Komentar baru

Advertisement

እኔ ፒተር ሩሶ አይደለሁም እና ሌሎችም ተረቶች!

Eriyot Alemu
Aug 10, 2022
Last Updated 2023-08-21T18:45:02Z
Advertisement



አማርኛ መምህራችን ተረት አብዝተው ይወዱ ነበር። አብዝተውም የመሰረት ያስብሉን ነበር። ሁልጊዜ ግን ተረት ነግረውን ከጨረሱ በኋላ ኮስተር ብለው "ከዚህ ምን ተማራቹ ልጆች?" ይሉናል… እኛም ተሽቀዳድመን የተማርነውን እንነግራቸኋለን… አንድ ቀን ይሄን ተረት ነገሩን። 

 <<ከእለታት አንድ ቀን አንዲት ልጃገረድ አባቷን እንድትጠራ እናቷ ትልካታለች፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ አባትዬው ከጓደኞቹ ጋር የእርሻ ስራውን እያከናወነ ነበር፡፡ ልጅቷ እንደደረሰችም የአባቷ ጓደኞች ለምን እንደመጣች ይጠይቋታል፡፡ “ለአባትሽ ምን መልዕክት ነው ይዘሽ የመጣሽው? ንገሪው!” ይሏታል፡፡ እሷም “አይ! ምስጢር ነው፡፡ እናንተ ባላችሁበት አልናገርም፡፡” ስትል ትመልስላቸዋለች፡፡ እነርሱም ልጅቷን ለማሞኘት ሲሉ “ግደለም ንገሪው፡፡ እኛ እንዳንሰማ ዓይናችንን እንጨፍናለን” ይሏታል፡፡ ልጅቷም “በጣም ጥሩ! ነገር ግን በገባችሁት ቃል መሰረት ዓይናችሁን በደንብ መጨፈን አለባችሁ” ትላቸዋለች፡፡ ሰዎቹም በገቡት ቃል መሰረት ዓይናቸውን በደንብ ይጨፍናሉ፡፡ ይሄኔ ልጅት ፊቷን ወደ አባቷ አዙራ በምልክት ለምሳ መጠራቱን ታስረዳዋለች፡፡ ይህንን ስታደርግ አንዲት ቃል አልተነፈሰችም ነበር፡፡>> 

 ከዛ አማርኛ መምህራችን እንደተለመደው ኮስተር ብለው "ከዚህ ምን ተማራቹ ልጆች?" አሉን። ከዛ እንዳልተለመደው ቀድሜ እጄን አስወነጨፍኩና… "ሰዎች ሊያታልሉን ሲያስቡ… በነሱ መንገድ እንደምንታለልላቸው መስለን፣ ፀዳ ብለን መልሰን ማታለል እንዳለብን ነው የተማርነው…" ስል… "ጎበዝ የኔ ልጅ ጎበዝ!" ብለው የተማርኩትን እንዳረሳው አርገው ፀጉሬን እያሻሹ አበረታቱኝ። 


★★★ መልመጃ ተረት ★★★
 ሁለት ትንንጥ ልጆች ደስቶ ፊንገር እየተጫወቱ ነው… አንደኛው ብልጣብልጥ ነው፣ ደጋፊም አለው። አንደኛው ደሞ ነገሮችን ቀለል አርጎ የሚያይ፣ በየዋህነት የሚኖር፣ እንደሞኝ ሲያዩት ደስ የሚሰኝ ገራገር ቢጤ ነው። 

 ብልጣብልጡ ከሌሎች ጋር (ደስቶ ፊንገር) ሲጫወት የሚጠቀመውን ተራ ብልጣብልጥ መንገድ፣ ሆን ብሎ ለገራገሩ አሳይቶታል። አሁን ተራው ደርሶ ሁለቱ ሊጫወቱ ቁጭ ብለዋል። ብልጣብልጡ (ኦሊ) ነው፣ ገራገሩ ደሞ (ፊንገር)… እንደተለመደው ብልጣብልጡ ከገራገሩ ኋላ ሌላ ሰላይ ጩጬ አቁሟል። የገራገሩን ጣት ከጀርባ አይቶ ለብልጣብልጡ የሚዘግብ ጩጬ ነው… ጭውቴው ተጀመረ። 

 ገራገሩ ከጀርባው ያዘጋጀው ጣት ብዛት ሶስት ነው… ሰላዩ ጩጬ ለብልጣብልጡ ሪፖርት አረገ። ስለዚህ ቀላሉ ጨዋታ ብልጣብልጡ (ኦሊ) ስለሆነ… ሁለት ይጨምርበትና ጨዋታው ያልቃል። ሆኖም ብልጣብልጡ ለገራገሩ ቀድም ያስጠናውን ትምህርት ግምት ውስጥ ከቶ፣ በኩራት አምስት ጣቱን አወጣ። የገጠመው ግን ያልገመተው ነው፤ ገራገሩ ያወጣው ጣት ሁለት ነው። እሱም ፊንገር ነው። ጠብቆ የነበረው ባዶ ጣት ነበር። ሆኖም ተበላ!!!! 

 ★★★ ተረት ተረት ★★★ 
(ይቺን የፈረንጅ ጆክ ወደኛ ተረት ቀይሬአት ነው፤ አስተማሪ ጣፋጭ ዘለላ ምክር ውስጧ ካለ ፈትሿት እስኪ)

 በጥንት ጊዜ አንድ አንበሳ ነበረ። ያ አንበሳ አሁንም አለ። ያ ጥንት ጊዜ ግን መኖሩን እንጃ። እና አንድ ቀን አይመረቅኑ አመረቃቀን መረቀነና ‘የጫካው ንጉስ ማነው?‘ የሚል ጥያቄ አንግቦ አገር ምድሩን መዞር ጀመረ።  

 መጀመሪያ ጦጢትን አገኛት። አጋጣሚ ዲኖ ቦርሳዋን እንዳነገተች ነበር። የአያ አንበሶም "የጫካው ንጉስ ማነው?" የሚል ጥያቄ ደረሳት። "መጠርጠሩስ!" ብላ ዞራ ቦርሳዋን አሳየችው። ድሮስ ጦጢት ብልጥ አይደለች። ዝሆንም ቢጠይቃት እኮ፣ ዝሆን ሎተሪ እያሳየች "መጠርጠሩስ!" እንደምትለው አልጠራጠርም። 

 ቀጥሎ ያገኘው አዞን ነው። የብሱ ላይ ጋደም ብሎ ፀሃይ እየሞቀ ነበር። አግጥጧልም። ብልኋ ወፍ፣ 6ተኛ ክፍል እንግሊዘኛ መጣፍ ላይ the clever bird ተብላ ያለችው ጥርሱን እየፋቀችለት ነበር። አያ አንበሶ ጠጋ ብሎ በተለመደ ጥጋቡ "የጫካው ንጉስ ማነው?" ብሎ ጠየቀው። አዞም ግልፍ ብሎበት አፍንጫውን ሲነፋ፣ ብልኋ ወፍ በጆሮው ጠጋ ብላ "የጫካው እኮ ነው ያለው… አንተ ምን ጨነቀህ" ብላ ሹክ አለችው።  "እህህ አያ አንበሶ ነዋ!" አለው።  "ጎበዝ አዞ! ጎበዝ! ሌላ ጊዜ፣ ስለ ጥቁር አዞ ተጠማዞ እንጨዋወታለን" ብሎ ስሞት ሄደ።   

 ቀጥሎ ያገኘው ግመልን ነበር። እያመሰኳችም ነው። ቀጥታ ጥያቄው ደረሳት።   "አቦ አንተ ነሃ! አትጨቅጭቀኝ!" ብላ መለሰችለት። አያ አንበሶም በልቡ ዋናው መልሷ ነው አለና… እነ ሙሉቀን መለሰ እነ ቴዲ አፍሮ "ላሜ ቦራ እምቧ በይ እምቧ በይ" እያሉ ካስቸገሯት ላም ላይ የወሰደውን ወተት ሰጣት። ስላመሰኳች በወተት ትስበረው ብሎ ይሆናል። ለራሱ እኮ መርቅኖ ነበር።

 ከዛ በምርቃና ሲሄድ ሲሄድ ሲሄድ ሁሉንም እንስሳት ሲጠይቅ… ከዛም ሲሄድ ሲሄድ ሲጠይቅ… ዝሆን ጋር ደረሰ። (የተቀሩትን እንስሳት ቃለ መጠይቅ አማዞንቱብ ላይ አለ ዳውንሎድ አርጋቹ እዩት) አያ አንበሶም ዝሆንን በንቀት አይን እያየ የለመደውን "የጫካው ንጉስ ማነው?" ጥያቄ ሰነዘረለት። ዝሆን ዝም። ደግሞም " የጫካው ንጉስ ማነው?"… አሁንም ዝሆን ዝም። ጥያቄውን ሰለሰው። ዝሆን በኩንቢው ሳብ አረገና አንስቶ ከመሬት ደባለቀው። እዛው እያለ ዘሎ ሲሰፈርበት መሬት ተንቀጠቀጠች። በሬክተር ስኬል 4 ነጥም ስምንት ምናምን። እንደዛ አካባቢ። እንኳን ዝሆን የሌስተር ሲቲ ደጋፊዎችም መሬት እንደሚያንቀጠቅጡ ካምቦሎጆዲያ ላይ በጉልህ ተፅፎ ይገኛል። አጅሬ አያ አንበሶም አቧራውን አራግፎ ተነሳና…  "ዝሆን ደሞ ምንድነው?… ዝምብለህ መልሱን አላቀውም አትልም እንዴ፣ እርግጫው ምን ቤት ነው?" ብሎ ሲያስቀይስ… ዝሆን በተወዳጅ ዝሆን ጥርሱ ከት ከት ከት ብሎ ሳቀ። አቀፈውም። እስካሁን ምድር ላይ እንደዚህ አይነት መተቃቀፍ ታይቶ አይታወቅም ይላሉ አንዳንድ ክባዶች።

 ዝሆንም እጅግ ዝቅ ብሎ … "አያ አንበሱ ሺ አመት ይንገሱ" አለውም። ዝሆን ለንግስና እምብዛም ነው ተባለለት። ከዛ አንድ ዛፍ ጥግ ሄደው ሲጫወቱ ሲጫወቱ ዛፉን እንደተደገፈ ዝሆን አንቀላፈ። የአይን እማኞች እንደሚሉት ከሆነ አስቱካ ቦታው ላይ ነበረች… ለዛም ነው ቀጣዩን የዘፈነችው። 

 "ዛፍ ተደግፎ ነው ዝሆን ሲያንቀለፋ 
የልቤን ሳልነግረው ከነእንቅልፌም ጠፋ" ከዛን ጊዜ ጀምሮ አያ አንበሶ፣ የሌለ ግግም ከማለት በሽንፈት መቀለድም እንደሚያዋጣ፣ ያለሙትን ግብ እንደሚያስመታ ተገነዘበ። ጨዋታና ቀልድ ለካ ማንንም ይገዛል አለ በልቡም።

★★★ ሌላ ተረት ደግሞ  ★★★
 አንድ ኮሚክ የሆነ ትያትረኛ ነበረ… ሁሌም ኩመካ ብቻ ነው የሚጫወተው… ታድያ በአንድ በክፉ ቀን፣ መድረክ ላይ እያለ ከጀርባ እሳት ይነሳል… ወደ ታዳሚው በቅርበት ተጠግቶ "እሳት እሳት!" እያለ መጮህ ይጀምራል…
 ታዳሚውም ሆታውን፣ እልልታውን፣ ጭብጫቦውን፣ ፉጨቱን ይለግሰዋል…
 "አረ የእውነቴን ነው! … እሳት እሳት" ታዳሚውም የበለጠ ፌሽታና ሆሆታ ለቀቀበት… 
 አንዳንዱ በልቡ "ከተወኑስ አይቀር እንዲ ነው!" አለ። 
ይሄኔ ኮሚኩ እግሬ አውጪኝ አለና፣ በህዝብ መውጫ በር አድርጎ አቀጠነው… ህዝቡም እየሳቀ፣ እያጨበጨበ፣ እሳት የተበላ የመጀመሪያው ሕዝብ ሆነ።
iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

Leave Your Comment

Post a Comment

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement