Advertisement
(፩)
ሚኩ ጌትነት………………………………………
እንደነሱ አለብስም። እንደነሱ አላወራም። እንደነሱ አልራመድም። እንደነሱም ወጥቼ መግቢያ የለኝም። ዘወትር ከእንቅልፌ ስነሳ ከግቢያችን በራፍ ላይ ባለች ድንጋይ ላይ ነው የምሰጣው። እነሱም ከድንጋዩ ለይተው አያዩኝም። ይንቁኛል፤ ሲበዛ ይንቁኛል። እኔ ግን ያሳዝኑኛል፤ ሲበዛ አንጀቴን ይበሉታል። ለሰላምታ እንኳን አይናቸው አልገባም። እኔን ስለማያዩኝ እነሱን በደንብ እንዳያቸው ረድቶኛል። ለዛም ነው የሚያሳዝኑኝ፤ ውስጥ ድረስ ዘልቄ ስለማያቸው።
ድግሪ አላቸው። ስም አላቸው። ብር አላቸው። ግን አብዛኞቹ ደስተኞች አይደሉም። ፊታቸው ላይ አየዋለሁ። አልፎ አልፎም ሲያወሩ እሰማለሁ። የችግራቸው ምንጭም ምን እንደሆነ ጠንቅቄ አውቃለሁ። ደስተኛ ለመምሰል ፊታቸው ላይ የማትጠፋ ፈገግታ አለች። እርስ በራስ ይሸዋወዱ ይሆናል እንጂ እኔን አያታልሉኝም። ማታ ከዋሉበት ወደቤታቸው ሲገቡና ጠዋት ይዘውት የሚወጡትን ፊት አይቼ ድራማቸው ትገባኛለች። ቤታቸው ሲገቡ ነፍሳቸው ክፉኛ ትተክዛለች። ያም ጠዋት ፊታቸው ላይ ታትሞ አየዋለሁ። በቀን ደሞ የተለማመዷትን የተነቃቃችውን ደስተኛ የምትመስል ፊት ለማሳየት ይጥራሉ። አጥብቆ ለማያያቸው ይሸውዳሉ። እኔን ግን በጭራሽ አያታልሉኝም።
ችግራቸውን እንኳን ለሰው ለራሳቸውም ደፍረው አይነግሩትም። ደፍረው ችግር እንዳለባቸው ያመኑት እንኳን መፍትሄውን የሚፈልጉት መሰል ችግር ካለባቸው ነው። ብዙ ጊዜ ተጠግቼ ብረዳቸው እመኛለሁ። ግን ፊታቸው ሳስበው አርፌ እቀመጣለሁ። በአጠገቤ ሲያልፉ እንኳን እንድንቀሳቀስ አይፈልጉም። እንደ ሐውልት ደርቄ ስቀመጥ ነው የሚወዱት። ይሄን ስለማውቅ እጠነቀቅላቸዋለሁ። ድንገት ተሳስቼ ነቅነቅ ካልኩ እንደ እብድ ይሸሹኛል። ጣደፍ ጣደፍ እያሉ ያልፋሉ። ያኔ አዝናለሁ። በጣም ይከፋኛል።
ሁሉም "ልዩ ናቹ" ተብለው ነው በእንክብካቤ ያደጉት። ልጅነታቸው ሁሉ በቤተሰብ፣ በጎረቤት፣ በዘመድ አዝማድ በሙገሳ የታጀበ ነው። ያ የተለየ በራስ መተማመን ሰቷቸዋል። ደስተኞችም ነበሩ። አለም ሁሉ ለሁልጊዜው ለነሱ የምትወግን ይመስላቸው ነበር። የፈለጉትን ማድረግ፣ የፈለጉትን መሆን እንደሚችሉ ይሰማቸው ነበር። ደግሞም ልክ ነበሩ። በልጅነት እድሜያቸው ፍላጎታቸውም ስለ አለም ያላቸው ግንዛቤም ውስን ነበር። ህይወት ማለት ዶክተር መሆን፣ ኢንጂነር መሆን፣ ጠበቃ መሆን፣ የሂሳብ ባለሙያ መሆን—ሲፈልጉ፣ መሆን ብቻ ይመሰላቸው ነበር። ያን ማድረግ በመቻላቸውም አብዝተው ይኮሩ ነበር። ደስተኞችም ነበሩ። እንዲህ በደስታ ባህር ውስጥ ኖረው ኖረው፣ ራሳቸውን ሁሉን ቻይ አርገው ነው ኮሌጅ የገቡት።
ኮሌጅ እንደገቡ ነው ፈተናቸው የጀመረው። የፈለጉትን የለመዱትን ካለመብላት ይጀምራል ፈተናው። እነሱ ከነበሩበት የደስታ አለም ከፍ ያሉ የሚመስሉ ብዙ ሰዎች ገጠሟቸው። ያኔ ዝቅ ማለትም እንዳለ ይሰማቸው ጀመር። የለመዱት ሙገሳ፣ አድናቆት፣ ማበረታታት ለጥቂቶች ብቻ ነው ኮሌጅ ያለው። ማንም ስለማንም ዴንታ የለውም። ያኔ ነው የውስጥ ብቸኝነት ሳያውቁት ውስጣቸው የዘለቀው። አብረው ይሆናሉ ግን አብረው አይደሉም። ያገናኛቸው ጥቅም ነው። በዶርም አብሮ መሆን፣ በክላስ አብሮ መሆን፣ በጥናት አብሮ መሆን፣ በጅዘባ አብሮ መሆን ነው። በንፁህ ጓደኝነት አብሮ መሆን ያኔ ሁለተኛ ደረጃ፣ አንደኛ ደረጃ እያሉ ቀርቷል። የያኔ ንፁህ ጓደኞቻቸውም በእድል ካልሆነ አብረው ኮሌጅ አይዘልቁም። ልጅነት ላይ ያለውም ንፁህ ተፈጥሮአዊው፣ ምንም አይነት ሂሳብ የሌለበት ጓደኝነት ኮሌጅ በሚባል ገደል ሰፍቷል። አያወሩትም እንጂ ከኮሌጅ ሲወጡ ብቸኝነትን በስሱ ይዘው ወተዋል። ይሄም አንድ ያስከፋቸዋል።
ኮሌጅም ሆነው ትኩረታቸው ትምህርታቸው ነበር። ውጪ ያለውን እውነተኛ አለም አያውቁትም። እንደተነገራቸው ግን ከኮሌጅ ጥሩ ውጤት ይዞ መውጣት ውጪ ላለው ህይወት ጠቃሚ ነው። ስለዚህ አብዝተው ለትምህርታቸው ይጨነቃሉ። ይማራሉ፣ ይማራሉ፣ ይማራሉ ስለ ህይወት ግን ምንም አያውቁም። በፊት በቤተሰብ አላፊነት ነበሩ። አሁን ደግሞ በኮሌጅ። ገና ህይወትን በራስ አላፊነት አልተቀበሏትም። ሆኖም ይመኛሉ። ኮሌጅ ያለውን ፈተና፣ የትምህርት ጭንቀቱን በድል ሲያጠናቅቁት ህይወት ሞቅ አድርጋ እንድትሸልማቸው ይመኛሉ። እንደዛም የሚሆን ይመስላቸዋል። ኮሌጅም ከትምህርት ውጪ ሌላም ነገር መማር ይጀምራሉ። ትንሽ ከሚባል ስቲሙላንቶች ጀምረው እስከ ትልልቅ ድረጎች መጠቃቀም ይጀምራሉ። ለጥናት ስለሆነ ችግር የለውም ብለው ያስባሉ። ያኔ ስለ ህይወት ከራሳቸው ልምድ የሚማሩበት እድል ይመነምናል። ህይወትን አጥርተው ማየት ያቆማሉ። እንደዚህ ብዥ እንዳለባቸው እንኳን ደስ አላችሁ ተዘፍኖላቸው ሰፊውን አለም ይቀላቀላሉ። ከተሰበሰቡት ስብስብ እንደሚዘራ ዘር ይበተናሉ። ሁሉም እንደ አዘራሩ ይወድቃል።
ስራው አለም ጋር ደረሱ። ሁሉም እንደ ልፋቱ፣ እንደ ጥረቱ፣ እንደ እድሉ የሆነ ቦታ ተሰክቷል። አርፍበታለሁ ብለው ያሰቡት ቦታ ሲደርሱ፣ ህይወት እንደ አዲስ መጀመሩን ይረዳሉ። ሆኖም ራስን ክህደት ውስጥ ይወድቃሉ። የትኛውም ቦታ ያለው… …… መጀመሪያ ዳጎስ ያለ ደሞዝ የበላውም፣ አለ የተባለ መስሪያ ቤት የተቀጠረውም፣ የተመኘውን ቦታ አገኘው ብሎ ያሰበውም ሲቆይ ሰራተኛ ነው ስሙ። ሁሉም ይሰለቻል። ያኔ ልጅነታቸው ላይ የተገነባው ለራሳቸው የሚሰጡት የተጋነነ ስሜት እና ስራው አለም ላይ የተሰላቸው ማንነታቸው ሊታረቁላቸው አይችሉም። "እኔ ልዩ ሰው ነኝ" የሚለው ከንቱ እሳቤ ውስጣቸው ተቀብሮ ዛሬን እንዳይቀበሉ ጋርዷቸዋል። ራሱን የማይቀበል ነፃነት የለውም። ነፃነት የሌለው ደስታ የለውም። እናም በባዶ ሜዳ ሲኮፈሱ ሳይ ያሳዝኑኛል። ውስጣቸውን ስለማውቀው ያሳዝኑኛል።
አንዳንዴ ተከትዬ ተራነታቸውን ነግሬ ራሳቸውን እንደወረደ ተቀብለው፣ አዲስ ህይወት እንዲገነቡ ልነግራቸው እልና ፊታቸውን አስብና እተወዋለሁ። ይንቁኛል። የሚንቁት ራሳቸውን እንደሆነ ስለሚገባኝ አልቀየማቸውም። አንዳንዴ ከንቀት አልፈው የሚገላምጡኝን ተከትዬ "ስራቹን አትወዱትም። ራሳችሁን አትወዱትም። ስራችሁን ብትተዉ ደግሞ ወዴት እንደምትሄዱ ስለማታውቁ ትፈራላቹ። በስራቹ አስታካቹ ከፍታችሁን ያሳያችሁት ሰው ዝቅ ስትሉ ምን ይለኛል ብላቹ ትፈራላቹ። ስለ ሰው ነው የምትኖሩት። ለዛም ከራሳችሁ ትሸሻላችሁ። እውነትን ማየት አትፈልጉም!" ልላቸው እፈልጋለሁ። ሆኖም ጨዋነቴ፣ ራሴን መግዛቴ አስሮ ይይዘኛል።
ሆኖም እዛው ድንጋዬ ላይ ተቀምጬ አብዝቼ የምጨነቀው ስለነሱ ነው። እንዴት ተብትቦ ያሰራቸውን ኩራት በጣጥሼ ነፃ ላርጋቸው እላለሁ። እንዴት ራሳቸውን ከሚሸሹበት ሱሳቸው ልገላግላቸው እላለሁ። እንዴት ዝቅ ብሎ ከፍ ማለትን ላስተምራቸው እላለሁ። እንዴት ከገንዘብ ባርነት ላላቃቸው እላለሁ። እንዴት ወደራሳቸው ሰላም ልመልሳቸው እላለሁ። እነሱ አንድም ቀን ትዝ ብያቸው እንደማላውቅ አውቃለሁ። ግን እረዳቸዋለሁ ውስጣዊ ክህደት ውስጥ ያለ ሰው ከራሱ ውጪ ሌላው አይታየውም። ለዛ ነው ለስልጣን፣ ለገንዘብ፣ ለዝና ሲቅበዘበዝ የሚኖረው።
የሚፈልጉት እረፍት እኔጋ አለ። የሚፈልጉት ሰላም እኔጋ አለ። የሚፈልጉት ደስታ እኔጋ አለ። ግን አያዩኝም። ይንቁኛል። ፊቴ እንዴት እንደሚያበራ አስተውሎ የሚያይ የለም። ለምን ተረጋግቼ እንደተቀመጥኩ የሚጠይቅም የለም። በምን እንደምኖር፣ ስለምን እንደምኖርም ግድ አይሰጣቸውም። ዋናው የሚያሳስባቸው ከእነሱ እንደ አንዱ አለመሆኔ ብቻ ነው። ልክነትን የሚለኩት በሚመስላቸው ሰው ልክ ነው። እውነትን የሚፈልጉት በሃይማኖት ከሚመስላቸው፣ በብሄር ከሚመስላቸው፣ በአኗኗር ከሚመስላቸው ሰው ነው። እንደዛ ነው ፕሮግራም የተደረጉት። ወደ ውስጣቸው ማየትን ይፈራሉ። ይሄ የሆነበትን ምክንያት ስለማውቅ አልፈርድባቸውም። ፍፃሜያቸው፣ ተመሳስሎ ተያይዞ መጥፋት ነው። ይሄ ያሳዝነኛል። ከልቤ ነው የሚያሳዝነኝ። ይሄ ደግሞ ለሰው በማዘን የሚገኝን ደስታ ይሰጠኛል።
አንድ ቀን ከምቀመጥባት ድንጋዩ ነጥሎ የሚያየኝ ሰው እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ። ያኔም እንዲህ እለዋለሁ "አንተ ሰው አንድ ወቅት አንተ የነበርህበት ቦታ ነበርሁ። ህመምህንም ሁሉ አቀዋለሁ። የሚከፈለውን ከፍዬ ነው ራሴን ነፃ ያወጣሁት። ፈቃድህ ቢሆንና ብትጠይቀኝ መንገዱን እጠቁምህና በራስህ እግር ልክ ደልድለህ እንድትጓዝበት የምችለውን ሁሉ አረግልሃለሁ!"
እንዲህ ብቻ ነው የምለው። ተስፋ አደርጋለሁ! አንድ ቀን ይሄ ይሆናል! አንድ ቀን ከድንጋዩ ለይቶ የሚያየኝ ይመጣል!
(፪)
ሚኩ ኮስተር ብሎ ሲያወራ ያስፈራኛል። ሚኩ ኮስታራ አይደለም። በፍፁም። ይልቅ ስለ ሚኩ እኔ ልንገራችሁ።
***
ዓለም ፍትሃዊ አይደለችም። ሁሌም ለስኬታማ ሰዎች እንዳሽቃበጠች ነው። ግን እንደ ሚኩ ዓይነት ብዙ ያልተሳካላቸው ሰዎች በጉያዋ ወሽቃ ይዛለች። ይሄ በውነቱ ያሳዝናል። ይሄን ፍርደ ገምድልነቷን ከምን እንዳመጣችው ለባለሞያዎች ትቼ… እጅግ ያልተሳካለትን ሚኩ ጌትነት ታሪክ ልንገራችሁ።
ሚኩ በጠዋት ይነሳና አልጋውን ያነጥፋል። ይሄ አስቂኝ አጀማመር ነው። ሲጀምር ሚኩ በጠዋት አይነሳም። ሲቀጥል ሲነሳም አልጋውን አያነጥፍም። ብዙ ሰዎች በጠዋት ይነሱና አልጋቸውን ያነጥፋሉ። በጠዋት ተነስተውም አልጋቸውን የማያነጥፉ አሉ። አርፍደው ተነስተውም የሚያነጥፉ አሉ። መረር ሲልም፣ ሆቴል ያደሩበትንም አልጋ ካላነጠፍን ብለው ከራሳቸው ጋር የሚግደረደሩ አይጠፉም። ቁምነገሩ ግን ሚኩ ስለ አልጋ ማንጠፍ የሚያስበው ነገር ነው።
ማታ ለብሶ የተኛውን ሲነሳ ግራ እጁንና ግራ እግሩን በማስተባበር ወደ ግራ ጥግ ግድግዳ አስደግፎት እንጣጥ ብሎ ከአልጋው ይወርዳል። ወደ ቀኝ ማረግም ይችላል። ግን ግድግዳው ያለው በግራ በኩል ስለሆነና የሚወርደው በቀኝ በኩል ስለሆነ ነው። "ይሄ ሮኬት ሳይንስ አይደለም!" እንዲሉ የፈረንጅ ፀሃፍት– የዚን ሃሳብ ቅለትና የሮኬት ሳይንስን ክብደት ባንድ ጊዜ መናገር ሲፈልጉ። "ባንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ" እንዲሉ የኛ ሰዎች።
አንዳንዴ አስብ አስብ ሲለው ቁጭ ይልና… በጥልቀት እንደሚያስቡ ሰዎች አገጩን በእጁ ያስደግፍና ፀሃይ እየሞቀ ያስባል። "አልጋ ማንጠፍ ምን ጥቅም አለው?… ለመጀመሪያ ጊዜ አልጋ ያነጠፈውን ሰውዬ ወይ ሴትዮስ ታሪክ መዝግቧቸዋል ወይ? … ተመዝግቦ ቢሆንም ባይሆንም ምን አስቦ ነው ያነጠፈውስ?" እያለ ማሰላሰሉን ይቀጥላል…
"በርግጥ አልጋ ስታነጥፍ… ማታ የተኛህበት ላይ ቆሻሻ ነገር ካለ ታራግፋለህ። እኔ ደሞ ሙሉ ራቁቴን ነው ወደ አልጋዬ የማመራው። ራሴን ካላራገፍኩ በቀር የሚራገፍስ ቆሻሻ የለኝም። … አሁንም በርግጥ አልጋው የተነጠፈ ካልተነጠፈ አልጋ እይታው ደስ ይላል። በተለይ ሌላ ሰው ሲያየው። እኔ ሁሌ አልጋዬን ስለማየው ቢነጠፍም ባይነጠፍም ልዩነቱን ልብ አልለውም። መኝታ ቤቴን ደሞ ለማንም አስጎብኝቼ አላውቅም። እንደውም ጠዋት ያስተካከልኩትን ማታ መደርመስ ኃጢያት መስሎ ነው የሚሰማኝ። በዚስ የተነሳ (በማንጠፉ ማለቱ ነው)… በዚስ የተነሳ የሚባክነው ጊዜስ?… ስለዚህ ባለማንጠፌ ጊዜዬን ቆጥቢያለሁ ማለት ነው" እያለ እያለ ከራሱ ጋር ይማከራል።
አሁን እንዲህ ሲያስብ ህይወቱን በአግባቡ የሚመራ፣ ስለ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ጭምር የሚጨነቅ ሰው አይመስልም? ሌባ በሉት። በአደገኛ ሁኔታ የተጫጫነውን ስንፍና በሃሳቡ የሚጫንበት ሁነኛ ዘዴው ነው። ዓለም ስለ ስንት ነገር በምትጨነቅበት በዚህ ቀውጢ ሰዓት ስለ አልጋ ማንጠፍ ጥቅምና ጉዳት ማሰብ በራሱ የሚኩን ህይወት ቁልጭ አርጎ የሚያሳይ ባይሆን እንኳ የሚያስገምተው ይመስላል።
ሚኩ ጌትነት ጋር ቁርስ ብሎ ነገር የለም። ከተነሳና ፀሃይ ካለች ይሞቃታል። ከሌለች ደሞ አይሞቃትም። "በጥሩ ቁርስ የተጀመረ ቀን… " ምናምን የሚል ወሬ ሲሰማ ከልቡ ያስቀዋል። "ዲስኩራም ሁላ!" ይላል። "የቁርስ መብላት 36 ጥቅሞች!" የሚል ነገር ሲገጥመው ደግሞ 36 ጊዜ ቆጥሮ ይስቅና (ቆጥሮ መሳቅ ምን ማለት እንደሆነ እሱ ይወቀው) … "እስከመቼ ስራ ፈተው… ስራ ያስፈቱናል?" ይላል ትንሽ ኮስተር ብሎ። ከሱ የባሰ ስራ ፈት እንዳለ ሁሉ።
አንዳንዴ አስብ አስብ ሲለው ቁጭ ይልና… በጥልቀት እንደሚያስቡ ሰዎች የቀኝ እጁን መሪ ጣት የቀኝ ጭንቅላት ክፍሉን ያስደግፍና ፀሃይ እየሞቀ ያስባል።
"ስለ አዳም ቁርስ መብላት እንዴት ነው የገባን?… አብስሎ መብላት ከመጀመሩ በፊት፣ ሰዎች የበሰለውን ሲበሉ (ፍራፍሬ ማለቱ ነው) ቁርስ ምሳ እራት ብለው ያሰምሩ ነበር እንዴ?… በመካከለኛው ዘመን ለአውሮጳውያን ቁርስ ባዕድ አልነበር እንዴ? ያን ልማድ ያስቀየረው የመጀመሪያው ቁርስ–በል ሰወዬስ ማነው? የግብፁ ፈርሆንስ ቁርስ በላተኛ ይሆን ይሆንን?" እያለ ይስቅና ማሰላሰሉን ይቀጥላል።
"ሰውነታችን ያለ ቁርስ መኖር እየቻለ… በግድ አስለምደነው ቢሆንስ?… ሰዎች ቁርስ በመብላታቸው ያገኙትን ጥቅም ባላውቅም… እኔ ግን ቁርስ ባለማወቄ ያጣሁት ነገር እንደሌለ አስረግጬ መናገር እችላለሁ። የሚያሳዝነኝ ቁርስ መብላት ግዴታ እንደሆነ ያመኑ ሰዎች… አልያም ሰውነታቸውን በቁርስ መብላት ያደነዘዙ ሰዎች… ቁርስ ሲያጡ የሚሰማቸውን ስሜት ሳስብ ነው ነፍሴ ክፉኛ የምትጨነቀው። የማይጠቅም ነገር በማጣታቸው በኀዘኔታ የሚያጠፉት ጊዜ፣ ሃይል፣ ጨጓራ ሌላም ሌላም… ብቻ ያሳዝናል" እያለ ማሰለሰሉን ይቋጨዋል። ከዛ ከት ብሎ ይስቅና ፀሃይዋን ይሾፋታል። የሚግባቡ ይመስለዋል።
እውነት ለመናገር ከልጅነቱ ጀምሮ፣ ጡት ከተወ በኋላ ሰዎች ከፋፍለው ቁርስ ብለው የሚጠሩትን ነገር በልቶ አያውቅም። በቀን ሁለቴ ነው የሚበላው። አንድም ቀን ግን ሚኩን አመመኝ፣ ራበኝ ገለመሌ ሲል ሰምቶት የሚያውቅ ሰው የለም። ፍፁም ጤነኛ ነው።
ሚኩ በሚኖርበት ግቢ ውስጥ እማሆይ ማንጠግቦሽ የሚባሉ መነኩሲት አሉ። እጅግ ሲበዛ መንፈሳዊ ሰው ቢሆኑም ሱስ አንዴ በህይወት ከገባ ባለጌ ነውና ያጨሳሉ። ሰዎች በዚህ የተነሳ የማይሏቸው ነገር የለም። ሚኩ ግን የሌሎች ሰዎችን ወሬ ከቁብ ሳይቆጥር "ከርሶ በላይ መንፈሳዊ ሰው አላውቅም" ስለሚላቸው አብዝተው ይወዱታል። "ሁሉንም ፆሞች ይፆማሉ። የራሳቸውንም ፆም ጨምረው ቁርስ ወደ አለመብላት ቅድስና የተሸጋገሩ ሰው ናቸው እኮ…" ይላል ለሰው ስለ እማሆይ ሲያወራ። "ትምባሆዋ ባትኖርቦት ይሄኔ ክንፍ አውጥተው በረው ነበር" እያለ ይቀልዳቸዋል ለራሳቸው ደግሞ!
የሚኩ ህይወት እንግዲህ፣ እንዲህ እንዲያ ዝብርቅርቅ ያለው ነው። ይሄኔ ግን ስኬታማ፣ ታዋቂ፣ ባለሃብት ቢሆን ኖሮ "ሚኩ እኮ ቁርስ አይበላም… እንትናም እኮ (ሌላ ስኬታማ ታዋቂ ሰው ነው) ራቱን ፖም ብቻ ነው የሚበላው፣ ያውም ግማሽ ፖም… ተብሎለት፣ የከተማችን አለች የተባለች ማክዳ መፅሄት የፊት ገፅ ላይ ይወጣ ነበር። ግን በአለም ኢፍትሃዊነት የተነሳ እሱ ቁርስ በላ አልበላ አይደለም… ፍግም ቢልም ማንም ግድ የለውም። ይሄ በጣም ያሳዝናል። ዓለም ዝም ብለው ያለ ዓላማ የሚኖሩ ሰዎችን የምታይበት መነፅር ልክ አይደለም።
(፫)
እማሆይ ማንጠግቦሽ!
ማጨስ አጢያት ነው? አይደለም? የሚለውን ለመከራከር ጊዜ የለንም። የኛ አላፊነት (ለጊዜው ራሳችንን ቢሆንም ያሸከምነው) መተረክ ነው። የመከራከር ፍላጎቱ እና ጊዜው ያለው ግን የድሮ ወወክማ ‘ዲቤት’ ማድረጊያ በሞንታርቦ ታግዞ ቢከራከር ጊዜ ካገኘን ለመታደም እንሞክራለን ከማለት ውጪ ለጊዜው የምንለው ነገር የለንም። እማሆይ ማንጠግቦሽ ግን የተጨበጨበላቸው ሞነክሲት ቢሆኑም ያጨሳሉ።
ይሄ ስለሚገርመን አይደለም ስለሚገርማቹ ነው የምንነግራቹ። 14 ዓመታት ደከመኝ፣ ሰለቸኝ፣ አሳለኝ፣ አፈነኝ ሳይሉ በትህትና አጭሰዋል። እማሆይ ማንጢ የጥሩ ሰው ልክ። በሚኩ አጠራር ደጓ ሳምራዊት!
እማሆይቷ የአንዲት ሴት ልጅ እናት ሲሆኑ አንድ ወንድ ልጃቸውን ደግሞ በሞት የተነጠቁ ናቸው። ሱስ የጀመሩት በልጃቸው የተነሳ ነው። አስጀምሯቸው ግን አይደለም። አስጨብጭበው፣ በቅሎ እና ፈረስ ሽጠው፣ መድፍ አስተኩሰው ዩንቨርስቲ የላኩት ጨዋው ልጃቸው ምንተስኖት አስቻለው የተጨበጨበለት ሱሳቴ ሆኖ ቤቱ ተመለሰ። ማንኛዋም እናት ቅስሟ እንደሚሰበረው የማሆይም ተሰበረ። ቢመከር ቢዘከር ባሰበት። ይጠጣል፣ ያጨሳል፣ ይቅማል፣ ይጦዛል ሌላም ሌላም ካለ ያደርጋል። ከቤት አባረሩት።
በተመረቀ በ12ኛ አመቱ ክፉኛ ታመመ። እማሆይን ውስጣቸው የቀረ ንግግር የተናገራቸው ይሄን ጊዜ ነበር። "እታባ አታጭስ፣ አትቃም፣ አትጠጣ ብለሺኝ እንጂ ለምን እንደምቅም እንደምጠጣ እነደማጨስ አንድም ቀን ጠይቀሺኝ አታውቂም። እስቲ ዛሬ እንኳ ጠይቂኝ…" ……… እማሆይ ግራ እየተጋቡም "ለምንድነው ልጄ?" አሉት። ምንቴ መለሰ "እታባ አመሰግናለሁ። ይቅር በይኝ ይቅር ብዬሻለሁ። ለምን እንደሆነ አላውቅም… ባውቅ ኖሮ…" አልጨረሰውም አይኑ እስከወዲያኛው ተከደነ።
እማሆይት መልስ ፍለጋ ብለው የለኮሱት ሲጋራ 14 ዓመት አብሯቸው ቆየ። እሳቸውም ለምን እንደሚያጨሱ ባለማወቃቸው እየተገረሙ ዘወትር ልጃቸውን ያስታውሳሉ። ከመነኮሱ ግን ገና ሰባት ዓመታቸው ነው።
ከዕለታት ባንድ ቀን ከሰርክ ፀሎታቸው ሲመለሱ መንገዳቸው ላይ አንድ ሰው ተዘርሯል። የሞተ መስሏቸው ነበር። ጠጋ ሲሉት ግን አብዝቶ የጠጣ ሰው እንደሆነ ተገለጠላቸው። ልጃቸው ሰናይትን ጠርተው ተሸክመው ቤታቸው አስገቡት። እስኪነጋ እንዲሁ ሳይተኙ ሲከታተሉት ቆይተው ሲነሳ ነብር ሆኖ ተነሳ። ንቅት ብሏል . . .