Komentar baru

Advertisement

ሰምራ

Eriyot Alemu
Feb 12, 2022
Last Updated 2023-08-18T04:10:13Z
Advertisement
(፩)
ሰምራን እወዳታለሁ። የምወዳት በራሷ ዓለም ደስተኛ ስለሆነች ነው። አታስጨንቀኝም። አብረን ስንጃጃል እጅግ ደስ ይለኛል። አብረው ከተጃጃሉት ሰው ጋር አብረው ቁምነገር መስራት የገለባ ያህል መቅለሉን የኖረው ብቻ ነው የሚያውቀው። ለምን እንደሆነ አላውቅም… አብሬያት ስጃጃል አብሮኝ ሰው እንዳለ ሁሉ እረሳና ብቻዬን የሆንኩ ያህል ይሰማኛል። ይሄን ያህል ትቀለኛለች። ብዙ አብረን ጅለናል… መጃጃል ምንድነው ብባል ግን ለሰው እንዲህ ነው ብዬ መግለፅ የምችል አይመስለኝም። 

ድሮ በጣም ድሮ  የምንጠጣ ሰዓት…ጠጥተን ጠጥተን ሲበቃን፣ መሬት ቁጭ እንልና የተቀቀለ እንቁላል በሚጥሚጣ እንበላለን። ስለማንም ግድ አይሰጠንም። ግድ የሚሰጣቸው ግን ነበሩ። "ይቺን ስዕል የመሰለች ልጅ መሬት እያንደባለለ የተቀቀለ እንቁላል ያበላታል" ይሉኛል። ለሰምሪ ይሄን ስነግራት ትስቃለች "አንተ አድራጊ እኔ ተደራጊ መሆኔ ነው?… አድራጊና ተደራጊ የሚል ነገር ያለው ለግስ ነው አትላቸውም… ስሞትልህ ተውሳከ ግስ ግን ምንድነው? እንደውም ተውሳኮች በላቸው… ተውሳከ ሁላ" ትስቃለች። አብሬያት እስቃለሁ።


እኔ ደግሞ "ስዕል የመሰለች ልጅ…" ለሚሉት እሞግታለሁ። "የማንን ስዕል ነው የምትመስለው? ሁሉ ስዕልስ ውብ ነው? የአንዱ ውብ ለአንዱ ፉንጋው ቢሆንስ?" ስላቸው… "አታምርም ልትል ባልሆነ!?" ይሉኛል። "ለኔማ ታምረኛለች ስዕላቹ ነው እንጂ የማይገባኝ አሁን ሂዱ ጥፉ ከዚ" እላቸኋለሁ።



ቀለል ያለ ህይወት ደስ ይለኛል። እሷም እንደዛው ነች። ትንንሽ የሚያስደስቱኝም ብዙ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ አግዳሚ ወንበር ላይ ቁጭ ብዬ ወደ ባዶ ቦታ እያየሁ፣ ላዬ ላይ ቀኑ ሲመሽ በጣም ደስ ይለኛል። ይሄን እሷም ታውቃለች። ከ11 ሰዓት በኋላ ልታገኘኝ የምትቀጥረኝ በግድግዳ የማይታጠሩ ቦታዎች ላይ የሚሆንበት ምክንያቷ ይሄ ነው። ብዙ ጊዜ ጎልፍ ክለብ። እዛ ሆነን ሲመሽ በጀርባ በኩል ወክ እናረግና ትንጥዬ ቆራጣ አግዳሚ ወንበር ላይ እንቀመጣለን። "ዛሬ ይወጣሉ… አይወጡም? እናሲዝ" ትለኛለች። ሸለምጥማጦቹን ነው። ሁሌም "አይወጡም!" ብዬ ነው የማሲዘው። እሷ ሲወጡ ደስ ስለሚላት ነው። አፏን አሞጥሙጣ "ይወጣሉ!" ብላ ትጮሃለች። ሁለት ናቸው ከአንድ ጥግ ጥሻ ውስጥ ይወጡና ረዥሙን ሜዳ በሩጫ ያቋርጡታል። ያኔ በደስታ ታብዳለች። በጣም ደስ እያለኝ ያስያዝነውን እ(በ)ላላታለሁ። 

"በዚ ሰዓት ለምንድነው ሁሌ የሚሮጡት ግን?" ትለኛለች ተነስተን መውጣት ስንጀምር። 

"ምናውቃለሁ ሰምሪ" እላታለሁ። 

"እወቃ!" ሁሌ ነው እንደዚህ የምትለኝ። ለማወቅ ጥረት አድርጌ ግን አላውቅም። ባይሆን "እከሌ እኮ ሸለምጥማጥ ነው" ሲባል የሰማሁት ከሸለምጥማጦቹ ሩጫ ጋር ሊገናኝ ይችላል ብዬ ገምቻለሁ። እርግጠኛ አይደለሁም። እከሌ እኮ ሸለምጥማጥ ነው…  አይያዝም፣ ሙሉጭልጭ ነው ለማለት ይመስለኛል። ይሄን ስነግራት <<"ሰማዩ የአህያ ሆድ መስሏል" ከሚለው አገላለፅ ጋር ይዛመዳል መሰለኝ… የድሮ ሰው ለእንስሳ ቅርብ ስለሆነ ይሆናል ምሳሌውም ለእንስሳ የሚቀርበው>> ብላ ትስቃለች። 


ሰምሪም እኔም መብረቅ ፎቢያ አለብን። ያስተዋወቀንም መብረቅ ነው። በድሉ ህንፃ ስር ዝናብ ተጠልዬ እያለ መጥታ ከፊቴ ቆመች። ብዙ ሰው ነበር። ገና ብልጭ ብልጭ ሊል ሲል ጆሮዬን ደፍኜ አይኔን ጨፍኜ ወደ መሬት አቀርቅሬ ቆሜያለሁ። ቀስ ብዬ አይኔን ስገልፅ በኔ ፊት ለፊት አይኗን ጨፍና ጆሮዋን ደፍና የቆመች ሴት አለች። መብረቁን ፈርታ ፊቷን ማዞሯ ነው። ሳላስበው ድብልቅልቁ ወጣ። በቃ ግንባሯን ነው በግንባሬ የገጨሁት። በቦታው የነበሩ ሰዎች ግራ ተጋቡ። ይቅርታ ስላት ትስቃለች። "መብረቅ ትፈራለህ? እስከዛሬ መብረቅ የሚፈራ ሰው ገጥሞኝ አያውቅም… " እንደ ልጅ ትስቃለች። በቃ ተዋወቅን። 


የሆነ ጊዜ ስለ ጅማ ዝናብ ስነግራት… "መብረቁ ብርሃን እንጂ ድምፅ ስለሌለው፣ ብዙ ጊዜ በዝናብ ውስጥ እጄን ኪሴ ከትቼ፣ የመብረቅ ብልጭታን አይኔን ገልጬ እያየሁ፣ ዝናብ ስበሰብስ የሚያውቁኝ ሁሉ ግራ ይገባቸዋል… ስሜቴ አይገባቸውም። ክረምት እንደምወድና የምፈራው መብረቅ እንደሆነ፣ ከመብረቁም ድምፁን ብቻ እንደሆነ… ያልነገርኩትን ሰው ለማሳመን ይመስለኛል ጥረቴ…  ግን ደሞ መበስበሱም ደስ ይለኛል በቃ" ብያት ነበር። የሆነ ክረምት ላይ ድንገት ደወለችና "የት እንዳለሁ ታውቃለህ?… ጅማ ነኝ ነገ ና!" አለቺኝ። ይሄን ያህል እብድ ነች። እኔ ለሷ ከማብደው ግን አትብስም። 


አንዴ አርብ ቀን እዮሃ ሲኒማ ፊልም ገብተን እያለ ፊልሙ ደብሮኝ ቀድሜያት ወጣሁ። በሁለታችን መሃል መጠባበቅ የለም። ማንም የፈለገውን የማድረግ ነፃነት አለው። መስቀል አደባባይ ደረጃው ላይ ተቀመጬ እየጠበኳት ነው። ከርቀት መኪኖች ውር ውር ሲሉ፣ በቅርብ የጤና ሯጮች ላዬ ላይ አቧራ እያቦነኑ ዱብ ዱብ ሲሉ፣ ራቅ ብሎ በቡድን ስፖርት የሚሰሩ "አንድ ሁለት— አንድ ሁለት —አንድ ሁለት… " እያሉ በቡድን ድምፅ እያወጡ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተመስጬ ስከታተል ካጠገቤ መጥታ ተቀምጣለች። "እንዴ የምትጨርሺው መስሎኝ ነበር!" አልኳት የምትወደው አይነት ፊልም መስሎኝ ነበር። "ኪስህ ውስጥ ግባማ" አለቺኝ። ቀኝ ጃኬት ኪሴ ስገባ የተጣጠፈ ወረቀት አገኘሁ። 


"ስንተኛው ደቂቃ ላይ ይወጣል የሚለውን ለማጣራት እንጂ እኔማ ቀድሜ ያየሁት፣ አይቼም የወደድኩት ፊልም ነው" ይላል ወረቀቱ። ሰዎች በኔ እርግጠኛ ሆነው ሲያወሩ ያናድደኛል። የሰምሪ ግን እጅግ ነው ደስ የሚለኝ። ሌላ ጊዜ ምንም አልገረምም ነበር። ሰምሪ ሲበዛ ቆቅ ነች። ያን ቀን ግን እኔ ነበርኩ ወደ ፊልም ቤት እንሂድ ያልኳት። ከሚታዩት ሁለት ፊልሞችም ይሄን ትቼው የወጣሁትን የመረጥኩትም እኔ ነበርኩ። ከዛ ሰዓት እስኪደርስ በስጢፋኖስ አቅጣጫ ወደ ታች ቁልቁል እያየን ተቀምጠን ነበር። ያኔ ነው ፅፋ ኪሴ የከተተቺው ማለት ነው። ሰምሪ በዚ ልክ እኔን ማወቋ ግን አስገረመኝ።



የተለያዩ ሃገር ሳንቲሞች መሰብሰብ ትወዳለች። 18 ነበራት። "እጄ ላይ አርጌ እያገላበጥኩ ሳያቸው በጣም ደስ ይለኛል" አለቺኝ። መጀመሪያ "ሳንቲም እጅ ላይ ማገላበጥ ምኑ ደስ ይላል?" ብዬ ነበር። ሳንቲም እንደውም አልወድም ነበር። የሆነ የማልወደው ሽታ ሁሉ ነበረው። ኪሴ ውስጥ ራሱ ሲበዛ ይጨንቀኛል። ከሷ በኋላ ግን ሳላውቀው በሳንቲም ፍቅር ወደኩኝ። እሷ ከነበራት 18 የተለያዩ አገር ሳንቲሞች ውጪ እኔ አሁን 44 ሳንቲሞች አሉኝ። ብዙ አድርጌ ልሰጣት ስላሰብኩ ነበር ስለ ሳንቲሙ የማላነሳባት። አሁን ግን የሳንቲሙ ነገር ከሷ በላይ እኔን  በጣም ደስ እያለኝ ነው። ለምን? ብባል "እጄ ላይ አርጌ እያገላበጥኩ ሳያቸው ደስ ስለሚለኝ" ብቻ ነው መልሴ።




ሰምሪ ጭራሽ ስልክ የላትም። ቤታቸው ወይ ቢሮዋ ሄጄ ሳስጠራት ድሮነት ይሰማኛል። እኔ ስማርት ያልሆነውን ደነዙን አውራ ጣት የሚያክል ስልክ ነው የምጠቀመው። "ሁለታቹም ማቶ ናችሁ እኮ" የሚሉኝ ዘመነኛ የዘመኔ ሰዎች አንድም በዚ ይመስለኛል። ምን አገባኝ እንጂ… ነውም። ቤቷ ሄጄ ሳንኳኳ እህቷ ትከፍታለች 

"ሰምሪ አለች?"

<<አዎ ግባና ጠብቃት!>>

"አይ አልገባም እዚህ ሆኜ እጠብቃታለሁ"

<<ካልክ እሺ>>


በቃ በነዚህ ንግግሮች ነፍሴ ትፈነድቃለች። ልክ ሰምሪ ስትወጣ ሰው ዞር ዞር ብዬ አይቼ እጠመጠምባታለሁ። ደስታዬ ሲለይባት ግር ይላታል። "ሰምሪዬ የምትሰጪኝ ህይወት እኮ ልዩነቱ አይገባሽም" እላታለሁ። ይሄኔ እቀፈኝ ብቻ ነው የምትለኝ። ስለ ሰው ትዝ አይላትም። አቅፋታለዋ!


(፪)



<<የምትወዳት ገፀባህሪይ ማናት?>>


<< Threshold of spring የሚል መፅሃፍ ላይ የምትገኝ ቻይናዊት ገፀባህሪይ ነች… ፀሃፊው ደግሞ እጅግ የምወደው ቻይናዊ ፀሃፊ lu xun ተማሪ rou shi ነው… ከዚ በፊት ነግሬሻለሁ አይደል የሉ መፅሃፎች በሙሉ በሃርድ ኮፒ ቤቴ ቢኖሩኝ እንደምመኝ!?>>


<<ምኗን ነው የምትወድላት እሺ?>>


<<ጭንቅላቷን፣ አስተሳሰቧን ማለቴ ነው። የገፀ ባህሪይ መልክ አንድም ቀን ስቦኝም አስጨንቆኝም አያውቅም። ያን በትክክል  የተረዳሁት መቼ መሰለሽ? The longest ride መፅሃፉን ቀድሜ አንብቤው ነበር፤ ከዛ ፊልሙን አየሁት። ፊልሙ ላይ ያለችውን ሩት የተባለች ገፀባህሪይ ካየሁ በኋላ ተመልሼ መፅሃፉ ላይ ሩትን አነበብኳት። ዳይሬክተሩ አስደመመኝ። ፊልም ላይ ካየሁት የማረሳው መልክ የእሷ ብቻ ነው። ሌላ ውስጤ ምንም የለም። ወዲያው ነው ከውስጤ የማጠፋው። በርግጥ ሳነብም የመልክ ገለፃን ሆን ብዬ ልብ አልለውም። አሎሎ አይን ክሊዮፓትራ አንገት ሲሉ አይገባኝም፣ ማዘለያውን ቶሎ እጫነዋለሁ። >>



<<እሺ ያቺ ገፀባህሪይ ምኗ ሳበህ?>>


<<ነፃ ነፍስ ነው ያላት። ልክ እንደሆነ ሰው። ለህይወቷ ህግ የምታወጣው ራሷ ነች። ለምሳሌ ፊዚክስ መርጣ የተማረችው ማህበረሰቧ ሴቶች ፊዚክስ አይችሉም ብሎ ስለሚያስብ ነው። ይሄን አሳይታ የሷ የነፍስ ጥሪ ወደ ሆነው ሙዚቃ ታማትራለች። በዚ መሃል የምታጣው ነገር ያለ ይመስላል ለጊዜው፣ ግን ምንም አታጣም። ከሌሎች ጋር ልዩነቷ ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? መስዋትነት መክፈል የሚባል ነገር አይሰማትም። አፈንጋጭነቷም መልክ አለው።>>


<<መስዋትነት ስትል አልገባኝም?>>


<<አየሽ ማህበረሰቡ ያሰመረው መስመር አለ። ነጠላ ነፍስሽ ደግሞ የምትዋትትለት ነገር አላት። እሱ ምንድነው ነው? የግለሰቡ ወሳኝ ስራ ነው መፈለጉ። ግን ሁሉም ሰው አለው። ማህበረሰቡ ባሰመረው መስመር ሄደሽ መያዝ ያለብሽን ከያዝሽ በኋላ የነፍስሽን ጥሪ የምትከተይ ከሆነ መንገድ አቀለልሽ ማለት ነው። ማህበረሰቡም የኔ በሚለው መስመር ስለሄድሽለት መንገድ አይዘጋብሽም። ያለ በለዚያ ነፍስሽን ሲጎትቷት ይኖራሉ። አንቺም ማህበረሰቡን መንቀፍሽ አይቀርም። ስትነቃቀፉ መኖር ነው። ያ ማንንም አይቀይርም። በማህበረሰቡ መስመር ሄደሽ ነፍስሽ የምትፈልገውን ነገር ስታሳኪ ብቻ ነው ማህበረሰብ ልትቀይሪ የምትችዪውም።>>


<<መስዋትነት ያልከው አሁንም አልገባኝም?>>


<<አንዳንዱ የሚሰራውን ስራ ሆነም የሚማረውን ትምህርት ለሰው ብሎ እንደሚያረገው ይሰማዋል። ከማህበረሰቡ ጋር ለመስማማት አልያም ማህበረሰቡን ለማስደሰት። እዚህ ጋር የኔ የሚለውን የራሱን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ እንደተጫነውም ይታወቀዋል። ታዲያ የሆነ ጊዜ፣ ጊዜው ሲፈቅድ የኔ ወደሚለው ነገር ፊቱን ያዞራል። ያኔ ለማህበረሰቡ ብዬ አደረኩት ብሎ የሚያስበውን ነገር መተዉ አይቀርም። እዚጋ ነው የሆነ  የሰዋውት ነገር አለ ብሎ ማሰብ የሚመጣው። በመጀመሪያ ደረጃ የምትሰዊው የምትወጂውን ነገር ነው። ጊዜው በከንቱ የባከነም ይመስለዋል። ከዛ በነፍሱ መስመር፣ ነገሮች ፈጥነው መስመር ሲይዙለት፣ የበለጠ የድሮ ህይወቱ መባከኑ ይታየዋል። እውነቱ ግን ለነፍሴ ለሚለው ህይወቱ መፍጠን ምክንያቱ ቀድሞ በማህበረሰቡ ውስጥ ያስቀመጠው አሻራ ነው። ቀድሞ ለሌሎች ብሎ ያለፈው መስመር ነው። በቡድን መኖር በነጠላ ማሰብ ሲባል ሰምተሽ ታውቂያለሽ?>>


<<አላውቅም?>>


<<እኔም አላውቅም! ምን ልልሽ ፈልጌ መሰለሽ ግን? እህትሽ የምትማረውን ትምህርት ባታቋርጠው ይሻላል። ነገ ጆሮ መግዣ ይሆናታል። ሙዚቀኛ ለመሆን በራቸውን ስታንኳኳ "እሷ እኮ ዶክተር ነች!" ብለው ሞቅ አርገው ይከፍቱላታል። አንዳንዴ መጀመሪያ አካባቢ ሞቅታ ውስጥ ስለምትገቢ፣ የነፍስሽን ጥሪ ብቻሽን ስለምትሰሪው፣ ሌላ ሰው መቼም የማያስፈልግ ይመስልሻል። ከሞቅታው ስትወጪ ነው ለሱም ቡድን እንደሚያስፈልገው የሚገለፅልሽ። "ቤተሰቦቼም አልተረዱኝም" ብላ የተነጫነጨቺው ራሷ እህትሽ ነች ህይወትን በሚገባ ያልተረዳቺው። እነሱም የገባቸው አለ እሷም የገባት አለ። እውነቱ የሁለቱም ነው።……


……በርግጥ ጊዜ ይፈልጋል። ማውጣት ማውረድም ይፈልጋል። ልምድም ይፈልግ ነበር። ለአንቺ እህት ግን ይሄን አልመኝም። ተሳስታ በልምድ እንድትማር ፈፅሞ አልመኝልላትም። እድለኛ በማስተዋል ይማራልም፤ይመራልም። ይሄን ነው ለእርሷ የምመኘው። ራስን መሆን ማለት ጀብደኛ መሆን ማለት አይደለም። ራስን መሆን ማለት ከማህበረሰብ ተቃራኒ መቆምም አይደለም። የኔ ሃሳብ የመጨረሻው እውነት ነው እያልኩኝ አይደለም። ካልኩት የሚጠቅምሽን ውሰጂ። ልክ አይደለም ያልሺውን አስበሽ ለእህትሽ ንገሪያት። መሳሳትን ስለማልፈራ መታረም ጌጤ ናት። ምንም ታናሼ ብትሆንም ልክነትን በእድሜ እንደማለካ ታውቂያለሽ። አስረግጬ ልንገርሽ "ጆሮ መግዣ" ነገር ያስፈልግታል። አሁን የጀመረቺው ትምህርት አንዱ ነው። ጨርሻለሁ!>>


የዚ ቀን የተኮሳተረ ወሬያችን መቼም አይረሳኝም። የሆነ ጊዜ ላይ "ከዚ በፊት የማውቅሽ የማውቅሽ ይመስለኛል" ስላት "የሆነ መፅሃፍ ላይ ያለች ገፀባህሪይ መስዬህ ይሆናል" ብላ አስደንግጣኝ ነበር። ያን ቀን ከብዙ ጊዜ በኋላ አረሳስታ ልታወጠጣኝ ስትሞክር ነው ይሄን ያወራነው። ሃሳቧ ገብቶኝ የእህቷም ነገር አስጨንቆኝ ስለነበር ነው ወሬያችን ይሄን የዳይመንድ ቅርፅ የያዘው። እሷ ከኔ አልፋ የነፍሴን ንጣፎች ማየት ጀምራ ነበር። እኔም ወደ ቤተሰቦቿ እየተጠጋው ነበር። 


(፫)



አላለቀስኩም። ጥሩ ሰው ነች! የጥሩ ሰው ልክ!… ነበረች ነው የሚባለው? እሺ የጥሩ ሰው ልክ ነበረች… እጆቿ በጣም ያምሩ ነበር… ማርያም ጣቴን ለብቻው ነጥላ በነዚያ ውብ ጣቶቿ ልታሟሟው ትሞክራለች… በሙሉ ዓይኗ አታየኝም፣ ታፍራለች… ለምን ወደ ህይወቴ መጣች? ለምንስ ብልጭ ብላ ጠፋች?… "መካሻ" ትለኛለች… "እንደዚ አይነት ስም አልወድም! ያስጠላል" ስላት ስለ ወንድሟ ትነግረኛለች … እያለቀሰች… "በቃ ከፈለግሽ ዳምጠውም በይኝ!" ስላት እየሳቀች ጉንጬን ትቆነጥጠኛለች… አንድ ፍሬ ልጅ ትሆናለች… ትልቅ፣ በጣም ትልቅ ሰውም ትሆናለች… ሁሉም ያምርባት ነበር። 


ሲያለቅሱ ከሩቅ ሆኜ አይ ነበር… እነዛ ትልልቅ አይኖቿ ሊከደኑ ነው? ያ ጥርስ ላይስቅ ነው ማለት ነው? በቃ ተጣጠፈች? 27 አመቷ እኮ ነው። ምን ሆና ነው? … ያለቅሳሉ!… ተስፋዋስ?… አራት ልጆቿስ የምትወልዳቸው? ስም ሁሉ አውጥታላቸው ነበር። "ልጆቼ የወንድም እና የእህት ጣዕም እንዲኖራቸው እፈልጋለሁ!" … ምን አርገው ነው ቤተሰቦቿ በሃዘን ላይ ሐዘን የተደራረበባቸው? … እየሳቀች እንዲህ አለቺኝ "እኔ ከአራት አያት አንድም አላውቅም… ለልጆቼ ልጆች ግን የሚገርም አያት ነው የምሆንላቸው!" … ሩቅ ነበር ህልሟ… ከልቧም ነበር። ህልም ያለው አይጠፋም ይሉ የለም እንዴ ታድያ? …


ሰዉ ተበተነ… እህቷ ስታየኝ እንዳዲስ ማልቀስ ጀመረች… መታ አቀፈቺኝ… ዝምብዬ አያታለሁ… "ውሸት ነው በለኝ ውሸት ነው በለኝ" … ነገር አለሙ ተገለባብጦብኛል… "የትም እንዳትሄድ እዚሁ ጠብቀኝ!" ብላኝ ነበር መጨረሻ ስትለየኝ… የትም አልሄድኩም እስኪነጋ ድረስ… ጓደኛዬ መቶ "ትንታ" ምናምን አለኝ… እጠብቃታለሁ አልሄድም ስለው… " ስትጣደፍ እህቷ ስታጎርሳት ያንተን ስም ስትጠራ ነው…"  ብሎ ነው ጎትቶ እዛ አስፈሪ ቦታ የወሰደኝ… ፎቶዋን ሰጡኝ… አልሳቀችም፣ አልተኮሳተረችም… ሉጫ ፀጉሯ ወደፊት ድፍት ብሏል… የስሟ ትርጓሜ ያለበት ፈዛዛ ቡኒ ፊቷ አተኩሮ ያየኛል… "እውነት ነው ወይ?" አልኳት… "ለምን መጣህ ጠብቀኝ አይደል እንዴ ያልኩህ?" ያለቺኝ መሰለኝም… ወደ ማንጎው ዛፍ ስር ሮጬ ሄድኩ… 


የኔ ጥፋት ነው… lu xun ደስ ይለኛል ባልላትስ… የሱ መፅሃፎች በሃርድ ኮፒ ቢኖሩኝ እመኛለሁ ባልላትስ… ልታስደስተኝ ትፈልጋለች… ለምን ወደ ህይወቴ መጣች? … "የትም እንዳትሄድ እዚሁ ጠብቀኝ!" ብላኝ ቆየችብኝ… ከኋላዬ መጥታ አይኔን ጨፍና ገምት እንድትለኝ ተመቻችቼ ነበር የተቀመጥኩት… መሸ… ቀልዳ አታውቅም… ቢያንስ በኔ አትቀልድም… ውስጤ ብዙ ተጨነቀ… በጭለማው ውስጥ "ቁርር ቁርር" የሚል ድምፅ ስሰማ ፈገግ አልኩ… ደስ ይለኛል… እሷም ደስ ይላታል… እያሰብኳት ቆየሁ… ደግነቷን፣ የዋህነቷን፣ ንፅህናዋን… "ከሸገር ውጪ መሆንህን እያወኩ አዲስ አበባ ውስጥ እፈልግህ ነበር" ትለኛለች… የምሯን ነው አምናታለሁ… "ካንተ ከሆኑ ነገሮች የግድ ጥላ ብባል የምጠላው… እኔን ብቻ ነው" ትለኛለች… ስታወራ ዞር አርጋ ነው… እጅግ ደስ ትለኛለች…

 

የላኩላትን የኢሜይል መልህክቶች የፃፈችበትን ማስታወሻ ደብተር አምጥተው ሰጡኝ… ነግራኝ አታውቅም… እህቷ ነች "ስንጋባ አሳየኋለሁ!" ብላ ነበር ያለቺኝ… ምን እላት እንደነበር ማስታወስ አልፈልግም… ራሴ አስጠልቶኛል… እሷ የምትለኝን ብቻ ነው ማስታወስ የምፈልገው… ጥፋቱ የኔ ነው… ከዛ ቀን ሳምንት በፊት ከአዲስ አበባ ውጪ ነበርኩ… ባልመጣስ ኖሮ… እሷን ወደ ሩቁ ልሸኝ እንዴት እመጣለሁ?… መቆየት እችል ነበር፣ ስጦታዋን አስቤ ነው የመጣሁት… ባትነግረኝም ስጦታ እንዳዘጋጀችልኝ አውቅ ነበር። ራስ ወዳድ ነኝ… 


ድምጿ ይገርመኛል… ረጋ ብላ ነው የምታወራው… "ይሆናል ካልኩህ ይሆናል" ስትል እጅግ ደስ ትለኛለች… ግን አልሆነም… "ከዚ የተሻለ ሰው ሆነህ ማየት እፈልጋለሁ!" … አሁን ምንድነኝ ታድያ እላታለሁ… "አትቀልድ! የምኖረው ላንተ ነው!" አለቺኝና አለቀሰች… አይኖቿን ተነስቼ ሳምኳቸው… ደስ አላት… "የትም እንዳትሄድ እዚሁ ጠብቀኝ!" ብላኝ ሄደች… ልክ ነበረች ሰው አልነበርኩም፣ ሰው አይደለሁም… ራስ ወዳድ ነኝ… 


ማንጎው ስር አልጠፋም… ህፃናትን አስጠናለሁ… አይኖቼ ግን ይጠብቋታል… አዲስ አበባ ስመጣ የገዛሁትን ቀለበት ማንጎው ስር ቀብሬዋለሁ… ያኔ አልቅሻለሁ ብቻዬን… ከማንጎው ከራቅኩኝ ቀለበቱን የሚወስዱብኝ ይመስለኛል… እንዲህ እንድኖር ሆኗል… ሩቅ አያለሁ… ቀሚሷ ትዝ ይለኛል… ከስክስ ጫማዋ ትዝ ይለኛል… እሷ ትዝ ትለኛለች… እራሴን እረሳለሁ… 







iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

1 comment:

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement