Advertisement
ዝናቡ ሃይሉን እየጨመረ ሲመጣ ሰው ሁሉ ሲሮጥ… እሱ እያዘገመ በአቅራቢያው ያለው የፍራፍሬ መሸጫ ሱቅ ውስጥ ሊጠለል ገባ። እኔ ከተጠልልኩበት ወጣሁና ወደ እሱ አቅጣጭ አመራሁ። እዛ ቤት የተጠለለው ሰው ሁሉ ፊቱ ወደ ውጪ አቅጣጫ የዞረ ነው። የወጣቱ ዓይን ግን ወደ ፍራፍሬ መደርደሪያ ላይ ነው። ቅድም የሰው ፊት ሲያይ በነበረው ሁኔታ፣ የተደረደሩትን እሽግ ጭማቂዎች አንድ በአንድ ማማተር ጀመረ። ከፊቱ ያሉትን ሰዎች ከነመኖራቻውም ልብ ያላቸው አይመስልም። አሁን ምን እየፈለገ እንደሆነ በስሱ ገባኝ። ቀስ አድርጎ አንዱን የታሸገ ጭማቂ በእጁ ነካውና እጁን ቶሎ ብሎ ሰበሰበው። ኤሌትሪክ የያዘው ነው የሚመስለው።
ብዙም ሳይቆይ ፊቱን ወደ በሩ አቅጣጫ አዞረው። ዓይኖቹ ዕንባ አቅርረዋል። ቀስ እያልኩ ተጠግቼ አጠገቡ ደርሻለሁ። "እንዲህ አልነበርኩም፣ እሆናለሁ ብዬም አላሰብኩም!" አለ። ለማን እንደሚያወራ እሱም የሚያውቀው አይመስለኝም። ሙሉ ትኩረቴን ስለሰጠሁት እኔ ብቻ እንደሰማሁት ነው የተሰማኝ። ሌሎቹ በራሳቸው ሃሳብ ተጠምደዋል። ወይ ትኩረታቸው ዝናቡ ላይ ነው።
እጆቹን ከኪሱ አወጣና ከአፉ በሚወጣ አየር ሊያሞቃቸው ጀመረ። እጆቹ ከመንፃታቸው በላይ ጎልቶ የታየኝ መንቀጥቀጣቸው ነው። ቀስ ብሎ በዛው፣ ከአንድ ዓይኑ ያመለጠውን ዕንባ በቀኝ ጠቋሚ ጣቱ ጠረገው። የማላውቀው ስሜት ወረረኝ። በልቤ የራሴን ግምት ባስቀምጥም ምን ሆኖ እንደሆነ ግን የሚያውቀው ራሱ ብቻ ነው ብዬ አሰብኩ።
ዝናቡ ስላባራ ሰዉ አንድ ባንድ ተቀንሶ እኔ እና እሱ ብቻ ቀረን። በድጋሚ ወደ ፍራፍሬ መደርደሪያው ዞረ። ምን ብዬ እንደምገልፀው የማላውቀው ሁኔታ ተሰማኝ። የሆነ የልብ ወዳጁን የሚያይ ነው የሚመስለው። በአፉ ባያወራም ከፍራፍሬዎቹ ጋር የሆነ ሃሳብ ሲለዋወጥ ይታወቀኛል። "ይቅርታ ይሄን በማሰቤ" የሚል የሚመስል ፊት አሳይቷቸው ወጣ። ተከተልኩት። ከፍሬውም ከጭማቂውም ቢያነሳ የሚደብብቅበት አለባበስ ነበር የለበሰው። ግን አላደረገውም።
አስፋልቱን ተሻግሮ ብዙ ሰው የማይተላለፍበት ጭር ያለ ቦታ ላይ ቆመ። አበባ የታጠረበትን አጥር ተደግፎ በእጆቹ የቆረጠውን አበባ እያፍተለተለ ነው። ከታችም ከላይም አንዳንድ ሰዎች ያልፋሉ። የመረጠውን ሰው ከተል ይልና መልሶ ይቆማል። አበቦቹን እያፍተለተለ ይጠብቃል። ሰው የምጠብቅ መስዬ ስልኬን እየጎረጎርኩ ተጠግቼው ቆምኩ።
እያየኝ እነደደሆነ ሲገባኝ ዞሬ ቀለል አድርጌ አየሁት። የሆነ ድፍረት እንደተሰማው ሲታወቀኝ ፈገግ አልኩለት። ፈገግ አለና ተጠጋኝ።
"ሰላም ነው? ሰው እየጠበክ ነው?" አልኩት… እንዲያወራ በር ልክፈትለት ብዬ ነው…
"አዎ ታውቃለህ… " ዓይኑን ከኔ ለማራቅ እየሞከረ…
"ታውቃለህ ል:ጄ ታ:ሞ:ብ:ኝ!" … እነዚህ ቃላት ከአፉ ሲወጡ ፊቱ ቲማቲም እየመሰለ ነው።
"የመጀመሪያህ ነው?" አልኩት ከዚህ በኋላ ማስጨነቁ ትርጉም የለውም። ከእግር እስከ ራሴ አየኝ።
"አዎ የመጀመሪያዬ ነው!… እንዲህ አልነበርኩም፣ እንዲህ እሆናለሁ ብዬም አስቤ አላውቅም… "
ኪሴ ገብቼ ያለኝን ሰጠሁትና "ዛሬ አብሬህ ብሆንና ስላንተ ባውቅ ደስ ይለኝ ነበር። ዛሬ ግን ብቻህን መሆን እንዳለብህ ይሰማኛል። ከዚህ ውጪ ምንም ልልህ አልችልም!" ብዬው ፈጠን ብዬ ከአካባቢው በፍጥነት መራቅ ጀመርኩ።
ከርቀት ድምፁ እየተከተለኝ ነው "ልጄ ማለት አልነበረብኝም? … ቆይ ቀጥታ ብጠይቅህ ትረዳኝ ነበር? … ልጄ ታሞ ከምልህስ ለልጄ ልብስ መግዣ ብልህስ?… እኔ ልጄ ታሟል ስላልኩስ ልጄ ይታመማል እንዴ?… ቆይ ጥፋቱ የማነው? እንዲህ አልነበርኩም፣ እንዲህ እሆናለሁ ብዬ አስቤም አላውቅም" ከኔ ጋር ሳይሆን ከሕሊናው ጋር የሚያወራ ነው የሚመስለው። እኔ ርቄያለው። ለሱ ግን የመጀመሪያው ነበር።
የመጀመሪያው ነው…………………………………………………………………………………………………………………………………
(፪)
ሙሉ ለሙሉ ላለመውደቅ የመጨረሻውን ትግሌን እየታገልኩ ነበር የመጣው። ሰው የሚባል ጠልቻለሁ። ከዚህ በፊት የሆነ ቦታ በዓይን አውቀዋለሁ።
<<አልአዛር ነው አይደል ስምህ? ሰላም!>> አለኝ እጁን ለሰላምታ ዘርግቶ… ጥዬው እንዳልሄድ ምን እንደያዘኝ አላውቅም።
<<ፈቃድህ ከሆነ ሻይ ቡና እንድንል እፈልጋለሁ>> ፊቱ ፈገግ እንዳለ ነው።
<<ምንድነው ሻይ ቡና? እንጠጣ ማለትህ ከሆነ እኔ ከሰው ጋር አልጠጣም። ብቻዬን ነው የምፈልገው… ብፈልግ በሰዓት ውስጥ 10 ልጠጣ፣ በሁለት እጄም መጠጥ ይዤ ልጠጣ ማንም አያገባውም… >>
<<ይገባኛል>> ብሎ ሲያቋርጠኝ የመጨረሻ ነው ጓ ያልኩበት።
<<እስቲ ንገረኝ ምንድነው የሚገባህ? ለምን 10 እንደምጠጣ ነው? ለምን በሁለቱም እጄ ይዤ እንደምጠጣ ነው? ምንድነው የሚገባህ?>> የምችለውን ያህል ጮህኩበት። አሁንም ለምን ጥዬው እንዳልሄድኩ አልገባኝም።
<<አልአዛር አንድ ወቅት አንተ ጫማ ውስጥ ነበርኩ… ምናልባት ዛሬ ፊቴን አይተህ አታምነኝ ይሆናል…>> አለና በእጁ ከያዘው መፅሃፍ ውስጥ ፎቶ አውጥቶ ሰጠኝ። ፎቶውን ለመቀበል እጄን ስዘረጋ፣ በውስጤ ቀደም ብሎ ለሰላምታ የዘረጋውን እጁን ባለመቀበሌ እያፈርኩ ነበር። ፎቶውን አየሁት። ተቀርፆ ያለቀ፣ ፊቱ እንደ እግር ቁርጭምጭሚት ያለው የሚመስል፣ ጠቆር ያለ ቀጫጫ ልጅ ነው። ፊለፊቴ የቆመውን አየሁት። እጅግ በጣም ቀይ፣ ወፍራም፣ ፊቱ ሙሉ ሱስ በዞረበት ዞሮ የማያውቅ የሚመስል፣ ወፍራም ቀይ ከንፈር ያለው፣ የተረጋጋ ሰው ነው። ደግሜ ፎቶውን አየሁት። ደግሜ እሱን አየሁት።
<<ከአራት አመት በፊት ነው 41 ኪሎ ነበርኩ። የመጨረሻ ጊዜ ያጨስኩ ቀን የተነሳሁት ነው>>
አላመንኩትም። ተጠራጣሪ ሆኛለሁ። ሲበዛ ማንንም አላምንም። በዛው ፍጥነት ብዙ ነገር አሰብኩ። ግን ፊቴ የቆመው ሰው እኔን የሚጎዳበት ምክንያት አልታይህ ቢለኝም ጥርጣሬዬን አልቀነስኩም።
<<ለምን መጣህ ታድያ?>> አልኩት። ድምፄ ሰልሏል፤ ውስጡ የሆነ የተሸናፊነት ስሜት አለው።
<<አንተ የኛ ሰው ነህ… እንድትረዳኝ እፈልጋለሁ>> ሲለኝ መልሼ ቱግ አልኩ። ቡድን እጠላለሁ የኛ ሰው የነሱ መባባል በጣም ነው የሚቀፈኝ… ሆኖም መናገር ጀምሬ ተውኩት። ፊቴ ሲነድ ይታወቀኛል።
<< የኛ ሰው ስላልኩህ ነው?… ተፈጥሮአችን ማለቴ ነው። ተፈጥሮ ሁላችንም እንዲመቻት ከፋፍላ ነው የምታስተናግደን… እኔና አንተ ደግሞ የነርቭ ሰዎች ነን>> ………… የሚለው ባይገባኝም ቁጣዬ ግን ወደ ቦታው ተመልሷል። እንሂድ ሲለኝ እንኳ ስከተለው አልታወቀኝም። ሁሌ የምጠጣበት ግሮሰሪ ቀደም ብሎኝ ገባ። እኔ የምቀመጥበት ቦታ ጋር የኔን ቦታ ለቆ ቁጭ አለ። አስተናጋጁ ለኔ የዘወትር መክፈቻ መጠጤን፣ ለሱ ደግሞ ውሃ አምጥቶ ሲያስቀምጥለት ቃላት አልተነፈስኩም። አከታትዬ 4 እስክጠጣ ምንም አልተናገረኝም፤ የተከፈተውን ሙዚቃ ተመስጦ እያዳመጠ ነበር።
<<አልአዛር ጊዜ ማባከን አልፈልግም… ስንት ጊዜ ሆነህ በሚስጥር መታገል ከጀመርክ?>> አለኝ። ቆጣ ያለም መሰለኝ። በእኔ ውስጥ እርግጠኛ ሆኖ የሚያወራ ሰው ከዚ በፊት ገጥሞኝ አያውቅም። አፌን ቀስ ብዬ አላቀኩኝ።
<<ሁለት አመቴ… ሱስ መተው ፈልጌ ሳልፈልግ በሱስ ስቀጥል ሁለት አመቴ ነው>> የራሴ ድምፅ ለራሴ እያሳዘነኝ ነው።
<<አየህ ለዛ ነው… ላለፉት ሁለት አመታት ልክ እንዳልነበርክ አውቅ ነበር። ትቆጣለህ፣ ትሳደባለህ፣ በጅምላ ትንቃለህ፣ ራስህን ከፍ ማድረግ ትፈልጋለህ… ምክንያቱም አንተ ያለኸው እ—ታች ስለሆነ ነው። ህዝቡን ትሰድባለህ ምንም የማይገባው ደንቆሮ ይመስልሃል። ችግርህ ግን ህዝቡ አልነበረም። ችግርህ አንተ ነህ። ህዝብ የችግርህ ማምለጫ ነው። ያንተ ችግር ሱስ ነው። ያንተ ችግር ተፈጥሮ እንድትኖርላት በምትፈልገው መንገድ ባለመኖርህ የተፈጠረ የመጣም የውስጥ ቁጣ ነው።>>
ሌላ ጊዜ ቢሆን እንዲህ ደፍሮ ለሚለኝ ጠርሙስ የማነሳበት ነው የሚመስለኝ። ቀድሜ ስለምጮህ ስለምቆጣ ማንም አይዳፈረኝም። ይህ ሰው ግን ፊቴ ተቀምጦ ያለኸው ከሰው በታች ስለሆነ ነው እያለኝ ዝም ብዬ አዳምጠዋለሁ። እንደውም ዋጥ አርጌው እንጂ እሱ ሲያወራ ውስጤ አልቅስ አልቅስ የሚለኝ ስሜትም እየታገለኝ ነበር። ለምን? አላውቅም። አሁንም የግዴን አፌን አላቀኩኝ።
<<ተፈጥሮ እንዴት ነው እንድኖርላት የምትፈልገው?>>
<<አየህ?! ቅድም ብዬሃለሁ አንተ የነርቭ ሰው ነህ… የነርቭ ሰው ደግሞ በነፃነት ማሰብ፣ በነፃነት ማንበብ፣ በነፃነት መታዘብ፣ በነፃነት መመሰጥ ያስደስተዋል። መጀመሪያ አካባቢ ሱስ ለነዚህ ስሜቶችህ ረድቶህ ነበር… ቆይቶ ግን ሱስ እንኳን ያለህን አይደለም የሚኖርህንም ነው የቀማህ። ይህ የሱስ ባህሪው ነው። አንተ ስለሆንክ ስላልሆንክ አይደለም። ዛሬ እንደትላንት ማሰብ አቅቶሃል። ዛሬ እንደ ትላንት ማንበብ አቅቶሃል። ፃፍ አትፃፍ አላቅም። ተደብቀህ የምትፅፍ ከሆነም ዛሬ እንደ ትላንት መፃፍ አቅቶሃል። ይህ ደግሞ ያበሳጭሃል። ይሄ ደግሞ የአንተ የብቻህ ህመም ስለሚመስልህ ከመሰሎችህም ጋር አታወራውም>> ውሃውን አንስቶ ተጎነጨ። የማጨሰው ሲጋራ ወደፊቱ እንዳይሄድ ፊቴን የጎን አድርጌ ጆሮዬ ሙሉ በሙሉ ሰጥቼዋለሁ። ቀጠለ…
<<ስለ ሱስ ብዙ አታውቅም። ማህበረሰቡም ስለማያውቀው አይረዳህም። ሙያዬ ብለው ሱሰኞችን በመርዳት የሚሰሩት ባለሙያዎች እንኳ ዕውቀታቸው ላይ ጥያቄ አለኝ። አንዴ ምን ሆነ መሰለህ… በጣም አጨስ ነበር። ሲጃራ እንደ መፋቂያ አፌ ወትፌ ነው የምንቀሳቀሰው። እና ታምሜ ሐኪም ቤት ሄድኩ። ዶክተሩ ወዳጄ ነው። "ከዚ በኋላ ካጨስክ ትነካዋለህ" አለኝ። እኔም እሱም ዙሪያችንም ሁሉ እሱም አጫሽ መሆኑን እናውቃለን። ያኔ ነው ሁላችንም የሆነ ስለ ሱስ ያልገባን ነገር እንዳለ የገባኝ። እሱ እንደዛ ካለኝ በኋላ ነው በፊት ከማጨሰው በእጥፍ ማጨስ የጀመርኩት። ባጋጣሚ አልሞትኩም። ፈርቶ፣ ለጤና ታስቦ ሱስ መተው ከባድ ነው። ዛሬ ያ ለምን እንደሆነ አውቃለው። ያኔ ግን ስለሱስ ሌጣ ደደብ ነበርኩ።>>
ለመጀመሪያ ጊዜ ፈገግ አልኩ። ራሱን አገላለፁ አስገረመኝም። እኔ ራሱ ብዙ ጊዜ ተው ስባል ይብስብኝ ነበር። እንኳን ሌላ ሰው አይደለም እኔ ራሴን ተው ስለው፣ በኡዝባኪስታንኛ በርታ እንዳልኩት ይሰማኝ ነበር። ይቺ ጥርሴን የነቀልኩባት ጉዳይ ነች። ይሄን ስሜት በደንብ አውቀዋለሁ። የሚጋራኝ ስላገኘሁ ደሞ ደስ አለኝ። ቅድም ካሳየኝ ፎቶ ይልቅ አሁን ባወራኝ ወሬ ሱሰኛ እንደነበረ አመንኩት። ፈግታዬ ሞቅ እንዳለ በሃሳብ ስነጉድ… <<የት ሄድክ?>> ሲለኝ ነው የነቃሁት።
<<ቅድም ተጠራጥሬ ነበር። በነገራችን ላይ ሲበዛ ተጠራጣሪ ሰው ነኝ። ሆኖም አሁን የኛ ሰፈር ሰው እንደነበርክ አምኛለሁ>> አልኩት ፈገግታዬን ሞቅ አድርጌ… ትንሽ ሞቅ እንዳለኝ አወራሬ ያስታውቃል።
<<አንተ ውስጡ ስላለህ አይታወቅህም እንጂ ተጠራጣሪነት ትክክለኛ ባህሪህ አይመስለኝም። ተጠራጣሪነት፣ ግልፍተኝነት፣ ስጉነት፣ የሌሉ ነገሮችን እየፈጠሩ ማመን ቀላል የሚባሉ ሱስ የሚፈጥራቸው ባህሪያት ናቸው። ተጠራጣሪነትህ ጊዜ ወለድ ይመስለኛል። የኖርኩበት ስለሆነ ነው የምነግርህ… ለዛሬ ይብቃንና ሌላ ሌላውን እንጫወት>>
<<እንዴ አቀሳስረኸኝማ ወዴት ነው? ቆይ እሺ ስንት ጊዜ ሆነህ ከሱስ ከተፋታህ?>>
<<4 አመት ከሰባት ወር ከ12 ቀኔ ነው ጫት ከተውኩ። መጠጥ እና ሲጋራ ከተውኩ ደግሞ ድፍን አራት አመቴ… በነገራችን ላይ ሱስ መተው ብዙ ከባድ አይደለም። ጨዋታው ያለው ትቶ መቆየቱ ላይ ነው። በህክምና ርዳታ ሱስ ከተዉ ውስጥ እንኳ ትንሽ የማይባሉ ዎች ተመልሰው ሱስ ውስጥ ይገባሉ። አንተን ከሚተዉት ውስጥ ብቻ አይደለም የምቀላቅልህ… ሱስ ውስጥ እንኳ እንደነበርክ ትዝ የማይልህ ኖርማል ሰው አድርጌ ነው መልሼ የምሰራህ!>> ……… ልቤን እንዳገኘው ተሰምቶታል መሰለኝ አወራሩ ውስጥ ደስ የሚል የኩራት ድምፅ አለ።
<<ለምን እኔን አሰብከኝ?>> መረጥከኝ ነበር ልለው ያሰብኩት ግን ቃሉ ጎረበጠኝ።
<<እንዳልኩህ ሱስ መተው አይደለም ከባዱ ትቶ መቆየቱ ነው። አንተ ደግሞ ሱስ ከተውክ በኋላ ወዴት እንደምትሄድ ስለማውቅ፣ አንተን ተከታትሎ ስለማገድ አልጨነቅም። እኔ ራሴን በማንበብ ነው ያገዝኩት። አንተም በማንበብ ራስህን ስለምታግዝ ብዙ ማገዶ አትፈጅም። ከህይወቴ ላይ 6 ወሬን ሳልሰስት እሰጥሃለሁ። አንተ ደግሞ ቃልህን ትሰጠኛለህ።>>
<<እኔ የምን ቃል ነው የምሰጥህ?>>
<<ሱስ ከተውክ በኋላ አንተም ደግሞ ሌላ ሰው ለማስተው ትሰራለህ። ይሄን ብቻ ነው የማስቸግርህ>> ………… እኔ ልተው እንጂ ሌላው እዳው ገብስ ነው ብዬ…
<<ይሄ ከሆነ ይኸው ቃሌ!>> ብዬ እጄን ሰጠሁት።
መጀመሪያ የሚሆን የሚሆን ባይመስለኝም፣ ብዙ ውጣ ውረዶች ቢኖሩትም… መጨረሻው ተሳክቷል። ከገባልኝ ስድስት ወራት እንዲሁ በጓደኝነት 6 ወር ጨምሮልኝ ከአመት በኋላ ለትምህርት ካገር ወጣ። ዛሬ ሱስ የሚባል ከተውኩ ድፍን ሶስት አመት ሆኖኛል። ሲበዛ እጅግ ደስተኛ ነኝ። የሚያውቁኝ ሁሉ ደስተኞች ናቸው። ሱስ ከተውኩ ሌላ ምንም ነገር አያቅተኝም በሚል መንፈስ ስለምንቀሳቀስ የምፈልገውን ሁሉ ለማሳካት አልቸገርም። ሱስ መተው እንደሚቻል ለሰዎችም እንደምሳሌ ስለምጠቀስ፣ ያም ደሞ ለሰው የሆነ ነገር አስተዋፅኦ እንዳረኩ እንዲሰማኝ ቢያረግም… ውስጤ ግን የማይሞላ ጉድጓድ አለ። የተከፈለልኝን ቀጥታ አልከፈልኩም። ቃሌን በልቻለሁ። ይሄን ጎዶሎ የምሞላበት ደግሞ ጊዜው አሁን ይመስለኛል።
ቀስ በቀስ እሱ እያዋዛ እንዳስተማረኝ ከሱስ የሚተውበትን መንገድ እዘረጋለሁ። ከኔ የሚሆነውን አድርጌ ሌላውን ለሌላው መተውን መማር ጀምሬአለው። ያኔ ደስታዬ ሙሉ ይሆናል። በስጋ ባይዛመዱኝም ወንድም እና እህት የሚሆኑኝ ሰዎች አፈራለሁ። እነሱም ሌላ ያፈራሉ። አሁን ፊለፊቴ ብርሃን ብቻ ነው የሚታየኝ። ብርሃኑን ደግሞ እከተለዋለሁ።
<<ዛሬ የፊታችንን መብራት ያዩ ትላንት እንደነሱ ጨለማ ውስጥ እንደቆየን ለማመን ይቸግራቸዋል። ልክ ሲያምኑን ግን ለነጋቸው የሚደርሱበት ቋሚ ምልክት ስለምንሆናቸው፣ የሚዳሰስ ተስፋ አድርገው እንዲያስቡን ይሆናሉ!… እኛ ካደረግነው እነሱም ማድረግ አያቅታቸውም… ምክንያቱም እኛ ደሞ ትላንት እንደነሱ በንፉቅቅ የምንሄድ ነበርንና>>
ሚኩ ጌትነት ሲሰናበተኝ የተናገረኝ የመጨረሻ ቃሉ ነበር።