Advertisement
እንደ ተለመደውም ንግስት ሆይ ሺ አመት ይንገሱ ብለው አደገደጉና፣ ብዙ ተራ ሰዎች ጥርሳቸውን ሲነቀሉ እንዳዩና ጥርስ መነቀል ተራ ኢምንት ነገር እንደሆነ ተናግረው… ያወሩትም እውነት መሆኑን ለማሳየት ፊለፊቷ ራሳቸው መነቀል እንደሚችሉ ያብራራሉ። ኤልሲም ያለ ምንም ይሉኝታ "እስቲ ያሳዩኝ" ብላ አዛውንቱን ፊቷ እንዲቀመጡ በንግስትኛ ትወስናለች… ያው በፒንሳ ይሆናል ብለን እናስባለን በዛ ጊዜ ፒንሳ ከነበረ… ካልሆነም በሆነ ብረት ነው የሚሆነው… ብቻ አዛውንቱ ጥርሳቸውን ነክሰው፣ ጥርሳቸውን ተነቅለው ለንግስቲቱ ያላቸውን ክብር፣ ፍቅር ወዘተርፈ አሳዩ። ከዛ በኋላ ኤልሲ የምትወደውን ቆሎ በነፃነት መቆርጠም ጀመረች። እንግዲህ እንዲህ ነው ኤልሳ ቆሎ የተጀመረው ሃሃሃሃ ወደጉዳያችን እንሂድ…
ሱስ አንዴ መተው ያሰበ ሰው፣ ራሱን ጥርሱ እንደተነቃነቀበት ሰው ይቁጠረው። "የተነቃነቀ ጥርስ ካልወለቀ ጤና አይሰጥም" እንዲል ብሂሉ… አንዴ መተው የፈለገ ሰው ሁነኛ መዳኛው ማስነቀሉ ብቻ ነው። ያለበለዚያ ትርፉ ከራሱ ጋር ሲጠዛጠዝ መኖሩ ነው። ይሄን የጥርስ ጉዳይ ያነሳሁት ሱስ ለሚተውም ሰው ጥሩ ምሳሌ ስለሆነ ጭምር ነው።
አንድ ሱስ ለመተው የሚታገል ሰው እፎይታውን የሚያገኘው… ልክ ጥርስ ታማሚ ጥርሱን ሲነቀል እፎይ እንደሚል… ሱሰኛውም እፎይ የሚለው ሱሱን ሙሉ በሙሉ ሲተው ብቻ ነው። "አጠቃቀሜን መቀነስ፣ ራሴን መቆጣጠር" እያለ የሚያስብ ካለ <<ሞክረህ ሞክረህ እስክትነቃ ድረስ መልካም የመጃጃል ዘመን>> ከማለት ውጪ ምንም አይባልም። ሱስ <መቀነስ> የሚባል ምርጫ የለውም። ያለው ምርጫ ሙሉ በሙሉ መተው ብቻ ነው። ለምን? የእለቱ አጀንዳችን አይደለም።
እዚህ ድረስ ከተግባባን… አንድ ሱሰኛ ሱስ መተው ሲያስብ ቀጥሎ የሚገጥመውን ደግሞ በሚገባ ማወቅ እንዳለበት እናወራለን። ቀድሞ ያወቁት ነገር ከብዙ አደጋ ያድናልና። ጥርሱን ታማሚው በጥርሱ መነቀል እፎይ ቢልም ድዱ ሙሉ በሙሉ እስኪያገግም ራሱን መንከባከብ አለበት። ከመጀመሪያ ትንንጥ ነገሮች ሊጀምር ይችላል… ምራቅ አለመትፋት ሊሆን ይችላል… ትኩስ ነገር አለመጠጣት ሊሆን ይችላል። የታዘዘለትን መዳኒት በአግባቡ ጨርሶ መውስድ ሊሆን ይችላል። ከንፋስ መከላከል ሊሆን ይችላል። ጊዜው እስኪያልፍለት ምላሱንና ድዱን አፋቅሮ መቆየትም ሊሆን ይችላል። ምላስ እና ድድ ያላቸውን ፍቅር ጥርሱን የተነቀለ ብቻ ነው የሚያውቀው… በሚገባ መዳኑን ለማወቅ ምላስ አስሬ ነው ድድን የሚቀምሰው ሃሃሃሃ ድድ የሚገጥምብበት የራሱ ጊዜ አለው፤ ሁሌ እንደዛ ሆኖ አይኖርም ነው ዋነኛው ነጥብ።
አንድ ሱሰኛም ሱስ ሲተው እፎይ ቢልም፣ እንደ ድዱ ትንሽ ጊዜ የሚያስታምማቸው ነገሮችን ሊያውቃቸው ይገባል። ለምሳሌ መደበር፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ትኩረት ያለ መሰብሰብ ችግር፣ መዝለፍለፍ፣ ራስ ምታት፣ ድባቴ፣ ቁጡ መሆን እነዚህ ቀላል የሚባሉ እንደ ድድ ህመም ያሉ ነገሮቹ ሲሆኑ……… ከወር በኋላ የሆድ ህመም፣ የልብ ምት መቀነስ፣ ጭንቅላት ውስጥ የመጨፍገግ ስሜት ሊኖርም ላይኖርም ይችላል። እንደየ ሰዉ ቢለያይም የትኛውም ሰው ግን የሆኑ ቀላል ችግሮችን አያጣም። ብዙ ሰው ሱስ ይተውና እነዚህን መሰል ችግሮች ሲገጥሙት፣ አላፊ መሆናቸውን ባለመረዳቱ ሮጦ ወደ ሱሱ ይመለሳል። እሱም በሚገባ አውቆት፣ ቤቶቹንም በሚገባ አሳውቆ የሚገባበት ግን ይሄ አያሳስበውም፤ ሁሉም አላፊ መሆነቸውን ያውቃልና። ቀድሞም ተዘጋጅቶ ስለሚጠብቃቸው እሱ ላይ ያላቸው ጉልበት አናሳ ነው፤ ሰውነቱ ሰልጥኖ ጠብቋቸዋልና።
ቤቶቹ ሲባል ብዙ ሰው በሱስ ጉዳይ ግልፅ እንዳልሆነ ይታወቃል። ሱሰኛ ስንሆንና ከቤት ውጪ የምንጠቃቀም ሲሆን ቤተሰብ የሚያውቅ አይመስለንም። ሆኖም የሱሰኛ ኑሮ ግመል ሰርቆ አጎንብሶ ነውና፤ ባንድም በሌላም ያስታውቃል። ቤቶቻችን ስለሚወዱን ላያስጨንቁን ፈልገው ቀጥታ ወሬውን ላያወሩን ይችላሉ። ግን ማወቃቸውን አትጠራጠሩ።
እናም ጊዜው አስገድዶን ስለ ሱሳችን አውርተነው ለማናውቀው የቤተሰብ አባል "ሱስ ልተው ነው የተወሰነ እገዛህ ያስፈልገኛል!" የሚለውን በቃል መናገር እጅግ ብዙ ነገር ነው የሚያቀለው። ይህን ለማድረግ ትንሽ ብቻ ነው ድፍረት የሚፈልገው። በተለይ በልዩ ሁኔታ የምንፈራውን ሰው ቢሆን… በለው! የመጨረሻ ምርጥ ነገር ነው የሚሆነው። አንደኛ አዕምሮአችን "ቤተሰቦቼ ቢያውቁ ምን ይሰማቸዋል?" ከሚል አላስፈላጊ ጭንቀት ያርፋል። ኦልረዲ እኮ ቤተሰብ ያውቅ ነበር። ይሄ ሸክም አዕምሮ ሲቀለው፣ በዛው ትርፍ ኢነርጂም ይኖረዋል። ሁለተኛ ቤተሰቡ ደግሞ፣ አጥቼዋለው ያለውን ልጁን በድጋሚ ያገኘ ስለሚመስለውና ተስፋም ስለተቀበለ፣ ለልጁ የሚሰጠው ፍቅር የተለየ ይሆናል። ከሱስ ስትፋታ ከሚያስፈልጉ ወሳኝ ነገሮች ውስጥ ደግሞ ብዙ ፍቅርና ብዙ ውሃ ይጠቀሳሉ። ሌላው ለቤቶቹ ማሳወቁ አንዱ ጥቅሙ… ቀድሞ ይገጥመኛል ያላቸው ችግር ስለሆነ ሲገጥመው የሚያዩት፣ ተጨንቀው ስለማያስጨንቁት ከባድ ጫና ያቀሉለታል። ባልደረባ ቢሆን "አቦ ቃም አትፍዘዝብን!……… ቃምበት ቃምበት… መታ መታ" እያለ ነው እሳት የሚያቀጣጥለው። እነዚህን ላልተወሰነ ጊዜ አርባ ክንድ መራቅ ነው ሃሃሃሃ
ከልምድ ሲወራ… ሱሰኛ የሆነ ሰው፣ ሱስ የሚተዉ ሰዎችን አበረታቶ አያውቅም! የሚያበረታታም አይመስለኝም። የአንዱ መተው ለሌላኛው ራሱን እንዲወቅስ ያደረገው ስለሚመስለው፣ የቻለውን ታግሎ በሱስ ውስጥ ማቆየትን ይመርጣል። ይሄ ጥሬ ሐቅ ነው። የትም ሃገር የሚሆን። ስለዚህ ይሄን ቀድሞ ያወቀ ሰው፣ የሱስ የመተው ሃሳቡን ሱስ ውስጥ ላለ ሰው ማካፈል የለበትም። አሳማኝ ምክንያት ፈጥሮ መለየቱ አዋጭ መንገድ ነው።
"ሱስ ልተው ነው" ብሎ ሌሎች ሱሰኛ ወዳጆቹን ከተለየ ራሱ ላይ ነው ፈተና የሚያዘንበው። ባልተለመደ ሁኔታ ጎትጉቶ ሊጋብዘው ደጁ የሚሰለፍ ሲበዛ ሊመለከት ይችላል። የአንድን ሰው ልምድ እዚ ጋር ስጠቅስ… ያ አንድ ሰው ስድስት ወር ጫት ሲተው ሁሉም ባልደረቦቹ የሚያውቁት ጫት ቤት መቀየሩን ብቻ ነበር። አንድም ሰው ጫት እየተወ እንደነበር አያውቅም። ከስድስት ወሩ በኋላ እንዳዲስ ልተው ነው ብሎ አውርቶ ያየውን ፈተና እሱ እና እሱ ብቻ ነው የሚያውቁት። ስለዚህ ለሁሉ ነገር መላ ያስፈልጋል። ሌላው ደግሞ የራሱ የሚለውን፣ የሚስማማውን መላ ይፍጠር ማለት ነው። በተለይ ለጫት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት እስከ ስድስት ወር ድረስ ሴንሴቲቭ ናቸው። እዚጋ መያዝ ያለብን ነጥብ ሱስ ውስጥ ያለ ሰው፣ ሌላ ሰው ሲተው… የሚፈትነው መጥፎ ሰው ሆኖ አይደለም። እንደዛ እንዳትረዱብኝ። እኛም ብንሆን ቦታው ላይ ብንሆን የምናደርገው ነው። "አንኮሽየስሊ" የሚደረግ ነገር ነው። ከጥሩነት ከክፉነት ጋር አይያያዝም።
ታድያሳ ጉዳያችንን ገፋ ስናደርገው "ዘፈንን ዘፈን ያነሳዋል" ቢሉም ባይሉም አቀናባሪዎች…
እሱባለው ይታየው የሺ፣ የህንድ ሙዚቃ የሚመስል ክሊፕ ያለው፣ <ሲከፋሽ አልወድም> የሚል ዘፈን አለው… እዛ ውስጥም ይሄ አለ
"የማልደራደርባቸው መሃል መሃል
የምወድሽ የኔን የኔን ያሃል ያሃል"
የመጀመሪያውን ስንኝ ይዘን እንቀጥል…
ከሱስ ስንፋታ "የማልደራደርባቸው መሃል መሃል…" ብለን ለሰውም ለራሳችንም የምንዘፍናቸው ጉዳዮች ሊኖሩ ግድ ይሉናል። ዝምብዬ እንደምሳሌ፣ እንደ ነገሩ 5 ላንሳ… ሌላው ደግሞ የራሱን ያዘጋጃል።
1) እምቢኝ ማለት መልመድ! ይሉኝታ ማቆም!
አዲሱ የህይወት መስመር ትንሽ መንሸራተት ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል አውቆ፣ ከአዲሱ ህይወት ጋር የማይሄድን ነገር ያለምንም ይሉኝታ እምቢኝ እያሉ ዙሪያን ማስለመድ መጀመር!
(እኔ አልጠጣም! እኔ አልቅምም! እኔ አላጤስም… ወዘተርፈ ደጋግመው እያሉ፣ ለራስም ለሰዎችም እምቢኝን ማስረገጥ!)
2) እንቅልፍ!
በዚኛው አዲስ ህይወት፣ ሱስ እንደተዉ ሰሞን ትንሽ ጊዜ ቢያስቸግርም፣ ቆይቶ እንቅልፍ ስርዓት ይስተካከላልና… ከዛ በኋላ የሚመጣውን (ቢያንስ አንድ አመት)… በቀን የ7 እና የ8 ሰአት እንቅልፍ ወሳኝ ነው። በምንም ሁኔታ በእንቅልፍህ አለመደራደር!
3) ጉልበት!
አንዳንዴ የምግብ ሰው ባንሆን እንኳ ቡሌ ወሳኝ ነገር ነው። መምረጡ በራሱ ጊዜ የምንማረው ነገር ቢሆንም፣ የተፈጨ ቀይ ስጋ ወሳኝ ስንቅ ነው–ለብዙዎች። እዚጋ ኑሮአችንን ግምት ውስጥ ያስገባ ነገርም ማሰብ አለብን። በምንም አይነት ሁኔታ እንሁን ግን ምግብ ሳይበሉ መንቀሳቀስ ግን ፈንጅ ወረዳን እንደመርገጥ ይቆጠራል።
4) ተፈጥሮ ውስጥ መዝለቅ!
ሱስ ውስጥ ስንቆይ አንደኛው መጥፎ ጎን ራሳችን ብዙ አይሰማንም። ራሳችንን ፊል አናደርገውም። ጠንከር ሳረገው እየኖርን እንደሆነ አይታወቀንም። እና ከሱስ ስንወጣ ያን መጥፎ ስሜት ከውስጣችን አውጥተን ህይወት እንደአዲስ እንድትሰማን… ተፈጥሮ ውስጥ መዝለቅ አለብን። ሳር ላይ ተኝተን ቁጫጮች ይሂዱብን… እንዴት ደስ እንደሚል ሲያዩት ነው የሚታውቀው። በግድግዳ ታጥሮ ቂጡን ደፍኖ ሲቅም ለነበረ ሰው ትንሽዬ ኩሬ በብዙ ታስቦርቀዋለችና። ያውም የት ነበርኩ ግን እስከዛሬ? እያለ…
5) ፊልም፣ ሙዚቃ፣ መፅሃፍ…!
ሙዳችን የሆነውን ራሳችን መምረጥ… ቦክስ አሎሎ ምርኩዝ ዝላይ ካስደሰተን የት እንዳሉ የምናውቀው እኛው ነንና ያሉበትን ፍለጋ እዛው መባጠስ ነው…… የሚያዝናናን፣ ሙያም ሊያረጉት የሚፈልጉትን ነገር መምረጥ የባለቤቱ ፈንታ ነው!
ከላይ ያሉትን እንደመነሻ መያዝ በትንሹ ስህተት ላለመስራት ይጠቅማል።
ከሱስ ከተፋታን በኋላ ደግሞ እስክንረሳው ድረስ ትግሉ የየቀን መሆኑን መረሳት የለበትም። አንዱን ቀን ካሸነፍነው በኋላ ነው ነገ ነገን እየወለደ ዓመት የሚሞላው። ስለዚህ ለዚህ የየቀን ትግል በቂ ጉልበትና በቂ እንቅልፍ አስፈላጊ ናቸው። ተዳክመን የተገኘን ቀን ውስዋሱ ከባድ ነው። እናም ጥሩ ጉልበት በጥሩ እንቅልፍ ሰንቀን ቀኑን ስንጀምረው… ምን ሆኜ ነበር ድሮ ብለን በበፊት ቀኖቻችን ላይ ራሱ ሙድ እንደ መያዝ ይዳዳናል። ያኔ ውስዋሱ በዜሮ ተባዢ ነው።
ከላይ እንግዲህ ለጉልበት የሚሆን ስንቅ ምን እንደሆኑ ከተረዳን ዘንዳ ለአዕምሮ ደግሞ ስለሚሆኑ መፅሃፍት እናውራ። ሶስት እጅግ ቀሽት ቀሽት በሆኑ ሰዎች የተፃፉ መፅሃፍት አሉ። በመጀመሪያ ግን እነዚህን ሰዎች የመረጥኩበትን ምክንያት እንጨዋወት… ለብዙ ጊዜያት አብረውን ስለሚቆዩ፣ ሞቅ አርገን በደንብ እንቀበላቸው። ጭብጫቦ ጭብጫቦ ሃሃሃሃ ምክንያቱ ይኸውና…
1) ፍፁም ኦሪጅናል ናቸው።
2) ስለሚያወሩት ነገር ጠንቅቀው ያውቃሉ።
3) እየመከሩ አልያም እየሰበኩ አያዝጉም… ነጥብ ነጥቡን ነው ጨዋታቸው።
4) ከራሳችን ከውስጣችን ጋር ቀጥታ ያገናኙናል።
ትንሽ እንዳነበብናቸው የኛ የብቻችን ችግር የመሰለን ጉዳይ፣ የሁሉም በኛ መስመር ያለፉ ሰዎች አልያም የሚያልፉ ሰዎች ችግር መሆኑን ስንረዳ፣ነገሩ ትንሽ ይቀለናልና… በአንዳች የመነሳሳት ሃይልም እንሞላለን (ትንሽ ላካብድ ብዬ ነው )
★ ፩) martin nikolaus {empowering your sober self}
ይህ ሰው ከዚህ በፊት አንድ ቦታ ላይ እንደፃፍኩት… አንድን ሱስ ውስጥ ያለን ሰው ሁለት ያደርገዋል። ሶበር የሆነውን (ከሱስ በኋላ የምትጀምረውን አዲስ ሰው) እና ሱሰኛ የነበረው ሰው። የሱ መንገድ፣ ከሱስ በኋላ ያለህን ህይወት ስታጎለብተው ሱሰኛ የነበረው አንተነትህ እየሞተ ይመጣል የሚል ነው። እኔ ትንሽ ከሱ የምለየው ሱሰኛውን እንዳይነሳ አርገን ከመጀመሪያውም መግደል እንችላለን ብዬ ስለማምን ነው። ሌላ ጊዜ በዚ ርዕስ አረሳስተና ስናወራ፣ በሰፊው እናየዋለን። የዚን ሰው መፅሃፍ እስከ ምዕራፍ አራት ካነበብነው ለጊዜው በቂ ነው። ሌላው ለጊዜው ወይንም ለመጀመር ያህል አይመለከተንም። ጊዜ በብዙ ያለው ይግባበት፣ ዕውቀት አይጎልምና!
ፒዲኤፉ ይኸው empowering your sober self
★ ፪) allen carr {easy way to stop smoking, The easy way to control alcohol}
አለማችን ላይ በሱስ ዙሪያ እንደሱ እጅግ ብዙ ተፅዕኖ የፈጠረ ሰው አለ ብዬ አላስብም። የሚሊየኖችን ህይወት የቀየረ ግለሰብ ነው። እኔ ስጀምር ሱስ የተውኩት በራሴ መንገድ ነው። አምስት ወር ካለፈኝ በኋላ ነው ይሄን ሰው መጀመሪያ ያወኩት። እውነት እውነት እላችኋለሁ ቀድሜ ባውቀው ኖሮ ድሮ ብዙ መውደቅ መነሳት ሳይኖርብኝ ሱስ እተው ነበር። ዘግይቼ ስላወኩት ቆጭቶኛል። ላለፉት 7 አመታት በሱስ ዙሪያ የተፃፉ አያሌ ፅሁፎችን አይቻለሁ… እንደዚህ ሰው በብዙ ቦታ ግንባር ቀደም ሆኖ የሚጠቀስ ሰው አልገጠመኝም። ከላይ ቁጥር አንድ ላይ ያነሳሁት መፅሃፍ ፀሃፊ እንኳ መፅሃፉ ላይ በክብር ያነሳዋል። ከታች ቁጥር ሶስት ላይ የምጠቅሰውም ጭምር በክብር ያነሳዋል። የሱስን ሳይኮ ጥጥት አድርጎ የጨረሰ እንግሊዛዊ ነው።
ፒዲኤፉም ይኸው easy way to stop smoking
★ ፫) Joel spitzer {never take another puff}
ይህ ሰው ደግሞ በራሱ መንገድ… የማጨስበት ናቸው ብለህ የደረደርካቸውን ምክንያቶች በዜሮ ያባዛልሃል። ከዛ አንተም ለምንድነው የማጨሰው ትላለህ። ሲጋራ ትተህ ቆይተህ፣ ሰው ነህና ሊያጋጥም ስለሚችል… አንድ ትንሿ የሲጋራ ፓፍ እንዴት ቀድሞ የነበርክበት ቦታ ላይ እንደምትመልስህ ያሳይሃል። ቆይቶ ኔቨር ቴኩ ጋር ይዞህ ይሰምጣል።
ፒዲኤፉ ይኸው never take another puff
በቅደም ተከተላቸው መጨምጨም ግዴታ ባይሆንም አሪፍ ነው ባይ ነኝ።… የምንፈርሽ ከሆነም በሃይለኛው ፈርሸን እንጨምጭማቸው! አንድ መፅሃፍ በራሱ ሙሉ ላይሆንልን ስለሚችል፣ እነዚህ ሶስቱ ግን በእርግጠኝነት ክፍተትን በሚገባ የሚሞሉ ይመስለኛል። በሁሉም አቅጣጭ ለዛሬም ለነገም የሚሆኑ መፅሃፍት ናቸው። እኔን እንድተው ባይረዱኝም ትቼ እንድቆይ መንገድ ስለጠረጉልኝ በዛው እያመሰገንኳቸውም ነው። ውለታ እየመለስኩም ነው። እናንት መፅሃፎች ክበሩልኝ!!!
ሁለተኛው ሰውዬ Allen Carr እንደውም (አንብበን እስክንጨርስ ድረስ የምናደርገውን ነገር እንድንቀጥለው) ሁሉ ይገፋፋናል። የምትጠጣ ከሆነ አንብበህ እስክትጨርስ ጠጣ ይልሃል። የምታጨስም ከሆነ እንደዛው። በማንበብ እንደሚተውም ደረቱን ነፍቶ ያወራል። እመኑኝ እውነቱን ነው።
አንድ ነገር ላይ ሳሰምርበት ስለ ሱስ ካልገባን አልገባንም ነው። ስለ አንዱ ሱስ ገባን ማለት ደግሞ ስለ ሁሉም ሱስ ገባን ማለት ነው። አንዱን ሱስ ብቻ መተው ቻልን ማለት… ሌላው ሁሉ ሱስ እንዴት እንደሚተው ተገለፀልን ማለት ነው። የሱሳ ሱሶች ስማቸው እና አንዳንድ ከፍታቸው ቢለያይም፣ አሰራራቸው ግን አንድ አይነት ነው። በአንዱ ስንነቃ ሌላው እዳው ገብስ ነው።