Komentar baru

Advertisement

ሽንኩርት ለምን ያስለቅሰናል?

Eriyot Alemu
Apr 10, 2022
Last Updated 2023-08-02T03:57:42Z
Advertisement
ባል እና ሚስቱ ከመሸ ደወሉልኝ… ስልካቸው ላውድ ላይ እንደሆነ ያስታውቃል። ሰላምታ የለ ምን የለ… 
"ዛሬ ሰይፉን አየኸው?" ባልየው ጀመረ።
<<አላየሁትም… ምነው?>> 
"የሙያ አጋርህ መሳይ መኮንን እየታየ ነበር!" … ከት ከት ከት… ግራ ብጋባም ሳቅ መኖሩ ጥሩ ነው ብዬ ቀጠልኩ። 
<<ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ ጋዜጠኛም አረጋቹኝ?…>> 
"እየው ትደሰታለህ! ስለ እነ ሐረገወይን ሁሉ ያወራል!" ሌላ ከት ከት ከት … ከርቀት የሚስቱ ድምፅ ይሰማኛል "ሪታ እኔ የለሁበትም… በስልክ የዶለቱት ነው" … አባወራው ያሽካካል። 
<<ሐረገወይን ደሞ ማነች?… ማናቸው ዶላቾቹስ?>> በጣም ነው ግራ የተጋባሁት። የሰከሩም መሰለኝ። 
"በቃ… ሰይፉን እየውና ታመሰግነናለህ… በቃ ቻዎ" 
<<እሺ ቻዎ… >> 

ምንም አላመነታሁም ከዩቱብ ላይ አውርጄ አጣምሬ ማየት ጀመርኩ። ሳይ ሳይ ሳይ ሐረገወይን አትመጣም። ማነች ሐረገወይን? እያለ ልቤ ይመታል። ከኔ ጋርስ ምን አገናኛት ይሆን? እያልኩ ሳይ ሳይ ሳይ… ድንገት ሰይፉ "ውጪ ሃገር መኖር ወንዶችን ባለሙያ ያደርጋል… አንተ እንዴት ነህ?" ሲለው ጆሮዬ ገባ። የነገር ጥንስሱ እየጠራልኝ ሊመጣ ነው መሰለኝ ሃሃሃ… መሳይ መኮንንም ኮራ ለጠጥ ብሎ "ለክፉ አንሰጥም ምናምን" እያለ ይሰክሳል ብዬ ስጠብቅ… ጭራሽ ያልጠበኩትን ዘረገፈው። በአጭር አማርኛ ያለውን ስተረጉመው "ሰይፉ ተወኝ ባክህ… ምንምኛ ገልቱ ሰው ነኝ!" … እንደዚ ነው በቃ ያለው ሃሃሃሃሃ… ቀጠለና ቃል በቃል "እንቁላል ጠብሼ ራሴ አልበላው!" አለ ሃሃሃሃ… እንግዲህ ወገኖቼ ፍረዱኝ ከመሸ ባልና ሚስት ደውለው "የሙያ አጋርህ ሰይፉ ላይ እየታየ ነው" ያሉኝ በሙያ ገልቱነቴን ሊነግሩኝ ነው። ልሳቅ ላልቅስ አላወኩም። ግን ለነገር ሰው እንዴት እዚህ ድረስ ይራቀቃል? ሃሃሃሃ… የነ ሐረገወይን ጉዳይም ተገለፀልኝ። ቆይ ልንገራቹማ! 

እንደዛሬው የመሳይ አይነት ወንድም ከማፍራቴ በፊት… ጓደኞቼ በላዬ ላይ፣ አይኔ እያየ፣ ጆሮዬ እየሰማ "ውሃ ማፍላት ይችላል? አይችልም?" ቁማር ተጫውተውብኝ ያውቃሉ። ታድያ እግዚሃር ደግ ነው መበደሌን መገፋቴን አይቶ ቀን ቆጥሮ ወንድም መሳይን ሰጠኝ ሃሃሃሃ 

ስራ እንደጀመርኩ ሰሞን የመጀመሪያ እርምጃዬ ከቤት በርሬ ወውጣት ነበር። ቤቶቼ ቢሉኝ ቢሰሩኝ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ ብዬ ወጣሁ። በወቅቱ ራሴን የመቻል ከፍተኛ ጉጉት እንዳደረብኝ በተመስጦ ሳወራ እኔ ራሱ ራሴን አምኜው ነበር። ዋነኛ ጉዳዬ ግን ሌላ ነገር ነበር። ሆድ ይፍጀው። 

መሰረታዊ ማብሰያ ዕቃዎች ተገዛልኝ። እህቶቼ ሁለት ቀን ምግብ ሲሰሩ በአንክሮ ተከታተልኩ…ከዛ ከስካፊየር የምግብ ማሰልጠኛ ተቋም የተመረኩ ይመስላል ተጀንኜ ከቤት ስወጣ። የተከራየሁበት ቤት ጓደኞቼ ብቅ ጥልቅ ይላሉ። ሊያቋቁሙኝ ሳይሆን ያው ሊያቋቁሙኝ ነው ብለን እናልፈዋለን። (አንባቢ እዚህ ጋር ቃላትን ያስተውል ሃሃሃሃ) … እናም በዛን ወቅት ሽንኩርት ግዛና ዘርረው ተብዬ እንደተመከርኩት እንደዛው አድርጌያለሁ። ጓደኞቼም ይሄን አይተዋል። ሳፈጥነው ቀን ቀንን እየተካ አንድም ቀን ምግብ ሳልሰራ ሽንኩርቶቹ እንደ ሐረግ መብቀል ጀመሩ። የነ ሐረገወይን ውልደት እንግዲህ እዚህ ጋር ነው የሚጀምረው ሃሃሃሃ 

ከዛ አንድ ቀን ፓስታ ልጋብዛቹ ብዬ እንደሃይለኛ አቅራርቼ ስጨርስ… የቀቀልኩት ፓስታ ድስት ውስጥ ሙክክ ብሎ በስሎ እብስት ዳቦ መስሎ ወጣ። በጀማው የተሳቀው ሳቅ አሁን ድረስ ጆሮዬ ላይ አለ። ለክፉ ቀን ብለው ፎቶ ያነሱ ሁላ ነበሩ። ከዛ በኋላ በቃ በሙያዬ መቀለጃ ሆኜ ቀረው። "እስቲ ዱባ ሞክር እሱ ሙያ አይፈልግም" ተብዬ መጀመሪያ አካባቢ እውነት፣ እውነት መስሎኝ ዱባ ሁሉ አፈላልጌኣለሁ ሃሃሃሃ የነ ሐረገወይን ታሪክ ግን በዚ ቢያበቃ ደስ ይለኝ ነበር። ግን አላበቃም። 

ሁሌ ማታ ማታ እንደማንኛውም መልካም ወጣት ከጓደኞቼ ጋር ነፋስ እየተቀበልን እንጨዋወታለን። በመሃል በመሃልም እንስት እህቶቻችንም ነፋሱን ለመቀበል ይቀላቀሉን ነበር። በዚ መሃልም አሁንም እንደማንኛውም መልካም ወጣት አንዲት ጆፌ የጣልኩባት ልጅ ነበረች። እሷ ስትኖር ስትኖር ብዙ አላወራም። ብዙም አልጠጣም። ነፋሱንም ብዙ አልቀበልም። ቶሎ ወደ ተከራየሁት ቤት ብድግ ብዬ እበራለሁ። ኃላፊነት የሚሰማኝ መልካም ወጣት መሆኔን ላሳያት እኮ ነው ሃሃሃሃ ታድያ ሁሌ ተነስቼ ስሄድ ቀሪ ጓደኞቼ ጮክ ብለው "እነ ሐረገወይንን ሳምልን!" ይሉኛል። "ያውም ተጠምጥሜ ነዋ!" ብዬ ስቄ እሄዳለሁ። ይሄ ነገር ብዙ ጊዜ ተደጋግሟል። 

የሆነ ጊዜ ላይ ልጅቷ ካገር እንደወጣች ሰማሁ። የቴዲ አፍሮ "ጉድ ያረገኝ ዓይኔ ነው" የሚለው ዘፈኑ ላይ "ስንት ቆንጆ አለፈኝ እስከዛሬ… ቀርቦ ለማናገር በማፈሬ" የሚለው ስንኝ፣ ሐረግ፣ አንጓ ላይ አተኩሬ አልቅሼ አልቅሼ ወጣልኝ። ሐረግን ይዛችሁ ቆዩልኝ። ከዛ ቆይቶ ለጓደኞቼ ተከይፌባት እንደነበር ስነግራቸው ሊበሉኝ ደረሱ። እንዴት ትደብቀናለህ በሚል ማለት ነው። ምንም የማልደብቅ ነበርኩስ ከዛ በፊት ሃሃሃሃ በተለይ ልጅቷን የሚያመጣት ልጅማ አኮረፈኝ። የመልካም ወጣቶች መተሳሰብ እኮ ከልብብ ነው ሃሃሃሃ አሁንም ሳፈጥነው ከሆኑ አመታት በኋላ ከውጪ ስትመጣ ይሄው ልጅ ደውሎ ነገረኝ። ህይወት ተቀያይሮ ነበር። እሷ አግብታለች። እኔም ከዛ ጀማ ተፋትቻለሁ። 

ባልጠበኩት ሁኔታ ግን ደወለቺልኝ። ገረመኝ፤ አገኘኋት። ስናወራ በመሃል ትመቸኝ እንደነበር ግልፁን ስነግራት ፊቷ ተለዋወጠ። ግራ ገባኝና ዝም አልኩ። <<እንዴት ብታስበኝ ነው ከብዙ ሴቶች ላይ ደርበህ የምታስበኝ? … ዱርዬ መሆንህን መጀመሪያም የናንተን ግሩፕ ከመቀላቀሌ በፊት አውቅ ነበር። ግን በብዙ ሴት አላስብህም ነበር… የምመጣው ራሱ ማንን ብዬ እንደ ነበር ታውቃለህ?… አንተ ግን ፈጣጣ ነበርክ>> ስትለኝ ምን እየተከናወነ እንደሆነ አልገባኝም። አንዱን ቀድሜ ልወቅ አልኩና "የምን ብዙ ሴት ነው የምታወሪው?" አልኳት ድምፄ ለኔ ራሱ የሌላ ሰው ነው የመሰለኝ። <<እንዴ ተው እንጂ! ዘወትር ተጠምጥመህ የምትስማቸው እነ ሐረገወይን ናቸዋ>> ስትልኝ ሌላ ጊዜ ቢሆን ያስቀኝ ነበር። ስሜታዊ ሆኜ ስለነበር ግን… ቆጣ ብዬ "እነ ሐረገወይን እኮ ሽንኩርት ናቸው" ስላት … <<ለምን ድንች አይሆኑም!>> ብላኝ ጥላኝ ስትሄድ የሳኩትን ሳቅ ዛሬ ድረስ አስታውሰዋለሁ ሃሃሃሃ 

በኋላ በጓደኛችን አማካኝነት እርቅ ሲወርድ እንደተረዳሁት ከሆነ "እነ ሐረገወይን እኮ ሽንኩርት ናቸው!" የሚለው ንግግር ራሱ ለሌላ ትርጉም የተጋለጠ ነበር። እኔ እኮ የዋህ ሰው ነኝ ሃሃሃሃሃ እና ረዥሙ ሲያጥር በሽንኩርት የተነሳ አንዲት ሴትን ሁለቴ ያጣው ምስኪን ሰው ነኝ ለማለት ነው። እናም ከዛ ጊዜ ወዲህ ሽንኩርት ልጬ በከተፍኩ ቁጥር አለቅሳለሁ። ወዳጆች የሚያስለቅሰኝ ሽንኩርቱ ይመስላቸዋል። ግን ደግሞ ታድያ ሌላ ምን ይሆናል ሃሃሃሃ 

ፆም ሲፈታ ደግሞ የበሬ ሻኛ ለምን ከፍ ብሎ ተሰቀለ የሚለውን ታሪክ ከኔ ህይወት ጋር እንዴት እንደሚገናኝ ስለምናይ… ትግስት በቀለ "አውዳመቱ ሲመጣልን ባመቱ… " የሚለው ዘፈኗ ውስጥ ያለውን "እንደ በሬ ሻኛ ከሰው በላይ ያውላችሁ" የሚለውን ሐረግ እየመዛዛችሁ ጠብቁኝ ሃሃሃሃ 

የዚያ ሰው ይበለን!!!
iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

Leave Your Comment

Post a Comment

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement