Advertisement
ይሄ ታሪክ እና መረጃን በአግባቡ የመሰነድ ደካማ ባህላችን አንዱ መገለጫም ጭምር ይመስለኛል። ጥቂቶቹ ናቸው የህትመት ብርሃንን የሚያዩት። አንዳንዶቹም በእንግሊዘኛ ቋንቋ ብቻ። ሆኖም በግል ባደረኩት ፍተሻ ከ1949 እስከ 1961 ድረስ የታተሙ ከ50 በላይ ተውኔቶች ወመዘክር ላይብረሪ እንደሚገኙ አረጋግጫለሁ። ለመድረክ የበቁ ይሁኑ አይሁኑ ግን እርግጠኛ መሆን አልቻልኩም። ከተለመዱት የተውኔት ደራሲያን ስሞች በተለየም ብዙ አዳዲስ ስሞች ስላየሁም ነው።
ወደ ነጩ ላይብረሪያችን ብትሄዱ ደሞ የአንዳንድ ሃገራት ተውኔቶችን እንደ ልብ ታገኛላቹ። የእምዬ ቻይናማ ከጥንት እስከ ቅርብ በበቂ አለ። ቻይናውያን አለን የሚሉት የተውኔት ፀሃፊ Cao Yu… Sunrise እና Thunderstorm የተባሉ ሁለት ስራዎቹ በአግባቡ ተጠርዘው ወመዘክር ይገኛሉ። በተለየ ሁኔታ የጠቀስኩት ተውኔቶቹ ቆንጆ ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን የተለየ ህትመትም ስላላቸው ጭምር ነው።
መፅሃፉ ላይ በየ ትዕይንቱ ያሉ የመድረክ አቀማመጥ እና የተዋንያን ሁኔታ በፎቶ ጭምር ይገለፃል። ይሄን ሌሎች በዛ ያሉ ተውኔቶች ላይ አላየሁትም። ሊኮረጅ የሚገባ ፀዳ ያለ ልምድ ይመስለኛል። ከኛ ሀገር በዚ ሁኔታ ሊገለፅ የሚችል አንድ ስራ አይቻለሁ። እሱም የጋሽ ጸጋዬ ገብረመድህን “የከርሞ ሰው” ተውኔት ሲሆን እነ አባባ ተስፋዬ ሳህሉ በየትይንቱ መድረክ ላይ የተነሱት ፎቶ ህትመት ውስጥ ተካቷል። ይሄ መሆኑ ብዙ ጥቅም እንዳለው ይሰማኛል።
ለዛሬ የአብዬ መንግስቱ ለማ ያላቻ ጋብቻን ላንሳውማ… አማርኛውን አላገኘሁትም። ያገኘሁት በልሳነ እንግልጣር the marriage of unequals በሚል የታተመውን ነው። በቀላል አገላለፅ፣ የማህበረሰብን የቆየ ያረጀ ያፈጀ ልማድ በስታይል ለመናድ የሚጥር ተውኔት ነው። ቅለቱ ደሞ እጅግ ገዳይ ነው። ያው እንደ ርዕሱ "ያላቻ ጋብቻ" ላይ ያተኮረ ቢመስልም፣ የሚዳስሳቸው አጀንዳዎች ከሱ በእጅጉ ይልቃሉ።
ያው ተውኔቱ ወቅቱን መምሰል ስላለበት ያላቻ ጋብቻ የተለመደው አጥንት ቆጠራን መቃወም ነው። እሱን በወቅቱ የነበሩ ፀሃፊዎች አብዛኛዎቹ ብለውታል። እኔ ግን የገረመኝ በቀላል በሆነ መንገድ የተሰሩት ሌሎች ገፀባህሪያትም ጭምር ናቸው። ስማቸው ደግሞ ማንነታቸውንም ገላጭ ነው።
እስቲ ስማቸውን እና አንዳንድ ነገሮችን እንይ…
★(ባህሩ አዳሽነህ) የተባለ ውጪ ኢኮኖሚክስ ተምሮ የመጣ… እና ከከተማ ወጣ ብሎ ህፃናትን እና ጎልማሶችን ለማስተማር የወሰነ ትጉህ ሰው ነው… መድረሻውን ሐረር አካባቢ ያረገ ወጣ ያለ ሰውም ነው።
★ የሱን አቋም፣ ፍላጎት እንደ ዱብዕዳ ዱብ ብላ የምትፈታተን፣ አልጋነሽ ዱብዳ የተባለች የፊታውራሪ ልጅ ከበርቴ የሆነች አክስቱ አለች…
★ በለጤ የተሰኘች ስሁል አዕምሮ ያላት የባህሩ ሰራተኛ (ሰራተኛን በተለየ፣ በዚህ ሁኔታ መሳል ተውኔቱ ከነበረበት ወቅት አንፃር፣ እጅግ ቀድሞ ማሰብ ይመስለኛል)… ሰራተኞች እንዴት እንደሚሳሉ አናውቅም እንዴ? እናውቃለን እንጂ! :) :) :)
★ ቢቢታ ጋሻው በዛ በአክስቱ አማካኝነት ለባህሩ ለሚስትነት የምትታጭ የአጥንት እኩያው ነች። ቢቢታ ካልተሳሳትኩ በወቅቱ እንደነ ቲቲ ዘመነኛም ስያሜ ይመስለኛል። ለነገሩ ከሆነ አሁንም ቢቢታ ያው ኪኪም ነው : –)
★ አለቃ የተባሉ ቄስ እና አንድ ሐጂ– በሃገራችን ያለውን የሃይማኖት ተከባብሮ እና ተስማምቶ የመኖር ጥበብ በሚገባ የሚታይባቸው ሰዎች ናቸው። ተውኔቱ ኮሜዲ ዘውግ ነው ያለው። የነዚህ ሰዎች ሚና ደሞ ለዚህ እጅግ የላቅ አስተዋፅኦ ነበረው።
★★★ አባ ማሚቶ የተባለ ጠጠር ጣይ ጠንቋይ እና አንድ ደብተራ ልዝቡ የተሰኘ ኮከብ ቆጣሪ አሉ። ማህበረሰቡ በነዚህ ሁለት ተውሳኮች እንዴት እንደሚጭበረበር እጅግ ቀላል በሆነ መንገድ በተውኔቱ ይገለፃል። ማህበረሰቡ በሚኖርበት መንገድ ቀላል ምሳሌዎችን ተጠቅሞ እነዚህን ሁለት አጭበርባሪዎች ራቁታቸውን ማስቀረት እንደሚቻል ከዚህ ተውኔት የተሻለ ማሳያ ገጥሞኝ አያውቅም። ባልተወሳሰበ አቀራረብ የቀረበም ለማለት ፈልጌ ነው።
★ ማህበረሰብ መጥፎ ልማድ እንዳለው ሁሉ ጥሩም ልማድ አለው። በተውኔቱ መጥፎ ልማዶቹ ዘር ቆጥሮ መጋባት፣ አጉል እምነቶች ሲሆኑ… ጥሩ ልማድ ደሞ የሙስሊም እና የክርስቲያኑ ተከባብሮ መኖር እና በአፈርሳታ ባህላዊ መንገድ ችግር እንዴት እንደሚፈታ በጥልቀት ባያነሳውም፣ ምሳሌነቱን አንስቶት ያልፋል።
★ ሌሎችም ሌሎችም…
ከላይ የጠቀስኩት የቻይናዊው ተውኔት መሰረታዊ መነሻው የእታለም ቻይና ማህበረሰብ ነው። ቻይና ውስጥ ያ ደራሲው የተቸው ማህበረሰብ ወይም ስርዓቱ አሁን የለም። ይሄን ያልኩት ደራሲው በመግቢያው የፃፈውን አይቼ ነው። የኛ ማህበረሰብ ግን ቅርፁ ቢለይም ችግሩ አሁንም አለ። እናም አብዬ መንግስቱ ለማ ይሄንን ነገር ለመቀየር ባደረጉት ጥረት አሁንም ድረስ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል ብዬ ነው ወደዚህ ያመጣሁት።
በግሌ የውርስ ትርጉም ተውኔቶች ብዙም ደጋፊ አይደለሁም። የምርጫ ጉዳይ ነው። የግድ አስፈላጊ ነገርም ነው ብዬ አምናለሁ። ተውኔቶች ለሰዎች ከጊዜ ማሳለፊያነት በዘለለ ማህበረሰብን ቅርፅ ማስያዣነት ቢውሉ፣ ህፀፅ ቢያወጡ፣ መንገድ ቢያመላክቱ ብዙ እናተርፋለን ብዬ ነው የማስበው። ሌሎችን ተውኔቶች እየተቃወምኩ ግን አይደለም። እግረ መንገድ በስሱ ነክቼ ስሜቴን ለመግለፅ ነው።
ከዚህ በፊት ተመስገን ገብሬ ተመስገን ገብሬ ስል አንድ ጠንቋዮችን ለማጥፋት በታገለው ትግል መረጃ መሰረት ነበር። አሁንም የሚዳሰስ ነገር ባላገኝም ቅሉ። ከዚ በፊት የፃፍኩትን ተመልከቱ። እዚሁ ብሎግ ላይ አለ። ከዛ ቀጥሎ ይሄንን የጥንቆላ ነገር ሻከር አርጎ የነካልኝ ስራ ያገኘሁት ይሄን የአብዬ መንግስቱ ስራ ነው። ሌላ ካለ ትጠቁሙኝና በደስታ እጎበኘዋለሁ።
ሰዎች በጥንቆላ ዙሪያ ያላቸው አመለካከት ዛሬም ድረስ የተንሸዋረረ ነው ብዬ በፅኑ አምናለሁ። ከአዋቂ ሃይማኖት ሰባኪ እስከ ተራው ምዕመን ድረስ ማለቴ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰባኪ "ጠንቋይ ቤት የምትሄጂ ወዮልሽ!" የሚል መልህክት ሲያስተላልፍ… በውስጠ ታዋቂ "ጠንቋይ ቤት ብትሄጂ የምታገኚው ነገር አለ። ያ ግን ትክክል አይደለም" እያለ ነው። ይህ ፈፅሞ ስህተት የሆነ አመለካከት ይመስለኛል። ጠንቋይ ቤት በመሄድ የሚገኝ ምንም ነገር እንደሌለና ጠንቋይ በሙሉ አጭበርባሪ እንደሆነ ነበር በይፋ መሰበክ የነበረበት።
"ሰው የተፃፈለትን ነው የሚኖረው" የሚለው ትክክል ያልሆነ አስተምዕሮ የወለደው ስህትት ይመስለኛል ጥንቆላን የወለደው። ሰው የተፃፈለት ካለ የሚያነብም አይጠፋም በሚል እሳቤ ማለት ነው። በኔ በደረስኩበት ግንዛቤ ልክ (ጠንቋይ ማለት:– ካለው፣ በጊዜው ካለበት ማህበረሰብ ትንሽ ነቃ ያለ የማሰብ አቅም ያለውና ያንን ለክፉ የሚጠቀምበት ግለሰብ ማለት ነው። በዛ ላይ ስራውን በሚሰራ ሰዓት የሚጨመር ጫትም አለ። የሰዎችን የአመለካከት ችግር ተረድቶ ለግል ጥቅሙ የሚጠቀም ማለት ነው። ሌላ ምንም ትርጉም የለውም!)
የሰዎች እምነት ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ይመስለኛል። ለምሳሌ አንድ ጠንቋይ ማህበረሰቡን ሲያጭበረብር ቢገኝና ተይዞ ለህግ ቢቀርብ … የሰዉን አስተያየት ብትሰሙ ትገረማላቹ። ተመሳሳዩ አስተያየት የሚሆነው "ይሄ አጭበርባሪው ጠንቋይ እንጂ በርግጥ የእውነት ጠንቋዮች አሉ" የሚል ነው። ደጋግሜ ደጋግሜ ያየሁት ነው። ከምን የመጣ እንደሆነ ግልፅ ነው። ሰባኪዎች ትምርታቸውን ሲያርሙት ተከታዩም አብሮ ይስተካከላል የሚል የጠራ አቋም አለኝ።
በነገራቹ ላይ ከውጪ ሆኜ አይደለም የማወራው እኔ ሃይማኖት አለኝ። በሃይማኖቱም ከኔ የትየሌለ በዕውቀት የሚርቁ ሰዎችን ሃሳብ ለመስማት ሞክሬአለሁ። እስካሁን መልስ አላገኘሁም ግን። እንደውም አንድ ወዳጄ፣ በማስረጃ ሊያስደግፍልኝ አልቻለም እንጂ "በጥንቆላ ዙሪያ እንዳንተ አቋም ያላቸው አንድ ጳጳስ አሉ" ብሎኝ ነበር። የኔን አቋም ስደግመው "ጠንቋይ በሙሉ አጭበርባሪ ነው" የሚል ነው ሲያጥር።
"የእውነት ጠንቋይ ብለን የምናስበው አይነት በምድር ላይ አለ… እንደዚ እንደዚ ነው…" ብሎ ሊያስረዳኝ ለሚችል ሰው ልቤን ከፍቼ እጆቼን ዘርግቼ ነው የምጠብቀው። ጠንካራ የራሱ አሳማኝ ምክንያት ይኑረው እንጂ… የኔ እግሩ ስር ቁጭ ብዬ መማር ዕዳው ገብስ ነው። ቀጥሎ በምሳሌ እንደማነሳው ዓይነት (ሰው ተደግፎ የሚያወራ) አስተያየት ግን ፈፅሞ መስማት አልፈልግም። ለምሳሌ "የሆነ ጊዜ ላይ አንድ ጠንቋይ አጎቴን ቀይ፣ ወፍራም ሚስት ታገባለህ ብሎት ያገባውም ቀይ ወፍራም ሚስት ነው ስለዚህ ጠንቋይ የእውነት አለ" የሚል ሃሳብ ያለው በቀይ ወፍራም የአጎቱ ሚስት ይዤዋለሁ አስተያየት እንዳይሰጠኝ።
ይሄን ሃሳቤን በደፈናው ልፃፍ ብዬ የፃፍኩት አይደለም። ብዙ ዓመት ያሰብኩት… ብዙ ያገላበጥኩበት፣ ሌላ ርቀትም ጭምር የሄድኩበት ጉዳይ ነው። ቀለል አርጌ ስላቀረብኩት ለድምዳሜ እንዳትቸኩሉብኝ። የሆነ መለወጥ አለባቸው ከምላቸው ሃገሪቱን ወደኋላ ከሚስቡ ጉዳዮች ውስጥ "ዋነኛው ነው" ብዬ ስለማስብ ነው። እንደ መክፈቻ ሃሳብ ነው ጣል ያረኩት። ሃሳቤን የሚያጠነክርም ሃሳቤን እንድፈትሽ የሚገፋም ሌላ ሃሳብ ካገኘው በሚል ተስፋም ጭምር ነው። ለኔ ሁለቱም ዓይነት ሃሳብ እኩል ነው።
Strange but true የሚል ፊልም ሳይ ትዝ አልከኝ። ከየትኛው ፅሁፍህ ጋር እንደሚገናኝ ለማስታወስ ብዬ በድጋሚ ብዙ አነበብኩህ። ምን እንደገረመኝ ታውቃለህ ሁሉም ፅሁፍ አዲስም ግልፅም ሆነልኝ። ከአድናቂ ወደ ከዳሚ ልትቀይረኝ ባልሆነ? ብቻ ፊልሙን እየውና ምን ያህል አንደርስታንድ እንደማደርግህ ትረዳኛለህ። ተጋብዘሃል።
ReplyDeleteሲመስለኝ ፊልም ለማየትም ፊልም ማየት ያስፈልጋል። እናም በተለያዩ ምክንያቶች ፊልም እያየሁ ስላልነበር ፍላጎቱ አልነበረኝም። ጊዜው ከፍላጎት ተነስቶ የሚፈጠር ነው ብዬ ነው። ሳልዋሽ ስነግርህ በወሬ መሃል ቢሆን ይሄን ያነሳኧው ላሽ ነበር የምልህ።
Deleteየአንተ ቦታ አሰካክ ምርጫ እንዳይኖረኝ ነው ያደረከኝ። አስገደድኧኝ ሃሃሃ
ፊልሙን ጀመርኩት። እንኳን የአንተ ሁኔታ ተጨምሮበት አይደለም እያንዳንዱ ዲያሎግ የተለየ ትኩረት ይፈልግ ነበር። የሆነ ክፍል ካመለጠህ አጠቃላይ ፊልሙን ሚስ እንደምታረገው ግልፅ ነው። ከግማሽ በኋላ ግን ፊልሙ ሊያልቅበት ይችላል ባልኩት መንገድ ሄጄ “አንደርስታንድ አርጎኝ ሞቷል” ብዬ በሆዴ አምቼህ ነበር። ኑዛዜ ነው ሃሃሃሃ
ፊልሙ ሲያልቅ፣ ፈፅሞ ፈፅሞ ፈፅሞ ባላሰብኩት መንገድ ፊልሙ ሲያልቅ፣ ተገርሜ ተገርሜ ተገርሜ የአንተን አስተያየት ማሰብ ጀመርኩ።
በህይወቴ ደስ ከሚሉኝ ነገሮች መሃል ሰዎች ሲገቡኝ እና እንደምገባቸው ሲሰማኝ ማሰብ አንዱ ነው። በጣም ነው ደስ የሚለኝ። እና ከፊልሙ ተነስቼ ሳስብህ፣ አስተያየት ካሰፈርክበት ፅሁፍ ጋር…. አንደርስታንድ ብቻ አይደለም ያረከኝ እኔን ሆነህ ነው ያሰብከው። ምን ያህል እንደደነቀኝ አጠይቀኝ…
እናም በዚህ በጀመርኩት ርዕስ የሚገጥምህን፣ የሚሰማህን፣ የምትደርስበትን አካፍለኝ ስልህ ከመሬት ተነጥፌ ነው። ላመሰግንህ ቃል አጣሁ። በሆነ ጉዳይ ደፍረህ አግዘኝ የምትለው ሰው ማግኘት የሚሰጠው ስሜት ተሰምቶህ ያውቃል? ያ ነው የተሰማኝ። ሌላ ማለት አልችልም።
የሆነ አድራሻህ እንዲኖረኝም የግድ እፈልጋለሁ። ኢሜይል አርግልኝ። ቀጥታም ኢሜይሌ ይኖርህ ዘንድ ወደድሁ natidanhaile@gmail.com
“ተገርሜ” አለ አቤል ሙሉጌታ በአፈጣጠሩ ሃሃሃ አንተ እኔ ምን እንደገረመኝ ታውቃለህ። አጃኢብ ነው በቃኝ።