Komentar baru

Advertisement

የወር–ቃሙ ልጅ ትዝታ

Eriyot Alemu
Mar 19, 2022
Last Updated 2023-08-21T03:47:46Z
Advertisement
(እውነተኛ ታሪከ ትንሽ ተቀባብቶ)
ያኔ………………………………
ገና ትኩስ ተመራቂዎች ሆነን ነው። ክረምቱ ራሱ ገና ትኩስ ነበር። ያው ከክፈለሃገር አዲስ አበባ የመጡ ተማሪዎች እንደሚያደርጉት… ከየቤታችን የየሶስት ታክሲ ጉዞ ርቀት ሄደን እንቅም ነበር። ለደህንነቱ ስል የማልጠቅሰው መናፈሻ ደግሞ እናዘወትር ነበር። 

አንድ ቅዳሜ ታድያ 10 ሰዓት አካባቢ ሲል ስልኬ ጠራ። አንስቼ "ሄሎ" ስል… 
<<ሪዮት የት ነህ?>> የሚል ድምፅ ከወዲያኛው ጫፍ ሰማሁ። 
"መጀመሪያ ማን ልበል ጌታዬ!" አልኩት። 
<<ማንነቴ ይደርሳል። ለጥብቅ ጉዳይ ፈልጌህ ነው። የት እንዳለህ ትነግረኛለህ?>> በድምፁ ምን እንደለቀቅብኝ አላውቅም አድርጌው የማላውቀውን ያለሁበትን ነገርኩት። እውነቱን ለመናገር ምንም የለቀቀብኝ ነገር የለም መርቅኜ የዋህ ሆኜ ስለነበር ነው ሃሃሃሃ ከራሴ ጋር እየተማመንኩ ልሂድ ብዬ ነው። እዛው መናፈሻ ከአንድ ሰዓት በኋላ ደርሶ ደወለልኝ። ሉሉ አርጌ እንደነገሩ ወጣሁ። እንደቃምኩ አስታውቃለሁ እንኳን ቅሜበት አይኔ እንዲሁም ፍጠጥ ፍጠጥ ይለኛል። 

ልክ እንዳየሁት ነው ያወኩት። ከ8ኛ ክፍል በኋላ ግን አይቼው አላውቅም ነበር። ሱፍ አርጓል። ሞቶሮላ ፍላት ስክሪን ስልክ ይዟል። በኖኪያ 1100 ዘመን የያዘውን ስልክ በአሁኑ በምታውቁት ፀዴ ስልክ ምቱት። አውራ ጣት የሚመስለውን ሞቶሮላ ብቻ የምታውቁ እሱን አይደለም የያዘው። ብቻ በዚ ሁሉ ነፍሴ አከበረችው ብል ማሽቃበጥ ይሆንብኛል? ሃሃሃሃ እንጃ የሆነ ክላስ ጨረር ግን ለቆብኛል። 
ትምህርት እንዴት ነበር ምናምን እያለ ሲጠይቀኝማ ጭራሽ እኩያዬ መሆኑን ሁሉ መርሳት ጀመርኩ። 
ቀጥታ ወደጉዳዩ ሲገባልኝ… እኛማ ትምህርት ትተን በአቋራጭ በልፅገን ቀደምናቹ ምናምን ወሬ አወራኝ። እና በመሃል የሆነ የሚያስቅ ነገር ነገረኝ። ስለቃምኩ ፈገግ ብቻ ነው ያልኩት። ይሄኔ ኮስተር አለ። 
<<ሪዮት አለም… ጥርስህ ላይ ጫት ነው የማየው? አንተም ጫት ትበላለህ? በዚ አይነትማ መጠጥም ጀምረህ ይሆናል… >> ተውረገረገ፣ ዘፈነ፣ ዘፈነ… የሆነ የማላውቃት አክስቴን ሁላ ነው የመሰለኝ። ግን ደንዝዣለሁ።  

<<እንዴት አንተ?…  ጫት እንኳን ሊበላ አይረገጥም የሚባልበት ሰፈር አድገን… ለነገሩ እድለኛ ነህ ደርሼልሃለሁ… የአምላክ ያለህ! ይሄን አሁን ማን ያምናል?…>> አወራሩ የሌለ ነው። እኔም ከምን ለምን እንደደረሰልኝ ሳላውቅ አዳኜ አድርጌ ተቀብዬዋለሁ። 
<<በቃ የወንድሜ የኮንስትራክሽን ድርጅት ውስጥ ሰኞ ስራ ትጀምራለህ… በእንደዚ ሺ ብር ደሞዝ። አነሰ ካልክ አይተን እንጨምራለን። ጫትህን ምናምን ግን በቃ… ፀጉርህን እ  እ…  አይ ፀጉርህ እንኳ ችግር የለውም>> ሲለኝ እፎይ አልኩ። ፀጉርህን ታሪካዊውን ፓንክ ቁርጥ ተቆርጠህ ና ይለኛል ብዬ ሰግቼ ነበር። በሌላው በቃ ተስማምቻለሁ መሰለኝ። እንደሚደውልልኝ ነግሮኝ ሄደ።  

ጓደኞቼ ተመልሼ የሆነውን ስነግራቸው በመሃከላችን ታላቅ ፌሽታ ሆነ። ተንከባካቢዬ በዛ። የመጀመሪያ ወር ደሞዜ ፕሮግራም ሁሉ ወጣለት። ምን አይነቱ ቅዱስ ሰው ነው ተባለ። ከድሮም ጀምሮ ስለ ነበረኝ ዕድለኝነት ተተነተነ። ለአንተ የዘነበ ለኛም ያካፋ ተባለ። ቀኑ ቅዳሜ ነውና ምሽቴን ሊያሳምሩልኝ ያላቸውን ማጋጨት ጀመሩ። እኔም ከወዲሁ ቅዳሜና እሁድ አብረን እንደምንቅም… ከሰኞ እስከ አርብ ግን እንደሚናፍቁኝ በዕንባ ቀላቅዬ ተናገርኩ። ከዛ ዳይ ወደ ጭፈራ…  

በዕለቱ የማረሳው ልንጠጣ የዞርንባቸው ቤቶች በሙሉ ማለት ይቻላል… ሁለት ዘፈኖች ይከፈቱ ነበር። አንዱ ወደ ላይ ወደ ላይ የሚያዘልል ሃገር በቀል ዘፈን ነው። ሚሶ ነጋያ መሰለኝ ከሌላ ዘፈን ጋር ተናጭቶብኝ ነው። ሁለተኛው የቴዲ ታደሰ "አመጣው ፍቅር ፍርጃውን" ነው… ያኔ ለምን እንደሆነ አላውቅም የሌለ ጦዞ ነበር። ወይ ሁሉም ቤት ያለው ዲጄ፣ ቤት ስንቀይር ሮጦ እየቀደመን ነው። እና ጣርያ ድረስ ዘለል ዘለል ለሚያስደርገውና ለብቻ ለሚያስጨፍረው የጨዋ ልጅ ዘፈን ዘልዬ ዘልዬ ደክሞኝ ቁጭ ስል ቴዲ ታደሰ ይመጣል። ያኔ ነው ወንድ ልጅ እንዲህ ሆድ እንደሚብሰው ያወኩት። የጥምቀት መዘምራን እንኳን እንዲህ እኩል የሚዘምሩ አይመስለኝም። 
"አመጣው ፍቅር ፍርጃውን
እንጃልኝ መሰንበቻውን
.
.
እኔማ ከሃዲ ብዬ… " እዚጋ እኩል ወንዶቹ ሲጮሁ አሁን ድረስ ጆሮዬ ላይ ያቃጭላል። ያኔ ልጅ ሆኜ ለአቅመ መበደል ስላልደረስኩ ነው አብሬ ያልጮህኩት። በኋላ አድጌ "ስትሄድ ሆዴ ባባ ተናነቀኝ ዕንባ" የሚለውን እያለቀስኩ ስዘፍን ነው ህመማቸው የተሰማኝ ሃሃሃሃ ብቻ ቅዳሜን ጠጣን ጨፈርንና እሁድም ሆነ። 

ደዋዬ እንዲሁም ቀጣሪዬ የሆነው ቅዱሱ ሰው ደወለልኝ… በከባድ አንጎበር ውስጥ ብሆንም በምችለው መጠን ተጠንቅቄ አወራዋለሁ። እንዳይቆጣኝ እኮ ነው። … ዶክመንቴን እንዳዘጋጅ ነገረኝና… ብቻ ለምን እንደሆነ ግልፅ ባልሆነልኝ ምክንያት ለድርጅቱ በኔ ስም አምስት መቶ ብር እንደከፈለ ጭምር ነግሮኝ ስልኩ ተዘጋ። ነገ ስራ ጀማሪ ነኝና አምስት መቶ አይደለም ሺ ብር ቢከፍልስ ከደሞዜ ስለሚቆረጥ አላሳሰበኝም። 

እሁድን ተኝቼ ነው የዋልኩት… ሲመሻሽ ቤት መጣ። ዶክመንቴን ሰጥቼው አምስት መቶ ብሩን ስሰጠው ሞቼ እገኛለሁ ለደሞዝህ ይደርሳል አለኝ። የዋለልኝ ውለታ አንሶ እንዲማ አይደረግም ብዬ ግግም ብዬ እንዲቀበለኝ አደረኩ። ሰኞ ዋስ የሚሆነኝ ሰው እንዳዘጋጅና ቢሮዬ አዲስ ስለሆነ ለሆነ ነገር ማስኬጃ ተጨማሪ አንድ ሺ ብር ይዤ እንድመጣ ነገረኝ። በወቅቱ ብሩን ለምን እንዳለኝ እንኳ ልብ አላልኩትም። ስራ ሰርተህ ስትጨርስ ኮምፒተርህን ለምታለብሰው ዳንቴል መግዣ ነው ብሩ የተፈለገው ቢለኝ እንኳ አምነው ነበር። ቀጠሯችን ሳር ቤት መሆኑን ነግሮኝ አመስግኜው አመስግኜው አመስግኜው ተለያየን። በተቀጣሪ ሙድ ከሰበሰብኳት፣ በቀረቺኝ ብር ጨብሼ ጓደኞቼን ላሰጨብስ ወደነሱ ሩጫ ሆነ።  

ጓደኞቼ ጋር ደርሼ የሆነውን ስነግራቸው የሆነ ፊታቸው ተለዋወጠ። ቀን ስላልቃምኩ መጀመሪያ ምርቃናቸው መስሎኝ ነበር። ቆይቶ እኔም እየጠጣሁ ደመቅ ማለት ስጀምር ሆዱ ሻሽ የሆነው ጓደኛችን ድንገት ቡፍ ብሎ ሲስቅ ሁሉም ተከተሉት። ከዛ ጉዴን አንድ በአንድ ነገሩኝ። ድንገት ባደረጉት ማጣራት፣ በኃይለኛው ዋቴ እንደተሰራሁ … ቅዱሱ ልጅ መተዳደሪያው የዚህ ዓይነት ማጭበርበር እንደሆነ… በስም የማውቃቸውን ልጆች እየጠሩ ሰለባ መሆናቸውን ከነገሩኝ በኋላ… ኃይለኛ ቃማቴ እንደሆነም ጭምር ሲነግሩኝ የእውነት አናቴን በመዶሻ የተመታሁ ነው የመሰለኝ።  

<<‘ጫት ትበላለህ እንዴ?… እኛ ሰፈር ጫት እንኳን ሊበላ አይረገጥም!’ ብሎኛል እኮ>> ስላቸው…  
<<በቃ እኛም አንተ ስራ ስለሆንክ ቅዳሜ እና እሁድ አብረን ጫት እንበላለን … ከሰኞ እስከ አርብ ግን ጫት እንዳትረግጥ… እኛ እንረግጥልሃለን>> ብለው ቀድሜ በተስፋ ልሳን በተናገርኩት በራሴው ንግግር ሙድ ያዙብኝ። ሳቅኩኝ። ግን ውስጤ የሆነ እሳት ነው የተቀጣጠለው። ተንገብግቤያለሁና ወዲያው ሃሳብ መጣልኝ። 
<<ነገ ዋስ ምናምን ስላለኝ… ሳሚ ገርጀፍ ያለ ስለሆነና ፊቱ ስለማያስባንን አብረን ሄደን ስልኩን እናፀዳዋለን>> አልኩ። ድጋሚ ሁሉም ቺርስ በቺርስ ሆነ። በሃይለኛው ሴራ ተሸረበ። ወንድ ልጅ ተወልዶ ብድር ካልመለሰ… ተሸለለ ተፎከረ። 

የማይነጋ የለም ነጋ። እኔና ሳሚ ቀድመን ተገኘን። ቁርጣችንን በአልኮል እያወራረድን ሳለ መጣ። ለከፋይነት ድግስ እንዳጨነው አላወቀም። ሌላ ሱፍ ነው ያረገው። መነፅር አያያዙ ለጉድ ነው ቄንጡ። ጓደኛዬ ጠጋ ብሎ <<ይሄ ቢሸውድህ ምንም አልፈርድብህም>> ሲለኝ በጣም ነው ደስ ያለኝ። ተሸውዳቹ እያለ መሸወዳችሁን ምክንያት የሚሰጥላቹ ሰው ሲገኝ ደስ እንደሚለው ዓይነት ደስታ ነው ደስ ያለኝ። አጭበርባሪዬን ተጠግቼ ሳየው ግን የመጀመሪያ ቀን ፈዝዤ እንጂ ቃሚ መሆኑ ቢያንስ ለቃሚ ያስታውቅ ነበር። ጥሬ አልበላም ብሎ ጥብሱን ሲያዝ እኔና ሳሚ በሆዳችን እልል እያልን ነበር። የሚከፍለው ብር ተቆልሎ ተራራ ቢያክል ደስታችን ነው።  

በጨዋታ በጨዋታ ለስራ ስለሚያስፈልጉ ነገሮች ሲነግረኝ አጃኢብ ብዬ ነበር። በኋላ ሲገባኝ ክፍለ ከተማ የተለጠፈውን ሸምድዶ እኮ ነው። ታማኝነት፣ ቅንነት፣ አገልጋይነት ወዘተረፈ እያለ ሲሰክሰን እያጭበረበረን እንደሆነ እያወቅንም በስብከቱ ሃ ብለን ስናዳምጠው ነበር። 
ለስንተኛው ዙር ለሽንት ሲወጣ ሳሚ <<እጁ ላይ ስልክ አላየሁም እኮ>> ሲለኝ… እኔ የአጭቢቲን ሞቶሮላ ስልክ፣ ከአምስት መቶ ብሬና  አሁን ከሚከፍለው ከምግብ መጠጡ ሂሳብ ጋር እየደመርኩ እየቀነስኩ "ተክሻለሁ አልተካስኩም?" የሚለውን እያሰላሁ ስለነበር ሳሚ ያለኝን ልብ አላልኩትም።  

አጭበርበሪያችን ሲመጣ እንደ ደንቡ "ኖር" አልነው… 
<<በልጆቻችን የምንልበት ቀን ሩቅ አይሆንም!>> ብሎ ቁጭ አለ። በሆዴ "እኛኑ ኮፒ" አልኩኝ። እኔና ጓደኛዬ ኖር ስንባባል የምንባባለውን እዛው ቀብ አርጎት ነው። ድንገት የሳሚቲ ስልክ ሚሴጅ ቶን "ጢን ጢን" "ጢን ጢን" አለች። ያው "እንዴት እንዴት እየሆነላችሁ ነው?" የሚሉ ጓደኞቻችን ናቸው። ሳሚ ፈገግ ብሎ ያነባል… አጭቢቲ ሳናስበው "ኦ ማይ ጋድ!" ብሎ ብድግ ሲል ሁላችንም ደነገጥን። አደነጋገጡ የምር ያስደነግጥ ነበር። 

<<ስልኬን የት አደረኩት?>> እያለ ኪሱ ይገባል ይወጣል። ደረቱን ይዳብሳል። ጆሮው ላይ ስልኩ ራሱን ችሎ ይቀመጥ ይመስል ጆሮውን ራሱ ሁለቴ ነካክቶ ቼክ አርጓል። በመሃል ሳሚን "ቶሎ ደውልልኝ ቢሮ ውስጥ ረስቼው ከሆነ… ቶሎ በል" ብሎ አጣደፈው። ሳሚም ቁጥሩን መታና ስልኩን ሰጠው… ብቻውን እንደ እብድ እያወራ ስልኩን ጆሮ ላይ አስደግፎ ከግቢው ወጣ። ሊመነትፈን ተዘጋጅቶ የመጣው ቀሪ አንድ ሺ ብር እኔ ጋር እንዳለው ስለሚያስብ እኔም ሳሚም ከግቢው በመውጣቱ አልሰጋንም። አንድ ሺ ብሩን ባልይዘውም ቅሉ። ዕቅዳችን የነበረው የሱን ስልክ በሆነ ሰበብ ተቀብለነው በዛው ልንቀጠስ ነበር። 

ሲቆይ ሲቆይ ግን ትንሽ በትንሹ መስጋት ጀመርን። ሳሚ የስልኩ ጉዳይ፣ እኔ ደግሞ የሂሳቡ ጉዳይ አናታችን ላይ ወጥቷል። በመሃል ስልኬ እንደ ሳሚ ስልክ "ጢን ጢን" አለች። "aznalew eriot chela yasfelgegn neber yikrta betam aznalew" … የሚል መልህክቱ ደረሰኝ። ስልኬን ደንዝዤ ለሳሚ አቀበልኩት። ሳሚ ያወራል <<ምን ማለቱ ነው ቼላ ያስፈልገኛል የሚለው… ቼላ ብንሰጠው ስልኬን ይመልሳል?>> ይለኛል፣ ይለፈልፋል፣ ይለፈልፋል…  <<ቼላ አይደለም ያለው "ጨላ ያስፈልገኛል" ነው ያለው… >> እያልኩ በተለሳለሰ ድምፅ ራሴንም ጓደኛዬንም ሳፅናና… አስተናጋጁ "ልወጣ ስለሆነ ሂሳብ!" ብሎ ፊቴ ቆመ።  

ድሮም የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል። ሂሳቡን ስሰማ ሆዴ ውስጥ እባብ ያለ ነው የመሰለኝ። ሆዴ እንዲህ ጮሆ አያቅም። እባብ ሆድ ውስጥ እንደሚጮህም አላውቅም። ሂሳቡ ግን ከኪሳችን በላይ ነው። ምንም አማራጭ ስለሌለን በወዲያ፣ ለጓደኞቻችን እንዲመጡ ነገርን… በወዲህ ደግሞ ከፋዩ ድንገት ስለወጣ እስኪመጣ ድረስ ይቅርታ ጠይቀን… አርፈን ቁጭ አልን። አስተናጋጁ አጭበርባሪያችን አወጣጡ እቃ ጥሎ እንደሆነ ስላመነ፣ ተረድቶን ለቀሩት አስተናጋጆች አስረድቶልን ሄደ። እኔና ሳሚ በዝምታ ደጅ ደጁን ማየታችንን ቀጠልን።  

ሞኝን እባብ ሁለቴ ይነድፈዋል ብዬ እንዳልተርት አመጣጣችን የሞኝ አልነበረም። ግራ ቢገባኝ "አቤቱ የሆነብንን አስብ" ብዬ ወደላይ አንጋጠጥኩ። ወደታች አንድ ጥቅስ መጣልኝ።  "ክፉ እመልሳለሁ አትበል፤ እግዚአብሔርን ተማመን፥ እርሱም ያድንሃል" … ክፉን በክፉ ለመመለስ ማሰብ ልክ ነው? ልክ አይደለም? … እያልኩ ሳሰላስል እቆይና… በመሃል ወዲያ ሄጄ "ወይኔ አምስት መቶ ብሬ!… ወይእሱ ስልኩ!… ወይእኛ አሁን የምንከፍለው ብር እያልኩ ስብከነከን በመሃል የሳሚ ድምፅ አነቃኝ። 

<<ከመሃላችን የነገረው ሰው ቢኖርስ ግን?… ታድያ እንዴት አንድ ሺ ብሩን ሳይጠይቅህ ይሄዳል… >> … ብሎ ያላሰብኩትን እያሳሰበኝ እያለ ጓደኞቻችን ድንገት ደረሱልን። ከፍለን ሹልክ ብለን ወጣን። የሚስቀው እየሳቀ ፀጉሩን የሚነጨው እየነጨ ጉዞ ወደ መቃሚያችን። 

በኋላ እየቃምን ጉዳዩን ስንፈልጠው አጭበርባሪያችን ከአንድ ሺ ብሩ በላይ ስልኩን የመረጠበት ምክንያት ይሄ እንደሆነ ገመትን።  
… ያዘዝነው ምግብ እና መጠጡን ሂሳቡን በውስጡ ደምሮ ቀንሶ አስቦ፣ ያው ከፋይ እሱ መሆኑ ስለገባው ማለት ነው… መቼም ቀጣሪያችን እኔና ሳሚን ክፈሉ ሊለን አይችልም። እና የስልኩ ሂሳብ ተሽሎ አግኝቶት ነው የሚሆነው። በዚ ተግባብተን ከዛ በኋላ የትኛውንም ሰው ሳይጠራጠሩ ላለማመን የሚል ትምህርት ቀስመን ፋይላችንን ዘጋን። ለሳሚም ስልክ ተጋጭቶ ሊገዛ ተወሰነ። ከመጀመሪያይቱ ጥፋት የሁለተኛይቱ በእጅጉ የከፋች ሆነች ሃሃሃሃ  

<<ቀድመህም ክፉ አሰብክ… ክፉ ስለተደረገብህ፣ ክፉ ለማድረግም አሰብክ… ያው ስሙ ክፉ ማሰብ ነው! ሌላ የለውም… መጨረሻው አያምርም>>
አጭበርባሪዬን 500 ብር፣ የጓደኛዬን ስልክ ከምሳ ጋር አስጨብጬ… እኔ የጨበጥኩት የጥቅስ ዘለላ ይሄ ነው። የቱ እንደሚበልጥ እንደሚዛናችሁ መዝኑት።  


 


iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

Leave Your Comment

Post a Comment

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement