Advertisement
ብቻዬን ነው የምኖረው አንዲት ቤት ውስጥ። ቤቴን በሶስቱም ግድግዳ ቤቶች ያዋስኗታል። መቼስ ለቤት በደቡብ በምስራቅ በአራቱም አቅጣጫ አይባልም እንጂ ብል ደስ የሚለኝ እንደሱ ነበር። ሆኖም በስተግራ በኩል አደፍርስ እና ልክየለሽ የተባሉ ባለትዳሮች አሉ። አንድ ድርሻዬ የተባለ ልጅም አላቸው። ድርሻዬ ግን ስሙ እያምታታታኝ ይመስለኛል ወልደውት ሳይሆን የሆነ ልጅ የሚታደልበት ቦታ ላይ ተሰጥቷቸው ይዘውት የመጡት ነው የሚመስለኝ። እንደ ስሙ የታደለ ነገር ነው በጣም ይንከባከቡታል። እና እነ አደፍረስ ብቸኛ ግቢም ጭምር የምጋራቸው አጎራባቾቼ ናቸው።
በስተቀኝ ወዝአየሁ እና አራቱ ጩጬዎቹ አሉ። ወዝአየሁ ስሙ ወንዝአየሁ ይሁን ወዝአየሁ በርግጥ አለየሁም። ግን ሚስቱ እያለች "ወዛየሁ አንተ ወዛየሁ…" ስትለው ሁለት ጊዜ ሰምቻታለሁ። እናም ወዝአየሁ ነው ብዬ ገመትኩ። ደሞ ግን ቤተሰቦቹ ወዝአየሁ ሳይሆን ወንዝአየሁ ነው ሊሉት የሚችሉት ብዬ ገምቼ እርግጠኛ ሳልሆን ይኸው በእንጥልጥል እንዳለሁ አለሁ። ሚስቱ አገር ውስጥ ያለች አይመስለኝም። እርግጠኛ ባልሆንም ልምል ሁሉ ግን እችላለሁ። አብሳላት ትሙት! ይኸው የመጨረሻ መሃላዬ ነው። እና ከነወዛየሁ ጋር ግድግዳ ብንጋራም ቅሉ በአጥር ተለይተን ሁለት የተለያዩ ግቢዎች ውስጥ ነው የምንኖረው። ለዛም ነው መሰለኝ የባዕድ አገር ሰው የባዕድ አገር ሰው ይመስሉኛል።
ከበስተኋላዬ ህዝቦች የሚኖሩበት ቤት አለ። የዛን ቤት ገቢውን ወጪውን ልለየው አልቻልኩም። ብቻ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ለሱሳቸው ሲሉ የተከራዩበት ቤት ይመስለኛል። መውጫቸውም ግቢውም በተቃራኒ አቅጣጫ ስለሆነ በመልክ የማየት እድሉ ገጥሞኝ አያውቅም። የሚሰማኝ ድምፅም ከሁለት ቋሚ ድምፆች በቀር ሁሌ የሚቀያየር ነው። እነዚህ ደግሞ የሩቅ ምስራቅ አገር ሰዎች ሆነው ነው የሚሰሙኝ።
እና እንደወትሮዬ ጉልበቴን ታቅፌ እየቆዘምኩ እያለ ከነ አደፍርስ ጣቢያ ድምፅ ሰማሁ። ሰዓቴን አየሁ ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ30 ይላል። ልቤ ክፉኛ አዘነ። ቀኑንም ቆጥሬ ደረስሁበት ህዳር 20። በቃ አደፍርስ የሚጠጣበት አቷል ማለት ነው። ያለበለዚያ በዚ ሰዓት ቤቱ የማይታሰብ ነው።
"ልክየለሽ" ብሎ ሚስቱን ሲጠራ እርግጠኛ ሆንኩ። አብዝቼ አዘንኩለት። ቢኖረኝ ኖሮ እንካ ጠጥተህ ና እለው ነበር። እንዴት አንዘላለዘለው ስሟን። ሁልግዜም ልኬ ልክዬ ነው የሚላት።
"ምን ላድርግህ?" አለችው ፊቷን ቅጭም እንዳደረገች። በርግጥ ፊቷ አይታየኝም ግን መቅጨም እንዳለባት ወስኛለሁ። መልሱን መጠባበቅ ጀመርኩ። አደፍርስ ግን ዝም። ብጠብቀው ዝም ሲል ጣቢያ ልቀይር ስል "ልክዬ…" አለ ተለሳልሶ። ፍጥነቷ "ወዬ" ስትለው። ሃሳቤን መገረብ ጀመርኩ። በቃ የሚጠጣበት አጥቶ ሳይሆን የሚጠጣውን በሃይላንድ ይዞት መጥቶ ነው። ቅድም ያለምክንያት በማዘኔ ለራሴ መልሼ አዘንኩ። ከዛ ተውኳቸውና ወደራሴ ሃሳብ ተመለስኩ። መነሻ ግን ሆነውኛል።
ቆይ ልክየለሽ ሲቆላመጥ ልኬ መሆኑ ተገቢ ነው ወይ? ልክየለሽ አፍራሽ ተቀጥያ ስላለው ብቻውን ተነጥሎ ሊቆላመጥ አይችልም። ስለዚ ከነሙሉ ግርማው ልክየለሽዬ ተብሎ እንጂ ልኬ ተብሎ በተቃራኒ ትርጉሙ ሊቆላመጥ አይገባም እያልኩ ሳወጣ ሳወርድ ብዙ ቅጥልጥል ስሞች መጥተውብኝ ማሰብ ጀመርኩ። የውብዳር ውቤ ሊባል ይችላልን? ሙሉጎጃም አልያም ሙሉዓለምስ ሙሉ ሊባል ተገቢ ነውን? የእናትፋንታንስ ነጥለን እናት ብንል ፋንታውስ ወዴት ሊገባ? እያልኩ ተጋጣሚ ስሞችን ስገጥም ስፈታ አብሳላት የተሰኘው ስም ከነሙሉ ግርማው በቤቴ ሞላ። አብሳላት የስም ቁንጮ። ስለምወዳት አይደለም እንዲሁ ስለሚያምር ነው። ልምል ሁሉ እችላለሁ አብሳላት ትሙት! አብሳላት የስም ቁንጮ ነው። እሺ ቁንጮዬ ነው።
"አፍንጫህን መላስ ትችላለህ!" የሚል የልክየለሽ ድምፅ ከሃሳቤ አነቃኝ። እንደጉድ ተንከተከትኩ። ይቅር ይበለኝና የአደፍርስ አፍንጫ የሀብታም ቤት ደጃፍ ኮት መስቀያ ነው የሚመስለው። ወደላይ ቁልምም ያለ ነው እና ሲልሰው አስቤ አሳቀኝ። ጯ የሚል ድምፅ መስማቴን ራሱ ዘግይቼ ነው ያወኩት። "ጯ" የአደፍረስ ሰፊ መዳፍ በልክየለሽ ቀይ ፊት ላይ ታተመ። መዳፉን ሳነበው ቀጥሎ የሚመጣውን ስለማውቀው ጣቢያ ለመቀየር ወሰንኩ።
ላይዋ ላይ ያለው ጂኒ ያለ ዱላ ይስራ አይስራ አላውቅም ሁሌም ከአንሶላ መጋፈፉ በፊት ይሄ ይከሰታል። መጀመሪያ ጯ የሚል ድምፅ ይሰማኛል። ከዛ የልክየለሽዬ ለቅሶ ይከተላል። ከዛ አደፍርስ ያባብላታል። ሲያባብላትም ያቅፋታል። ሲያቅፋት ይሞቃታል። ሲሞቃት ይሞቀዋል። ሙቀት ተላላፊ ነገር ነው እኔም አብሬ ይሞቀኛል። መጨረሻዬ ግን አያምርም። ልክ አሟሙቆ ቤንች ላይ እንደሚቀመጥ ተጫዋች አይነት እፍረት ነው የሚሰማኝ። ጣቢያ ቀየርኩ።
ወደቀኝ አቅጣጫ ወደነ ወዝአየሁ ቤት ዞርኩ። ወደ ሳውንድ ትራኬ። አብሬ መፅሃፍ ከፈትኩ። የወዜ አራቱ ጩጮዎች የተባረኩ ናቸው አይረብሹኝም። በርግጥ እንደጩጬ ይናጫሉ ይንጫጫሉ ግን አይረብሹኝም። አባታቸው ዘወትር 4 ተኩል ሲል ቤቱ ደራሽ ነው። ሰዓቱ ዝንፍ አትልም። አላርሜ ነው ባልተኛም ሰዓት አቅበታለሁ። ባለሱቅ ስለሆነ የሱቁ ገደብ ይኖረው ይሆናል። እስካጣራ ይቆየኝ!
እናም ያዘጋጀሁትን መፅሃፍ የመጨረሻውን ምዕራፍ ግጥም አርጌ በውሃው ፕላስተር አሸኩት። የአንድን ነገር መጀመሪያውን እንጂ መጨረሻውን ሰዎች እንዲነግሩኝ አልፈቅድም። መጨረስ ለራሴ የሰጠሁት ስልጣኔ ነው። መገመት በጣም በእጅጉ ደስ ይለኛል። ድምዳሜ ያስጠላኛል። ህይወት ብሎ ሞት የሚሉት ፈሊጥ አይገባኝም። ህይወት ብሎ ሌላ ህይወት ነው ለኔ አለቀ በቃ። አራተኛ ክፍል ሒሳቡ ስንማር ያለው ቀስት ስሜም ጭምር ነው። መነሻ እንጂ መድረሻ የሌለው ነገር። ነጮቹ አሬይ የሚሉት ነገር ማለት ነው። ደብል አሬይም ምቾት ይሰጠኛል። እናም ከዋናው ስሜ ይልቅ በቅፅል ስሜ ቀስቴ እያሉ ሲጠሩኝ ደስ የሚለኝ ለዛ ነው።
ደሞ መጡ ከኋላዎቼ። በመንጋ ነው የሚወጡት በመንጋ ነው የሚገቡት… በመንጋ ነው የሚስቁት። ሲያለቅሱ ግን እንደ ወንድ ልጅ ተደብቀው የሚያለቅሱ ይመስለኛል። አንድ ድምፅ ሞቅ ብሎ ይሰማኛል። እየሳቀ ነው የሚያወራው "አይጄ እኮ አትክልት በል ነኝ ብሎ… ቅቅል አዞ አጥንቱን ሳይበላ ነው የሚወጣው… የሚቀቀለው ድስቱ ይመስለዋል መሰለኝ… " አብረው ይስቃሉ። አይጄ ብቸኛ የደረስኩበት ስምና ድምፅ ነው። አይጄ የእንግሊዘኛ ምህፃረ ቃል ሲሆን ኢንተርናሽናል ጀዝባ ማለት ነው። ብዙ ጊዜ የፉገራቸው ሴንተር ነው። ሲቀልዱበት አብሮ ይስቅና በወፍራም ድምፁ "ቅልጥማም" ይልና ጉሮሮውን ጠርጎ የመልስ ምት ይሰጣል።
"ትዝ ይላችኋል ይሄ የፊደል ሰው ባለፈው ሻማ ምሽት ላይ አንጀት ሊበላ ያቀረበው ግጥም?
: : : : : : : : : : : : : : : : : : : : :
አብልሽን ሆኜ በጡቶችሽ መሃል
ጭራሽ አልፈልግም እየዘለልኩ መዋል።
ይልቅ በጨዋነት ላንቺም ለጌጥሽ
በ‘ጅሽ ላይ ያኑረኝ እንደ ሰዓትሽ።
: : : : : : : : : : : : : : : : : : : : :
አሁን እኮ ነው የሚገባኝ… ሕብረ ቃሉ "በእጅሽ ላይ ያኑረኝ እንደ ሰዓትሽ" ሲሆን ድብቅ ፍቺው… ያው እንደምታውቁት የሴቶች ሰዓት ብዙው አይሰራም። እናም በአንቺ እጅ ሳልሰራ ልኑር ማለቱ እኮ ነው። መጀመሪያ አንጀት ሊበላ መስሎኝ ነበር ቆይቶ ነው ሳይሰራ ሊበላ እንደሆነ የገባኝ ሃሃሃ ሃሃሃ…"
ሌሎቹም ሳቁን አገዙት።
ድንገት በመሃል መጀመሪያ አካባቢ ጉረኛ የሚመስለኝ ልጅ ዘፈን ጀመረ።
"እኔ መዩ ቱርክ ባይ
የምሸሽ ነኝ ወይ
የምሸሽ ነኝ ወይ"
በሚለው ሽለላዊ ዘፈን ዜማ ነው…
"እኔ ዋሊ ሚስኮል ባይ
ደዋይሽ ነኝ ወይ
ደዋይሽ ነኝ ወይ" ብሎ ሲያንጎራጉር "አሁንም ሚስኮል አረገች?" የሚሉ የሁለት ሰዎች የጋራ ድምፅ ተሰማኝ።
ዜማው ራሱን ቀጠለው…
"ትላንታ ማታ ሚስኮል በረከተ
የነሱን ባላውቅም የኔ ባትሪ ሞተ
የኔ ባትሪ ሞተ
እኔ ባሊ ሚስኮል ባይ
ደዋይሽ ነኝ ወይ
ደዋይሽ ነኝ ወይ"
ሁሉም ነው አብረው የሚሉት ይሄንን። ብቻውን ሲለው ዋሊ የመሰለኝ ስም በጋራ ሲሉት ደግሞ ባሊ ሆኖ ተሰማኝ። ሁለቱም አልተገመተልኝም። እነዚህ አጎራባቾቼ የሚገርመኝ ነገራቸው እጅግ መናበባቸው ነው። "እንዳደውል እንዳደውል እንዳደውል እንዳደውል…" የሚል ብዙ ድምፅ ሰማሁ። ምን ቢሆን ነበር እንደዚህ ለማለት የበቁት የሚለውን ለመገመት ማሰብ ጀመርኩ…