Advertisement
በዚህ መሃል ሆኜ ድንገት "ሄኖክ ሄኖክ!" የሚል፣ ከርቀት የሚመጣ ድምፅ ሰማሁ። አልዞርኩም፤ ድምፁ እስኪቀርበኝ ድረስ ቆሜ ጠበኩት።
"ምን ሆነሃል ሄኒ? … ስልክህን አታነሳም፣ ብዙ ጊዜ ደወልኩልህ እኮ!" ሳሚ ነው። ከጓደኞቼ ሁሉ አብልጬ የምወደው የልጅነት ጓደኛዬ ሳሚ።
"ሳሚ ስልኬን አልያዝኩትም" ኪሴን አሳየሁት።
"ለነገሩ ጊዜው ሁሉን ያስረሳል"
"ደስታዬን እንዳታበላሸው! ስልኬን ሆን ብዬ ነው የተውኩት"
"የእውነት?…"
"ስልኬን ጥዬው ስወጣ እያሰብኩህ ነበር። ያለ ስልክ የኖርንበትን ዘመንንም እያሰብኩ ነበር። … ብዙ ነገሩን ረስቼው ነበር። አሁን ማስታወስ ፈለኩ። ያለ ስልክ ትንሽ መኖር እፈልጋለሁ። የፈለገኝ ሁሉ እንዲያገኘኝ አልፈቅድም። ከልቡ የፈለገኝ ብቻ ነው ጊዜዬ የሚገባው። ከልቡ የሚፈልገኝ ቤቴን ያውቃል። ባያውቅም ይጠይቃል። ጊዜ ውድ ነገር ነው አሁን ለኔ… ብዙ የማስተካክለው ነገር አለ"
"ሄኒ ጥሩ ሙድ ላይ እንዳለህ ፊትህ ያስታውቃል። እኔ ላይ ግን እንደዚህ ስትሆንብኝ እፈራሃለሁ። ስትጫወት ስትስቅ ነው ደስ የሚለኝ። አቦ እንደድሮ ሁና… እንደውም እጅግ የማወራህ፣ የሚገርም ወሬ አለ። ቁጭ ብለን ነው የምናወራው"
"መሳቅ መጫወት እድሜ ልኬን የኔ ነው! የትም አይሄድብኝም። እየሳኩ የምፈልገውን ልነግርህ እችል ነበር። ግን ምን ያህል ስርስ እንዳልኩ እንዲገባህ ነው። ‘አንተኮ ጣጣ የለህም!’ ስባል ነው የኖርኩት። አሁን ሲሪየስ፣ እጅግ ጣጣ ያለው ሰው መሆን ነው የምፈልገው። ወደፊት ከሁለቱም (ጣጣ ካለውም ከሌለውም) ስቀይጥ ህይወት ትጣፍጥልኛለች ብዬ አስባለሁ። እና ይቅርታ አድርግልኝና ቁጭ አልልም። በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ። እሱን ማወቅህ ብቻ በቂዬ ነው ላሁን። አብዲን አግኝተኸው ታውቃለህ?"
"ቤት ከቀየርን በኋላ አላገኘሁትም። ተደዋውለንም አናውቅም!… ሰላም ነው?" (ቤት የሚለው ግሮሰሪን ነው)
"ልጁን አሞት ነበር!"
"ኦው! ያሳዝናል"
"ሳሚ የልጁ ስም ማነው?"
"እንዴ ምን ሆነሃል ዛሬ!? የአብዲን ልጅ ስም ነው የምትለኝ?"
"አዎ የአብዲን ልጅ?"
ቆሞ ማሰብ ሲጀምር እኔ መሄድ ጀመርኩ። እየተከተለኝ "አይገርምም ለካ አላቀውም!" አለኝ። ሌላ ጊዜ ቢሆን እስቅ ነበር። ዛሬ መሳቅ ዋጋ ስለሚያስከፍለኝ አልሳኩም።
"አየህ! ከአምስት አመት በላይ አንድ ፅዋ ማህበር ጠጪዎች ነበርን። በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበን ስናወራ እጅግ የምንተዋወቅ፣ እጅግ ደስተኞች እንመስላለን–ከሩቅ ለሚያየን። ያሰባስበን የነበረው ብርጭቆ ነው። ጠረጴዛው ተነስቶ ያለብርጭቆ ስንቀር ሁላችንም አንተዋወቅም። ሁላችንም ጎዶሎዎች ነን። በየቀኑ ብርጭቆ የሚሞላን የሚመስለን—ጎዶሎዎች። ደስታችንም እዛው ጠረጴዛው ጋር ቀሪ ነው። ሁሌም ስንበተን ሁላችንም የግል ሐዘናችንን ይዘን ነው ቤታችን የምንገባው። ብርጭቆ ነው ከርክሞ እኩል የሚያስመስለን እንጂ ያለ ብርጭቆ አንዳችን አጭር አንዳችን ረዥም ነን። አየህ!…"
ፀጥ ብሎ ያየኛል። ፀጥታው ለኔ ራሱ ሲከብደኝ ማውራት ቀጠልኩ…
"አየህ! የአምስት አመት ጓደኛህን የአብዲን ልጅ ስም አታውቀውም። ለምን የጠየኩህ ይመስልሃል? እኔም አላውቀውም ነበር። ያ አስደነገጠኝ። ያ አሳፈረኝ። ያ አስፈራኝ። ያ… አላውቅም። ሰሞኑን ብዙ ስላላወራው ሳወራ ይደክመኛል። ሳሚ በአጭሩ እኔ ራሴን ከጠረጴዛው ቀንሻለሁ"
"አረ ሄኒ!… " ዓይኔን ማየት ሲሸሽ አየሁት። ጓደኛዬ እኮ ነው— እጅግ የምወደው።
"ሳሚ ለመጨረሻ ጊዜ ጠረጴዛ ልጋራህና የምትነግረኝን ልስማህ። ጠጣ ብትለኝ ግን ጥዬህ እሄዳለሁ። ደግሜም አላገኝህም!" እንደ ልጅ ፈገግ አለ። አብሬው ፈገግ አልኩ።
"እንደዛሬ ፈርቼህ አላውቅም!"
"እንደዛሬ ብዙ ጊዜ እንድትፈራኝ ስለማደርግህ አትቸኩል!" መልሼ ኮስተር አልኩ።
ቀለል ያለ ግሮሰሪ ተያይዘን ገባን። ለመጀመሪያ ጊዜ ለግሮሰሪ እንግዳነት ተሰማኝ ። ግማሽ ሊትር ውሃ ፊቴ ተቀምጧል። እኔ ግሮሰሪውን እንደ እንግዳ ነገር ሳየው ሳሚም እኔን እንደ እንግዳ ነገር እያየኝ እንደሆነ ይታወቀኛል። የተለየ ነገር ይነግረኛል ብዬ አልጓጓሁም። ብዙ አመት በጠረጴዛ እና በብርጭቆ ዙሪያ ካወራነው እንደ አንዱ አይነት ወሬ ነው የሚነግረኝ። ራሳችንን የምንፎግርበት ዘዴ ነች… "የሚገርም ነገር እናወራለን" ተባብለን ተገናኝተን… ስለ መግረሙም ስለ ወሬውም ሳንጨነቅ ቀምቅመን እንለያያለን።
እንዲህ እንዲያ የመሳሰሉ እልፍ ምሽቶች አሳልፈናል። በማግስቱም ይሄን ለመድገም ቀጠሮ እንይዛለን። ይህ ታክቶኝ ነበር።