Advertisement
ማስታወሻ 1:– የዚህ ብሎግ መነሻም መድረሻም ፌስቡክ መጠቀም መተው ፈልጎ ላቃተው ብቻ ነው። ፌስቡክ ተመችቶት (ለፈለገው አላማ ሆኖለት) በፌስቡክ ምርቃና…
ፌስቡክዬ የኔ አላማ
ስላንቺ ክፉ እንዳልሰማ
ብሎ ግጥም የገጠመ…
ማስታወሻ 2:– በግል ፌስቡክ መጠቀም ካቆምኩ ጀምሮ በህይወቴ የጨመርኩት ነገር ቢኖር፣ ህይወቴን ለማንም ሰው አለማብራራት ነበር። ለምሳሌ "ፌስቡክ መጠቀም ተውኩ።" … አለቀ በቃ! ከማንም ሰው ጋር ቁጭ ብዬ "ለምን ስለምን ተውኩ?" ብዬ አላወራም። ፋይል እዘጋና ወደ ሌላ ህይወቴ አመራለሁ።
በሆነ የቀን አጋጣሚ ግን ይህ ተከሰተ… … …
የጓደኛዬ ሚስት ደወለችልኝና… <<ትላንት ጓደኛህ ስልኩን ሰባበረው!>> አለችኝ። እርግጠኛ ሆኜ <<ያቺን የምናቃትን ጠጥቶ ነው ኣ?>> ስላት <<የማንኪያ ጠብታ እንኳ አልቀመሰም!>> ስትለኝ ግራ ተጋባው። ወዳጄ አንዳንዴ እንደሚቀብጥ አውቃለሁ። <<እና አዲስ ነገር ብሎ፣ ስልክ መስበር እየተለማመደ ይሆን?>> ስላት ቆጣ ባለ ድምፀት <<አንተ ምን አለብህ ቀልድ… ከትላንት ወዲያ ማታ ሶስት ሰዓት አካባቢ ቤት ገባ። ከዛ ቀን በፊት ‘ፌስቡክ መጠቀም አቁሜያለው’ ብሎኝ ስለነበር… ‘ለአንድ ሰላሳ ደቂቃ የሆነች ቼክ የማረጋት ነገር አለች!’ ብሎኝ እስከ ለሊቱ ሰባት ሰዓት ስልኩ ላይ ተጥዶ ነበር። … >> ብላኝ ትንፋሽ ወሰደች።
<<ጠዋት ስነሳ ስልኩ መሬት ተሰባብሮ ሶፋ ላይ ተኝቶ አገኘሁት። ሳልቀሰቅሰው ትቼው ወጥቼ ማታ ቤት ስገባ ከሰላምታ በፊት ይሄን አለኝ… ‘ፌስቡክ መተው ከፈለኩ አመት አለፈኝ። አልቻልኩም። በራሴ በጣም ተናድጃለሁ! … ቆይ ይሄ እንዴት ያቅተኛል?’ … የሱ ጥያቄ የኔም ነው። በርግጥ እኔ እንደሱ ብዙ ተጠቃሚ አይደለሁም። ግን ትንሽም የምጠቀመውን መጠቀም ሳልፈልግ ነው የምጠቀመው። እና ስላንተ አለመጠቀም ስነግረው ‘ተይው እሱ አስማተኛ ነው!’ ሲለኝ አስማትህን ትነግረኝ ዘንድ ይኸው ወዳንተ ደወልኩ>> ስትለኝ በአስማቴ ስልኩን ሳትዘጋው ተሰናብቻት ቁጭ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ።
የኔ መንገድ ሰዎችን አልያም አንድም ሰው የሆነ ቦታ ላይ ይረዳው ከሆነ ለምን ብሎጌ ላይ አልፅፈውም ብዬ ተነሳው። በርግጥ ይሄን ሃሳብ እንዳነሳው ያደረገኝ ከላይ ያነሳሁት ስልኩን ሰባሪ ጓደኛዬ ነው። ከሱ ጋር በፌስቡክ አጠቃቀም ዙሪያ ሳወራ ቃል በቃል እንዲህ አለኝ… <<አንተማ እኔ ውስጥ ኖረሃል!>> … ስሜቱን ስለተረዳሁለት ይመስለኛል። እርግጠኛ ሆኜ ባላወራውም ስጋ ለባሽ ሆኖ ራሱን የማይዋሽ ሰው የሰዎች ስሜት ምን እንደሚመስል ማወቅ ይከብደዋል ብዬ አላምንም። በአርቴፊሻል ቅራቅንቦዎች ስለምንለያይ እንጂ መሰረታዊ ሰውኛ ባህሪያችን አንድ ነው ብዬ አምናለሁ። ወደ ጉዳያችን እንግባ…
እንደ መንደርደሪያ
ፌስቡክ መተው ቀላል ነገር እንዳልሆነ አውቃለሁ። ይሄን የምለው እኔ ስለተውኩ ራሴን በከባድ ሚዛን ለማሳየት አይደለም። እኔ ተራነትን የምወድ ተራ ሰው ነኝ። እውነቱ ፌስቡክ መተው ቀላል አይደለም ብዙዎች ግን አድርገውታል ነው። እጅግ ብዙዎች። ፌስቡክ መተውን ካከበዱት ነገሮች አንዱ የሆነውን የፌስቡክ ዘፍጥረትን በግርድፉ እናያለን።
የፌስቡክ ዘፍጥረት
በመጀመሪያ ፌስቡክ አልነበረም። በመቀጠልም ማርክ ዙከርበርግ የተባለ ግለሰብ ፌስቡክን ፈጠረ። በውስጡም ጥቂት ጓደኞቹ ነበሩበት። አላማውም መልካም ስለነበረ በብዙ ምዕመናን ዘንድ አድናቆትን አተረፈለት። ይሄም መልካም እንደሆነ አየ።
አንደኛው ክፍለጊዜ
በሁለተኛው ክፍለጊዜ በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ እየተጠራሩ ወደ ፌስቡክ መርከብ ገቡ። ሰዉ የሩቅ ዘመዱን፣ የልጅነት ጓደኛውን፣ እጅግ የሚያከብረውን ሰው፣ መሪውን ሁሉንም አይነት ሰው በቅርቡ ማግኘት ጀመረ። ይሄ አጃኢብ አሰኘው።
ሁለተኛው ክፍለጊዜ
በሶስተኛው ክፍለ ጊዜ ዙከርበርግ እና ቡድኑ ይሄ ሁሉ ሰው የሚመገበው ምግብ ማሰናዳት ጀመሩ። ላይክ፣ ኮመንት እና ሼር የተባሉ ምግቦች ለሰው ልጅ ዶፓሚን መቆጣጠሪያ አስፈላጊ ነገሮች እንደሆኑ ተረዱ። ሰዉም እንደ ፓቭሎቭ ዶግ በኖቲፊኬሽን ብቻ ፈገግታ መጫር ጀመረ። አሁን ማስታወቂያ ሰሪዎችን እናምጣቸው ተባባሉ። ይህም ሆነ።
ሶስተኛው ክፍለጊዜ
አራተኛው ክፍለጊዜ ላይ ሰዎች ሁሉ አብረው መቆየት ስላበዙ የጋራ የሆነ አጀንዳ ብቻ ወደ መፍጠር ተሸጋገሩ። በሂደት የአዕምሮአቸውም ጠባይ ተለውጦ ስለነበር ብዙም አልተቸገሩም። የጋራ አጀንዳውን ፖለቲካ ብለው ይጠሩታል። ከጫፍ እስከ ጫፍ አብረው ብዙ የቆዩ ሰዎች የሚያግባባቸው ይሄ ብቻ እንደሆነ አመኑ። በዚህ መሃል ሰው ሁሉ የራሱን ቀለም እያጣ እንደመጣ አልታወቀውም። ሰው ሁሉ አንድ አይነት እንስሳ ሆነ። “ሰው ማህበራዊ እንስሳ ነው!” የሚለው የአርስጣጣሊስ ጥቅስ እንዲፈፀም ግድ ነውና!
አራተኛው ክፍለጊዜ
አምስተኛው ክፍለ ጊዜ ላይ አንዳንድ ነብያት ተነስተው “አረ ወዴት እያመራን ነው?” ሲሉ በምድረ በዳ መጮህ ጀመሩ። ጥቂቶች የጥቂቶችን ጩኸት በመስማት ከፌስቡክ መርከብ መውጣት ጀመሩ። ይሄ ለፌስቡክ ባለቤቶች የማንቂያ ደወል ነበረ። ገና ሲነሱም ጀምሮ የሰዎችን ባህሪ አጥንተው ስለገቡ… ለሰዎች ከፌስቡክ መጥፊያ ጊዜ 14 ቀን ቆረጡ። የሰው ልማድ ለመቀየር በትንሹ ከ6 እስከ 14 ቀን እንደሚፈልግ ያውቁ ስለነበር ነው። ሰውም የፌስቡክ አካውንቱን ዲሊት ብሎ ከተጫነ በኋላ 14 ቀን ሳይሞላው፣ አቅቶት ተመልሶ ከች ይላል። የፌስቡክ መስራቾች ይሄም መጥፎ እንዳልሆነ አዩ።
አምስተኛ ክፍለጊዜ
በስድስተኛው ክፍለጊዜ የፌስቡክ እውነተኛ ችግሮች እያፈጠጡ መጡ። ተገናኝተናል ብለው ያሰቡ ሰዎች የበለጠ ተለያዩ። ሰዎች ለድብርት፣ ለብቸኝነት፣ ለግልፍተኝነት፣ ለእንቅልፍ ማጣት፣ ለትኩረት ማጣት፣ የማስታወስ ችሎታቸው የመዛባት፣ አቴንሽን ስፓናቸውን የማጣት፣ ፈጣሪ የሆነው የአዕምሮ ክፍላቸው የመደንዘዝ፣ የቅናት ባህሪያቸው ከፍ የማለት፣ የበታችነት ስሜት የመሰማት ሁኔታቸው ከፍ እያለ መምጣቱን ሲሪየስ ህክምና የሚፈልጉ ሰዎች መፈጠራቸው ገሃድ አወጣው። ወደ ህክምና ያልሄዱ ሰዎች ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮችን የፈጠረባቸው ፌስቡክ እንደሆነ እንኳ አይረዱም። የግል ችግራቸው ይመስላቸዋል። በዚህ የተነሳ የ14 ቀኑን ቀጠሮ ተቋቁመው ከፌስቡክ ከነአካቴው የሚጠፉ ሰዎች እየተበራከቱ መጡ። የፌስቡክ ባለቤቶች ይሄ መልካም እንዳልሆነ ተገለጠላቸው ።
ስድስተኛ ክፍለ ጊዜ
በሰባተኛው ቀን የፌስቡክ መስራቾች ተሰበሰቡና ተማከሩ። ከፌስቡክ ሙሉ በሙሉ የመጥፊያውንም ጊዜ 30 ቀን አደረጉት። በእነዚህ ቀናት ብዙ ሰው ለመውጣት የቆረጠ ሁሉ ተመልሶ ሲመጣ ስላዩ ተረጋጉ። 30 ቀን ብዙ ነው። በነዚህ 30 ቀናት ከፌስቡክ የሚወጣ ሰው ከፌስቡክ ወቶ እንዲቀር የሆነ አንዳች እገዛ እንደሚያስፈልገው ተረዱ። ያኔ በኩራት ሰዎቻችን ወደየትም አይሄዱምና እንረፍ ተባባሉ። አረፉም።
ሰባተኛው ክፍለጊዜ
ይሄን ዘፍጥረት ያዘጋጀሁት እጅግ ተጨንቄበት አይደለም። መሰረታዊ ሂደቱን በግርድፉ ሰው እንዲረዳው ብዬ ነው። ዋነኛው ጉዳያችን እሱ አይደለም። ቀጥሎ የራሴን ልምድ በስሱ አጋራለሁ።
የራሴ የፌስቡክ ልምድ
ፌስቡክን የተቀላቀልኩት 2009 ነው በፈረንጅ አቆጣጠር… መጀመሪያው ብዙ ነገሩ ደስ ይል ነበር። ብዙ ወሳኝ ሰዎች ተዋውቄበታለሁ። ራሴን አስተዋውቄበታለሁ። ከጓደኞች ጋር ስንገናኝ ወሬያችን ሁሉ ፌስቡክ ነበር። ፌስቡክ ላይ የማየው ሁሉ ያስደስተኝ ነበር። ከላይ ዘፍጥረቱ ላይ እንደጠቀስኩት ሰዎች የጋራ አጀንዳ መፍጠር ስላልጀመሩ ሁሉም ራሱን ሆኖ ስለሚጫወት ነገሩ ሁሉ ደስ ይል ነበር።
በሂደት ግን ደስ በሚለውም ነገር መሰላቸት ጀመርኩ። እየተሰላቸውም ግን አደርገው ነበር። በሂደትም ፌስቡክ አንድ አይነት አጀንዳ የሚሰፈርበት መድረክም መሆን ጀመረ። ይሄም መጀመሪያ አካባቢ አልጎረበጠኝም። ሲቆይ ግን አስጠላኝ። እያስጠላኝም ግን በራሴ ነጠላ አጀንዳ ለመቆየት ሞከርኩ። ብዙ በጋ ብዙ ክረምት አለፈ። ቀንም ማታዬም ፌስቡክ ሆነ። የምነቃው በፌስቡክ የምተኛውም በፌስቡክ ሆነ። እየተሰላቸውም እያስጠላኝም ፌስቡክ የመተው ሃሳብ በጭራሽ አልነበረኝም።
ድንገት በሆነ የህይወት አጋጣሚ በህይወቴ ቅድሚያ የምሰጠው አጋጣሚ ፊቴ ተደቀነ። ሁለት ምርጫ ነበረኝ ራሴን ታግዬ ከብዙ ሱሶች ማዳን አልያም ተረት ሆኜ መቅረት። ምርጫዬ ታግዬ መኖር ሆነ። ቁጭ ብዬ አሰብኩና ከራሴ ጋር መራራ ነገሮችን ልጋፈጥ ቆረጥኩ። በዚህ መሃል ፌስቡክ ለትግሌ እክል እንደሆነ ውስጤ ያውቅ ስለነበር ወዲያው ራሴን ለአመት ከፌስቡክ መድረክ አጠፋው።
በዛ አንድ አመት ላቤን፣ ደሜን፣ ሳንቲሜን፣ ያለ የሌለ ሃይሌን ገብሬ ራሴን ማኖር ቻልኩ። የሚያወቁኝ እንደ አስማት የሚያዩትን ራሴን ከሱስ አፀዳው። ወደ ጉዳዬ ስመለስ… በዛ አንድ አመት ውስጥ ነው ፌስቡክ ምን እንዳሳጣኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጠልኝ። ከዛ በፊት ፌስቡክ ቢያሰላቸኝም ያን ያህል ህይወቴ ላይ ተፅህኖ እንደነበረው ልብ አላልኩም ነበር። ምናልባት ውስጡ ሆኜ ይሄን ማሰብ ስለማልችል ይመስለኛል። ከውጪ ሆኜ ሳየው ግን ነገሩ ተገለጠልኝ።
ከፌስቡክ መተዌ በፊት
ማታ አዕምሮዬ የሚጨነቀው ማታ ፖስት ስላረኩት ነገር፣ ነገ ፖስት ስለማረገው ነገር፣ሌሎች ፖስት ስላረጉት ነገር፣ የቀን ተባራሪ ፖስቶችን ስለማሳደድ ነው። ይሄ ወደየትም የማይወስድ ተመሳሳይ ሳይክል ነበር። ተራ መዝናናት። ውስጡ መነሻ ህልም ቢኖረው እንኳ ጊዜ የሚያጠፋው ተራ ድግግሞሽ ነበር። ይሄን ያወኩት ውጪ ሆኜ ካየሁት በኋላ ነው።
ከፌስቡክ ከጠፋው በኋላ
ማታ አዕምሮዬ የሚያስበው ነገን ከሱስ የምፋታበትን ቀን ትግሉን እንዴት እንደማሸንፍ ነው። ሊገጥሙኝ የሚችሉትን ነገሮች በሃሳቤ እየሳልኩ ቀድሜ እየተጋፈጥኳቸው ስራ አቀል ነበር። በቶሎ መአት ሱስ እንዳራግፍ የረዳኝም ያ ይመስለኛል። ይሄ ትግል ነፃነት ይፈልግ ነበር። ይህ ትግል ፅሞና ይፈልግ ነበር። በቂ ጉልበት፣ በቂ እንቅልፍ፣ያልተሸራረፈ የስምንት ሰዓት እንቅልፍ የግድ ይፈልግ ነበር። በፌስቡክ እያለው እንቅልፌ የአምስት እና የአራት ሰአት ነበር። ለሽንት ስነቃ እንኳ ፌስቡክ ቼክ አደርግ ነበር። ኮመንት ካለ መልስ ሰጥቼ ድጋሚ መተኛት እብደት ነበር። ይሄ ከውጪ ሆኜ ሳየው ያስቀኛልም ያሳቀኛልም።
ድጋሚ ወደ ፌስቡክ መመለስ
በአንድ አመት ውስጥ ራሴን ለውጬ ስጨርስ ፌስቡክ መመለስ አማረኝ። አሁን ግን አላማ እንደሚያስፈልገኝ ለራሴ ነገርኩት። እንዲህም አልኩት <<አሁን ፌስቡክ የምመለሰው፣ በፌስቡክ በሱስ የሚሰቃዩ ወንድምና እህቶቼን በምችለው መጠን በሃሳብ ለማገዝ ነው!>> … ይሄን ካልኩ በኋላ የሚዳሰስም የሚገመጥም አላማ ስላገኘሁ ራሴን አቅፌ ሳምኩት። እነሆም የደስታ እንባ አነባው። …
ከዛ በትኩስ ጉልበት ወደ ተግባር አመራው። ሰዎችም ጥሩ አቀባበል አደረጉልኝ። በዛም ሃሴት አደረግሁ። ከወር ከሁለት ወር በኋላ ቀስ በቀስ ወደ በፊቱ እንቶፈንቶዬ ተመለስኩ። አላማዬ ያልኩትንም ነገር በተለያየ ሰበብ ፈጥሬ ተውኩት። ፌስቡክም እንደ ቀድሞው ሳንቲሜን፣ ጉልበቴን፣ እንቅልፌን ሁሉ ነገሬን ከበፊቱ ባልተናነሰ ሁኔታ ይነጨው ጀመር።
በዚ ጊዜ የፌስቡክ ባህሪ ከሌሎች ሱስ ከምንላቸው ነገሮች የሚለየው ውስጡ አነቃቂ ንጥረ ነገር ስለሌለው ብቻ እንደሆነ በራልኝ። ምናልባት አነቃቂው ንጥረ ነገር ኖቲፊኬሽኑ ይሆናል። ስለ ሌሎች ሱሶች በእሳት ያለፈ ልምድ ስላለኝ ባህሪው መመሳሰሉ ገረመኝና ጥናቶች ካሉ ብዬ መፈላለግ ጀመርኩ። ባልገመትኩት ሁኔታ አንድ ጥናት ላይ የፌስቡክ ተጠቃሚ የጭንቅላት ኬሚስትሪ እና የድረግ ተጠቃሚ የጭንቅላት ኬሚስትሪ እንደሚመሳሰል አነበብኩ። ሌላም ሌላም ብዙ ጥናት አየሁ። የፌስቡክ መስራቾች እንዴት ሰዎቻቸውን መያዝ እንዳለባቸው መነሻቸው ከቁማር ማሽን ፈብራኪዎች ጋር መመሳሰሉን ሳውቅ ቆም አልኩ። ዋነኛ አላማቸው እንዴት ሰዎችን ሱሰኛ አድርገው ማቆየት እንደሚችሉ ማሰብ ነበር። ተሳክቶላቸዋልም።
ቀጥሎ በግል ድፍረት ፌስቡክን የሰውን ልጅ ከሚጎዱ ሱሶች መሃል አካተትኩት። እንደ ትንቢት ስናገር የፌስቡክ ዕድሜ ከ20 አመት አይበልጥም። ሲጋራ ፋሽን በነበረ ጊዜ ሁሉም ሰው ይጠቀመው እንደነበርና ጉዳቱ እንደማይወራ ሁሉ… ፌስቡክም አሁን እዛ እድሜው ላይ ነው ያለው። አገራት በይፋ ዜጎቻቸው እንዳይጠቀሙ ማገድ ይጀምራሉ። እመኑኝ ያ ቀን ይመጣል። እስከዛው በቀጣዩ ክፍል ፌስቡክንም ልክ እንደሌሎች ሱሶች የምንፋታበት መንገድን ቀለል ባለ መንገድ እናያለን።
ማስታወሻ 3:–ማጨስ፣ መቃም፣ መጠጣት ከሚባሉ ሱሶች ከተፋታው ሰባት አመት አልፎኛል። ፌስቡክ በነዚህ ሰባት አመታት የተጠቀምኩት አመት ከአራት ወራት ለሚሆን ጊዜ ብቻ ነው። ለመጨረሻ ጊዜ ድምፄን ካሰማው አራት አመት ከስምንት ወር አልፎኛል።
ክፍል ሁለትን በዚህ ያንብቡ የፌስቡክ አጀንዳ አቆዪ ኮሚቴ