Advertisement
(፩)
"አራትመቶ ፍቅር
ሶስት መቶ ብርጭቆ
ከፊቴ ታጭቆ"
የሚል ማንጎራጎር ሰማሁ። ፍሬው ተመስገን ነው። ብዙ ጊዜ እንደዚህ ያደርገዋል… ሌላ ሰው መጠጥ ቤት ውስጥ እያለ ፈፅሞ ትንፍሽ አይልም። ሁሉም ጥርግርግ ሲሉና እኔና ባለግሮሰሪው ብቻ ስንቀር ግን ማውራት ይጀምራል… ምናልባት የሚሰክርበት ሰዓት ስለሆነም ይሆናል፤ አላውቅም።
ጨዋታ ሊጀምርልኝ ነው…አንዳንዴ ያነበቡትን ከሚነግሩኝ ይልቅ የኖሩትን ለሚያወጉኝ ሰዎች በደንብ እወጋላቸዋለሁ። ፍሬው ደሞ የካበተ የኑሮ ልምድ ካላቸው ውስጥ አንዱ ነው። በዛ ላይ ያነባል። ፊለፊት ስለሚናገር ብዙ ሰው አይወደውም… ግን ውሸት አውርቶ አያውቅም።
"ደስተኛ ህይወት እንዲኖርህ ከፈለክ… ራስህን ከማንም ሰው ጋር አታወዳድር፣ ከራስህም ጋር ቢሆን" አለኝ ግንባሬን መታ መታ እያረገ… ይሄን ልማድ ከየት እንዳመጣው አላውቅም። ቁምነገር ሊነግረኝ እንዳሰበ ስጠረጥር ግንባሬን አስጠጋለታለሁ… እሱም መታ መታ ያደርገውና ይቀጥላል።
"ፍቅረኛ ሲኖረኝ፣ ሳገባ፣ ቤተሰብ ስመሰርት ደስተኛ እሆናለሁ ብለህ የምታስብ ከሆነም ተሸልቅቀሃል… የደስታ ምንጬ ቤተሰቤ ብላ ብላ ቅብጥርሴ እያለ የሚደሰኩር ሰው ከገጠመህም ሌባ በለው…"
ባለ ግሮሰሪው ጆሮውን ቀሰረ…
"መጀመሪያ ራስህን በደንብ እወቅ… የሚያስደስቱህን ነገሮች ለይ። ሰዎች በተፈጥሮ ይለያያሉ። በርድስ ኦፍ ዘ ሴም ፊዘር ብላ ብላ ብላ ልልህ አደለም። ሳይንስ ነው የማወራህ። ጥቁር ነጭ ሴት ወንድ እያሉ የከፋፈሉ ሰዎች የእውነት ደነዞች ነበሩ። እናት ተፈጥሮ ሰዎችን የእውነት የምትከፋፍልበት ጥበብ አላት… የሚያሳዝነው አለም አሁንም እየተሾፈረች ያለችው በ20ኛው ክፍለዘመን በነበሩ ፂማም ሰዎች አስተሳሰብ ነው" ባለ ግሮሰሪው ሰለቸው፤ ፊቱን አዞረ።
"ለምን ሚስቴን እንዳገባኋት ታውቃለህ?" አንገቴን በማነቃነቅ አላውቅም አልኩት።
ባለ ግሮሰሪው መልሶ ጆሮውን ቀሰረ…
"እኔ ልቀየርበት የማልችለውን የህይወት ክፍል… የሚስቴ ተፈጥሮ ሊረዳው ስለቻለ ነው። እንዲሁ ታውቀኛለች። ስለዚህ ተጋባን…"
ሚስቱን አንድ ቀን አይቻታለሁ። ጎበዝ አስተናጋጅ ነበረች። በትምህርት የመግፋት እድሉ አልነበራትም። ግን "ማንበብና መፃፍ ዋናው ቁምነገር" እንዲል ፀሃዬ ዮሐንስ ራሷን ለማበልፀግ በቂዋ ነበር። ፍሬው ደሞ ሌላ ነው። እጅግ የተማረ፣ የተመራመረ ኮሌጅን ደጋግሞ የበጣጠሰ ሰው ነው።
"በተገናኘን በሶስተኛው ቀን ነበር የአንድ አለም ሰዎች መሆናችንን ያወኩት። በጊዜ… እጅግ በጊዜ። ያኔ የማርውሃም የተፀነሰችበት ቀን ነው … ሁለታችንን ያሰረች ግድግዳችን ነች–ዓለሜ የማርውሃ… ሁለታችንም የግል ህልሞቻችንን የምንፅፍባት ግድግዳ… በኔ ቅርፅ የሷ ፊት ፊቷ ላይ ታትሟል… ያኔ ነው ሚስቴንም እኔንም ያየሁት… በቅርፅ ውስጥ ማንነት እንዳለ የገባኝ ራሴን በልጄ ውስጥ ካየሁ በኋላ ነው… አያቴ ‘ያንተ አይነት ጆሮ፣ ያንተ አይነት ግንባር ያላቸው ሰዎች…’ እያለች ስለ ኮመን ባህሪ ስታወራ አልሰማትም ነበር። ከማየት፣ ከማስተዋል የደረሰችበትን ዕውቀት ድንቁርናዬ ጋርዶት ነበር… " ዓይኑ ዕንባ አቅሯል። ለሽንት ተነሳ። ባለግሮሰሪውን ዞሬ አየሁት። በአይኑ እየተማፀነኝ ነው። አስጨርሰው እያለኝ ነው። ምኑ እንደሳበው ግን አልገባኝም።
"አስበኸዋል ደስታ መለኪያ ቢኖረው? አራት ደስ ይበል… አምስት ደስ ይበል… ስምንት ዴሲበል አይነት ነገር…" ፈገግ አለ። ፈገግ አልኩ።
"ስሸና ሃሳቤን እሰበስባለሁ … ቀድሞ የበታተንኩትን… ደስተኛ የሆነች ሴት ራሷን ያወቀች ሴት ናት። ራሷን ያወቀች ሴት ምርጫዋን ታውቃለች። ብዥታ፣ ውዥንብር ውስጥ ብትሆን እንኳ ምርጫዋ ከሆንክ ታውቅሃለች። ወንድ ይሄድባታል እንጂ መራጯ ሴቷ ነች። ይሄን ስልጣን የሰጠቻት እናት ተፈጥሮ ነች… ይሄ የገባኝ ዘግይቶ ነው–እጅግ ከረፈደ…" ሲጋራውን ለኮሰ። ከዚህ በኋላ እንደማያወራኝ አውቃለሁ። ግማሽ ድረስ ያጨስና በብርጭቆ ቂጥ ይገርዘዋል። መልሶ ቆይቶ የተረፈውን ያጨሰዋል። በዚህ ሂደት ምንም አያወራም። አንድ ቀን ነው፣ እጅግ ተመስጬ እያየሁት እያለ "የተገረዘ ሲጋራ ሽታው ደስ ይለኛል" ሲል የሰማሁት። ከዛ ወደ ረዥም ዝሙ ተመለሰ።
ሌላ ቦታ ሰው ቢፈራውም የሚያስተምርበት ኮሌጅ እጅግ የተወደደ አስተማሪ ነው። "ለተማሪዎቼ ስለ ልጅነታቸው የሚያወሩበት ሰዓት ስለምሰጣቸው ነው" ይላል ብዙ ጊዜ። ሰዎችን ጥሩም ሆነ መጥፎ ልጅነታቸው ውስጥ ማመላለስ ይወዳል።
(፪)
Childhood Disrupted: How Your Biography Becomes Your Biology, and How You Can Heal የሚል መፅሃፍ እጁ ላይ ብዙ ቆይቷል። እንደዚህ አይነት ወጣ ያሉ መፅሃፎች አነፍንፎ ነው የሚያገኘው። አዲስ ሃሳብ እንደሱ የሚወድ ሰው ገጥሞኝ አያውቅም። ከአዲስ ሃሳብ ቀጥሎ ስለ አዲስ ሃሳብ ሰዎች የሚሰጡት አስተያየት የመጨረሻ ይማርከዋል።
መፅሃፉን እንዳነበው የሰጠኝ ለአስየያየቴ ብሎ ነው። ካነበብኩት በኋላ "ትንሽ መፅሃፉ ላይ በሚጠቀሱት ኤክስፐርቶች መተማመኗ እጅግ በዛ እንጂ መፅሃፉ አያሌ ነጥብ የሚያነሱ ግዙፍ ሃሳቦች ያዘለ ነው። ርዕሱ ደምዳሚነት የተጫነው መስሎኝ ነበር ስጀምረው… ውስጡ ስገባ ትንሽ ሃሳቤን አስቀይሮኛል። ሂሊንግ ፓርቱ ተመሳሳይ የተለመደው ዓይነት የሰልፍ ኸልፕ ይዘት እንደተጫነው ቢሰማኝም ፅቡቅ ፅቡቅ ሃሳቦችም አሉበት" ስለው ግንባሬን መታ መታ አደረገና "ደግመህ እንደምትፈልገው ስለሆነ ውሰደው፤ እኔ ሌላ አገኛለሁ።" አለኝ። ልክ ነበር ደግሜ ደጋግሜ እፈልገው ነበር።
ፍትህ መፅሄት ላይ የብርሃኑ ደቦጭን መፅሃፍ ዳሰሳ በፍቅር ነበር የሚያነበው። አንድ ቀን ይሄን አለኝ "ጥሩ ሃያሲ ያላነበብኩትን መፅሃፍ እንዳነበብኩት አድርጎ የሚሄስልኝና መፅሃፉን እንድገዛው የሚያስገድደኝ ነው። ሁለተኛ አዲስ ሃሳብ ይዘው የሚመጡ ሰዎችን የነሱን ሃሳብ በአንድ ቋት የራሱን በራሱ ቋት አድርጎ በነፃነት ሃሳብ የሚሰጥ ግለሰብ ነው"
በስራ ቦታው እጅግ የተወደደ መምህር የመሆኑን ያህል ብዙ ጠላቶችም አፍርቷል። "ለምን በተማሪዎቹ ዘንድ ተወደደ? ለምን በለጠን?" የሚሉ ናቸው ጠላቶቹ መደባቸው። ፍሬው ችግሩ የመጣው ከልጅነታቸው ነው ብሎ ያምናል።
አንዴ ስናወራ በወሬ መሃል ይሄን አለኝ።
"ራሴን ከማንም ጋር አወዳድሬ አላውቅም። በልጅነቴ የገባኝ እውነት ነው። አንዳንዴ ስለራሳችን ለራሳችን ስንነግረው ነው ስለ ራሳችን የሚገባን። ይሄም በልጅነቴ ነው የገባኝ። አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች እያለን አንደኛ ወጣሁና በአደባባይ ስሸለም ሁለተኛ የወጣው ልጅ በአደባባይ እዬዬውን አቀለጠው። ደነገጥኩ። የጥፋተኝነት ስሜት ሁሉ ተሰምቶኝ ነበር በወቅቱ። ቆይቶ ዳይሬክተሩ ቢሮ ተጠራሁ። ሰብሰብ ያሉ አስተማሪዎች… እንደመቀለድ እያሉ፣ ሁለተኛ ሴሚስተር እንደሚያልቅልኝ፣ እንዲህ አይነት እልኸኛ ተማሪ ገጥሟቸው እንደማያውቅና… ያኔ በተራዬ እኔ እንደማለቅስ ያወራሉ። ግራ ተጋባሁና "ያላችሁት ነገር ቢሆንና— ለምንድነው የማለቅሰው?" አልኳቸው። ተነጋግረው ይመስል "ስለበለጠህ ነዋ!" አሉኝ። ያኔ ነው ለራሴም የእድሜ ልክ እውነቴን ያወቅሁት።
ተረጋግቼ ነበር ያወራሁት… ‘እኔ እኮ ሰው መብለጥ አልፈልግም። ሰው ቢበልጠኝም ምንም ግድ አይሰጠኝም። የምፈልገው አንድ ነገር ነው፤ እሱም የአባቴ ስም ሲጠራ መስማት ብቻ ነው። ሁለተኛም ሶስተኛም ሆኜ ሲጠራ መስማቱ ብቻ ደስታ ይሰጠኛል። ሌላ አስቤ አላውቅም’ ሁሉም ረዥም ዝምምም አሉ። ለራሴም ራሴን የሰማሁት ያኔ ነው። አንድ ነገሬን አወኩ ማለት ነው። አንድ ነገርም አወኩ። ራሳችንን ስንገልፀው ነው ራሳችንን የምናውቀው። ከዛ በፊትም በኋላም ራሴን ከማንም ከምንም ነገር ጋር አወዳድሬ አላውቅም። የምጨነቀው የራሴ የሆነው ላይ ብቻ ነው።
ልጅነት ላይ ብዙ ነገር አለ…ጉርምስና ላይ የተበላሸ ስብህና ልጅነት ላይ ባለ መሰረት ልታክመው ትችላለህ፤ ልጅነት ላይ የሚበላሽ ስብህናን ግን ለማከም ብዙ ማገዶ ቢፈጅም ያው መታከሙ ባይቀር እንኳ እጅግ ያስቸግራል። ይሄን ሰው ደጋግሞ ሊረዳው ይገባል።
የሆነ ቀን አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ እያየሁ እያለ…
የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ስነ ምግባር መማር እንደሚያስፈልጋቸው የሚወተውት ምሁር ሲናገር ደረስኩና አጃኢብ አልኩ። ዩንቨርስቲ ተሰርተው ያለቁ ልጆች የሚሰባሰቡበት ቦታ ነው ብዬ ነው የማስበው። እነሱን ስነ ምግባር ማስተማር ድንጋይ ላይ ውሃ ከማፍሰስ የተለየ ትርጉም አይኖረውም። ያጋነንኩ ከመሰለህ በራስህ ግነት ልክ እንድታርመኝ ፈቅጄልሃለሁ።
ከዛ በፍጥነት ማርዬ ወደምትወደው ጣቢያ ቀየርኩት …"የኢትዮጵያ ልጆች" … ጥያቄና መልስ ላይ ነበር የደረስኩት… አንደኛው ጥያቄ እንዲህ ይላል…
ጥያቄ
<<ወደ ፊትም ወደ ኋላም ሲነበብ ተመሳሳይ የሆነ ቃል ምንድነው?>>
መልስ
<<ትኩስ ብስኩት>>
ብዙም ስህተት ፈላጊ እንዳልሆንኩ ታውቃለህ። ጥያቄው በራሱ ስህተት አልነበረም። ግን መልሱ ትኩስ ብስኩት ከሆነ ጥያቄው ልክ አልነበረም። ምክንያቱም ትኩስ ብስኩት አንድ ቃል አይደለም። ይሄን በዚሁ አልፈነው ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ተስፋዬ ገብረአብ የደራሲው ማስታወሻ ላይ ይመስለኛል… የሆነ ጊዜ የሆነ ኢንተርቪው ላይ ይሄን ጥያቄ ተጠይቆ መልሱን ስላላወቀው እንደወደቀ ፅፏል።
ጥያቄውን እንየው… የማሰብ መለኪያ አይደለም። ወይ ታውቀዋለህ ወይ አታውቀውም። በሁላችንም ልጅነት ውስጥ ያለፈ ጥያቄ ይመሰለኛል። ለምሳሌ በኔ አልፏል። መልሱን ካወቅነው በኋላ ስንት ኡጫጭ እያሳደድን ይሄን ጥያቄ ጠይቀናል። በጥያቄው ውስጥ ማሰብ የለም፤ ያለው ቀድሞ የማወቅና ያለማወቅ ጉዳይ ብቻ ነው። እንዲህ አይነቱ ጥያቄ አደንዛዥ ነው። በጋሽ ብርሃኑ ድንቄ አገላለፅ "የተዘክሮ ጮሌነትን የሚያበረታታ ነው!"። ቀለል ስናረገው ሸምዳጅነትን አበረታች ነው ማለት ነው። ሸምዳጅነት ሲበዛ ማሰብን ያቀጭጫል ብዬ አምናለሁ! ልጆቻችንን ከሸምዳጅነት ይልቅ ማሰብን ብናስተምራቸው… በራሳቸው የሚቆሙ፣ ብሩህ ነገ የሚታያቸው፣ የተሻለች ሃገር የሚፈጥሩ እልፍ ልጆች እንፈጥራለን ብዬ አስባለሁ። በራሳቸው የሚቆሙ ልጆች የሰው ነገር ለማየት ብዙም ጊዜ የላቸውም። ካዩም ወይ በቀናነት ነው አልያም የሚጠቅማቸውን ለመውሰድ ነው።
ለምሳሌ ለልጆች ጥያቄውን እንዲህ ብናረግላቸው…
"ወደፊትም ወደ ኋላም ሲነበብ ተመሳሳይ የሆነ ቃል ወይም ሐረግ ወይንም ዓርፍተ ነገር ፍጠሩ!" ያኔ ጭንቅላታቸው መስራት ይጀምራል። መልስ ባይፈጥር እንኳ ጭንቅላታቸው በመጠየቁ ብቻ የተወሰነ ዕድገት ይኖረዋል። በራስ መተማመናቸውን ከፍ ያደርገዋል። "ፍጠሩ!" ስንላቸው በሌላ ቋንቋ መፍጠር እንደሚችሉ እየነገርናቸው ነው።
ለምሳሌ ከ<<ትኩስ ብስኩት>> የሚያወጣ አንድ ነገር ብንጨምር "ትንሽ ዋሽንት" አለ… ፈጠራ ገደብ የለውም። ለዛ ነው እስከ ዓርፍተ ነገር ቦርቀቅ ያደረኩት።
ልጅነት ላይ መስራት ሀገር ላይ መስራትም ነው። ራስም ላይ መስራት ነው።
ተማሪዎቼ የሚወዱኝ በሶስት ነገር ነው። ራሳቸውን እንዲሆኑ የምሰጣቸው ገደብ የተጋነነ ስለሆነ፣ ልጅነታቸው ውስጥ እንዲመላለሱ ስለማረግና እንዲያስቡ መንገድ ስለምጠርግላቸው ነው። ሰው ስለተላመደው እንጂ በማሰብ ውስጥ እንጂ በመሸምደድ ወስጥ ደስታ የለም። ሁሉም ባሉበት ልክ እንዲያስቡ ስለምገፋቸው ደስ ይላቸዋል፤ መልሰው ደስም ያሰኙኛል። ይሄ የሚያበሳጫቸው ደግሞ ብዙ ናቸው። ስለዚህ አሁንም በተቃራኒው ስለ ልጅነት እንዳስብ ይገፉኛል።
ደግሞ ሰው የመብለጥ ፍላጎትን ተፈጥሮአዊ እንደሆነ አርገው የሚያወሩ ሰዎች ራሱ ልጅነታቸውን ቢመረምሩት ባይ ነኝ። አስረግጬ የምነግርህ ሳናውቀው በልጅነታችን የምንማረው እንጂ ተፈጥሮአዊ ባህሪያችን እንዳልሆነ ነው። እናም ከዚ ልጅነታቸው ላይ ሳያውቁት በጀመሩት ክፉ ልማድ ብችል ነፃ ባረጋቸው እመኛለሁ። አስበው እስኪ ልበልጠው የማልፈልገው ሰው እየተወዳደረኝ እንደሆነ ማሰብ በራሱ አያስቅም? እኔ እኮ እየተወዳደርኩት አይደለም። እና እየተላፋ ያለው ከራሱ ሃሳብ ጋር እኮ ነው።
ዘፋኝ ትግስት ትሰማሃለች? "እንደ በሬ ሻኛ ከሰው በላይ ያውላችሁ" እያለች ነው… "ለምንድነው እንደ በሬ ሻኛ ከሰው በላይ መሆን(መዋል) የምንፈልገው?"… መልሱ ሲመስለኝ ልጅነታችን ላይ ባለ አላስፈላጊ ውድድር ስለተበተብን ይመስለኛል። እንደምትወዳደረው ከማያውቅ ሰው ጋርስ በሃሳብ መወዳደር ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? … እንዲሁ እንኑር ብለን እንጂ፣ እንኳን ይሄ አይደለም ለጥጠን ካየነው ተመሳሳይ አቅም ያላቸው ሰዎች የሚፎካከሩበት ስፖርታዊ ውድድር ራሱ ውስጡ የሆነ ስቱፒዲቲ አይጠፋውም።
እናም እንዲህ ከሰው በላይ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች ይሄን ቢያስቡ ደስ ይለኛል። ልጅነታቸው ላይ ማን ነበር? ማንን ነበር ሊበልጡ የሚፈልጉት? ለምን? ወይም ዙሪያቸው ያለ ሰው ብለጡት እያለ የሚገፋቸው ሰው ማንን ነበር?
ያ ሰው ዛሬ አለ? ካለ፣ አሁንም እየተፎካከሩት ነው? ወይስ በዛ ልምድ ተነሳስተው ካገኙት ጋር ሁሉ ይላፋሉ? ይህን ማሰብ ወደ ልጅነታቸውም ወደራሳቸውም ይመልሳቸዋል ብዬ አስባለሁ። ወደ ልጅነት መጠጋት ደግሞ ወደ ነፃነት መጠጋትም ነው። ብዙ ስላወራሁ አፉ በለኝ። ግን ሃሳብህን መስማት እፈልጋሁ። ምን ትላለህ?" አለኝ።
"እኔ ምን እላለሁ ፍሬው… የአይሱዙ መኪና ጥቅስ ልጥቀስ እንጂ "ያሉትን ይበሉ" ሃሃሃሃ