Komentar baru

Advertisement

How to analyze people on sight!

Eriyot Alemu
Jan 26, 2022
Last Updated 2023-08-02T03:56:15Z
Advertisement


በዓሉ ግርማ በግሌ ምርጥ በሆነው ስራው፣ ከአድማስ ባሻገር ላይ ይሄን ያነሳል <<የትምህርት አላማው እያንዳንዱን ሰው ራሱን፣ ማንነቱን፣ የተፈጥሮ ችሎታውን እንዲያውቅ ማድረግ ነበር።>> መቶ በመቶ የምስማማበት ሃሳብ ነው። ጋሽ ብርሃኑ ድንቄም በአልቦ ዘመድ ስራቸው ላይ እንዲህ ይላሉ…
 << ትርጓሜው የማይገባኝን ትምህርት በቃሌ ማጥናት ያስቸግረኝ ነበር። እንደሚታወቀው የዛሬው ትምህርት አሰጣጥ የሚያበረታታው ተዘክሮን (memory) ነው። ፈተናን ለማለፍ የሚያስችለው የተዘክሮ ጮሌነት መሆን አለበት። እኔ በ(ትሪክ ኦፍ ሜሞሪ) አላምንም። የዚህ አይነት ትምህርት ሰውን እንደ መኪና (ሜካኒካል) ያደርገዋል ብዬ እፈራለው። ሰው ተዘክሮ ብቻ አደለም። >> ወረድ ብለው ደግሞ <<ሰው እንደየችሎታው ጠቅላላውን የተፈጥሮ ሕግ በመከተል ነፃነት ያለው የትምህርት አስተዳደግ እንዲያገኝ ይበረታታል>> ብለው ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ። 




ሰው የተፈጥሮ ማንነቱን እንዴት ሊያውቅ ይችላል? ብባል መልሴ ውስጡ ስላለና ውስጡ ስለሚገፋው ብቻ ሊሆን ይችላል። መስማት አለመስማት የሰውዬው ፈንታ ቢሆንም ቅሉ። አሁን ላወራው የፈለኩት ከባለቤቱ ውጪ እኛም ልናውቅ የምንችልበት መንገድ አለ ወይ? የሚለውንም ጭምር ነው። 

ጥቂት በሶምሶማ እንሩጥ… 

በ1921 የወጣ አንድ ጥናታዊ መፅሃፍ አለ። how to analyze people on sight ይሰኛል። በተለያየ አጋጣሚ  ካየኋቸው ጥናታዊ ስራዎች ሁሉ ያለማመንታት "በጣም ትርጉም የሚሰጥ ስራ" ብዬ የምምልለት ብቸኛ መፅሃፍ ነው። ህይወቴንም ዓለምንም የማይበትንም መነፅርም የቀየረ ስራ ነው። በሃሳቤ ለሳልኩት ዩቶጵያዬም መነሻ የሆነኝ ብርቅዬ ስራ ነው። እንደ ማናቸውም ጥናት ፍፁም አይደለም። ሊሆንም አይገባም። አንዳንድ ግድፈቶችን ላሻ እያሉ መኮምኮም ነው። የታተመበትን ጊዜም ከግምት ማስገባት ማስተዋል ነው። 

መፅሃፉ ላይ ይህ ነገር ሰፍሯል። 
Modern science has proved that the fundamental traits of every individual are indelibly stamped in the shape of his body, head, face & hands –– an X–ray by which you can read the characterstics of any person on sight. 
በሌላ በሙሉ መፅሃፉ ሃሳብ አገላለፅ… የሰዎች ተክለሰውነት፣ የፊታቸው፣ የጭንቅላታቸው፣ የእጃቸው መጠንና ቅርፅ ተፈጥሮአዊ የሆነውን ባህሪያቸውን ይናገራል እንደማለት ነው። መፅሃፉን አንብቦ በአግባቡ ራሱን የተረዳ የመፅሃፉን ልክነትም የሌሎችንም መሰረታዊ ባህሪ ይረዳል ማለት ነው። 





መፅሃፉን አንብበው ሲጨርሱ ራሶትን በማወቆ ይገረማሉ። ቀጥሎ ሰዎችን አበጥረው የሚያውቁበት ዕድል ሰፊ ቢሆንም… ሰው ከራሱ ውጪ ብዙም ሌላው ላይ አለማተኮሩ ሌላው ተፈጥሮአዊ ባህሪ ነውና… ገፍተው ባይሄዱም አይገርምም። ሲያነቡ ኤክስ ከገባብዎት ካነባበዎ ችግር ሊሆን ስለሚችል… ፊደሉን በደንብ እስኪለምዱት ድረስ ደጋግመው በማስተዋል ያንብቡ። አይቸኩሉ። ሳይሳሳት ልክ የሚሆን ማንም የለምና። ሀሁ ኤቢሲዲ እንደመቁጠር ነው። ያኔ ለአለም፣ ለሰዎች ያሎት መነፅር ይለያል። እንዲህ ነውንዴ ለካ ይላሉ ጮክ ብለው። ጮክ ባይሉም ችግር የለውም።

እንደ መነሻ ሰዎች አምስት አይነት የፊት መለያ ቅርፅ አላቸው። ክብ፣ ወላንዶ (kite አይነት ቅርፅ)፣ አራት ማዕዘን፣ ካሬ እና ሶስት ማዕዘን ናቸው። እነዚህ መነሻ ኤቢሲዲዎች ናቸው። አብዛኛው ሰው የነዚህ ድብልቅ ስለሆነ። መጀመሪያ የሚጠናው ንፁህ ክብ፣ ንፁህ ወላንዶ፣ ንፁህ አራት ማዕዘን፣ ንፁህ ካሬ እና ንፁህ ሶስት ማዕዘን ስለሆኑ ሰዎች ነው። ከዛ ድብልቁን ማንበብ ቀላል ነው። 

ትንሽ ሁሉንም በጣም በስሱ ስናይ… እንደ ትንሽ መገለጫ… ቅርፃቸውን ከታች መጠቀሙ፣ ለችኩል ሰው አላስፈላጊ ለሆነ የችኩል ድምዳሜ ስለሚዳርግ፣ ቅርፁን ዘልዬ የዳበረውን ክፍል ብቻ ዘርዝሬ ልልፍ…

1) አንደኛዎቹ:— የሆድ ዕቃቸው ከሌላ የሰውነት ክፍላቸው በአንፃራዊነት እጅጉን የተደራጀ ነው።

2) ሁለተኛዎቹ:— ሰርኩላተሪ አና ሪስፖራቶሪ ሲስተማቸው ከሌላ የሰውነት ክፍላቸው በአንፃራዊነት የተደራጀ ነው። 

3) ሶስተኛዎቹ :— ጡንቻዎቻቸው ከሌላ የሰውነት ክፍላቸው በአንፃራዊነት የተደራጁ ናቸው። 

4) አራተኛዎቹ :— የአጥንት ክፍላቸው ከሌላ የሰውነት ክፍላቸው የተደራጀ ነው። 

5) አምስተኛዎቹ:— ነርቨስ ሲስተማቸው ከሌላ የሰውነት ክፍላቸው በአንፃራዊነት የተደራጀ ነው። 

ከላይ በግርድፉ የተዘረዘሩት ንፁህ ታይፕ የሚባሉት ናቸው። ያው በአንፃራዊነት በደንብ እንደተደራጀው ሲስተማቸውም ማንነታቸውም በዛው ልክ ቅርፅ ይይዛል ማለት ነው። ምሳሌ ብናይ ነርቨስ ሲስተማቸው ከሌላ የሰውነት ክፍላቸው በአንፃራዊነት የተደራጀው የጭንቅላት ስራ ከጉልበት ስራ የበለጠ ይስባቸዋል። አወቁትም አላወቁትም ራሳቸውን መሰል በሆነ የጭንቅላት ስራ ስር ሲውተረተር ያገኙትና… ከቆይታ በኋላ ማንነቴ ብለው የሚገልፁት ራሳቸውን ቀርፀው ያወጣሉ። 

ሆኖም አለም ላይ በብዛት የሚገኘው ድብልቁ ነው። ተደባልቀው ሳለም ዶሚኔት የሚያረገው ታይፕ፣ የአንድ ሰው መገለጫው ይሆናል። 
ለምሳሌ አንድ ሰው የመጀመሪያ ሜክኣፑ ነርቨስ ሲስተሙ በእጅጉ የተደራጀው ሆኖ ሁለተኛ ሜክኣፑ ደግሞ የጡንቻ ክፍሉ በእጅጉ የተደራጀ ሊሆን ይችላል። እና ይህ ሰው በህይወቱ ማሰብ ማሰላሰል የሚፈልግ የጉልበት ስራ ላይ እንደጉድ ይራቀቅበታል እንደማለት ነው። ግብብዲያ ሮቦቶች በዚህ ሰው ታስበው ሊፈጠሩ ይችላሉ። ዞሮ ዞሮ ግን የዚህ ሰው ዋነኛ መንጠላጠያው ማሰቡ ላይ ነው። ምክንያቱም ዋነኛ መገለጫው የመጀመሪያ ሜክአፑ ስለሆነ። 

አሁን በቅርፅ ትንሽ እናውራ… 
ከላይ እንዳነሳሁት ምሳሌ አንድ ሰው ሶስት ማዕዘን በወላንዶ ሊሆን ይችላል። አልያም ወላንዶ በሶስት ማዕዘንም ሊሆን ይችላል። በጣም ሲሄድም ሶስት ማዕዘን በወላንዶ በክብ ሊሆንም ይችላል። ስለዚህ በደንብ ማንበብ ሳንችል አንድ ሰው ክብነት ያየን ስለመሰለን ብቻ እንደዚህ ነው ማለት አንችልም። ለምሳሌ አንድ ሰው የሶስት ማዕዘንም የክብም ሜካፕ ካለው ክብም ሶስት ማዕዘንም እንዲሁ ገፅታው ሊያሳየን ይችላል። ቀርቦ ማንበብ መቻሉ ጥቅሙ እዚህ ላይ ነው። ግንባሩ፣ የጭንቅላቱ እና የሰውነቱ ፕሮፖርሽን፣ እጆቹ ናቸው ምን እንደሆነ የሚነግሩን። ቀርበን ስናነብ ወይ ክቡ ወይ ሶስት ማዕዘኑ ዶሚኔት አርጓል ማለት እንችላለን።

እና ሰዎችን የምናነበው የጭንቅላታቸውን፣ የፊታቸውን፣ የእጃቸውን ቅርፅ በአንድነት በማየት ነው። እያንዳንዱ ታይፕ የራሱ የሆነ የእጅ ቅርፅም አለው። በመጠንም ይለያያል። የእጅ መዳፍ ማንበብ ከዚህ ሃሳብ ጋር ምንም አይገናኝም። እሱ ሌላ ረዥም ታሪክ ነው። አጀንዳችን ስላልሆነ ማዘለያውን ተጭነናል።


ምዕመናን ወ ምዕመናት ሶስት ማዕዘን ወላንዶ ካሬ ስል ባይገባቹም የሚጠበቅ ነው። እኔ ከመፅሃፉ ጋር ብዙ አመታት ስለቆየሁና ለኔ አዲስ ስላልሆነ እንጂ መጀመሪያ ለሚሰማው ግራ እንደሆነ ግልፅ ነው። ልክ ፊደል ስንማር ግር እንደሚለን ነገር። በምችለው መጠን የሆነ የሚዳሰስ ምስል ለመፍጠር እንደሞከርኩ ግን ተሰምቶኛል። የበለጠ ለጥጦ ለማውራት መፅሃፉን ማንበብ፣ አንብቦም በሃሳቡ የተወሰነም ቢሆን መስማማት ስለሚያስፈልግ ነው። ፍፁም በመፅሃፉ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ መስማማትም ጭራሽ እናት ተፈጥሮን አለማውቅ ነው። ልዩነታችን ውበታችን ነው። መፅሃፉን ጀምሮ የማይጥመው ሊኖር እንደሚችል ከወዲሁ ስለማውቅ ነው። ምክንያቱንም ጭምር። ብቻ ጠቅለል ያለ ስዕል መሳሌን ቀጥያለሁ።

እና ምንድነው… 
አጋጣሚውንም ተጠቅሜ ሰዎች እንደስሪታቸው እንደሚለያዩ አውቀን፣ ራሳችንን ከተፈጥሮኣችን ውጪ በሆነ ጉዳይ ማነፃፀር ብናቆም ደስ ይለኛል  እንደማለትም ነው። አንዱ ከአንዱ በተለያየ ሁኔታ ቢለያይም፣ ማንም ከማንም ሊወዳደር አይችልም። ማንም ማንንም አይበልጥም። ማንም ከማንም አያንስም። ማሰላሰል የሚወድ ዝንባሌው ነውና እንደዛው ይሁን፣ ወጥሮ መስራት የሚያዝናናውም ወጥሮ ይወርክ፣ ምግብን በፍቅር ኢንጆይ የሚያረገውም ይቸመው፣ የሚፈርክ ይፈርክ፣ የሚዘንጥ ይዘንጥ፣ የሚዘል ይዝለል፣ ዝም ነፍሱም ዝም ይበል። እና አንዱ ባንዱ አይወሳሰብ። ሰው ራሱን ይሁን ራሱንም ይውደድ ትላለች እናት ተፈጥሮ። ማንበብ የማይመቸው ቡሌ ነፍሱ የሆነ ፀዴ ፀዴ ምግቦች እየሰራ ይራቀቅ። ግን በትንሹም ስለ ምግብ አሰራር መሰል ወንድሞቹ የፃፉትንም ማንበብ የመብላቱን ያህል ያዝናናዋል ብዬ አስባለሁ። ዋናው ግን ራስን መሆን ነው። እኒህ ሁሉ ከላይ ያሉት በአንድነት ሲኖሩ እንጂ አንድ አይነት ሲሆኑ አለም አይደላትም። ራሳችንን ስንሆን የቅናት ዛራችን ፀጥ ረጭ ይላልና። ራሳችንን ስንሆን የሚመስሉንን የምናየው በፍቅር ሆኖ ስለሌሎች ደግሞ ብዙም ግድ አይሰጠንም። 

እንግዲህ ብዙ ጊዜ አለማችን ላይ የተለያዩ ችግሮች እንዲፈነጩ ያደረጋቸው አንድም ማንነትን በሚገባ ካለማወቅ የመጣ ነው። አንድም በሌላው ማንነት ተፅህኖ ስር በመውደቅ ነው። አንዳንዶች ተቀባይነት ያስገኛል በሚሉት የራሳቸው ያልሆነ ተፈጥሮ ሲዳክሩ ይታያል። ይህ ልክ አይደለም። ተፈጥሮ ፍፁም ነች። ከኛ በላይ የሚያስፈልጋትን ጠንቅቃ ታውቃለች። ሁሉንም እንደሚያስፈልጋት ልክ አርጋ ነው ያበጃጀችው። ሆኖም በአለም ላይ በተለያዩ ምክንያቶች የአንዱ ማንነት አንዱን ሲጫነውም ይታያል። ግን ተፈጥሮን ማሸነፍ አይቻልም። አንድ ቀን ሁሉም ቅርፅ ይይዝ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። 

እናም ብዙ ጊዜ ነጭ ጥቁር፣ ሴት ወንድ፣ ብሄሬ ብሄርሽ፣ ሕዝቦች ሕዝባር ወዘተርፈ የሚሉ ቡድናዊ ትግሎች በራሳቸው ስህተት ባይሆኑም የምንጊዜም ዘላቂ መፍትሄ ስለማይመስሉኝ ከልቤ ልብ ብያቸው አላውቅም ነበር። (እንደ አሁኑ ጊዜአችን ካልተገደድኩ በቀር)። ግን ምንም ተቃውሞ የለኝም። በርግጥ አሁን የማስበው ሃሳብ ከእውነታው አለም ብዙ የራቀ ቢመስልም ግን አራቀም። አንዳንድ ነገሮችን በመቀየር ሰው ተፈጥሮአዊ ማንነቱን እንዲቀርብ እያደረጉ በመስራት የችግሩን ምንጭ ማድረቅ ይቻላል ብዬ በፅኑ አምናለሁ። የተሻለች አለም መፍጠሪያው የተሻለው መንገድ ሰውን ከራሱ ጋር በማስማማት የሚጀምር ይመስለኛል። ለዛም አለምን እንደአዲስ ማራገፍ ቢጠይቅም መቶ በመቶ ዝግ አይመስለኝም። የብሄር ፖለቲካ (ስሙን እንደፈለጋቹ ማሰማመር ትችላላችሁ) ከተፈጥሮአዊ ማንነት እጅግ የሚያርቅ ንጥረ ነገሮች ሁሉ በውስጡ ስለያዘ… ከሌሎች ፖለቲካዊ አስተዳደሮች በሙሉ ለሰው ልጅ ደስታ እጅግ ፀር ነው ባልል ግን ይቆጨኛል። ዋነኛ አላማዬ እሱ ባይሆንም በዚ ብሎግ። 

እናም አንድ ቀን የትምህርት አሰጣጡ፣ የአስተዳደር ሁኔታው በሂደት ቢቀየሩ ሰዎች ምድር ላይ በሰላም በእኩልነት በነፃነት ሊኖሩ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ። ጥቂት! ብዙ አመታት ቢፈጅ ነው። በጊዜ ከጀመርነው ቶሎ እንደርሳለን አልያም በተመሳሳይ አዙሪት ስንቋሰል እንኖራለን። እንደ አለም ነው እዚህ ጋር የማወራው። የኛን ውጤቱን እያየነው ስለሆነ መከራ ካስተማረን ትንሽ ፈቀቅ የምንል ከሆነ ስለነገ ተስፋ አደርጋለሁ። 

አስተዳደር ስል ፕሌቶ ጥንት ድሮ ሰዎችን በዚህ መልኩ ከፋፍሏቸው ነበር… 
Plato lists three classes in his ideal society.
1. Producers or Workers: The laborers who make the goods and services in the society.
2. Guardians/Soldiers: Those who keep order in the society and protect it from invaders
3. Philosopher Kings: are the most intelligent, rational, self-controlled, in love with wisdom, and well suited to make decisions for the community, and who promote the interests of the society as a whole. 

እንደዘመኑ እጅግ ገራሚ ነገር ነው። ከላይ በቅርፃቅርፅ ከተዘረዘሩት ውስጥ ሶስቱን ከሞላ ጎደል ተመሳስሏቸዋል። አሳቢ የትኛውም ዘመን ላይ አሳቢ ነውና ላይገርምም ይችላል። ምናልባትም ከላይ ያነሳሁትን የጥናት ፅሁፍ መነሻ የሆናቸው ይህ የፕሌቶ ሃሳብም ሊሆን ይችላል። አላውቅም። ነጥቡ ግን ሰዎች ተፈጥሮአዊና ጤነኛ በሆነ መንገድ እንደሚለያዩ ማወቃችን ነው። ማንም ከማንም ግን አያንስምም አይበልጥምም። ሲጀምር ሊነፃፅር የማይችል ነገር ስለተላመድን ነው ይሄን የምደጋግመው። እንደማስታወሻ የፕሌቶን የክፍፍል ስያሜዎች እንደዘመኑ ተረድቼው… ትኩረቴና መስማማቴ ያለው ግን ግብሩ (መገለጫው) ላይ መሆኑን ገልጬ ልለፍ። 

በመጨረሻም ሁላችንም የተፈጠርንበትን ነገር ከለየን በኋላ (በአንድም በሌላም እስከአሁን ያወቅነው አንጠፋም በሚል) ምን እንደምናደርግ አንስቼ አበቃለሁ። የተፈጠርንበት ነገር ኦልረዲህ ጠንካራ ስለሆነ የጎደለን ላይ መስራት ተገቢ ነው። ለምሳሌ አሳቢዎች ጉልበታቸውን ማዳበር ላይ ቢሰሩ መልካም ነው። እና ፕራክቲካል ቢሆኑ… ኢማጅን ማድረግ ስለሚያዝናናቸው፣ ፕራክቲካሉን አለም ይፎረግቱታል። ብዙ ስላየኋቸው ነው ሃሃሃሃ ሌሎቹም ያላቸውን ከለዩ በኋላ በመጠን የጎደላቸው ላይ ቢሰሩ አለማችንን ፀዴ ማረግ ይቻለናል ብዬ አካብዳለሁ። አንድም ይሄ አንዳችን ያለ አንዳችን ምንም መሆናችንን ያሳየናል ብዬ ስለማስብ ነው። የአንዱ ጥንካሬ ለሌላው ድክመቱ ነውና! 

ቡሩንዲዎች ምን ይላሉ? <<ስታደርገው ደስ የሚልህ ነገር የመገለጫህ ነፀብራቅ ነው>> በርግጥ ቡሩንዲዎች እንደዛ አላሉም። ቢሉስ ብዬ ነው ሃሃሃሃ  ወገኖቼ እንግዲህ ረዥሙን ስናሳጥረው ይሄን ይመስላል። ወደፊት ደሞ የሰዎችን ታይፕ በቀላሉ የሚናገር ሶፍትዌር ተሰርቶ ሰዎችን በፎቶ መረጃ ብቻ  አይቶ… የትኛው ታይፕ እንደሆኑ የሚናገር ማሽን ያለበት፣ ሳይንስ ፊክሽን ፊልም ተሰርቶ ማየት እናፍቃለሁ እላለሁ እኔ ናፋቂያቹ። በዲጂታል አለም ይህ እጅግ ቀሊል የሆነ ጉዳይ ነውና። የዳይኖሰሮች ድብድብ ማየት ሰልችቶኛል ሃሃሃሃ  

ከግርጌ ከፍ ብሎ ያለ ማስታወሻ:– የዚ ብሎግ አላማ… እዚህ ድረስ ሳይታክት ያነበበ ሰው ስለ ቅርፁ አልያም ስለ ሌሎች ቅርፅ፣ ቅርፃቅርፅ እንዲጨነቅ ሳይሆን… ሰዎች እንደሚለያዩ የሚያሳይ ሳይንሳዊ ጥናት እንዳለ ለመጠቆምም ጭምር ነው። ሰው መፅሃፉን ሳያነብም የሆነ ስዕል ይኑረው ብዬ ነው ረዥም ያበራሁት። ሆኖም የተወሰወሰ ሰው ሳልለው መፅሃፉን ጎግል አርጎ አውርዶ እንደሚያነበው እገምታለሁ። እንደፍጥርጥሩ…… 

ፒዲኤፉን በዚህ ያግኙ how to analyze people on sight
iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

Leave Your Comment

Post a Comment

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement