Komentar baru

Advertisement

ፍቅሬ ሁሉ ነገርሽ ደስ አይለኝም…

Eriyot Alemu
Nov 4, 2022
Last Updated 2023-08-21T21:38:27Z
Advertisement
<<በነ ሚስተር X ሃገር… ማንም እየተነሳ ገጣሚ ነኝ ሲል ያሳፍራል!>> ይህ የአንድ ወዳጄ የተለመደ ንግግሩ ነው። በርግጥ ሚስተር X ከኔም ከምርጫዎቼ እንደ አንዱ ነው… ልዩነታችን ግን ሚስተር ኤክስን ለማድነቅ እነ ሚስተር ዋይን አጀንዳዬ አለማድረጌ ነው። ሆኖም ሁላችንም "የኔ ምርጫ…" የምንለው አወዳድረን በመሆኑ፣ የሱ አገላለፅ አይከይፈኝም እንጂ… እውነቱን አላዳምጠውም ማለት አይደለም። መስማት እንደምፈልገው ሳንሱር አርጌ አዳምጠዋለሁ። ሆኖም በአንድ በተለየ መደበሪያ ያጣሁበት ቀን፣ በአንድ ሰው ላይ የሚያተኩር የዳሰሳ ጥናት ለምን አልሰራም አልኩና ልፈታተነው ተነሳሁ። የመልህክት ሳጥኔን ከፈትኩኝ፣ ቀጣዩን መልህክት ሰደድኩለት።

"ስማማ በነ ሚስተር X ሃገር… ማንም እየተነሳ ቅጥ አንባሩ የጠፋ ነገር… ግጥም ብሎ ሲግተን ተመልከትማ… ወይኔ ሚስተር ኤክስ ምን ይል ይሆን ይሄን ቢያይ?! … ስድ ግጥሙ ይኸውልህማ!… 

**** ውልታ **** 
አንድ ቀን አየኋት፣ ሳያት ሸነተፈኝ፤ 
አልባሌ ሆና ስትሄድ በጎዳና፣ አሽከር ተከትሏት፣ 
አየኋት ተኩሬ። 
ገና ሎባ ሶባ፣ 
አየኋት፣ አየኋት፣ አየኋት፣ ዝም አልሁኝ አይቼ።
ቆንጆ ናት?
ምን ትመስላለች? ቆንጆ ናት?
ቆንጆ ናት ወይ?
ቃሉ ደካማ ነው፣ ንፉግ ነው ስሱ ነው፣
እጅግ ተወጥሮ ስንኩል ነው ጎደሎ፣
ቆንጆ ናት?
ቆንጆ ናት ተብሎ ፍፁም አይጠየቅም። 
ያን ለታ ሳያት ነጠላ ጣል አርጋ ሻሽ መሳይ ሸብ አርጋ፣
ይታየኝ ነበረ ልውጣ ልታይ ብሎ ከሻሽ ከነጠላ ሲታገል ውበቷ።
አስደንጋጭ ፈገግታ በፊቷ ላይ ሰፍኖ ይታይ ነበር፣
ባንድ በኩል ደግሞ ረቂቅ ፈገግታ፣
የምጸት ፈገግታ የመናኝ ፈገግታ፣
ይኼን ዓለም፣ ይኼን ኑሮ፤
ሐሴት ደስታውን፣ ትካዜ ለቅሶውን፣
ማጣቱን ማግኘቱን፣ መሾም መዋረዱን፣
ሁሉንም፣ በመንፈስ ርቆ ሁሉንም በመናቅ ሁሉንም በመተው፣ 
የሚገኝ…………………………………… ፈገግታ፣
የፊቷን ፈገግታ ይታይ ነበረ በኃይል ሰንጥቆ።
ቆንጆ ናት፤ ውብ ናት፤ ድንቅ ናት፤ ግሩም ናት፤
ዕጹብ ናት አልልም፣ በፍፁም አልልም፣
ለማለት አልችልም።
እኒህ ቃላት ለሷ፣ ለሷ መልክ፣ ለሷ ቆም መቼ ተፈጠሩ፣
ለኛ!
እኛን ለመሰሉ ውር ውር ለሚሉ፣ ለሟቾች ነው እንጂ!
ማለት የምችለው፣
ከዕለታት አንድ ቀን ስትሄድ አየኋት፣
ውበቷ ረቂቅ ነው፣ ድብቅ ነው አይታይም፤
ብልጭ ብላ ጠፊ፣ አይኖራትም ዕድሜ።
ይኼ የኛ ዓለም–– ይኼ!
መች ተባረከና በውበት ሊቀደስ። " 

ቆይቶ መልህክት ደረሰኝ… <<አየህልኝ አደል ቁጭቴን? እንዲህ አይነቱን ዱንዙዝ፣ እንስራ አናቱ ላይ አሸክመህ የሚስተር ኤክስን ግጥሞች ጮክ ብሎ እንዲያነበው ማድረግ ነበር… ለመሆኑ ፀሃፊው ማን ነኝ አለ?>>  

የፈራሁት ደረሰ… በውስጤ የተመኘሁትም ሆነልኝ። 
"ይሄ የውብ ውብ ፈጠራማ የራሱ የሚስተር ኤክስ ነው… አንተ ራስህ፣ የአረጋኸኝ ወራሽን (እንስራሽን ያዢና) የሚለውን ዘፈን ከፍተህ (ዘፈኑ በክብር ነው የተነሳው)… ድምፅ እያወጣህ አንብበውማ… ያኔ ሚስተር ኤክስን የምትረዳው ይመስለኛል። እንስራ በአናትህ ከምትሸከም ብዬ ነው ሃሃሃሃሃ" የሚል መልህክት ሰደድኩለት። 

አልሞት ባይ ተጋዳይ እንደሆነ አውቃለሁ። አሁንም መልህክት ልኮልኛል… <<ጥፋቱ እኮ ያንተ ነው። መጀመሪያ መግቢያህ የተሳሳተ ነበር… ለምንድነው ግን እንደዛ ያረከው?>> 
"አሁን ግጥሙን ወደድከው ማለት ነው? … ፍሬ ነገሩ እኮ የላኩልህ ግጥም ነው። የኔ መግቢያ ጥሩም ሆነ መጥፎ ላንተ ትርጉም መስጠት የነበረበት… መጀመሪያ (ሊቀየር ለማይችለው)፣ ፍሬው ስለሆነው ነገር የራስህ ሚዛን መኖሩ ብቻ ነው። አለበለዚያ በነፈሰበት እየነፈስክ ባክነህ ትቀራለህ… ሰው በማወቅም ባለማወቅም፣ ለማልማትም ለማጥፋትም ብዙ መግቢያ ሊኖረው ይችላል… በመግቢያዎች ሁሉ ከተስማማህ ትበላለህ ለማለት አካባቢም ነው!… 

በነገርህ ላይ ሚስተር ኤክስን ለማድነቅ ሁሉንም ስራዎቹን ማወቅ ይጠበቅብህ ነበር፣ በሚል እሳቤ ገምቼህ ትዝብት ውስጥም አልከተትኩህም… ተገቢም አይመስለኝም። የሚስተር ኤክስን ሁሉንም ስራዎች መውደድ አለብህም ብዬም አላስብም። እንዲሁ በዳሰሳ ጥናት ልዳስስህ ብዬ ነው ሃሃሃሃ… በተረፈ በቃኝ አላሰልችህ" አልኩትና የስልኬን ቁጥሮች መነካካት ጀመርኩ። ልደውልለት ነው። 

★★★
የሀገራችንን ደራሲያን በተለይ ልብወለድን ሳስብ መጀመሪያ በአዕምሮዬ የሚመጡት 3 ሰዎች ሀዲስ አለማየሁ፣ በዓሉ ግርማ እና አዳም ረታ ናቸው። ማወዳደር ባልወድም መጀመሪያ የሚመጡት ግን እነኚህ ናቸው። በጨዋነት ሌሎቹንም አልፎረጎትኳቸውም እያልኳቹ ነው። ሶስቱም የየራሳቸው ቀለም እና ቅርፅ ፈጥረው አቅርበውልናል። ዘመናትንም አይተንባቸዋል። ሆኖም አላማዬ ስለነሱ መፃፍ አይደለም እንደ መግቢያ ላንሳው ብዬ ነው። የዚህ ብሎግ ዓላማ አንድ ሁሌም ሳስበው ግርም የሚለኝ ነገር አለ።እሱን ማንሳቱ ላይ ነው። 

ለምሳሌ በዓሉ ስል በአዕምሮዬ ጥንድ ገፀ ባህሪያት ይከሰታሉ። አበራ ወርቁ እና ሉሊት ታደሰ… ጸጋዬ እና ፊያሜታ ጊላይ (ሮዛ ተፎርጋታ)… ሀዲስ አለማየሁን ስል ደሞ በዛብህ እና ሰብለወንጌል… ጥላሁን ፈይሳ እና ሶፊያ… አዳም ረታ ጋር ስመጣ ብዥታ ነው የሚጠብቀኝ። አዳም 10 መፅሃፍት አሉት። የስንብት ቀለማት ለመፅሃፉ ላለኝ ክብር የተነሳ ከምንም ነገር ጋር ቀላቅዬ አላወራውም፤ ለብቻው ይቀመጥ። 6ቱ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ሲሆኑ 3ቱ ረዥም ልቦለዶች ናቸው። ግራጫ ቃጭሎች፣ መረቅ እና አፍ። እና ከነዚህ ሶስት ስራዎቹ ውስጥ ጎልተው የሚታዩኝ ጥንዶች አለመኖራቸው ግርም ይለኛል። የሉም አላልኩም ግን ደብዛዛ ናቸው። ለምሳሌ ግራጫ ቃጭሎች ላይ መዝገቡ እና ገነት ብሎ መጥራት ፌዝ ይመስለኛል። መረቅ ላይ ደሞ ዓላዛር እና ተባረኪ አሉ። ግን ሁለቱ ሲጠሩ የሆነ ፍዝ ነገር አለው። አፍ ላይ ጌርሳሞት እና ገለታ ናቸው የሚጎሉት። ይሄም ከመረቅ እጅግ በላቀ ሁናቴ ፍዝነት አለው። አዳም ግሩም ፀሃፊም ግሩም ፈጣሪም ነው። ሲበዛም ብሩህ ሰው ነው። ለቅርፅ እንደሚጨነቅም አውቃለሁ። ግራጫ ቃጭሎች እንጆሬያዊነትን፣ መረቅ ሕፅናዊነትን፣ አፍ ደሞ ቅልልቦሽ ጨዋታን መሰረት እንዳረጉ አልዘነጋሁም። ከሌሎቹ ደራሲያን በተለየ ጎልተው ያልታዩኝ ጥንድ ገፀባህሪያት ያልታዩኝ ቅርፅ ውጧቸው ሊሆን እንደሚችልም አስባለሁ። ግን የገዛ ሃሳቤ አላረካኝም። ጥያቄው ከተፈጠረ መልስ ሊኖር ግድ ነውና ሌላም መልስ ፍለጋ፣ በሃሳብ መጋለቤን አላቆምም። ወይ እኔ ፈዝዤባቸው ሊሆንም ይችላል። 

አዳም የአድናቂ ሀብታም ነውና (አንዱም እኔ ነኝ ከእጅግም አክብሮት ጋር ነው የማደንቀው) ይሄን ያነበበ "አረ እኔ እንዲህ አልተሰማኝም… " አልያም ደሞ "አንተ የተሰማህ ተሰምቶኛል… ግን ያ የሆነው በዚህ ምክንያት ይመስለኛል!" የሚለኝ ባገኝ በጣም ደስ ይለኛል። የምር ማለት ነው። "…ይመስለኛል!" ብሎ አስተያየት እንዲሰጠኝ የፈለኩት (ድምዳሜ) ይዞ የሚመጣ ከወዲሁ እንዲጠነቀቅ ነው። ደምዳሚዎች መሬት ሲደመድሙ እንጂ ሃሳብ ሲደመደም ደስ ስለማይል ማለት ነው። ነገሮችን ክፍት አርጎ መተውን የመሰለ ነገር የትም አይገኝም። የሀሳብ ተከፍቶ መኖር ለዘላለም ይኑር። በየመሃሉ መፈክር ካስፈለገ ብዬ ነው። ለጨዋታው ድምቀት ማለት ነው። 

በዚህ አጋጣሚ ከምትወዳቸው ደራሲዎች ውስጥ የማትወደው ስራ ሲጠቀስ ብዙ ስለማይገጥመኝ ነው ይሄን ብሎግ ማድረጌም። "ፍቅሬ ሁሉ ነገርሽ ደስ ይለኛል" ከሚል የፉገራ ፍቅርም አንዳንድ ሰዎችን ማውጣት እፈልጋለሁ። "ፍቅሬ ሁሉ ነገርሽ ደስ አይለኝም" ለፅሁፉ ይሄን ርዕስ መጠቀሜንም ልብ ይሏል። ብዙ ደስ የሚለኝ ነገር አለሽ እንዲሁም ደስ የማይለኝም ነገር አለሽ ለማለት ነው። ርዕሱ ግን አሻሚ ይመስለኛል። እንግዲህ መሻማት ነው ሃሃሃ ስለዚህ እኮ የሚል ታኮ ያስፈልገዋል። ፍቅሬ ሁሉ ነገርሽ እኮ ደስ አይለኝም። 

የአዳም ረታ ብቸኛ የማልወደው ስራው ከሰማይ የወረደ ፍርፍር ነው። ስድስተኛ ስሜቴ እንደነገረኝ ከሆነ አዳም ራሱ ከስራዎቹ ሁሉ ስስ ስሜት ያለው ለሱ ይመስለኛል። የሀዲስ አለማየሁ ወንጀለኛው ዳኛ ሲበዛ ይሰለቸኛል። ማስተላለፍ የፈለጉት ነገር ይገባኛል። ምንድነው እንዳትሉኝ! አሁንም ግን ይሰለቸኛል። የበዓሉ ግርማ ደሞ የቀይ ኮከብ ጥሪ ነው። ምናልባት የአብዮቱን ሂደት በልቦለድ መልኩ ለመግለፅ ታስቦ ስለተፃፈ ይሆናል። ብቻ ከበዓሉ ስራዎች የማልወድለት ይሄንን ነው። 

ይሄ የግል ስሜቴ እና የራሴ ብቻ እውነት ነው። የናንተን አላውቅም። በስሜት ደረጃ ላንሳው ብዬ ነው። ፍቅር የበለጠ "በምወደው እና በማልወደው… በሚሉ መመላለሶች መሃል" መገለፅ አለበት የሚል ስሜት ስለሚሰማኝም ነው። እርሶስ ምን ይሰማዎታል እንደማለትም ነው። የሆነ ነገር ከተሰማዎት ስሜቶን ያጋሩኝ። ካልተሰማዎት ደሞ ላሽ ይበሉኝ።  

ስሜት ስል የለስላሳ መጠጦች ማስታወቂያ ከስሜት ጋር ያላቸው ቁርኝት እንደሚገርመኝ ተናግሬ ላብቃ… 
 ኮካ ኮላ "ስሜቱን እናጣጥም!" ይለናል 
7 ኣፕ "እውነተኛ ስሜት!" ይላል 
 ሚሪንዳ ደሞ "ከስሜትዎ ጋር ይጫወቱ" ይለናል። እርሶም በመረጡት… ወይ ከስሜትዎ ጋር ይጫወቱ አልያም ስሜቶን ያጣጥሙ… እሱ የእርሶ ጉዳይ ነው። አያገባኝም ሃሃሃ 
ይመቾት!!!!
iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

Leave Your Comment

Post a Comment

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement