Komentar baru

Advertisement

ተመስገን ገብሬ

Eriyot Alemu
Mar 6, 2022
Last Updated 2023-08-21T03:47:22Z
Advertisement





ከዕለታት በአንድ ቀን የጉለሌው ሰካራም የተሰኘ እጅግ ያጠረ አጭር ልቦለድ አነበብኩ። የሆነ ነገሩ ገረመኝ ግን ስፋቱን አላስተዋልኩትም ነበር። ወይም በወቅቱ ስፋቱን የምረዳበት ሁኔታ ላይ አልነበርኩም። ጊዜ ሄዶ ጊዜ መጣና በሆነ አጋጣሚ በድጋሚ አነበብኩት። በስፋቱ ተደመምኩ። ምናልባት ተመስገን ገብሬ ፅሁፉን የፃፈበትን መስመር በግል ተመክሮም በንባብም በደንብ የተረዳሁበት ወቅት ላይ ስለነበርኩ ነው። ፅሁፉ ቢያጥርም ነገሮቹን ሰብስቦ የገለፀበት መንገድ ባሰብኩት ቁጥር ደጋግሞ ዛሬም ድረስ ይገርመኛል። ተመስገን በልብወለድ ውስጥ የፃፈው ሳይንስ ነው። ያውም እጅግ ድሮ ላይ። በዛች አጭር ፅሁፉ አዕምሮውንም ያየሁ ይመስለኛል። ከዛ ስለሱ ብዙ ማወቅ ፈለኩ። 

በሁለተኛ ዙር ባነበብኩት ጊዜ በሆነ ንሸጣ የፅሁፉን የግሌ ትርጓሜዬን ፌስቡክ ላይ አጠር አርጌ ፃፍኩ።  ቀይቷል ያኔ ፌስቡክ እጠቀም ነበር(ለአንዳንዶች :-) )። በኋላ ፅሁፉን እዚም ብሎጌ ላይ ፃፍኩትና ብዙ ሰው አየው። 
ፅሁፉ ይሄ ነው የጉለሌው ሰካራም ከልቦለድነት…  እናም በተለያዩ አጋጣሚ ከቅርቦቼ ጋር ሳወራ ስለ ተመስገን ገብሬ ሲነሳ እኔ ትዝ እንደምላቸው ይነግሩኛል። በዚህ ጉዳይ ሁሌም ቅር እሰኛለሁ። ውስጤ ተመስገንን በሚገባው ልክ እንዳልገለፀው ያምን ነበር። 


በኋላ አርአያ ሰብ የሚል ፕሮግራም ላይ ህሊና አዘዘ በሁለት ክፍል የገዛ ልጁን እና ጥበቡ በለጠን ዋቢ አርጋ የሰራችውን ቆንጅዬ ዝግጅት አየሁና ተመስገን ሌላም ሌላም በአድናቆት የሚተርከው ሰው እንዳለ ተረዳሁ። እጅግም ደስም አለኝ። ይሄ ፕሮግራም ደግሞ እሱ የሰራቸውን ሁሉ ፈልጌ እንዳይ ቢገፋኝም መዳረሻቸው ግን ሩቅ ነው። ለምሳሌ እንግሊዝ ውስጥ new times and ethiopia news በሚል በሚታወቅ፣ በሲልቪያ ፓንክረስት  አማካኝነት በሚታተመው ጋዜጣ ላይ ተመስገን የፃፋቸውን  ፅሁፎች ራሴ ማንበብ ብችል አንዱ ምኞቴ ነበር። በምችለው መጠን ግን ፈላልጌያለሁ። The Addis Ababa Massacre Italy’s National Shame የሚል መፅሃፍ ላይ የተመስገንን የአይን እማኝነት እና ጋዜጣው ላይ ከወጡ ፅሁፎቹ ውስጥ በገፅ ዋቢ አርጎ ይጠቅሰዋል። በሃገራችን በሃገራችን ዙሪያ የተሰሩ ስራዎች ለምን እንደማይኖሩን ግን ሁሌም ግራ የሚገባኝ ጉዳይ ነው። 

እዛ መፅሃፍ ላይ ከተጠቀሰው ስራው ውጪ በጥንቆላ ዙሪያ ያለውን አመለካከት የማግኘት እድሉ ቢኖረኝ ዋነኛ መዳረሻ ግቤም ነው። ምናልባት በዕድል ይሄን የሚያነብ ሰው መንገድ ቢጠቁመኝ ውለታውን በምስጋና ከፍዬ ከፍዬ አልጨርሰውም። ምናልባት በኤርትራ ድምፅ ጋዜጣ የፃፈውን የማግኘት ዕድሉ ያለው ሰው ማለቴም ጭምር ነው። ብቻ መንገድ ጠቁሙኝ።

ህይወቴ ላይ ስለ ጥንቆላ ያለውን አጠቃላይ ሃሳብ አይቼዋለሁ። ተጨማሪ ስለፈለኩ ነው። ሌላው ህይወቴ ገፅ 62 ላይ “ከዚያ ጌታ በሌለው ቦዘን ጊዜዬ ‘ባለፀጋው በድሃው ጥላ’ የምትባል አንድ አዋልድ መጽሐፍ ፃፍሁ” ይላል። ስለዚህ መፅሃፉ ምንም አልሰማውም። እንዳልታተመ ራሱ ቢናገርም ማን ያውቃል በሚል ላንሳው ብዬም ነው።

በቅርቡ ታድያ የቆዩ ዶሴዎች ሳገላብጥ 2005 ከታተመ አንድ ፅሁፍ ጋር ተፋጠጥኩ። ፀሃፊው እንዳለጌታ ከበደ ነው። በሁለት ሳምንት ተከታትሎ በኢትዮ ታይምስ (ፍትሕ) መፅሄት ላይ የወጣ ፅሁፍ ነው። የፅሁፉ አላማ ሕዝባችንን በተለያዩ ታዋቂ ሰዎች ተምሳሌትነት ማቅረብ ነው። ገረመኝ። ደነቀኝ። ተደመምኩ። እዚጋር የእንዳለጌታን ነገሮችን በዚ መልኩ ነገሮችን ጠቅልሎ የማቅረብ አቅምን ዝም ብሎ ማለፍ ነውር ስለሆነ አድናቆቴን እጅግ ዝቅ ብዬ ገልጬ ብቻ ልለፍ። የዚ ፅሁፍ መንፈስ የፅሁፉ ዝርዝር  ስላልሆነ ነው በአጭሩ ያለፍኩት። 

እዚህ ጋር በምሳሌነት ከጠቀሳቸው ታዋቂ ሰዎች መሃል ስለ ተመስገን ገብሬ የፃፈውን ልጋብዛችሁ ነው። የሌሎቹ ታዋቂ ሰዎች ስም የዚ ፅሁፍ አላማ ስላልሆነ በምንም መልኩ አላነሳውም። እንዳለጌታም ይሄን የማንበብ አጋጣሚው ድንገት ከኖረው ከፅሁፉ ውስጥ ቆርጬ ያወጣሁት የስም ዝርዝሮቹ በዚ መንፈስ እንደሆነ ሳልነግረው ቢረዳኝም ማለት ስላለብኝ ግን ብዬዋለሁ። 

ወደ መጨረሻው በእንዳለጌታ ወደተፃፈው ፅሁፍ ከማለፌ በፊት ግን፣ እዚጋር ራሱ እንዳለጌታ ስለ ተመስገን አድናቆት በፃፈው ልክ እኔ ደግሞ እርሱ ራሱን እጅግ ተንከባልዬ ማድነቄን ሳልነግረው አላልፍም ። ብዙ ክብር እና እጅ መንሳት ለእንዳለጌታ ከበደ ብዬ ስለ ተመስገን ወደፃፈው ፅሁፍ እወስዳችኋለሁ። 



ሠ. ተመስገን ገብሬዎች እነሆ! 
(በእንዳለጌታ ከበደ)

ስለተመስገን ገብሬ አሁንም  ልተርክ  ነው፤ ከዚህ  ቀደም  ‹ከማደንቃቸው  ሰዎች አንዱ›  ስለመሆኑ  በሌላ  አጋጣሚ፤ ለአድማጮች አውርቼ ነበር፤ ተመስገን  ገብሬ፤  ብዙ  ያልተባለለት፤ የኢትዮጵያ  የመጀመሪያው  ዘመናዊ አጭር  ልቦለድ  ደራሲ፤  የመጀመሪያው ያሰኘውን  ብቸኛ  እና  ነጠላ  አጭር ልቦለዱን  ‹የጉለሌው  ሠካራም›ን ለማየት  ሁለት  ሦስት  ወራት  ሲቀሩት ሞት  የቀደመው፤  ከ63  ዓመት  በፊት (72 ዓመት በሚለው ያዙት) ግብዓተ ሕይወቱ የተፈፀመ፡፡ 

ከአምስት  አመት  በፊት (ይሄ ፅሁፍ የወጣው በ2005 ስለነበር ከ14 አመት በፊት በሚለው ያዙት) ፤ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር፤ አጫጭር  ልቦለዶች  ብቻ  የሚነበቡበት አንድ  ጉባዔ፤  በኢትዮጵያ  ብሔራዊ ቴአትር  አሠናዳ፤  መታሰቢያነቱም ለተመስገን  አደረገው፤  ‹የጉለሌው ሠካራምም›  ተተረከ፤  ስለ  የሕይወት ታሪኩም  ብዙ  የሚታወቅ  ነገር እንደሌለ  ተነገረ፤  መድረክ  ላይ የሆነው  ሁሉ፤  በኢቲቪ  ተላለፈ፤ ይህን  ያዩ  የደራሲው  ቤተሰቦች፤ አባታችንን  እናንተ  በምትሉት  ልክ አናውቀውም፤  ሳናውቀው  ነው  ሞት የቀደመው  አሉና፤  እናታችን  አደራ በማለት  የሰጠችን፤  በእርሳስ  የተፃፈ፤ ያልተጠናቀቀ፤  ከመቶ  ገፅ  የበለጠ፤  60 ዓመት  ያስቆጠረ  ረቂቅ  ድርሰት  ይዘን መጥተናልና  እዩት  እስኪ  አሉንና፤ ሳይሸጥ  የቀረ፤  ቤት  ውስጥ  የተቀመጠ (———) አለና  ማኅበሩ ይረከበን ብለው ይዘው መጡ፡፡ 

ከዚያ  በኋላ፤  በእርሳስ የተፃፈችዋ፤  ‹ሕይወቴ›  ታተመች፤ ተመስገንን  ብቻ  ሳይሆን፤  የዘመኑን መንፈስ ቃኘንበት፤ የአተራረክ ብቃቱን  ብቻ  ሳይሆን፤  እሱና  ሌሎች አርበኞች፤ በየካቲት 12/1929 ዓ.ም.፤  ስለተጎነጩት  የመስዋዕትነት ፅዋ  አወቅንበት፤  በጣሊያን  ወረራ ጊዜ የዚያን ዘመን ትውልድ አባላት፤  ሀገር  እና  ባንዲራ  የሚባል መስቀል  ተሸክመው፤  ምን  ያህል ጊዜ  እንደተገረፉ፤  ምን  ያህል  ጊዜ እንደተወገዙ፤  ምን  ያህል  ጊዜ  ቀራኒዮ ተራራ  ላይ  ወጥተው  ለነፃነት  ብለው በፋሽስት  ምስማር  እንደተቸነከሩ አየንበት፡፡ 

‹የጉለሌው  ሠካራም› ውስጥ  ተበጀ  የተባለውን  ገፀባህርይ የሚገልፅበት  አንድ  ዐረፍተ  ነገር፤ ራሡ  ተመስገን  ገብሬን  ይገልፀዋል ብዬ  አምናለሁ፤  ‹የሕይወቱ  ታሪክ ፍፁም ገድል ነው› 

ተመስገን ገብሬ፤ በአክብሮት እንደሚያነሳው፤  የልጅነት  መምህሩ፤ እንደ  ኑሬ  ነው  ‹…ኑሬ  እውር  ነው፤ ግን  ለተማሪዎች  ሁሉ  የሚያስደንቅ ብርሃን  ነበር፡፡  እኛ  ጭቃማ  በሆነው በጠባቡ  መንገድ  መራነው፡፡  እርሱ  ግን በተሻለው  በእውቀት  መንገድ  መራን፡፡ ምሽት  የለውም፤  ግን  የሁላችን  አባት ነበር፡፡  ወላጆቻችን  ገንዘብ  ስላልከፈሉት ይርበው  ነበር፤  እና  ግን  ብዙ  በሆነ ጊዜ  ረሃብን  ይረሣው  ነበር….(ገፅ  21- ሕይወቴ) 

ተመስገን  ስለራሱ  ሲፅፍ አፅድቶ  እና  አንፅቶ  አይደለም፤  በ15 ዓመቱ  ኮከብ  እየቆጠረ፤  የጥንቆላ መጻሕፍት  እያነበበ፤  ጉቦ  እየተቀበለ፤ ራሱን ያስተዳድር እንደነበር ሲፅፍ፤  ግልፅነቱ  እንጂ  ችሎታው አይመስጠንም፡፡  ‹…ምንም  እንኳን አሁን  ድሆችን  በጉቦ  በማስጨነቅ ብጨክን፤  ምን  መሆኑን  ለማላውቀው አንድ  ታላቅ  ነገር  ሰማዕት  ለመሆን ከልጅነቴ  አብሮኝ  ምኞት  አድጎአል› ይለናል-ራሱ፡፡

ይህቺ  ከልጅነቱ  ጀምሮ አብራው  ያደገችው  ምኞት  ብዙ  ዋጋ አስከፍላዋለች፤  ‹…ለታላቅ  ተጋድሎ ይልቁንም ሌሎችን ለመታደግ ራሳቸውን  ለመስዋዕትነት  አሳልፈው ለመስጠት  ታላቁን  የእሳት  ነበልባልና የተሳለውን ሰይፍ በመድፈር ባደረጉት ለመገናኘት ሌሎችን በማሰማው  በሰማዕታት  ታሪክ  ደስ ብሎኝ  ከእነርሱ  እንደ  አንዱ  ለመሆን ተመኝቼ  ነበር  (ገፅ  41)›  ብሎ የተጓዘበት  መንገድ  አሁን  ስሙን እንዳነሳው ምክንያት ሆኖኛል፡፡ 

ተመስገን  ተናጋሪ  ነው፤ እሱና  ወዳጆቹ  ባቋቋሙት  ማሕበር፤ በየቤተክርስቲያን  ቅፅር  ግቢ  እየተገኘ፤ ስለሰማያዊ  ሕይወት  በሚነገርበት መድረክ፤  ስለምድራዊ  ኑሮ  በመተረክ፤ ብዙ አድናቂዎችን  ቢያተርፍም፤ የእንግሊዝ  ሰላይ  ነው  ተብሎ፤ በሚከተለው  ሃይማኖት  ሰበብ  መወገዝ ሆኖ  ነበር  ዕጣ  ፈንታው፤  ያደነቁት አናናቁት፤  ያከበሩት  አዋረዱት፤  እሱና ጓደኛው  በጃንሆይ  ትዕዛዝ  ከአደባባይ ራቁ  ከመድረክ  ወረዱ፤  ‹በሃገር  ላይ ሁከት  የሚሰሩ…›  ስለመሆናቸው ተነግሮ አንደበታቸውን እንዲቆልፉ ተደረገ።

ተመስገን፤  በጣሊያን  ወረራ ጊዜ፤  ብዙ  ተንገላትቷል፤  ወገኖቹ ተማርከው  በውሃ  ጥም  ምክንያት  ደም የተቀላቀለበት  ውሃ  ሲጠጡ  አይቷል፤ በእሱ  እና  በወገኖቹ  ላይ  እየደረሰ ያለውን  በደል  ለጃንሆይ  በሚፅፍላቸው ጊዜ፤  ጃንሆይ  በስደት  አገር  በለንደን ሆነው  ያለቅሱ  እንደነበር  ተፅፏል፤ ጣሊያን  ድል  ከሆነች  በኋላ  ግን፤ ሀገር  የማስተዳደር  አቅም  ያላቸው ተብለው  አንዳንድ  አርበኞች  ሲሾሙ እና  ሲሸለሙ፤  ተመስገን  ጃንሆይ ፊት  ቀርቦ  መሬት  እንዲሰጡት እና  የቡራኬው  ተቋዳሽ  እንዲሆን፤ በሹማምንት  ግፊት  ቢደረግበትም፤ ግብዣውን  ሳይቀበል  በመቅረቱ መንግስት ጥርስ ውስጥ ገባ፡፡ 

የሆነው  ሆኖ፤  ‹ኒው ታይምስ  ኤንድ  ኢትዮጵያን  ኒውስ› የሚል  ጋዜጣ፤  ‹ኢትዮጵያን  ከራሱ አብልጦ  የሚወድ….  ስራዬ  ከቶ በሕዝብ  ዘንድ  ይታወቅልኝ  ባይ ያልሆነ…  እግዚአብሔርንና  ሰውን ለማገልገል  የተፈጠረ…  የተወደደ ባል  እና  አስተዋይ  አባት›  ብሎ የገለፀው  ተመስገን  ገብሬ፤  እነማን እንደሆኑ ያልታወቁ  (የጃንሆይ ወዳጆች  ወይም  ሕዝቡን  በዘበዛችሁት ብሎ  ያጋለጣቸው  ጠንቋዮች  ወይም  ሌሎች  ሊሆኑ  ይችላሉ)  የተመረዘ ምግብ አብልተውት ሞተ፡፡ 

…ተመስገን  ገብሬ  ከርቀት ይኼ  ነው፤  በቅርበት  ለማወቅ ‹ሕይወቴ›ን ማንበብ ግድ ነው፡፡ እንደ  ተመስገን  ገብሬ  ያሉ ሰዎች  ጥቂቶች  ናቸው፤  ተመስገን ገብሬዎች  የምላቸው፤  እውነተኞችን ነው (እስካሁን ድረስ (ከሀ እስከ መ ስለጠቀስኳቸው ሰዎች ስፅፍ)፤  ራሴን  ከትቼ  እኔን  አስገብቼ ነበር፤  በድክመታቸው  ውስጥም  ሆነ በብስለታቸው  ውስጥ  ራሴን  አግኝቼው አውቃለሁና፤ በከፊልም ሆነ በጨረፍታ  እነሱን  የሚመስል  ነገር በሕይወቴ  ውስጥ  አልፎ  ያውቃልና፤ ስለተመስገን  ገብሬዎች  ስተርክ  ግን፤ ራሴን ከዚህ ቅጥር አስወጣለሁ) 

…እና ተመስገን ገብሬዎች፤  ለአገራቸው  ደህንነት  እና ለወገናቸው  የተሻለ  ሕይወት  በብዙ ይደክማሉ፤  የድካማቸው  ፍሬ  ግን አይከፈላቸውም፤  ሹመት  ሽልማት አይቸራቸውም፤  እንኳንስ  አገር  ውለታ ቆጥሮ፤  ‹አሁን  እንደዚህ  እንድኖር ደምና  አጥንት  ከከፈሉት  ወገን  አንዱ ነህ!›  ሊለው  ቀርቶ፤  በሥጋ  እና  በደም የሚዋለዱት  እንኳን  ‹ጠንቅቀው አያውቁትም፤  ሕይወቱ  በፍፁም  ገድል የተሞላ መሆኑን አይመሰክሩም፡፡ 

ተመስገን ገብሬዎችን ተከትለው፤ እሱን ፊታውራሪ አድርገው  ከኋላ  የሚሰለፉ  ሰዎች፤ ብዛታቸው  ጥቂት  ነው፤  ጥቂት ቢሆኑም  ለአገራቸው  ምሰሶዎች ናቸው፤  ምሰሶ  እንደነበሩ  የሚታወቁት ግን  ዘግይቶ  ነው፤  እድሜያቸው  ከሄደ፤ የልጅ  ልጆቻቸው  ከመጡ፤  50  እና 60ኛ  የሙት  ዓመታቸው  ሲከበር…  (የሀበሻ  ጀብዱ  ላይ  ያነበብነው፤  የሰላሌ ኦሮሞ  ተወላጅ  የሆነው፤  ምኒልክ ይሙት  ብሎ  ለማንም  ወደኋላ የማይመለሰው፤  በአፄ  ኃይለሥላሴ ዘንድ  እንኳን  የተፈራው  አቢቹን  ልብ ይሏል?)

ተመስገን ገብሬዎች መንገዳቸው የጨዋ ነው፤ አነጋገራቸው የጭምት  ነው፤  በገድላት  እና በድርሣናት  ውስጥ  እንደምናገኛቸው ሰማዕታት፤  ራሳቸውን  ለተከበረ  ነገር ያጩ  ናቸው፤  ለተከታዮቻቸው  ግድ አላቸው፤  የሆነ  ሰው፤  የሆነ  ቦታ  ሆኖ፤ ለአርአያነት  ሊመርጣቸው  እንደሚችል ግምት  አላቸው፤  ተከታዮቼ  ወዴት ናችሁ  ብለው  ግን  አይፈልጉም፤ የሚታመኑት ለሃሳባቸው ነው፡፡ 

ተመስገን ገብሬዎች አሟሟታቸው  ሁሉ  ምስጢራዊ ይሆናል-  አንዳንድ  ጊዜ፤  የሞቀ  የደመቀ ስርዓተ  ቀብር  አይፈፀምላቸውም፤ ስለራሳቸው  ገድል  እና  ስለስራቸው  ድል የመዘመር  አባዜ  ስላልተፀናወታቸው፤ ስማቸው  የተደበቀ  ነው፤  በመጋረጃ የተከለለ፡፡  በተቀናቃኞቻቸው  እጅ  ነው የሕይወት  ገመዳቸው  የሚያጥረው፤ የቆሙለት  እውነት  ነው  ጠላት የሚያፈራባቸው፡፡ 

…የሆነ  ነገር  ጀማሪዎች ናቸው፤  ‹ማንም  ባልሄደበት  መንገድ እንሂድ›  ብለው  ግን  አይደለም ጉዞአቸውን  የሚጀምሩት፤  እነሱ ስለፈለጉ፣  የሚያስፈልግ  ስለመሰላቸው እና  ልባቸው  ስለፈቀደ  አንድ  አዲስ ሀሳብ  አምጠው ይወልዳሉ፤ የወለዱትን የሃሳብ ፍሬ ግን አያዩትም… 

እንደዚህ  ዓይነት  ሰዎች፤ ደግሜ  እነግራችኋለሁ፤  በቁጥር ጥቂቶች  ናቸው፤  አስፈላጊነታቸው የሚገባን  ዘግይቶ  ነው፤  ለመታየት በሚጓጉ  እና ሌላውን  ዝቅ  አድርገው ከፍታ  ቦታ  ላይ  ለመቆም  በሚታትሩ ሰዎች  ይሸፈናሉ፤  አርበኝነታቸው  ጦር ሜዳ  ሄዶ  ተጋድሎ  ለመፈፀም  ብቻ የሚዘከር  አይደለም፤  አንደበታቸውም፤ ብዕራቸውም  ለሃቅ  የቆመ  እና ለእውነት የተገራ ነው፡፡ እንዲህ  ናቸው  ተመስገን ገብሬዎች።
iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

2 comments:

  1. ተስፋዬ ለሜሳ አርሂቡ ላይ ሲቀርብ አንተ ድሮ የፃፍከው ትዝ ብሎኝ ደውዬልህ ነበር። አንተ ከፃፍከው በፊት አላውቀውም ነበር። ሪታ ፈልፍሎ በማውጣት የሚችልህ የለም ስለ ተስፋዬ የፃፍከው ግን እዚህ የለም። ጠፍቶብህ ከሆነ እንኳ እኔ ሴቭ ያረኩት አለ። ሪታ ሼር ማደረጊያውንም አስብበት። ይገባኛል ግን የምሬን ነው።

    ReplyDelete
    Replies
    1. ሳሚ ሳሚነት ብረቱ ይቅር በለኝ አላየሁትም ሆኖ ነው። ኮመንት ማያውን ብዙ ጊዜ አላየውም። ከዚ በኋላ ለመታረም ዝግጁ ነኝ። አዎ ደውለህ ነበር። አስታዋሽ አያሳጣህ። ያኔም ዛሬም አመሰግናለሁ። የተስፋዬ ስራ ሙዚቃ ነው። ሙዚቃ ደሞ ሰው ያስታውሰኝና እቆዝምብሃለሁ ሃሃሃሀሃሃ ስቀልድ ነው natidanhaile@gmail.com አሁኑኑ አያይዝልኝ። እዚህ ባልፖስተው እንኳ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ። ሌላም ሴቭ ያረከው ካለ በነካ እጅህ….. ሳሚ ከልቤ ከልቤ አመስግኛለሁ። የቀረውን አስተያየትህን መቀበሌን በቃል ሳየረሆን በተግባር ነው የማሳይህ። ዛሬ ወይ ነገ! ይመችህ ጓዴ።

      Delete

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement