Komentar baru

Advertisement

ሱቃቴዋ

Eriyot Alemu
May 16, 2022
Last Updated 2023-08-02T03:52:28Z
Advertisement






ችግራችን እንደ መልካችን ብዙ ነው። ለአንዳንዶቻችን የአንዳንዳችን ችግር ምንማችንም ነው። ለምሳሌ እኔ የሰናይትን "ሱቃቴ" መሆን ከቁብ ቆጥሬው አላውቅም ነበር። ስሜቱንም ላውቀውም ልገምተውም ስለማልችል አይሞቀኝም አይበርደኝም። ሱቃቴ ማለት ዕቃ የመሸመት ሱስ ያለበት ማለት መሰለኝ። shopaholic እንደማለት ነገር። ሱቃቴ የሚለው አማርኛ ቃል ሲሆን ሱቅ እና ኣቴ ሲገናኙ የተፈጠረ ነው። የአለቃ መዝገቡ ተገኘ ሙዳየ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይፈታዋል… 

{ሱቃቴ– በሆነውም ባልሆነውም ሱቅ የሚሮጥ ሰው ሲሆን ያንን ካላደረገ ደግሞ የመረበሽ ስሜት ውስጥ የሚዘፈቅ ነው}

ሰናይት ሱቃቴ ነች። ባሏ ደሞ ጓደኛዬ ነው። የሴቶችን የሸመታ ባህሪ ብዙ ጊዜ ወንዶች ሲያማርሩ ስለምሰማ የሰናይትም እንደዛ ይመስለኝ ነበር። ሆኖም ትዳራቸውን እስከማፍረስ የሚደርስ ችግር መሆኑን ስረዳ ነው እጢዬ ዱብ ያለው። በርግጥ ዱብ አላለም። እና ገረመኝና ሰናይትን ላናግራት ሄድኩ። 

<<ሰኒዬ በናትሽ እንዴት እንዴት ነው የሚያረግሽ? እስቲ ብትንትን አድርጊልኝ… ዕቃ ካልገዛሽ ያዘልልሻል ወይ? ከውስጥ ከሆድሽ አምጪ አምጪ ግዢ ግዢ የሚል ስሜት አለው ወይ? … መግዛት ካልቻልሽስ እንዴት ነው የሚያደርግሽ?… እግርሽን ታቅፈሽ ስቅስቅ ብለሽ ታለቅሺያለሽ ወይ?… ስሜቱን ላጣጥመው እስቲ በተን በተን አድርጊልኝ>> 

<<አትቀልድ በሚስትህ ሊደርስ ይችላል… ገና አንተ አግብተህ ያልጨረስክ ሰው ነህና ተጠንቀቅ>> አለቺኝ። ወልደህ ያልጨረስክ ነህና በልጅ ይደርሳል አትሳቅ እንደሚሉት መሆኑ ነው። የሱቃቴዎች አንደኛ መገለጫ ተረት አጣመው መጠቀማቸው ይሆንን? ምናልባት በሱቅ በኩል ሲያልፉ፣ ሱቁን በፍቅር እስከሚጣመሙ ድረስ አይተውት ስለሚያልፉስ ይሆንን? … "መልስ የለም መልስ የለም" አለ ገጣሚው ቢጨንቀው። ምናልባት የሱም ሚስቱ ሱቃቴ ትሆናለች። 

 <<ሰኒዬ 46 ጫማዎች ናቸው እንዴ ያሉሽ?>> 
 <<ምን ይገርማል? ሐመልማል አባተም ከዛ በላይ አላት!>> 
 <<ምንም አይገርምም አንቺማ ድሮም ጥሩ ሰው ነሽ። አሉ እንጂ የሃገራቸው ሰው እያለላቸው የነ ቢዮንሴን የነ ሪሃናን ግልገል ሱሪ ጭምር የሚቆጥሩ። ሐመልማል "ጅምሬ የፍቅርን ሀሁ የቆጠርኩብህ" ለሚለው ልብ አቅላጭ ዘፈኗ ብቻ!… አይደለም ጫማዋ ሺቲዋ ቢቆጠርም ቅር አልሰኝም። በእውነት ዘሪቱ ያላትን ጫማ ብዛት አለማወቄ ግን ቆጭቶኛል። ድሮም የማረባ ሰው ነኝ። እኔን ብሎ አድናቂ! አስቱካስ ብትይ 26 ምናምን እያሉ አልበሟን ከመቁጠር……… ተይው ብቻ ማድነቅስ እንዳንቺ! ነው>> 

<<ወዳጄ ሙድ ልትይዝ ነው እንዴ የመጣኸው?… ጥሩ ሙድ ላይ እንዳልሆንኩ እያወክ>> 
<<አይደለም ሰኒዬ ለጨዋታው ድምቀት ነው። ጓደኛችን አልፎ አልፎ እንደ ቀልድ ሲያወራ እንጂ እዚ ደረጃ የደረሰ አልመሰለኝም>> 
<<ወድጄ እኮ አይደለም። ለመተው ያላረኩት ጥረት የለም። በተጨነኩ ቁጥር ደግሞ እየባሰ መጣ እንጂ መቀነስ አልቻልኩም። በቃ እሱ ይጠጣል እኔ ደሞ እሸምታለሁ። ሱስ ሆኖብኛል። እንደዛ ካላደረኩ ባዶነት ይሰማኛል። ለዛ ደግሞ ብዙ ገንዘብ ያስፈልገኛል። እሱ ደግሞ የባሰ እያስጨነቀኝ ነው። … ጓደኛህ ደግሞ የራሱ ችግር አይታየውም። ቆይ አትጠጣ ብለው ይተዋል?>> 

<<አሁን በቃ ፈታ በይና ቀስ ብለን መፍትሄ እንፈልግለታለን። የሚገርምሽ አለማችን ላይ ያልተለመደ ችግር ዕድልም ጭምር እየሆነ ነው። ፊለፊት ትወጪና "እኔ ሱቃቴ ነኝ! እናንተስ?" ትያለሽ እንደ ሬድዮ ፕሮግራም። ከዛ "እኔም እኔም ሲገርም ሲገርም" እየተባባሉ ተግተልትለው ይመጡልሻል። ያኔ ሰብሰብ ብላችሁ የሱቃቴ ማህበር አቋቁማችሁ ርስ በራስ መረዳዳት ነው። ከዛ ልምድ የሚሸጥበት ዘመን ላይ ስለሆንን… ልምዳቹን መቸብቸብ ነው>> 

 <<አይ አንተ ይሄ ተስፋህ እኮ ነው የሚገርመኝ>> 
<<"ያው ተስፋሽ ነው እንጂ ፊቴን የሚያወዛው" የሚለውን ዘፈን ራሴን ጋብዤዋለሁ። ስቀልድ እንዳይመስልሽ ያልተለመደ በሽታ አሪፍ ቢዝነስ ነው። እንዳንቺ አንድ shopaholic ነበረች። sophie kinsella ትባላለች። the shopaholic series የሆኑ 10 መፅሃፍት ፅፍለች። ከሁለት መፅሃፏ ተውጣጥቶ confessions of a shopaholic የሚል ፊልም ተሰርቶበታል። እግዜር ያሳይሽ በአንድ ርዕስ 10 ልቦለድ መፃፍ እልል ያለ ቢዝነስ ነው። ሱቃቴዋ፣ ሱቃቴዋና እህቷ፣ ሱቃቴዋና የአጎቴ ልጅ እያሉ መቀጠል ነው። አንቺ ብቻ የሱቃቴ ህይወትሽን ማስታወሻ ያዢ እንጂ ልቦለዱ ነገ ይደርሳል። "ሱቃቴነቴና የባሌ እርምጃ" ትይዋለሽ ርዕሱን በአገርኛ። በዕውቀቱ ስዩም ወዶ ይመስልሻል… እንዲህ ብሎ የገጠመው። 
"የሌሊት ወፍ ሲሆን ሸማቹ በሙላ 
ጨለማህን ሽጠህ እንጀራህን ብላ" 
ሰኒዬ አትሞኚ ነገ ታመሰግኚኛለሽ። ሱቃቴ መሆን ጨለማሽ ነው። ጥሩ አድርገሽ ከዘገብሺው መሰል እህቶችሽ ይሸምቱታል። እንደዚ አይነት ጠንካራ ግብ ይዘሽ "ሱቃቴነት በቃኝ!" ብለሽ ከተነሳሽ ደግሞ ምንም አያቆምሽም። ጥሩ ሰው ስለሆንሽ ጨለማሽን ብቻ አትሸጪም… መፍትሄውን ደግሞ ቀጥለሽ ትሸጫለሽ። አይመስልሽም ሰኑ?>> 

ፊቷ ፈክቷል። አይኗ ዕንባ አቅርሯል። እጆቿ ሊያቅፉኝ ተዘርግተዋል። ተንደርድሬ ሄጄ ታቀፍኩላት። ትንፋሿን ሰብሰብ አድርጋ… የሚከተለውን ተናገረች። 
<<አመሰግናለሁ ወዳጄ! ተስፋህን ያለምልመውና… አስበኸዋል?! አንተ ያልከውን ቢዝነስ እያጧጧፍኩ ተረጋግቼ ሱቃቴ ስሆን?>> 
ማልቀስ ይኑርብኝ መሳቅ ይኑርብኝ አላወኩም። አንድ ነገር ግን በልቤ ብያለሁ…
 
<< እውነትም ይሄ ሱቃቴነት የእውነት ሲሪየስ ሲሪየስ ችግር ነው!>>
iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

Leave Your Comment

Post a Comment

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement