Komentar baru

Advertisement

ስዋሜራን

Eriyot Alemu
Jun 19, 2017
Last Updated 2023-08-21T04:30:30Z
Advertisement


<<ጎዳና የወጣው በሷ ሞት ምክንያት ነው>> ይላሉ...ሞቷን ሊያሳምኑኝ!... ውሸት ነው ጎዳና የወጣሁት በራሴ የተነሳ ነው.... ስላቃተኝ ነው....ሁሉ ነገሬን ጨርሼ ሞቴን ለመጠባበቅ ነበር... ግን ሞት ሴታ ሴት ነው ጎዳና ወጥቼለትም ጓዳ ለጓዳ፣ ሆስፒታል ለሆስፒታል ይርመጠመጣል.... 

<== <== <== <==


<<የሚያምር ትላንት አለህ እኮ!>> አለችኝ።

ምን ይጠቅመኛል...ለራሴ ትላንቴን ከረሳሁት ቆይቻለሁ....  ለሰው እንዳልተርከው እንኳ የምተርክለት ማንም የለኝም....ከሷ ውጪስ ማን ሲሰማኝስ?.... ለሷ ደሞ....

እኔ ነገም ትላንትም ዛሬም የሌለኝ ሙት ነኝ—ለኔ... 


==> ==> ==> ==>


<<ጎዳና ነው ቤቴ ጎዳና ነው ቤቴ...>> እያሉ ለሚዘፍኑ ህፃናት ሳንቲም ዘግኜ እሰጥ ነበር... ምንም አይገርምም... ምንም አይገርመኝም... ፈልጌ ባልወጣበትም እንደጠበኩት አልተቀበለኝም... ነፃ ሆኖ ነው ጎዳና የተቀበለኝ... ራብ የሚገለኝ መስሎኝ ነበር... ይኸው እየበላሁ አለው... ብርዱም የሚገለኝ መስሎኝ ነበር... ይኸው ለምጄው አለው... በከተማዬ ሰው ርቦኝ ነበር... በጎዳናዬ ግን ሰዎች ከበቡኝ.... ፍቅር ሰጡኝ!!! ለዚ ነው ህይወት የምታስቀኝ.... እንዲገድለኝ የተመኘሁት ጎዳና.... እኔን ለመጠገን ይዳዳዋል...


<== <== <== <==


<<አንተ እኮ ሁለት ነህ!>> አለችኝ አስረግጣ...

ትክ ብዬ አየኋት... ከንፈሯ እንደዚ ለስላሳ እንደነበር ልብ ብዬው አላውቅም... ግራ ገባት እንዲህ አይቻት ስለማላውቅ...

<<ዛሬ እውነት ነገርሺኝ! እኔ ሁለት ነኝ... አንድ ለመሆን የምታገል ሁለት ነኝ... እኔ የትኛው ትክክል እንደሆነ የማይገባኝ... ዘወትር እርስ በራስ የምጣረስ፣ አንድ በድን ያለኝ ሁለት ነኝ... ይሄን የአመታት ህመሜን ስቃዬን ሁለት ነህ ብለሽ ቀጨሺው... ይገርማል በሽታዬን አመንኩ ማለት ነው?>> …

ደስ አላት! ሳመቺኝ... ከንፈሬን ሳመቺኝ... እንደደነዘዝኩ... ማመን እንዳቃተኝ፣ በደስታ እንደሰጠምኩ ሄዳለች:: ወዲያው ወሰንኩ... <<እሷ በሳመቺኝ ከንፈር ላይ ሲጋራ አላጨስም!>> ብዬ ወሰንኩ...

ላለማጨስ የፈጠርኩት አንድ ሺኛ ምክንያቴ ነበር... ግን ከ30 ደቂቃ በኋላ ድንጋይ ላይ ቁጭ ብዬ እያጨስኩ ራሴን አገኘሁት... ራሴ አሳቀኝ!... ብዙ አልቆየሁም ስቅ—ስቅ ስቅ ብዬ አለቀስኩ እዛው ድንጋዩ ላይ...


==> ==> ==> ==>


አለም ጠልቶኛል፣ አለም ንቆኛል፣ አለም አንቅሮ ተፍቶኛል ብዬ አስብ ነበር… ደሞም እውነት ነበር... አንሼ አንሼ አንሼ እያለሁ ጠፍቼ ነበር... ከሰውም፣ ከራሴም... ጎዳና ሰው ከበበኝ... ጎዳና ከኔ ምን እንዳየ አላቅም... ጎዳና ይመግበኛል... ጎዳና ያስቅመኛል፣ ያስጨሰኛል፣ ያስጠጣኛል... ስለ አይነቱ አልጨነቅም... ብጨነቅም ምንም አላመጣም... ስቆይ ስቆይ ለመሰረታዊ ፍላጎቴ ማሰብ ተውኩኝ... የከበቡኝ ሰዎች ስራ ሆነ... ጎዳና የውስጤን አንዱን ትልቁን ፓውዛውን ጫጫታ አጠፋው... ቆይ ጎዳና ምን አየብኝ ግን?????


<== <== <== <==


<<በጣም ነው የምፈልግህ!>> ስትለኝ ገርሞኝ ነበር… ያለችበት ድረስ ለመሄድ ምንም አላመነታሁም… ባ‘ለም ላይ ብቸኛ ቀሪዬ ሰው እሷ ነበረች…

<<ቃል ግባልኝ?!>> አለችኝ

<<ለምኑ?>> ጠየኳት

<<ከዚ በኋላ ላትጠጣ!>>

<<እሺ አሁን ግን ጠጣ ማለትሽ ነው?>>

ሳቀች። ጥርሶቿን ከልቤ ያየኋቸው ያኔ ነው… በሁለቱም በኩል የተደራረቡ ጥርሶች አሏት... ስትስቅ ያማረቺኝ ለዛም መሰለኝ...

<<ልሄድ ነው!!!>>

አልገረመኝም። ተጓዥ ነች... ሁሌም ትሄዳለች... እዚ ሲሏት እዛ ነች—ሁሌም።

<<የምሬን ነው!>>

<<ሌላ ጊዜ እያሾፍሽ ነው እንዴ የምትሄጂው?>>

ጉንጬን ስማኝ ሄደች....... ልትሞት ነው የምትሄደው ብዬ ግን ፍፁም አልገመትኩም ነበር...


አልሞተችም!... ማነው ሞተች ያለው... እስኪ ወንድ የሆነ እኔ ይበለኝ... ሁሉም ገደል መግባት ይችላል...

ብቸኛ ተስፋዬ ነበረች... ታግሳኛለች... አድርግልኝ ያለችኝን ለማድረግ በየቀኑ ከራሴ ጋር እታገልላት ነበር—በየሰከንዱ፣ በየደቂቃው፣ በየሰዓቱ—በየቀኑ!... በየቀኑ ሲያቅተኝ አለቅስ ነበር... ይሄን እሷ አታቅም!!!... እምክርላታለው ያቅተኛል... እሞክርላታለው ያቅተኛል... አለቅሳለው... ራሴን እጠላዋለው... ታድያ ሳልነግራት እንዴት ትሞታለች... ማነው ሞተች ያለው???... አልሞተችም... ለምን ሳልነግራት... ለምን ለምን ለምን?  ? ?


<== <== <== <==


<<ካላስቀየምኩህ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ?>> አለችኝ…

<<ማስቀየም ስትችይበት አደል!>>

<<ለምንድነው የምታጨሰው?>>

አስቀየመቺኝ። የእውነት ተቀየምኳት… ፊቴ ላይ አይታዋለች። ደነገጠች,,,, ወዲያው አሳዘነቺኝ።

ማንም ይሁን ማንም፣ የፈለገ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ሰው ለምን አይሆንም ይሄን ጥያቄ ከጠየቀኝ እበሳጫለው… ብዙ ጊዜ ለምን እንደምበሳጭ ግን በውል አላውቀውም… ምናልባት እኔ ራሱ በውል ለምን እንደማጨስ ስለማላውቀው ይሆናል… ምናልባትም አላውቅም…


እያየኋት አይኖቿ እንባ ቋጠሩ… ለስሜት ቅርብ እንደሆነች ባቅም የዚኛው ግን መልሶ እኔኑ አበሳጨኝ። ባቀጣጠልኩት ሲጋራ ሌላ ሲጋራ ለኮስኩ (ክብሪት ቁጠባ ልበለው ይሆን?)

<<ስለሚያዝናናኝ ነው!>> አልኳት የአዲሱ ሲጋራዬን ጭስ ወደ ወስጥጥጥ ማግ ካደረኩት በኋላ…

መልሴ ባይዋጥላትም ከደቂቃዎች በኋላ ስላዋራኋት ደስ አላት…

<<ያሁኑ አለኳኮስህ ግን ለመዝናናት አይመስልም!!!>>

<<ያው መጠጥ ሰዎች ሲደሰቱም ሲበሳጩም እንደሚያምራቸው ነገር መሆኑ መሰለኝ>>

ፈገግ አለች… የግርምት ፈገግታ ነው። መረጋጋት ጀመርኩ…

<<አንድ አይነት ነው መልሳቹ>> ብላኝ ተነሳች… ከአባቷ ጋር ነው። አባቷ የሆንኩ እስኪመስለኝ ድረስ ብዙ ጊዜ ታመሳስለናለች። አንዳንዴ ደስ ይለኛል፤ ብዙ ጊዜ ግን እፈራለው። …መጥፎ ስሜት ይወረኛል… ያባቷን ሞት ማሰብ አልፈልግም… ብዙ ነገሩ ያስጨንቀኛል…



*** *** *** ***


ያን ቀን ማታ የማጨሰውን ሲጋራ ቁጥር ለመቀነስ ቆርጬ ወደ ቤቴ ሁለት ሲጋራ ብቻ ይዤ ገባው። ያለ ልክ ጠጥቼ ነበር… ሁሌም ልክ የለኝም። የዛንለቱ ግን ካለልክም ይለይ ነበር… ድብን ብዬ የምጠጣው ድብን ያለ እንቅልፍ እንዲወስደኝ ነው… ግን ከአመት ወዲህ ሁሌም ሌሊት መንቃት ጀምሬያለው… ሌላ ተጨማሪ ጭንቀት ማለት ነው። ልክ ስነቃ አንድ ሶስት ሲጋራ አከታትዬ ስለቅበት እንቅልፌ ካቆመበት ይቀጥላል… ለምን? አይገባኝም!!! ብዙ የማይገቡኝ ነገሮች አሉ…


እንደ አጠጣጤ ለሊት የምነቃ አልመሰለኝም ነበር… እስከወዲያኛው!… ግን 8 ሰዓት ከአስር ሲል ነቃው… አንድ ሰዓት ከምናምን ነው ያሸለበኝ… ኖርማል ነገር ነው ብዬ ወደ ሲጋራዬ ስመለከት… አናቴ በመዶሻ የተመታ መሰለኝ… የለሊት ጠባቂ ሲጋራዬ ተጭሷል። ራሴ ነው ያጨስኩት!… እንዲ ነው እንጂ ድብን ብሎ መጠጣት!


<<ስለሚያዝናናኝ ነው የማጨሰው?>> ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፅ አውጥቼ ራሴን ጠየኩት… ግን ሰዓቱ የጥያቄና መልስ ሰዓት አልነበረም… የማጨስ አልያም የማጨስ ሰዓት ነበር። እንዴት አድርጌ ልብሴን እንደለበስኩ አላውቅም…


<<መሳለሚያ… አውቶቡስ ተራ…ፒያሳ አትክልት ተራ…>> ረዳቱ ሲያየኝ ተጣራ…


በዚ ሰዓት ሱቆች ዝግ ናቸው። በዚ ሰዓት ከአውቶብስ ተራ ውጪ፣ ወደ ሌላ አቅጣጫ ታክሲ የለም። ታክሲው ውስጥ ዘልዬ ገባው… ረዳቱ እያጨሰ ነው የሚጣራው… ‘ትንሽ ታገስ አትሞትም’ ብዬ ራሴን መከርኩት።


እንደወረድኩ እንዴት እንደለኮስኩት አላውቅም… ከደረቴ አካባቢ ነጭ ላብ ፈሰሰ… ስለ ቀለሙ አልጨነቅም ቢጫም ይሁን… ብቻ ተነፈስኩ። ብዙም ሳልቆይ ውሃ ክፉኛ ጠማኝ… ሃይላንድ ውሃ ገዝቼ እንዳልጠጣ ፈራው… እንዲህ ጠምቶኝ ስለማያውቅ ብጠጣ የምሞት መሰለኝ… ወደ አንድ ጥግ ሄጄ ራሴን ደገፍ አደረኩት… መሬት ተሽከረከረችብኝ። ማስቲካ እንደሚያኝክ ሰው ጥርሴን ሳጋጨው ደጋግሜ ሳጋጨው ማዞሩ ለቀቀኝ… ከአንድ 20 ደቂቃ በኋላ ቀለል አለኝ… ትዝ ሲለኝ ወደቤት የሚመለስ ተመላሽ ታክሲ የለም።


ሁለት ሲጋራ ገዛውና አንዱን አስለኩሼ ጉዞዬን ቀጠልኩ… ራሴን እየተራገምኩ… ራሴን በድፈረት ጠላሁት… <<ምን ሆኛለው ግን?>> ለማን እንደምጠይቅ አልገባኝም… ምራቄን ጭለማው ላይ መረግኩበት። ስሄድ በጣም እየፈጠንኩ ነው… ራሴን መጠራጠር ጀመርኩ <<ምን እየሆንኩ ነው?>> … ሁለተኛውን ሲጋራ እንደጨረስኩ ደረቴና ሳንባዬ የተጣበቁ መሰለኝ… ሁለተኛውን ሲጋራ የለኮስኩበት ምክንያት ግራ ገብቶኛል ለራሴ… መጮህ አማረኝ… ውሾች ፈርቼ ዋጥኩት… ከውስጤ ብዙ ድምፆች እየተሰሙኝ ነው… ከውጪ ግን አንድ ድምፅ ከፍ ብሎ ተሰማኝ… <<ስለሚያዝናናኝ ነው የማጨሰው>>… አሳቀኝ… ከት ከት ብዬ ሳኩ… ውሻ አይደለም ጅብ አልፈራሁም ለመሳቅ… ከት ከት ከት ወደ ጭለማው…


==> ==> ==> ==>


አንድ ነገሬ እንደጨለመ ነው ጎዳና የወጣሁት… ምን እንደሆነ ግን አላውቅም… ብዙ ሳወራ፣ ብዙ ሳላዝን ነበር አሉ… ታድያ አሉ ነው… አሁን ተረጋግቼ የጎዳናን ህይወት እየገፋው ነው… ከረዥም ጊዜ በኋላ ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች ለኔ ሲጨነቁ አየው… በህይወት ያለው እየመሰለኝ መጣ—በስሱ… ብዙ ጊዜ እንደሌለው ነው የሚሰማኝ… ስጋዬን እየነካው ሳጣው ደሞ ይገርመኝ ነበር… አሁንም አልለቀቀኝም… ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ስሜቱ ተሰማኝ… ለቅፅበት መንፈሴና ስጋዬ እየተገናኙ ይለያያሉ… ራት ሁሉ መብላት ጀመርኩ—ጎዳና… ቤቴ እያለው እያለኝ አልበላም ነበር… ገንዘብ ኖሮኝ ይርበኝ ነበር… ሰውም ምግብም… ጎዳና ግን ምንም ሳይኖረኝ ሁሉም ኖረኝ…



ለምን? አይገባኝም!… ብዙ የማይገቡኝ ነገሮች አሉ…

iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

Leave Your Comment

Post a Comment

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement