Komentar baru

Advertisement

የዝንጀሮ ቆለጥ፣ ፍሩጣ (ሆጲ)

Eriyot Alemu
Jan 26, 2022
Last Updated 2024-05-18T01:57:37Z
Advertisement


<<ቤዛዊት ቤት ግቢ ‘የዝንጀሮ ቆለጥ’ ነበር። በፀሐያማ የበጋ ቀናት በምቾቱ ተስቦ ከአጥር ውጪ የተንዥረገገውን ወይናማ ፍሬውን እየዘለልኩ በጥሼ፣ የለበሰውን አቧራ ሳላፀዳ በልቼአለሁ። አበባዎቹን ካማሩበት አውልቄ ወለላቸውን መጥቼአለሁ። አባቷ ‘ችግኙ ከአንኮበር የመጣ ነው’ ሲሉ ሰምቼአለሁ።>> 
አዳም ረታ፣ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ ገፅ 115








አገላለፁ ለሌላም ተክል ክፍት ቢሆንም እንኳ ይሄ ከላይ አዳም የዝንጀሮ ቆለጥ ብሎ የገለፀው ተክል ልጅ ሆነን ግቢያችን ውስጥ ነበር። እኔ የማውቀው ፍሩጣ ወይም የጦጣ ቆለጥ በሚል ስሙ ነው። እዚህ አዳም መፅሃፍ ላይ እስካገኘው ድረስ ስለዚህ ተክል ያልጠየኩት ቅጠል አዋቂ አልነበረም። ገና የጦጣ ቆለጥ ምናምን ብዬ ስጀምር የማሾፍ እየመሰላቸው አፍ አፌን ይሉኛል። ስያሜው እውነታውን አደብዝዞት ይመስለኛል። ሲሰለቸኝ ተውኩት። በኋላ አዳም መፅሃፍ ላይ ሳየው ፍለጋዬ ዳግም አንሰራራ። 

ለምን እንደሆነ ልንገራችሁማ…
ይህ ፍሬ ድሮ ከኛ ግቢ ውጪ ጋሽ አበጀ የሚባሉ የጓደኛዬ አያት ግቢ ውስጥ ነበር። እና ግቢያቸው ደሞ ደን ነበር የሚመስለው። ታድያ የሆነ ቀን ግቢያቸው ውስጥ የሆነ ስራ አገዝናቸውና ሰብስበው ይሄን ፍሬ ሰጡን። ግቢያችን ውስጥ ቢኖርም እንደሚበላ አላውቅም ነበር። አቡበከር የሚባል ጩጬ "ይሄ እናቴ መርዝ ነው ስትል ሰምቻለሁ! አልበላም" ብሎ ፍርጥም አለ። ዮሴፍ "እርሶ ከበሉት እኛም እንበላለን" አለ። ሁላችንም ተስማማን። 

ጋሽ አበጀም ፍሬውን ፈልቀቅ አርገው ከከፈሉት በኋላ ከግማሹ ውስጥ በአውራ ጣታቸው ፈልቅቀው የሆነ የቲማቲምና የብርቱካን ዲቃላ የመሰለ ነገር ወደ አፋቸው አስገቡ። ከዛ በኋላ ነገረ ስራቸው ደስታ ከረሜላ እንደሚመጥ ትንጥዬ ልጅ ነበር። በልጅነት አዕምሮዬ ትልቁ ሰውዬ ልጅ ሆነው ሲታዩኝ አስታውሳለሁ። 

ከዛ በኋላ ሁላችንም እሳቸው እንዳደረጉት አርገን አፋችን ውስጥ ከተትን። ለመጀመሪያ ጊዜ የመጎምዘዝም የመጣፈጥም ስሜት እኩል የተሰማኝ በዚ ፍሬ ነው። ከኔና ዮሴፍ በቀር ሌሎቹ ወዲያው ከአፋቸው ተፉት። ዮሴፍ ሁኔታው እንደጣፈጠው ነገር ነው። እኔ መሃል ላይ ነኝ። 

አንድ ቀን ከትምህርት ቤት ስመለስ ከጓደኛዬ ጋር ሆነን ወደ ጋሽ አበጀ ቤት አመራን። ቁጭ ብለው ፍሩጣ ሲበሉ አገኘናቸው። 
"ምን ጥቅም አለው ግን?" አልኳቸው ለማለት ታህል ነው። ልጃቸው በማን ወጥቶ እንደሆነ አላውቅም ኮክ እንኳ ለመብላት ብዙ አይደፍርም።

<<አያስረጅም። አየኸኝ እኔ በዚ እድሜዬ ጠንካራ የሆንኩት፣ በሽታ የማያቀኝ ይሄን ስለምበላ ነው…>> ብለው አንድ በሐምራዊና ጥቁር መሃል ላይ ያለ ፍሬ ሰጡኝ። ባለፈው የሰጡኝ ጥሬ ቢጫ ቲማቲም የሚመስል ነገር ነበር። ስቀምሰው መጎምዘዙ ቀንሶ ጣዕሙ ጨምሯል። የጣዕም ለውጡ ከቀለም ለውጡ ጋር አብሮ የመጣ እንደሆነ ተረድቻለሁ። ከዛ ጊዜ ጀምሮ ግቢያችን ውስጥ ካለው ፍሩጣ ስር  አልጠፋም ነበር። አያስረጅም ምናምን ያሉኝ ግን ከልባቸው አልመሰለኝም። ያው ለልጅ እንደምትቀልደው አይነት ቀልድ ነው የወሰድኩት። 

ብዙ ጊዜ ሄዶ…እኔም ትንሽ ከፍ ብዬ ያው ሞት አይቀርምና ጋሽ አቤጀ አረፉ። የቀብራቸው ጊዜ ሲወራ የነበረው "በሽታ የማያውቃቸው" ምናምን የሚል ነገር ነበር። እንደተኙ ነው አርፈው የተገኙት። እኔ ግን አንድ ሃሳብ ውስጥ ልቤ ተቸንክሯል። <<አያስረጅም። አየኸኝ እኔ በዚ ዕድሜዬ ጠንካራ የሆንኩት፣ በሽታ የማያቀኝ ይሄን ስለምበላ ነው…>>… ልጅነት ይሁን አላውቅም ከፍሩጣው ጋር አገናኘሁት። ከዛ የጋሽ አበጀም ቤት ተሸጠ። ቤቱ ፈርሶ ሌላ ቤት ተሰራበት። እኛም ግቢ የነበረው የጦጣ ቆለጥ እንደ አረም ተቆርጦ ደረቀ። ጥላዬ ነው ብዬ እንዳልከራከር ሌላ ብዙ ጥላ ነበር። እንደምበላው ለመናገር ድፍረት አላገኘሁም። ጥቂት የሰፈር ልጆች በደንብ ያስታውሱታል ብዬ አስባለሁ። ብቻ ፍሩጣው በልቤ ውስጥ ብቻ ታሪክ ሆኖ ቀረ።

ከብዙ ጊዜ በኋላ አድጌ ወደራሴ ስመለስ ስለዚህ ተክል ትንሽ ነገር ይኑረኝ ብዬ ፍለጋ ወጣሁ። ተማሪዎች ሆነን ምናልባት የክፍለሃገር ልጆች ሊያውቁት ይችላሉ ብዬ ብዙ ጠይቄ ነበር። ወፍ የለም። ምናልባት አካባቢያዊ ስሙ ሊለያይ ይችላል ብዬ አለፍኩት። ለአቅመ ጎግል ደርሼ "ፍሩጣ" ብዬ ሰርች ሳደርግ… ጎግልዬ "ፈርጥ" ማለት ፈልገህ ነው? ብሎ ሙድ ያዘብኝ። የጦጣ ቆለጥ ብዬ እንደጀመርኩ ጎግልዬ ሌላ ታሪክ ውስጥ ገብቷል ሃሃሃሃ

ይሄ ሁሉ ድካሜ የዚህ ፍሬ ቅሪተ አካል በስጋም በፎቶም እጄ ላይ ባለመኖሩ ነው። አንዴ ታድያ ራስ ሆቴል ቁጭ ብዬ እንደዛ እንዳልፈለኩት አጠገቤ ተንጠልጥሎ አገኘሁት። ለክፋቱ ግን አንዲት ፍሬ ነበር የነበረው። ፌስቡክ በምጠቀም ሰዓት "ኸረ የዚን ተክል አካባቢያዊ ስያሜውን አልያም ሳይንሳዊ (እንግሊዘኛ) ስያሜውን የምታውቁ ካላቹ…  እስቲ ቅበሩኝ" አልኩ። ያገኘሁት መልስ ፎቶው ደብዛዛ ስለሆነና ፍሬው ወፍ የበላው ስለሆነ ለመለየት አስቸጋሪ መሆኑን ነው። ፍሩጣም የጦጣ (የዝንጀሮ) ቆለጥ የሚለው ስምም ያኔ የፌስቡክ ፖስቴን ላዩት ግራ እንደሆነባቸው ተረድቻለሁ። እልህ አስያዘኝ። እዚጋ ራስ ሆቴልን ያነሳሁት… ሊበቅልበት የሚችለውን ቦታም ጭምር ለማንሳት ነው። 

የሆነ ጊዜ የጓደኛዬ እናት ቤት የኩላሊት ጠጠር አለቦት ተብለው ጥየቃ ቁጭ ብያለሁ። አንዲት ተለቅ ያሉ ሴትዮ እግዜር ይማርሽ ሊሉ እንደኔ ተከስተዋል። የአዋሳ ሰው ናቸው። ለታማሚዋ ኦሪጅናል ሃኪም አፕል ጥሩ ነው ብሏቸው ጠረጴዛው ላይ በብዛት አለ አፕሉ። እኔም አንድ ደርሶኝ "an apple a day keeps the doctor away… " ብያለሁ በሆዴ። ኤ ዴዩን ተውቱና ተከተሉኝ… እኚ ተለቅ ያሉት ሴትዮ ታድያ በጨዋታ ጨዋታ "ሐኪም ፍሬማ ብዪ ካለሽ… ለዚህ መድሃኒቱ ሆጲ ነው" አሉ። አዲስ ነገር መስማት እንደሚያስደስተው ሰው ሴትዮዋ አፍ ውስጥ ነው መግባት የቀረኝ። 

"ምንድነው ሆጲ?" አሉ የጓደኛዬ እናት። ያው እናቶች መድሃኒት የሚያዝላቸው በሙሉ ሐኪማቸው አይደል? እንደኔ ለመስማት ጓግተዋል። 
"ያው እንደዚ ፍሬ ነው (ወደ አፕሉ እያሳዩ ነው)… ሲዳሞ በሽ ነው። እዚ ያለ አይመስለኝም። አንድ ቦታ ግን የዝንጀሮ ዳቢ ሲሉት የሰማው መስሎኛል" 
ጆሮዬ እንዲህ ቆሞ አያውቅም። ግን ለመጠየቅ ቸገረኝ። "የዝንጀሮ ቆለጥ ማለቶት ነው?" ብል ቦታውን የሚመጥን አይደለም። እኔ የማፍር ሰው ሆኜ ሳይሆን ቦታና ሁኔታ ስለምመርጥ ነው። እና ዝምብዬ ውስጡ የሚመስለውን ስጠይቃቸው ራሱ የዝንጀሮ ቆለጥ እንደሆነ ደረስኩበት። አቤት የተደስትኩት ደስታ። የተለየ ግኝት ያገኘሁ ነው የሚመስለው። በሁኔታዬ ሳይገረሙ አይቀርም።

ወዲያው ለጎግልዬ የሚሆን ተጨማሪ ግብአቴን ይዤ ኮምፒተር ፊት ተሰየምኩ። ላይሰራ ይችላል ብዬ በገመትኩት… የዝንጀሮ ዳቢ የሚለውን አስቀደምኩ። ወፍ የለም። ሆጲ ሳስከትልላቹ ያ ልጅ ሆኜ በኛና ጋሽ አበጀ ግቢ የማውቀው ፍሬ ምስል ኮምፒተሬ ላይ መጥቶ ዝርግፍ አለ። ደስ አለኝ ደስ አለኝ ደስ አለኝ። ከልጅነቴ ጋር በድጋሚ የተጨባበጥኩ ነው የመሰለኝ። ከዛ ስለዚህ ተክል የኛ ሰዎች ያሉትን ሁሉ እያደንኩ ሳጣራ… እኛ ሰፈር ፍሩጣ የሚባል ስሙ… ትክክል እንደነበር ተረዳሁ። አዲስ አበባ ውስጥ ስያሜው ያ ነበር። በሌሎች አካባቢ ተጨማሪ ስያሜዎች አግኝቻለሁ። እነዚህም አሻንፉሪት እና ፍሩንትሽ ነው። 

እንግሊዘኛ ስያሜው passion fruit ሲሆን… ይሄን ስም ያወጡት በ1700 ደቡብ አሜሪካ ውስጥ የነበሩ የስፔን ሚሶናውያን ናቸው። የዚ ተክል አበባ ቅርፁ… ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ ስለሚመስል፣ ህማማተ መስቀልን ይገልፃል በማለት ይመስለኛል—ይሄን ስያሜ የሰጡት። የmel gibson  the passion of the Christ ፊልምን ልብ ይሏል እዚጋ። 



በኛ ቤተክርስትያን አስተምህሮ ደግሞ "ሳዶር አላዶር ዳናት አዴራ ሮዳስ በተባሉት በአምስቱ ቅንዋተ መስቀል…" እንደምንለው ማለት ነው። በጣም የገረመኝ የአበባውን ቅርፅ በደንብ ብታዩት የገበረክርስቶስ ደስታ የስቅለት ስዕል በዓይናቹ ሙሉ ይመጣል። አስደግፎ ሁላ ነው የሳለው ብትሉ አልፈርድባችሁም። አንዳንዴ ነገሮች የሚገናኙበት ርቀት ይገርመኛል። 





እናላችሁ ወደ ፍሬው ስንሄድ…
በአንዳንድ አካባቢዎች መርዝ ነው አይበላም የምንለው ተክል ውጪ አገር በጥሬውም በጁስ መልኩም የሚጠቀሙት ውድ ፍሬያቸው ነው። በአገራችንም ይሄንን ፍሬ እያለማ በጁስ መልኩ ለውጪ ሃገራት በሃይለኛው የሚቸበችብ የውጪ ሃገር ድርጅትም አለ። ከሞኝ ደጃፍ ማር ይቆረጣል ምናምን ብዬ አይደለም ይሄን የማነሳው። ቢያንስ ሞኝ ደጃፉ ማር እንዳለው ያውቃል። የኛ ባስ የሚለው ማር እንዳለን እንኳ አለማወቃችን ነው። የምስራቅ አፍሪካ ገበሬዎች ቡና እየነቀሉ ጭምር ይሄን ተክል ማልማት ጀምረዋል የሚል ዘገባ አይቼ… ነገሩን ጥሩም መጥፎም ሳልል የዚን ፍሬ ዋጋ ግምት ግን ገምቼበታለሁ። 

ልጅ ሆኜ ጋሽ አበጀ ያሉኝን አሁን እንደወረደ የምቀበልበት እድሜ ላይ አይደለሁም። ግን ስለዚህ ፍሬ ጥቅሞች ሳነብ… በሽታ ተከላካይነቱን፣ በአንቲኦክሲዳንት የዳበረ መሆኑን፣ ለቆዳ ጥራት ፍቱን መሆኑን… ተደጋግመው ተመስክረውለት አይቻለሁ። የሆነ ነገሩ "አያስረጅም፣ በሽታ አያውቀኝም" ካሉት ነገር ጋር የሆነ ስምም አለው። ጋሽ አበጀ ያሉኝን እንዴት አሉኝ ነው ቁምነገሩ… በራሳቸው ላይ ጥናት ሰርተው ይሆንን? ከዚ በፊት ሌላ ሰው ነግሯቸው በራሳቸው አረጋግጠው ይሆንን? ምን ያህል አመት ከዚ ፍሬስ ጋር ቆዩስ? ወይስ ዝምብለው በአጋጣሚ ብለውኝ ቢሆንስ? ሌሎችም ብዙ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። ግን እሱ አይደለም ፍሬ ነገሩ። ከፋም ለማም ምን ያህሎቻችን አውቀን ተጠቅመነዋል ነው ለጊዜው መነሳት ያለበት ቁም ነገር የሚመስለኝ።
ሌላው ዋናው ጥያቄ ግን እኔ ይሄን ያህል ዓመት በልቤ ለምን ይዤው ቆየው ነው። ማን ያውቃል? ወዴት እንደሚወስደኝ………………………………………… 

አንድ ነገር እልህ ካስያዘኝ የምሄድበት ርቀት ለራሴ ይገርመኛል። ለአንድ ፌስቡክ ተጠቃሚ የልቤ ሰው የዚን ተክል ጉዳይ አማከርኩት። አፍቃሪ አትክልት ስለሆነም ጭምር ነው። ከዚህ በፊት "ፌስቡክ ላይ የጓሮ ማኅበረሰብ… የሚባል ግሩፕ አለ። የሌላቸው አይነት ችግኝ የለም" ብሎኝ ስለነበርም… ስለ ፓሽን ፍሩት ነግሬው አደራ ብዬውም ነበር። የሆነ ቅዳሜ (14/05/14) በፈንድቃ የጓሮ አትክልት ኤግዚብሽን ነበራቸው መሰለኝ። ኤግዚብሽኑ ላይ ደግሞ የዚን ተክል ችግኙን ሊያመጡለት ቃል የገቡ አትክልተኞች እንደነበሩ ሹክ ብሎኝ ነበር። 

ከዛ በኋላ ባለው ቀን ቤቱ ስለላ ሄጄ፣ ቤት ያፈራው ጁስ ብሎ የሆነ ቢጫ ጁስ አቀረበልኝ። ገምቻለሁ የፍሩጣ ጁስ እንደሆነ። መአዛው ምን ምን ቢል ጥሩ ነው?… ይገርማችኋል ራኒ ጁስ ራኒ ጁስ ነው የሚለው። ይሄ ፍሬ አሁንም ወደሌላ አቅጣጫ ሊወስደኝ ነው መሰለኝ አልኩ በልቤ። ደሞ እንደፈረደብኝ ስለ ራኒ ጁስ አሰራር ፍለጋ ልወጣ ነው ሃሃሃሃ በዛው ግን እንጀራዬ ሆኖ "ፍሩጣ ጁስ" ብዬ ብመጣ ዕጣ ፈንታ ነው የሚባለው መሰለኝ ይሄ ነገር። ያርግልህ በሉኝ… ይሄ ፍሬ በጣም ነገር እየፈለገኝ ስለሆነ ነው። ጣዕሙ ያው በመጎምዘዝ እና በመጣፈጥ መሃል ያለ የተለየ ጣዕም ነው። በጣም ነው ግን አፍ ላይ ደስ የሚለው። የቀመሱት ሁሉ መርዝ ነው አይበላም በተባለ ሐረግ መሳይ ተክል ፍሬ ተደመሙ። ተደመውም አልቀሩ ወደቤታቸው ሄዱ ሃሃሃሃ ይለቅ ብዬ ነው ታሪኩ። 

እስቲ አስቡትማ 
የፍሩጣ ጁስ የሃሳቡ አፍላቂ፣ መስራች፣ ገንዘብ ያዥ፣ ዋና አከፋፋይ ሆኜ በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቀርቤ፣ የፍሩጣ ጁስ ታሪካዊ አመጣጥን ይሄን ለናንተ የነገርኳችሁን ለጣቢያው ጋዜጠኛ ስነግረው… የደስታ ዕንባ በአይኔ ሞልቶ በጭላጭል እያየሁ ነው ይሄን የፃፍኩላችሁ ሃሃሃሃ 

ሁለት ነገር ነው ስለዚህ ተክል ብሎግ እንዳረግ ያደረገኝ። አንደኛው በልቤ የቆየው የተለየ የዚህ ተክል ፍቅር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጓደኛዬ "ስለዚህ ተክል ያለህን ፍቅር የምትገልፅበትን መንገድ አይቼ ስለ ችግኙ እንወያያለን" ስላለኝ ነው። ተሳክቶልኝ ይሆንን??? እንጃ ብቻ እኔ ግን ደስ ብሎኛል። 

iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

3 comments:

  1. Replies
    1. እንኳን ደህና ቆዩኝ!!! አመስግኛለሁም በእጅጉ!!! ያው እሪዮ በሚለው ግምት ወስጄ በመገመት እንጂ ፕሮፋይሎ አንኖውን ነው የሚለው። ለዛ ነው አንቱ ብዬ በእጅጉ ያከበርኮት። ይገባዎታል መቼም! ፆታ ድንገት ብሳሳትስ ብዬ ነውም። ለአንተም ለአንቺም ለማለት የገጠመ ነገር ገጥሞት ያውቃል? እንደሱ ነገር ነው ሃሃሃሃሃ እርሶ ከሆኑም ክበሩልኝ። ካልሆኑም ክበሩልኝ። እጅ ነስቻለሁ።

      Delete
  2. Lenem negeregne

    ReplyDelete

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement