Komentar baru

Advertisement

እመኛለሁ —ዲንዲን ዲዲን —እመኛለሁ…

Eriyot Alemu
Aug 18, 2022
Last Updated 2023-08-21T03:50:04Z
Advertisement


 


"እመኛለሁ እመኛለሁ 
ዘውትር በየለቱ 
ላሳካ ኑሮን ከብልሃቱ 
እመኛለሁ እመኛለሁ" 

ህፃን ልጅ ድክ ድክ ማለት ጀመረና ወደ እሳት ማምራት ጀመረ። ዝምብለን "እፉ ነው!" ብንለው የሚሰማን ይመስላችኋል? በጭራሽ አይሰማንም። እፉ እንዲገባው እፉን መጀመሪያ ሊቀምሰው ይገባል። በመጀመሪያ እፉን የሚያስተምረው ሰውነቱ ለእፉ የሚሰጠው ምላሽ ነው። ከዛም ጭንቅላቱ (ባወቶማቲክኛ) ያንን ነገር ደግሞ መንካት እንደሌለበት፣ ከቆንጆ የማትረሳ የህመም ስሜት ጋር ጥሩ አድርጎ ያትመዋል። ለጥቆ እኛ ወደ እሳቱ ሲሄድ "እፉ ነው!" ስንለው፣ ጭንቅላቱ ቀድሞ ለመዘገበው ነገር ስያሜ ያገኝለታል። ስለዚህ ሌላም ነገር ሊነካ ሲል "እፉ ነው!" የሚል ማስፈራሪያ ትርጉም ስለሚኖረው ማሙሸት ይጠነቀቀዋል ማለት ነው። የተፈጥሮ አሰራር ሁሌም ተአምራዊ ነው። ሰሚ ካገኘች ሁሌም ውብ ቋንቋ አላት። 

እኛ አዋቂዎችም ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጃራ ስንለኩስ፣ ሰውነታችን— ህፃን ሆነን የተፈጠረብንን ዓይነት የማስጠንቂያ ስሜት ለጭንቅላታችን ይልካል። ተፈጥሮ ሁሌም ያው ነች። እኛ ግን እያደግን ስንመጣ እንለወጣለን። ትክክል ያልሆነ ነገር እያስተናገድክ ነው ተጠንቀቅ—የሚል መልህክት። እኛ ግን በአብዛኛው ጊዜ ውስጣችንን ከማዳመጥ ይልቅ ዙሪያችንን (እነ እንትናን) ማየት ይቀናናል።  

ለምሳሌ ሁሉም አጫሽ የመጀመሪያውን ሲጃራውን ሲለኩስ ያስለዋል። ትክክለኛ ላልሆነ ነገር የሚሰጥ የሰውነት ምላሽ ነው—ሳሉ። እኛ የምናየው ግን የኛን ማሳል ሳይሆን፣ የተፈጥሮን ህግ ደጋግመው በማድረግ የተላለፉትን ሲኒየር አጫሾችን ነው። እነሱ አያስሉማ። እነሱን ለመሆን ጠንክረን መስራት እንጀምራለን። አብዛኛው ፍሬሽ አጫሽ ቀድሞ ተደብቆ የሚያጨሰው፣ አንድም O Q ቅርፅ ሰርቶ አጫሹን ማህበረሰብ ለመቀላቀል ነው።   

ታድያ በዚህ የመጃጃል፣ ከተፈጥሮ የማፈንገጥ ሂደት ነው፣ በሰውነታችን ውስጥ ሱስ የሚያሲዘው ንጥረ ነገር (ኒኮቲን) መጠራቀም የሚጀምረው። እዚጋ ታሪኩ ይለወጣል። ኒኮቲን ሲጠራቀም ነፍስ መዝራት ይጀምራል (ምሳሌአዊ ነው)። የራሱ ሆድ የራሱ ጭንቅላት ይኖረዋል። ከዛም ሲርበው አምጣ እያለ ማንቁርት መያዝ ይጀምራል። ይርበዋል እንመግበዋለን። ይርበዋል እንመግበዋለን። ይርበዋል እንመግበዋለን። ማለቂያ የሌለው አዙሪት ነው። 

ከዛም ጭንቅላቱ ደግሞ ቀድሞ በሲጋራ አምራች ፉብሪካዎች በፊልም፣ በመፅሃፍት፣ በሙዚቃ በመሳሰሉት የተሰራውን አዕምሮ መስለቢያ መንገዶች መጠቀም ይጀምራል። እንደዚህ እንድናስብ በማድረግ:— የምናጨሰው ደስ ስለሚለን፣ ስለሚያነቃን፣ ትኩረት ለመሰብሰብ እንዲረዳን፣ አራዳ ለመሆን፣ ከድብርት ለመላቀቅ ወዘተርፈ ነው። አብዛኛው ምክንያት ወደ ውስጡ አሸንፎ ለሚያይ ብዥታ መሆኑ ይገባዋል። እናም የምናጨሰው የተጠራቀመ ኒኮቲን ሲጎል አምጣ ስለሚለን ብቻ ነው።በያንዳንዱ የመመገብ ሂደት ጭንቅላት ለሚያረገው ነገር ትርጉም ለመስጠት በሚል የሲጋራ ጥቅም እያለ መዘርዘር ይጀምራል። ሁሉም ግን ውሸት ነው። የሁሉም አጫሽ ውስጡ እውነቱን ያውቀዋል። የምናጨስበት ብቸኛ ምክንያት ውስጣችን የተጠራቀመ ኒኮቲን የሚባል ሱስ የሚያሲዝ ነገር ስላለ ነው። እንደ መኪና ነዳጅ ዝቅ ሲል ሙላኝ ይላል። ሌላው ምክንያት ሁሉ ፈጠራ ነው። ዝቅ ሲል ጥሩ ስሜት አይሰጥም። ስንሞላው ጥሩ ስሜት እናገኛለን። ልብ አርጉ ሲጃራ በራሱ ጥሩ ስሜት ፈጥሮ ሳይሆን ራሱ ያበላሸውን ራሱ አስተካክሎ ነው። ሁሉም የሲጋራ ጥሩ የሚመስሉ ስሜቶች ከዚህ ሃሳብ ጋር ተያያዥ ናቸው። እንዲህ ከሆነ ታድያ ሰዉ ለምን ሲጋራ አይተውም? 

ሲጃራ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በሰው ጭንቅላት ውስጥ የተሰራ ኃይለኛ ሿሿ አለ። ሰው ሁሉ ሲጋራ እንደማይተው እንዲያምን ተደርጓል። ማን ፈጠረው? አጀንዳችን አይደለም። ፋብሪካዎች ነጋዴዎቹ ብለነው ግን እንለፍ። ሰው መተው እንደማይችል ካመነ ደግሞ እውነቱ ሆኗል ማለት ነው። ደረቅ ግትር አማኝ ደግሞ የሲጋራን ጥቅም በሃላል ሊያስረዳህ ሁሉ ይሞክራል። አንተም ያኔ "ታድያ ይሄ ሁሉ ጥቅም ካለው ለምን ለልጅህ አታስተምረውም?" ትለዋለህ። ያኔ በር ዘግቶ ሊያለቅስ ይችላል። ይህ በእውኑ የገጠመኝ እውነት ነው። አንዳንድ እውነት ሳወራ ለእውነት ያልተዘጋጀ ሰው ሊጠላኝ ይችላል። ምክንያቱም እውነት መራራ ነች። እውነቱን ታውቁታላችሁ እውነቱም ነፃ ያወጣችኋል ሃያል ሃይለ ቃል ነው። ችግሩ ካለማወቃችን አይደለም ካተገባበራችን እንጂ። ከክህደታችን እንጂ… ሌላም ሌላም። 

ስለዚህ ሲጃራ ለምን እንደሚያጨስ የገባው ለምን እንደማያጨስ ይገለጥለታል ማለት ነው። ብቸኛው መንገድ ውስጥህ የተጠራቀመውን ኒኮቲን ጠራርጎ ማውጣት ነው። የብዙ ጊዜ ጥርቅም ስለሆነ የራሱ ጊዜ ይፈልጋል። በዚህ መሃል ዝቅ ሲል ሙላኝ ትግሉ አለ። የመጀመሪያው ሶስት ቀን ውስዋሱ ጠንካራ ነው። ከዛ እስከ 6 ቀን ስሜቱ ለስለስ ብሎ ይቀጥላል። ከዛ በኋላ ምንም ሃጃ የለውም። ይሄን ያህል ቀላል ነው። ክብደቱን ያሳመኑን ሻጮቹና በትክክል ሳይገባቸው ሞክረው ያቃታቸው ወዳጆቻችን ናቸው። ድክመታቸውን ሽንፈታቸውን እውነት አርገው ይግቱናል። እኛም አሜን ብለን እንቀበላለን። ሲጋራ ማቆም ከባድ ነው ይሉናል። ሚሊየኖች ግን አቁመዋል። ነገሩን እንጂ አንድ ሰው ካቆመ ማቆም እንደሚቻል በቂ ማሳያ ነው። 

ይህ ሳይኮሎጂካልም ፊዚካልም ጉዳት ያለው ሱስ የምንላቀቅበት መንገድ ነው። ሆኖም ልማድ የሚባል ነገርም አለ። ልማድ ደጋግመን የምናደርገው ነገር መጀመሪያ ምክንያት የነበረው በኋላ ላይ ግን እንዲሁ በዘልማድ የሚደረግ ነገር ነው። አንድ ልማድ ጭንቅላት ውስጥ ፎርም ለማድረግ ከ6 እስከ 14 ቀን ይፈጅበታል። ይሄን ያነሳሁት ሲጋራ ሱስ ከሚያሲዘው ንጥረ ነገር ውጪ ሲቆይ እንዲሁ በልማድም የሚጨስባቸው ሁኔታዎች ስላሉ ነው። እና ሲጋራ መተው የፈለገ ሰው ቢያንስ ለ15 ቀን አዲስ ልማድ መፍጠር አለበት። ቤቱ አልጋው ላይ ሆኖ የሚያጨስ የነበረ አልጋውን አቅጣጫ ማዞሩ ቀላል ቢመስል እንኳ ትልቅ ኢፌክት አለው። እንደ ምሳሌ ጥቂቱን ማንሳቴ ነው። ጨረቃ እያየ የሚያጨስ፣ ወክ እያረገ የሚያጨስ ሌላም ሌላም ማጨሱን ቅርፅ ለመስጠት ብዙ ልማድ ያለው ስላለ እነዚህን ነገሮች መቀየር ግዴታ ባይሆንም ስራ ያቀላል። አዲስ ነገር አዲስ ስሜት ስለሚሰጥም ጥሩ ጉልበት ይሆናል። 

ይህ ፅሁፍ አጭር ነው። ከዚህ በፊት የሆነ ቦታ ላይ ለተወሰኑ ሰዎች በዝግ ይደርስ ዘንድ ፅፌው የነበረ ነው። ከዛ ረሳሁት። ሁሌም ምንም ስሰራ የማምነው አንድ ነገር አለ። የሆነ ጥግ ላይ የሆነ ሰው ሃሳብህ ሃሳቡ የሚሆንለት አለ። በቃ አንድ ሰው ብዙ ነው ለኔ። እናም በዚህ መሰል ጉዳይ ስፅፍ ታተሮ የሚያነበኝ አንድ ሰው ነበር። በውስጥ መስመር ያወራኝም ነበር። አንድ ወቅት ላይ ደውሎ "ጫትም መጠጥም ከተውኩ አንድ ወር ሞላኝ!" ሲለኝ በወቅቱ እውነት እውነት አልመሰለኝም ነበር። እህቱም በስልክ ጭምር አውርታኝ ለምን እንደሆነ ባልገባኝ ምክንያት አልተዋጠልኝም ነበር። 

በፅሁፍ ደረጃ ሰዎች ሱስ ይተዋሉ አይተውም? የሚለው ለራሴም ያልመለስኩት ጥያቄ ነበረ። በፅሁፍ ጀምሬው በአካል ማግኘት እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር። ወይም በፅሁፍ መነሻ ሆኖት ሌላ ሰው በአካል ማግኘት እንዳለበት ይሰማኝ ነበር። ልክ ግን አልነበርኩም። ያ ያኔ የደወለልኝ ሰው ዛሬ ሌላ ቦታ ነው ያለው። ከኔ በተሻለ ወደፊት ብዙ የሚገፋ ሰው ነው አሁን እሱ። እኔ የፊለፊት ሰው አይደለሁም። የምሆንም አይመስለኝም። በሱስ ዙሪያ በፅሁፍ ብቻ ብዙ መስራት እንደሚቻል በሚገባ መልሶ ያሳመነኝ ሰው ነው። 

እናም በዚህ ብሎጌ በብዙ የራሴን አንዳንድ ትንንሽ ነገሮች እየተጫወትኩ… ሲነሽጠኝ ሲነሽጠኝ እንደዚህ ዓይነት ፅሁፍ አካፍላለሁ ለማለት ነው። በውስጥ ባናወራ እንኳ፣ አንዳንድ ፅሁፎች የሆነ ሰው የሆነ ቦታ ላይ ዛሬ ባይጠቅመው ነገ ይጠቅመዋል ብዬ አስባለሁ። አስቤም እፅፋለሁ። በአንድ ርዕስ ስደጋግም ራሴም ስለሚሰለቸኝ፣ መነሳት ያለባቸውንም ሁነኛ ሁነኛ ነጥቦች ያነሳሁ ስለመሰለኝም፣ በየመሃል ነገር እየደጋገምኩ ሰው አላዝግም። አጋጣሚ ለማንሳት ያህል፣ ስለ ሱስ ስፅፍ እንደጎዳሁት የሚሰማው ሰው ገጥሞኝም ያውቃል። ስሜቱን ስለምረዳው በክፋት አልወስድኩበትም። ሆኖም አላማዬ ማንንም የማይጎዳ እንደነበር ግልፅ ይመስለኛል። ዛሬም ነገም ከነገ ወዲያም ማንንም የሚጎዳ ነገር ከውስጤ ሊፈጠር አይችልም። ትላንትም ተፈጥሮ አያውቅም። ሰው ራሱ ፈጥሮ የጎዳሁት ከመሰለኝ የኔ ባይሆንም ችግሩ ይቅር ይበለኝ ብዬ እለምነዋለሁ። አንዳንዴ ባይዲፎልት አታክ እንደተደረገ የሚሰማው እንዳለ ስለሚሰማኝ ነው። ለዚህም በድጋሚ ይቅርታ!!! 

የአንዳንድ ጉዳዮችን አስፈላጊነት የምትረዷቸው ቦታው ላይ ስትቆሙ ብቻ ነው ለማለት እገደዳለሁ። ለምሳሌ በቴሌቪዥን ይሁን በሬዲዮ የመጠጥ ማስታወቂያ መታገዱ ሱስ ውስጥ ላለውም፣ ሱስ ለተወውም (በከባዱ)፣ ለሚመጣው ትውልድም ምን ያህል ጠቃሚ መሆኑን ብዙ ሰው የተረዳው አይመስለኝም። በራሴ እንዴት እፎይ እንዳልኩ ለመግለፅ ቃል የለኝም። ሱስ የጭንቅላት ጨዋታም ነው። ሰው ቢረዳውም ባይረዳውም ውጤቱ የጋራ ነው። በተለይ ሱስ በመተው ሂደት ላይ የምታልፉ የመጠጥን ነገር በፍፁም ያለመስማት ያለማየትን ጥቅም ስትደርሱበት ይገባችኋል። የልጆቹ ነገም የሚያሳስበው እንደዛው የማስታወቂያዎቹ መቅረት ትርጉሙ ሊገለጥለት ይገባል። በማስታወቂያዎቹ ለምሳሌ በስራ የደከመ ሰውነት ድራፍት እንደሚያስፈልገው ሳናውቀው እንሰበካለን። ሳናውቀው እናምነዋለን። ልጆች አድገውም ያንን ለማድረግ በልባቸው ቀጠሮ ይይዛሉ። በእውነቱ ግን በስራ የደከመ ሰውነት የሚያስፈልገው ድራፍት ሳይሆን እረፍት ነው። እንዲህ ነው የሚያመቻቹን። እናም ያ የማስታወቂያ የማስቀረት ውሳኔ ጎልያድን የሚያክል ውጤት አለው። አምጥቷልም። 

ከ12 አመታት በፊት ፌስቡክ ላይ የመጀመሪያ ፎቶዬ የተደረደረ የመጠጥ ፎቶ ነበር። "ጠጡ ወደ እኔ እስክትመጡ" ብዬበትም ነበር። ዛሬ ለምን እነደዳሳፈረኝ ገልጬ ላብቃ… ብዙ ነገር ተሳስቼ የጀመርኩ እንደነበር ማሳያ ነው። አንዳንዶች ዛሬ የምታረጉትን ልክ አይደለም ስል ትላንት አድርጌው ስለነበር እንጂ በቅድስና ተገልፆልኝ አይደለምም ለማለት ጭምር ነው። ትላንት ከ12 አመት በፊት እኔ የመጠጥ ፖስት በማድረጌ ውስጥ ብዙ ታናናሾቼ ላይ ያልሆነ ምስል ፈጥሬአለሁ። በእውኑ የተሰጠኝ አስተያየት ነው። ያኔ ሱስ ለመተው ከራሱ ጋር ሲታገል የነበረ ሰው ካለም፣ ትግሉን በጠረባ ብዬበት እንደነበር ዛሬ ተረድቻለሁ። ይሄ የገባኝ አሁን ነው። እናም እንደ ቴሌቪዥኑና ሬድዮው ማስታወቂያ፣ ሶሻል ሚዲያው ላይ ሰዎች በፈቃዳቸው መጠጥ ይሁን ሌላም ሱስ የሚያስተዋውቁበትን መንገድ ቆም ብለው እንዲያስቡበት እመኛለሁ። የሚጠጣ እስከቻለው በፍቅር ይጠጣ! ግን መጠጣቱን ቀባብቶ ማቅረቡ የሆነ ቦታ የሆነ ሰው ላይ ልክ ያልሆነ ስሜት መፍጠሩን እንዲረዳም እመኛለሁ። መቼም አውነቱን ውስጡ አበጥሮ እንደሚያውቀው አውቃለሁ ያቃል። ብቻ ብዙ ነገር እመኛለሁ። ሰዎች ከኮሌጅ ከመግባታቸው በፊት ስለ ሱስ በቂ እውቀት የሚያገኙበት መንገድ በሲስተም ደረጃ ተቀርፆ ማየት እመኛለሁ። እንደ ሃገር ሱስን በሃይለኛው የምትከላከልበት መንገድ "ቀድሞ መጠንቀቅ" የሚለው መሆኑን በተቋም ደረጃ ያሉ ሰዎች እንዲረዱት እመኛለሁ። ነገ ለታናናሾቻችን ፍፁም የተሻለ ነገር እመኛለሁ። ብዙ ነገር እመኛለሁ! 

ብቻ እመኛለሁ…

"እመኛለሁ እመኛለሁ 
ዘውትር በየለቱ 
ላሳካ ኑሮን በብልሃቱ 
እመኛለሁ እመኛለሁ" የሚለውን ሙዚቃ ተጋበዙልኝ።
iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

Leave Your Comment

Post a Comment

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement