Advertisement
"በአንቺ ጫማ ቆሜያለሁ ህመምሽ ይገባኛል!" አልልሽም። ማናችንም የማናችንም ህመም አይገባንም። እንዲገባኝ ግን ጥሬያለሁ ማለት እችላለሁ። እናም ይሄን ልልሽ ወደድሁ…
ያዘንሽበት፣ የተጨነቅሽበት፣ የሰበረሽ ነገር የማይመስል የማይመስል ቢመስልሽ እንኳ ሁሉም ሊያልፍ ነው የመጣው። በርግጥ ቦታው ላይ ስላለሽ ይሄ አባባል ፌዝ ሊመስልሽ ይችላል። ግን ካልተሸነፍሽለት ሁሉም ፈተና አንቺን ሊቀይር ነው የሚመጣው። ዛሬ ግን ልክ ነው ላይመስልሽ ይችላል። አልፎ ስታዪው ነው የሚገለፅልሽ። ከአንቺ የባሰ መዓት ውስጥ ያሉ፣ መዓቱንም አልፈው እንደ ታሪክ የሚያወሩ እልፍ ናቸው። እዚጋ ያንቺን እንዳላቀለልኩት በጥረቴ ልክ ትረጃለሽ ብዬ አስባለሁ። በህይወት ያልተፈተነ የማይፈተን የለም። ትንሽዬ ተስፋ፣ ትንሽዬ "ለበጎ ነው" ነገ ድንኳን ትሰራለች። ነገሽን ታደምቃለች።
ዓለም ክፋቷ ስናዝን እኛ ብቻችንን ያዘንን አስመስላ… ስንደሰት ደግሞ ሁሉም የሚደሰት ታስመስላለች። ሐዘናችንን የሚጋራ እንዳለ ማሰቡ ክፋት መመኘት አይደለም። ተስፋም አለው ውስጡ። እሱ ሐዘን ተጋሪዬ እንዴት አለፈው? እንዴት ያልፈው ይሆን? የሚል ጥያቄ እንድንጠይቅ ይገፋፋናል። ጥያቄው ደግሞ ውስጡ ጥቂት ተስፋን ይፈጥርብናል። አብቅቶልኛል፣ አለም ተደፍቶብኛል ከሚል ወደ (እንዴት ልለፈው?) ወደሚል ጥያቄ መሸጋገር፣ ትንሽ የተስፋ ድልድይ መገንባት ነው። ተስፋ ደግሞ ያኖራል። ተስፋ ጉልበት ይሆናል። ተስፋ መንገድ ያሳያል።
ተፈጥሮ ለሁሉ እኩል ናት። ሁሉንም በአቅሙ በልኩ ትፈትናለች። በልኩ ነው ያልኩት። ስጦታም አላት። ወድቀው የተነሱ ወድቀው ካላወቁ የበለጠ ስለ መንገዳቸው ደስታ አላቸው። እናም "ይሄ ሊያልፍ ይችላል እንዴ?" ብሎ ጥቂት ማሰብ ትርጉሙ ብዙ ነው። ውስጥሽ የሆነ ነገር ይለውጣል። መነቃቃትንም ይሰጥሻል።
ከዛ "ይሄ ሊያልፍ ይችላል እንዴ?" ከሚል መነሻ "ይሄ እንዴት ሊያልፍ ይችላል?" ወደሚል ከፍታ ያድጋል ጥያቄው። ከዛ የሚሆነውን አታውቂም። ህመምሽ ተረስቶ መልስ ፍለጋ ላይ ራስሽን ታገኚዋለሽ። ተስፋሽ እያደገ መንፈስሽ እየጠነከረ ሲመጣ ተፈጥሮም ምላሿ እየተቀየረ ይመጣል። መልሱን ሁሉ ባልጠበቅሽው መንገድ በትክክለኛው ሰዓት ትልክልሻለች። መጀመሪያ ግን ፍለጋ ወጪ አንቺው ነሽ። ያለ ራስ ሰራ፣ ያለ ራስ ጥረት ምንም የለም። "ሁሉም ያልፋል" የሚል ጦር ስለሽ የምትወጪው መጀመሪያ አንቺው ነሽ። ተፈጥሮ ደግሞ ይሄን ልታግዝሽ ሕግ ያስገድዳታል። ሁላችን የምንተሳሰርበት የሁሉ ማሰሪያ የሆነው የፍቅር ሕግ የረቂቅነቱ ነፀብራቅ እዚጋ ነው። ተስፋ ላለው ይጨመርለታል። የሌለውም ራሱ ይወሰዳል ነው ነገሩ። ተስፋ ግን ለመፈጠር ትንሽዬ ቡጥቆ ነገር ይበቃዋል። ጨለማ ውስጥ ለቆየ የስልክ ስክሪን መብራት ፓውዛው ነው።
ሁሉ አይወራም። ቤቲ ጂ አንድ ገራሚ ዘፈን አላት። "ነገ አልፎ ተረት ሆኖ ሊያስቅህ፣ ተወው ለበጎ ይለፍህ… ካንተ አይበልጥም" ምናምን አይነት። ችግር ውስጥ ስትሆኚ ሁሌ ስሚውማ የህይወትሽን ቃና ይለውጠዋል። ዛሬን በነገ ዓይን የምታዪበት መነፅር ያላብስሻል። የዛሬው ችግርሽ ነገ አልፎ ሲያስቅሽ ማሰብ በራሱ ዘና ያረጋል። በወቅቱ ላይመስልሽ ቢችል እንኳ ተስፋ ይጭራል። ያ ደግሞ እጅግ መልካም ነው። ብቻ የቆምሽ አንቺ፣ የምቅወድቂም አንቺ ነሽ። ፈተናው ሁሉ ጎብኝቶሽ አላፊ እንጂ አንቺ አይደለም። ሁሉም እንዳመጣጡ ያልፋል። እንደሚያልፍ ማወቁ ራሱ መንገድ ይጠርጋል። ብቻ አንቺ ጥቂት ደፈር ብለሽ "እንዴት ያልፋል?" ብቻ በይ። መልሱን ራስሽ ታገኝዋለሽ። ይህ ካልሆነለሽም እጅግ ለሚወድሽ ጠጋ በይና "ይሄን እንዴት ልለፈው?" በይው። ከባድ ነው አውቃለሁ ግን አንድ መንገድ ነው። እናም ከሁለቱ አያልፍም ችግርሽ። ሃይማኖት ካለሽ ከኛ በላይ ተፈጥሮን አቀናብሮ የሰደረ መልስ ይሰጥሻልና ቀና በይ። አንደ ማመንሽ ልክ ትግልሽን ያቀለዋል። ሃይማኖት ከሌለሽም በአቅምሽ ልክ ታገይ። እግዜሩም ያግዝሻል ብዬ አስባለሁ።
ዛሬ የትላንት ጨለማቸውን ያለፉ በትላንታቸው ይስቃሉ። ዛሬ ፈተናቸውን ቢያስታውሷቸው "ፍፁም በህይወታቸን ያልተከሰተ" ብለው ሊሸመጥጡ ይችላሉ። ዛሬ ያን የማያልፍ የሚመስለውን ጊዜ አልፈው ህይወትን እያጣጣሟት ነው። ግን ህይወት ከዛ በኋላ እስከዘለዓለም በሰላም ኖሩ አይነት መዝጊያ የላትም። ሌላ ፈተና ሌላ ሽልማት ሌላ ፈተና ሌላ ሽልማት ነው ቅጥልጥሏ። አንዴ ከገባችሽ ፈተናዋን አትፈሪም። ያም አልፏል። የሚመጣውም ያልፋል። አባቶቻችን እናቶቻችን በዚህ ውስጥ ያለፉ ናቸው። የዘንድሮ ልጆች ትቸኩላላችሁ… ይላሉ ለአስተያየት ቸኩለው። ያወቁትን አውቀው ነው።
እናም አፅናኝ፣ ተስፋ ያለው ቃል አንዳንዴ ጠቃሚ ነውና… ይሄን ልልሽ ስለወደድሁ ነው። ላያልፍ የሚመጣ ምንም የለም። ብዙ ስቃይ ብዙ ህመም ጎብኝቷቸው ያለፉ የህይወት ጣዕም ይገባቸዋል። አንዳንዴ ህይወት ምላሧን የምታወጣብን ፈትናን እንድንቀምሳት ልታረገን ነው። ያለ መራራነት ጣፋጭነት የለም። ያለ ማልቀስ መሳቅ የለም። ተለቅሶ ከሳቁ በኋላ የሚለቀሰው ለቅሶ እንኳ ውስጡ ትንሽዬ ሳቅ አለው። እንደመጀመሪያው አይሆንም። እድሜ ሲጨምር የሚገለጥ ነገር ነው ይሄ። ህይወት ብዙ ጊዜ እንደዚህ ነች። እኛ ላይ ብቻ የጨከነች የሚመስለን ጊዜ አለ። ግን ሚስጥሯን ስለማትነግረን እንጂ… ህይወት ማንም ላይ ጨክና አታውቅም። ብቻ ስለሚመስለን ነው። እና ሁሉም ሊያልፍ የሚመጣ ነው። ልኩን ታግሎ መጣል የሚያቅተው ተጠያቂው ራሱ ነው። ጥቂት ትግል ቡዙ ነገ… ብዙ የሚያስቅ ትላንት ውስጥ ነው ህይወት የተዋቀረችው። ይህ ለማንም አይቀርም። እናም እንደዚህ ነው።
አንድ ነገር ሞከርሽ ቶሎ ተሳካልሽ… ሰዎች አጃዪብ ነው አሉ፤ አወደሱሽ። ከዛም ህይወት ፈተነችሽና ወደ ነበርሽበት ተመለስሽ። ልብ ካልሺኝ…ሞክረሽ የተመለሽበትን ጉዳይ እንደ አጀንዳ እንኳ አላየሁትም። "እንዴት ተመለሰች?" የሚለው ጉዳይ እንደሚያሳፍርሽ አውቃለሁ። ቀጥ ብሎ የሚሄድ መሳዩ ሁሉ ደጋግሞ ሞክሮ ደጋግሞ ወድቆ ነው እዚህ የደረሰው። ሰዎች የሚያሳዩሽን ብቻ አይደሉም። የአንቺን መንገድ ብዙ የሄደው ሰው ሲነግርሽ… ብዙ በላይ በላዩ ወድቆ ነው ቀጥ ብሎ መጓዝ የለመደው። እሱ ጉዳይ ተራ ነገር ነው ልልሽ ነው። ወደማትፈልጊው ህይወት እንድትመለሽ ሰበብ የሆነሽ ጉዳይ ላይ አተኩሪ። አንዴ የቻልሺው ጉዳይን ደግመሽ ስትቺይው ወደፊት ላለመውደቅ በሁለት ይባዛልና ተራ ጉዳይ ነው ብለሽ እለፊው። እያበረታታሁሽ ግን አይደለም (እዚጋ ግን ትንሽ ፈገግ ብያለሁ)
እናም ብቻችንን ልንሆንባቸው የሚገቡ ጊዜያት እንዳሉ ባምንም ሲበዛ ግን ይታወቀናልና ብቅ በይ ለማለት ነው። "ፀሃይ ሁሌም ብርሃኗን ያለማቋረጥ ትሰጠናለች። ሁሌ ከፀሃይ ጋር አብሬ መነሳት ደስ ይለኛል!" ትይ አይደለ? "እኔ የጨለማው አይደለሁም!" ትይም አይደለ? … ፀሃይ እኮ አትተኛም ባለማለቴ እስካሁን ይፀፅተኛል ለማለት ፈልጌ ነው… ፈገግ ልበል ደግሜ? እሺ ፈገግ ብያለሁ…
ባለሽበት ሆነሽ አንዴ ፈገግ በይማ… ፈገግ ጎበዝ… እኔም ፈገግ ብያለሁ… አልነገሩሽም እንጂ አንቺ ራስሽ ፀሃያቸው የሆንሽላቸው ብዙ አሉ እኮ… "ፀሃይ ውጪ ውጪ… " የጂጂ ዘፈን ነው።
Eriy
ReplyDelete