Advertisement
ንቤ ዝም ብትል ቃል ባይወጣ ካ'ፏ
ባዶ እጄን እንዳልቆም ከክቡር ደጃፏ
"ለዓይኗ ሞላ የሚል ሲገባም ከ'ቅፏ
ምን ይዤ ልጠጋት ፍቅርን የሚያረግ ፏ"
እያልኩ...
እጅ መንሻ ሳስስ ዝሆን የሚያካክል
አንድም ባይመጣልኝ ፍቅሬን የሚወክል
"ራሱን ዝሆን ነው ከሰጠኋት አይቀር
በፍቅር ልክ ነው ስጦታንስ መስፈር!"
ብዬ…
ንቤ ዝም ብትል ቃል ባይወጣ ካ'ፏ
ያ’ሳብ ጥጌን ይዤ ለዝሆን ስለፋ
ብዙ ክረምት ሄዶ ብዙ በጋ መጣ
ዝሆን ሎተሪ እንኳ ለስንት ሰው ወጣ።
ንቤ ዝም ብትል ቃል ባይወጣ ካ'ፏ
ዓይኗ እየተጣራ ከዝሆን ስላፋ
ስክብ ስንድ ስክብ ጊዜ እየበረረ
አቅሜን የሚያማክል ሀሳብ ተፈጠረ
"ጥርሱን ብሰጣትስ ከነፍሱ ምን አላት?
ካልወደደቺውም እንጃልኝ እንጃላት"
እያልኩ
እንደራሷ ጥፋት በሀሳቤ ስጣላት…
ውዴ ዝም ብትል ቃል ባይወጣ ካ'ፏ
ዓይኗ እየነገረኝ ከዝሆን ስላፋ
ዝሆን ሰጪው እኔን በፍፁም ዘንግቼ
በከንቱ እሳቤ ላይ ሳለሁኝ ተኝቼ…
ንቤ ዝም ብትል ቃል ባይወጣ ካ'ፏ
በ'ኔ ልክ ያየችው ቆሞ ከደጃፏ
ፈገግታ ያጀበው እኔነቱን ሰጥቶ
ንቤን ወሰደብኝ እኔን ቅጣት ቀጥቶ።