Advertisement
ኩኩ መለኮቴ
ኩኩ መለኮቴ
እሷ በበላችው
በኔ አላከከችው
አባ ተቆጡልኝ
እማ ቆንጥጡልኝ
ኩኩ መለኮቴ
ኩኩ መለኮቴ
ተረት ተረት
"የንጉሱ አዲስ ልብስ"…
ይሄን ተረት ብዙዎቻችን በልጅነትም በአዋቂነትም የምናውቀው ይመስለኛል። ተረቱ የኛ የራሳችን ሃገር በቀል ተረት አስኪመስለኝ ድረስ ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ ሰምቼዋለሁ። ንጉሱ በአለም ላይ የሌለ ልብስ እንዲሰራለት ተመኝቶ… ሁለት አጭበርባሪዎች "ለብልሆች ብቻ የሚታይ፣ ለሞኞች የተሰወረ ልብስ እንስራልህ" ብለውት… እሱም አምኖ… በስተመጨረሻ ራሱን በብልህ ሂሳብ ቆጥሮ ራቁቱን በአደባባይ ይሄዳል። ህዝቡም ዝም! አሸብሻቢውም ዝም!… በ"ብልህ ነን" ሂሳብ ማለት ነው ዝሙ። ህፃን እና ወይን እውነት ያወራሉ እንዲል ጠቃሽ… አንድ ፈላ ጮክ ብሎ "አረ ንጉስ ራቁቱን ነው!" ይላል። በጣም ሲያጥር ተረቱ ይህ ነው። እጅግ በብዙ መልህክቶች የታጨቀ፣ አስተማሪ ተረትም ነው። ታድያ ተረቱ ከኤዞፕ ተነስቶ ዞሮ ዞሮ በባለቤትነት የተመዘገበው በዴንማርኩ ተራች hans christian andersen ነው። ገራሚ ገራሚ ተረቶች ባለቤት ነው አንደርሰን።
ሃንስ በ1843 የፃፈው nightingale የተሰኘም ሌላ ተረት አለው። የተረቱ መቼት ጥንታዊ ቻይና ነው። ናይቲንጌል ከወፎች ሁሉ የተለየ ውብ ዜማ ያላት ወፍ ነች። ታድያ የሆነ ጊዜ ወፏ የቻይናው ንጉስ ፊት ቀርባ ለመጀመሪያ ጊዜ ስታዜም የቻይናው ንጉስ ከአይኖቹ ዕንባ ፈሰሰ። ይህ ለወፏ እጅግ የከበረ ስጦታ ሆኖ ተቆጠረላት። ጊዜ ሄደ ጊዜ መጣ። ወፊቱ የቤተመንግስት ኑሮ ከተፈጥሮዋ ጋር አይሄድምና የቤተመንግስት እጅ መንሻዋን ትታ… ወደ ተፈጠረችለት ጫካዋ ተመለሰች። ቆይቶ ቆይቶ ንጉሱ ታሞ በተኛ ጊዜ ውለታውን ለመመለስ በንጉሱ መስኮት በኩል መጥታ ውብ ዜማዋን ትጋብዘዋለች። ንጉስም አገግሞ ይነሳል። የቻይና ህዝብም ይሞታል ያለው ንጉስ ሲነሳ አጃኢብ ነው! ጉድ ነው! አለ። ያው በቻይንኛ ነው። ተረቱ እጅግ ውብ ነው። የክርስቲያን አንደርሰን ተረቶች ስብስብ መፅሃፍ ወመዘክርም አለ። በቃ ከዛ ቀን ጀምሮ ይቺ ናይቲንጌል የምትባል ወፍ ትገርመኝ ጀመር። ዜማዋ ብቻ ሳይሆን ተረቱም በመልህክት የታጨቀ ነው። ጊዜ ሄደ ጊዜ መጣ።
የናይቲንጌል ተረት ይሄ ነው nightingale
የሆነ ጊዜ ላይ የyanniን ናይቲንጌል የሚለውን ኢንስትሩመንታል ሰማው። ምን እንደተሰማኝ ለማወቅ ከፈለጋቹ ራሳችሁ ስሙት። ይህ ሰው እንዴት ቢረቅ ቢመጥቅ ቢመነጠቅ ነው ትላላቹ። እና እጅግ የገረመኝ… ይሄንን nightingale የተሰኘ ስራ ለመስራት ምን እንዳነሳሳው ሲገልፅ… የሆነ ጊዜ ጣልያን ውስጥ እያለ በመስኮቱ በኩል ናይቲንጌል የምትባል ወፍ መጥታ ትዘምራለች። ተደነቀ፣ ተገረመ፣ ተደመመ። ጊዜ ሄደ ጊዜ መጣ። የሆነ ጊዜ ከቻይና ፍሉት ጋር ሲገናኝ ናይቲንጌል የተሰኘ ስራውን ያን ተንተረሶ ለመስራት ወሰነ። ከዛ በኋላ ያ ውብ ዜማ ተፈጠረ።
ሌላ እጅግ የደነቀኝ፣ የገረመኝ ያኒ ስለዚ ስራው ሲያወራ hans christian andersen ባለ ተረቱን አለመጥቀሱ ነው። ሊያውቀው ይችላል ግን መነሻው እርሱ አልነበረም ማለት ነው። እና ይሄ አይገርምም? … ዴንማርካዊው አንደርሰን በ1843 መቼቱን ቻይና ያደረገ የወፍና ንጉስ ታሪክ ሲፅፍ… ወፏ ለንጉሱ በመስኮቱ በኩል መጥታ እንዳዜመችለት… ለሙዚቃው ንጉስም ያኒ ቆይታ ያቺው ናይቲንጌል በመስኮቱ በኩል መጥታ ስታዜምለት መገጣጠሙ አይገርምም?። ያኒም ስለዚህ ስራው ሲያወራ "ለዚ ስራ የሚሆነኝ የቻይና ፍሉት ነው" ብሎ ማሰቡስ አይደንቅም? አንዳንዴ በዘመናት የሚገናኘው መግነጢሳዊ የተፈጥሮ ትስስሮሽ አያስገርማቹም???
ኩኩ መለኮቴ ኩኩ መለኮቴ
እሷ በፈሳችው በኔ አላከከችው
አባ ተቆጡልኝ
እማ ቆንጥጡልኝ
ኩኩ…
ይህ የልጅነት ትዝታችን የሆነ ዜማን ከእርግብ የቀዳው ኢትዮጵያዊስ ማን ይሆን? መነሻውስ ምን ይሆን? መጀመሪያ የእርግቧን ዝማሬ በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ይሆን የሰማው? የዜማውስ ሙሉ ታሪክ አለ ይሆንን? እንኳን ሙሉ ታሪኩን እኛ በልጅነት የዘመርነው መዝሙር ራሱ ቃል በቃል መረጃ መረብ ላይ ቢፈለግ የለም እኮ… ሲኖር የሚጠቁመን እንፈልጋለን። እሷ ማነች በሱ የላከከቺው? እሱስ ማነው የተላከከበት? ጠቁሙን ጠቁሙን ጠቁሙን…………
"መልስ የለም_መልስ የለም" ያለው ገጣሚማ ይሄንም ብሎ ነበር…
<<በድንቅ አብቃይ ምድር>>
(በዕውቀቱ ስዩም)
አገሩ በሙሉ፣ የብስና ባሕሩ፣ ውኃ ሠራሽ ኾኖ
ለምን ያስቡታል? አባይን ለመስኖ
ለ‘ኛ አልተሰጠንም? ዓለምን መመልከት፣ ከጥቅሙ ነጥሎ
ውኃ ተሸምኖ፣ ባዬር ሲተጣጠፍ፣ ማዬት ዝም ብሎ
ሐሳብን ማሳረፍ፣ ከማር፣ ከሰም ስሌት
ለኛ አልተሰጠንም፣ ማዳመጥ፣ማጣጣም፣የንብን
ማሕሌት
ዶሮን ከዶሮ ወጥ ነጥሎ መመኘት
ለሳት ቀለም ክንፉ፣ ለንጋት መዝሙሩ፣ ላጫጫር ምስጢሩ
ቃል መርጦ መቀኘት
ፈልጠው፣ ሳይማግዱት ወይም ሳይዳስሱት፣ ከስሩ
ሳይሰግዱ
ዋርካ አይደነቅም? በእንግዳ ህላዌው፣ በቅጠል በግንዱ?
መልስ የለም
መልስ የለም።
ከጢስ እና ውኃ የተሰራ ሸማ፣ ባዬር ይታጠፋል
ንቡም ይዘምራል፣ ዶሮውም ይጭራል፣ ዋርካውም በእጆቹ
አየሩን ይቀዝፋል
የማይገርመው ትውልድ፣ በድንቅ አብቃይ ምድር
እየኖረ ያልፋል።
ኩኩ መለኮቴ
ኩኩ መለኮቴ
በቸር እንዳዋልከኝ
በቸር አሳድረኝ
የሰማይ አባቴ
ኩኩ መለኮቴ
ኩኩ መለኮቴ…