ጠዋት ወዷ ስራዬ መሄድ _ አልቻልኩም... በሌላ _ የእሁድ ስካር አንጀቴና ልቤ ተገርፎ:: መስከረም ስልክ ደውላ ለአለቃዬ እንደታመምኩ እንድትነግረው ጠየቅኋት። እየተበሳጨች ፈፀመች፡፡ እየተበሳጨች ዓይንህን አላይም ብላ ሄዷች። ከሰዓት በሁዋላ ተመልሳ ስትመጣ ኰቴዋ ቀሰቀሰኝ:: በኩርፊያ ቡና አፈላች። ጠጥተን ስንጨርስ የጠጣችው ቡና አገዛት መሰለኝ ኩርፊያዋን ረሳች። እሷ ሳሎን ሆና እኔ ደሞ መኝታ ቤት ተጋድሜ ለጥቂት ሰዓታት እዛና እዚህ ተቀምጠን አነበብን። ኩርፊያዋ የንባቤን ፍሰት እየሰበረ አልፎ : አልፎ : ለልቦናዬ ይሰማኛል፡፡ እሱን ለማጥፋት በእግር እንንሽራሽር ብዬአት አስራ ሁለት ሰአት አልፎ ከግቢያችን ተያይዘን ወጣን:: "

 

ብዙ መንገድ ዞረው ቤታቸው ይገባሉ፡፡ የመንገዱ ዓላማ፣ በመንገዱ የተከናወነውን ዘልዬው ነው፡፡ ግን ለሱ ቀጣይ ህይወት በእጅጉ የሚጠቅመው ነገር ነው፡፡ ቤት ከገቡ በኋላ እንቀጥል.....


ማታ ላይ ንዑስ-ሚስቴ መስከረም ልታስቀኝ እየተንጠራራች (ኰሚክ አይደለችም ግን) የማዕድ ላይ ዳንሷን ሳይ አመሸሁ:: ከስንት አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፌ ቢራ ሳልፋ ያደርኩበት ቀን ነበር፡፡

 

ይህ የሆነው ሰኞ ነው፡፡ ማክሰኞ ስራው ይገባል፡፡ ስራው ቦታ እና ምሽቱን ይተርካል፡፡ ትኩረታችንን ምሽቱ ላይ እናድርግ.....


ከምሣ በኋላ ለስራ የነበረኝ አትኩሮት ተመለሰና እስከ ምሽቱ አሥራ ኩለት ሰዓት ተኩል ድረስ ታርሼ ከቢሮ ወጣሁ:: ቀዝቀዝ ያለው ያዲስ አባ ምሽት የተቀበለኝ ልቤ ስር ግራ የሚያጋባ ፍርሃት በመትከል ነበር። የት መሔድ እንዳለብኝ ሳይገባኝ እየዞረብኝ መሐል ከተማ ስባዝን፤ ሆዴና አንጎሌ በመጠጣት ፍላጎት ነደው፣ ቤቴ ልግባ አልግባ ከራሴ ስሟገትና ስንከራተት፣ አንድ ሰዓት ተኩል ሆነ። ዝም ብዬ እግሮቼን ወዳጋጠመኝ ስወረውር ከመሃል እንደራበኝ _ አወቅሁ፡፡ ወደ ቤት ቶሎ ገብቼ ከመስከረም ጋር መቀመጥና ማውራት አእምሮዬ ውስጥ አማራጭ ሆኖ ቢመጣም፣ (ሌላ ሌላውን ተለማመጠኝ ትላለች ስታድዮም ዙሪያ አንድ ምግብ ቤት ገብቼ ቢራ አዝዤ ተቀመጥኩ። ሱስ ቢረባም ባይረባም አንዳንዴ ከፍቅር ይበልጣል። እጠጣለሁ፡፡ እጠጣለሁ:: ብዙ ቢራ እንደጠጣሁ ትዝ ያለኝ አርፍዶ ነው:: ረሐቤ ነው የጠቆመኝ፣ አጠገቤ ሰዎች ጥብስ አዘው ይበላሉ፡፡ ሶስት ናቸው። ሁለት ምግብ አዘው እንጨምር 'ይበቃል' ይከራከራሉ፡፡ መጀመሪያ የመጣውን ሆታዘዘውን መጨረሱ ላይ ተስማምተው ለመብላት ዝም አሉ:: እጆች ወደትሪው መሃል _ ከነክሳዳቸው ይሮጣሉ:: ትሪ ዳርዳር ቅልጥም እንደ ኮረት ይቧርራል:: አንገታቸው ያጠረ (ድሮ ባላውቃቸውም፣ ቅርፅቸው ጎበጥ ያለ ይመስላል፡፡ የሞዴል እራት መሆን አለበት። የሙሉ ደመወዝ ሲሆን ጨዋታ ይበዛል።

 

ፍርፍር...... ከራሱ ሊሸሽ የጣረ እንጀራ ብዙ ሳይሄድ ዞሮ ራሱን ሲሆን ነው:: የሁለት ብር ከሃምሣ ፍርፍር፡፡ እንጀራን በእንጀራ፡፡ ራሱን በራሱ። የፍርፍር የመለወጥ ቃልኪዳኑ፡፡ አልሸሹም ዞር አሉ፡፡ ፍርፍሩን ቀድሞት _ የገባው የቢራ ባሕር ውስጥ ሳሰምጠው ጊዜ አልወሰደብኝም። በስካርና በድብርት ጨግገው የነበሩት ዓይኖቼ ለአፍታ ተከፈቱ፡፡ እዚህ ደረጃ ስደርስ ነው ......ለመስከረም የገባሁት ቃል በእሳት ተከቦ እየተንቦገቦገ ትዝ ያለኝ፡፡

 

ለምን ዘግይቶ ትዝ አለኝ? ለምን ያኔውኑ ተረሳኝ? ቃሌን ካጠፍኩ በኋላ ለምን ቃሏ በእሳት ተከቦ መጣ?

 

እዚህ ስታዲዮም ቂጥ ስር፣ አናቴ ላይ ቢራ እያፈሰስኩ፣ ሁለተኛ ደረጃ ፍርፍር እየበላሁ፣ ምን ማድረግ እንደሚገባኝ ዞሮብኛል። ጥብሳቸውን ከበው በፀጥታ ትኩረት ራታቸውን(ወይስ መክሰሳቸውን) ሲበሉ የነበሩት ሰዎች ለአፍታ ትዝ ብለውኝ ዞር ብዬ አየኋቸው:: ሕልማቸውን እንዳገኙት..... ግባቸው እንደደረሱ……ሳፋ ከንፈር ዙሪያ እንደ አይጥ አድፍጠው፣ ሲሳደዱ ሲባረሩ እንደዋሉ ዓይኖች-- ያው እዚያ ማዶ ፈጣጣ ውሮ፣ በሰላ ጥፍሩ ሊሞነጭርህ :: እዛው ተረሳስተው (የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል) ዓለማቸውን ወደ ገበታ ቀይረው(ሕብረተሰብ ከመፈላሰፉ በፊት፣ የሚበላው የሚጠጣው የሚጠለልበትን ሲለፋ ማዘጋጀት አለበት ካርል ማርክስ) ሌላው ላይ ግራጫ መጋረጃ ወርውረው፣ ከማንም እርቀው...የእንስሳ ነፍሳቸውን ለአጭር ጊዜ ለማዳን በማያገባቸው የማይገቡ ጨዋ ሰዎች እንደሆኑ ገባኝ።

 

ባልጠበኩት ፍጥነት መሽቷል፡፡ የምከለብሰው ቢራ የተሸከምኩትን ድብርት አላጠበውም። ሆዴም ጭንቅላቴም ከብዶኛል፡፡ መስከረም እየተመላለሰች እቤት ገብቼ እንደሆነ እንደምትፈትሽ አስባለሁ፡፡ የአንጀቷን መበጠስ አስባለሁ፣ በሬን እያንኳኳች መልስ ስታጣ፣ ያን የሚያምር አጭር ዞማ የፈሰሰበት አናቷን በሐዘን ደጋግማ ትነቀንቃለች፡'ውነት አበዛው ትላለች። 'ሱስ በአንድ ቀን አይነቀል' ብላም ታስብ ይሆናል። ከእንግዲህ አታምነኝም። የመጀመሪያ ወንድ ጓጿኛዋ የነበረው ልጅ ለሁለት ዓመታት ያህል ለትምህርት ውጭ አገር ተልኮ በዚያው ከቀረና ደብዳቤ መፃፍ ካቆመ ወዲህ፣ ብዙ ጊዜ ወንድን ማመን እንደሚከብዳት ነግራኛለች፡፡ ክፉ መሆኗም አይደለም፡፡ እዚህ በስሎ የከረመ ግምቷ ውስጥ አደላድላ እንደምታስቀምጠኝ ጠርጥሬአለሁ። እኔ ደደቡ (ማመን አለብኝ መሆኔን) መስከረምን የመሰለች ልጅ ቤቷ ተቀምጣ እየጠበቀችኝ (የደስ ደስ ያላት ጐራዳ)......

 

ድርጊቴ አይደለም፤ አፌ ነው ጨዋ ያልሆነው::

 

ድርጊት የለኝም፡፡ አብዮት እየተስገመገመ፣ እያጓራ፣ እየጮኸ፣ እያለቀሰ አልፎኛል፡፡ በአፌ ግን ለውጥ እፈልጋለሁ። በዚያ ያለፉት...... ከዛ ጩኸት የተሻሙ፣ ጥንካሬያቸው የነበረውን እምነታቸውን ተገፈው በጥርጣሬ ገመድ ራሳቸውን እየሰቀለ ነው:: በማያገባን የምንገባበት ዘመን አለፈ ከተባለ በኋላ ደሞ...በምላሴ እየጎተትኩ እንደ ዕርጎ ዝንብ ወደ ማያገባኝ ልገባ......

 

ከአንድ ቡና ቤት ወጥቼ መንገድ መሃል _ ስወድቅ... ሰዓት ብዙ አልፎአል፡፡ ብዥ ብሎብኛል፡፡ ባዶ የሆነ አውቶቡስ ቀርቶ ታክሲ እንደማላገኝ ይገባኛል። ዕድሌ ሆኖ አንድ ታክሲ አገኘሁና ትንሽ ገንዘብ ጨምሬ ከጦር ሐይሎች ሳሪስ ድረስ ወሰደኝ። የቀረውን በእግሬ መሄድ ግዴታዬ ነበር፡፡ እያለፉኝ የሚሄዱ የቤትና የጭነት መኪኖች እንኳን ቁጥራቸው አንሷል፡፡ እንደ ዛገ ጥርስ ከተደረደሩት የጄኔራል ስመት ጐዳና የመንገድ አምፑሎች አንዳንዶቹ ብርሃን የላቸውም:: ቀሚሳቸው ጨለማ ነው፡፡

 

——ከመሃል _ አንድ ቦታ ጐራ አልኩና፣ ለመንገድ የሚሆን ሁለት ቢራ ጨለጥኩ። አንዳንዴ የምጠጣው ፈሳሽ ጕሮሮዬን ሲያፍነኝ ደስ ይለኛል። ብዙም ላይቆይ ስካር ማድባቱን አቁሞ ሁለመናዬን ተቆጣጠረኝ። በበዘዘው አእምሮዬ ለመስከረም የገባሁትን ቃል መስበሬ አንጀቴን ይበላዋል፡፡ ግን የስካሩ እንሳፎት ይማርከኛል፡፡ እየበረርኩ የማመልጥ፣ ሁሉ ነገር የሚታየኝም ይመስለኛል--- የራሴም ስህተት። መንገዳገድ ጀምሬአለሁ፡

 

የቀበሌ መሸታ ቤት ነው:: መጠጥ ቤቱ ይኼ ቤቱ... ይኼ የቀበሌው እንደ ቤተክርስቲያን ዳገት ላይ ነው የተሰቀለው...በመሰላል _ እየወጡ የሰሩት ይመስላል፡፡ የጌሾ ደብረዳሞ…..በትንሽ የሳንቲም ገመድ ተሳፍረን ድራፍት የምንፀልይበት፡፡ መስከሪያ ዕምብርቱ የሚደረሰው(ሳሎኑ ፈረስ ያስጋልባል) ቀጥ ብሎ በሚወጣ ገነት የሚዶል በመሰለ ረዥም ደረጃ ነው፡፡ በሰፊው የብረትና የመስታወት በሩ በኩል የሚወጣው መብራት ሕንፃውን አንድ ዓይናማ ጭራቅ ያስመስለዋል። ለምን እግሬ እያዞረ እንዲህ ዓይነት ቦታ እንደሚያመጣኝ እየገረመኝ ነው::

 

እዚህ ያለው ጠጪ ብዙ አያወራም፡፡ የሚያወሩት ደግሞ አፍ ለአፍ የገጠሙ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ የቀበሌ ሹሞች ይመስላሉ፡፡ ከነዚህ ተቀምጠው ከሚያወሩት አንዳንዶቹ ተላላኪ ሲዘገይ ተነስተው ወደ እንግዳ ይቀርቡና ምን ይምጣ?' ይላሉ። አንድ ድራፍት በቁሜ ጨልጬ እየተንገዳገድኩ ከዚያ ቦታ ወጣሁ:: ደረጃውን ጨርሼ እንደ ወረድኩ (እንዴት እንደወጣሁት ትዝ አይለኝም የሁለት ሰዎች ጥላሞት ፊት ለፊቴ ሲወድቅ ታየኝ። ምክንያቱ ምን እንደ ሆነ ሳላውቅ ጆሮዬ ቀጥ አለ፡፡ የጥላ ሞቶቹ ድንገተኛነት ይሆን? ሰዎቹን ከጥላዎቹ ቀድሜ ስላላየኋቸው ሰዎቹ ራሳቸው ድንገተኛ ሆነውብኝ ይሆን? ልቦናዬ በጥላሞትና በቢራ ጕም ተሞልቶ፣ ታዲያ ተመሳሳዩን ከውጭ፣ እግሬ ስር በማግኘቴ ተደናብሬ ይሆን?

 

ከዚ በኋላ ሰዎች ተከታትለው በመኪና ጭነው አርቀው ወስዷው ይጿበድቡታል፡፡


ከላይ ካለው ተረክ ውስጥ ጥቂት ገለፃውን እንይ.... አንድ ሙሉ ቀን መጠጥ የዘለለው ሰው ከመጠጡ ጋር መልሶ ሲገናኝ የሚሰማው ስሜት ፍፁም ልዩ ነው፡፡ ቅፅፈታዊ ቢሆንም ስሜቱ ኑረዲን ስሜቱን እንዲህ ይገልፀዋል፡፡


ሱስ ቢረባም ባይረባም አንዳንዴ ከፍቅር ይበልጣል፡፡ እጠጣለሁ፡፡ እጠጣለሁ፡፡


ግን ይህ ስሜት ወዲያው አላፊ ነው፡፡ እንዳየነው ኑረዲን ወዲያው ፀፀት ውስጥ ሲዘፈቅ እናየዋለን፡፡ ብዙም መጠጥ፣ ብዙም ቦታም እየዞረ ይጠጣል፡፡ ስለ ሱስ ባንዴ እንዷማይተውም ያስባል፡፡ እያንዳንዷ መስመር በዚ ፅሁፍ ውስጥ ትርጉም አላት፡፡


ከዛ በኋላ ያለውን አሳጥሬ ልንገራችሁ፡፡ ከጓደኛው ሞገስ ጋር የነበረው የፖለቲካ ወሬ በኋላ መደብደቡ... ይሄ ጉዳይ ሄዶ ሄዶ የስራ ቦታው ላይ ይደርሳል፡፡ አለቃው የመደብደቡን ሚስጢር ያውቃል፡፡ ደብዳቢውንም ያውቃል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ኑረዲን ወደፊት ሊሰራው ስለሚፈልገው አዲሱ ኑረዲን እጅግ ያስፈልጉት ነበር፡፡ ብዙዎቹን ጉዳዮች የዘለልኳቸው ፖስቱ ከዚ በላይ እንዳይረዝምና አንድ ወጥ ጉዳይ ላይ ማተኮር ስለፈለኩ ነው።


ከላይ እንዳየነው ኑሬ ሰኞ ሳይጠጣ አድሮ ማክሰኞ በብዙ ጠጥቷል፡፡ ስለዚህ ሱስ ለመተው ትንሽ ከጫና የነፃ ትንሽ የመጀመሪያ ቀናት እንደሚያስፈልግ እሙን ነው፡፡ እና በድርሰቱ ውስጥ በተገለፁት በስራው ቦታ እና ሌላ ቦታ ባሉ መጠላለፎች ምክንያት ራሱ አለቃው ነው ደውሎ ለሳምንት ረፍት እንዲወስድ የሚነግረው፡፡ ከዛ በኋላ መስከረም የምትባል እናት የሆነች ሴት እያለችው አይደለም... ለብቻም ፍላጎቱ ለነበረው ሰው ሱስ መተው እጅግ ቀላል ነው፡፡


መደምደሚያውን ግን ራሱ ኑረዲን ይተርከው........


ይኸው ከመስከረም ጋር ተያይዤ ከቤት መውጣት ካቆምኩ ስድስት ወራት። ከጠጣሁ ስድስት ወራት፡፡ ታላላቅ ስም ተሰጥቷቸው አውርድልኝ ከተሰቀሉ ሃሳቦች.........መስከረም በለጠችብኝ። ጓደኛዬ' ከዚህ የተለየ ሰራ? ውስጤ ያለውን የሕልዮ ግጭት በመስከረም ፍቅር ሰፍቼ፣ የምላስ ቀንን ውጬ፣ ከመስከረም ጋር ስለሠርግ እያሰብን…እናቷና ዘመድ ቃሪያ እየመዘነና እየወቀጠ፣ ድልህ እየሠራና እያጠራቀምን። ይኼ ሲያልቅ ስለ ዕለቱ የአየር ፀባይ….ትንተናን የሚፈሩ፣ ከኮስታራ ዕውነት የሚያስኰበልሉ ጮሌዎች የፈጠሩልንን እያወራን። ምላሴም ተቀርፃ ሾለች-መስከረምን ሚሊ ሜትር በሚሊሜትር የላሰችበት፡፡ የፍርሃት ቦርጩን ሰንቄ፣ ጠዋት ማታ የፍትፍት ዣንጥላ ከአናቴ በላይ ላይ ከስሬ መስከረምሽ ሳታቋርጥ ተሰቅላ...ከተከፈተው አፌ ስኳር የመሰለ ደረቅ ቬሎ በጥርሶቿ እየመዘዘች......

 

ለሁሉም ጊዜ አለው፡ ለመደብደብና ለመደባደብ፣ ለመረገጥና ለመርገጥ፡፡ ለሕልም እንደመታን ለቅዠትም እንማታለን፡፡ ለመውደቅም ጊዜ አለው፡፡ አለቃዬ ባየኝ ቁጥር ጠዋት ማታ ይስቃል፡፡ በተለይ ግንባሬ ላይ ያለውን አልጠፋ ያለ ጥቁር ጠባሳ ሲያይ፡ ምን ሆንክ? ሂሂሂ

የማውቅ ባይመስለውም፣ ማን እንዲያ እንዳደረገኝ እንዷሚያውቅ ግን አውቃለሁ፡፡ 

 

ኑረዲን “ለሁሉም ጊዜ አለው..." ብሎ የሚተርክበትን ዘዬ የጀመረው ራሚሱ የዞረበት የብሉይ ሰው' ብሎ የሚያንጓጥጠው ጠቢብ ነው፡፡ ልዩነቱን እየመዘገባችሁ፡፡


ጤናማ ኢአማኒም እንደ ኑረዲን ያለው ነው ብዬ ኑሬን ላሰናብተው፡፡


ብዙ ጊዜ አዳምን ስጀምረው “አዳም ረታ የምታደንቀው ሰው ብቻ ሳይሆን የምትፈልጠውም ሰው ጭምር ነው" ብዬ ነበር።

ዛሬ ስጨርሰው ባረገውስ? ምን ይለኛል?


iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

Leave Your Comment

Post a Comment

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement