Komentar baru

Advertisement

የጉለሌው ሰካራም ከልቦለድነት ባሻገር…

Eriyot Alemu
Feb 9, 2017
Last Updated 2023-08-21T18:46:48Z
Advertisement

በሃገራችን የመጀመሪያው አጭር ልቦለድ የጉለሌው ሰካራም ነው። በ1940 በተመስገን ገብሬ ተፅፎ በ1941 ህዳር 22 ለህትመት የበቃ ፅሁፍ ነው።


[ይሄ ፅሁፍ በኔ የግል እይታ ሲተረጎም]


የጉለሌው ሰካራም አጭር ልብወለድ ብቻ ሳይሆን ሳይንሳዊ ፅሁፍ ነው ለማለት የሚያስደፍር ምርጥ ስራ ነው። ወይንም ግጥም በሚፃፍበት መንፈስ የተፃፈ አጭር ልብወለድ ነው። አንድ ውብ ግጥም ውበትን በደፈናው አይገልፀውም፤ ከውበት የመረጠውን ክፍል ውብ አድርጎ ያጎላዋል እንጂ!!!


የጉለሌው ሰካራም ስለምን ያወራል ብንል… ርዕሱም እንደሚጠቁመው ስለ ሰካራም እንደሆነ ማንም አይጠፋውም። ሰካራሙ ደሞ ተበጀ ነው። እንዲሁ በግርድፉ ስናየው አንድ አንባቢ ካነበበው በኋላ "በቃ ሰካራሙ ተበጀ ይሄ ነው! አለቀ በቃ!" የሚለው ፅሁፍ ይመስላል። በመስመር ስናየው ግን ይህ አጭር ልቦለድ ሳይንሳዊ ፅሁፍም እንደሆነ ጭምር እንረዳለን። ተመስገን ገብሬ ሊያወራው የፈለገው ስለ ሰካራሙ ተበጀ ብቻ ሳይሆን… ስለ አጠቃላይ ስካርም ጭምር ነው። ልክ እንደ አንድ ግሩም ግጥም… ሰካራምነትን በማተት፣ በማብራራት ሳይጠመድ… ከሰካራም የመረጣቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች በመጥቀስ… በትልቁ፣ በጥልቅ ሰካራምነትን፣ ስካርን ማሳየት ነበር– የፅሁፉ አላማ። አላማውንም በሚገባ አሳክቷል ብዬ አስባለው።


የምናውቀው የጠጪነት እውነታ እንደሚያሳየው… የአንድ ሰው የመጠጥ ህይወት ቅደም ተከተሎች የሚከተለውን ይመስላሉ። 

 
1) የቅዳሜ ጠጪነት (ለመዝናናት ለመሳሰሉት መጠጣት) ብዙ ዝርዝር ውስጥ አልገባም አላማዬ እሱ አይደለምና!
2) ሱሰኝነት (ሰካርነት)
3) ልተው አልተው ውዝግብ
4) መተው 

 
እነዚህ ከላይ ያነሳኋቸው በውስጣቸው ሌላ ብዙ ንዑስ ክፍሎች ቢኖራቸውም፣ የፅሁፉ ዋና አላማ ያ ባለመሆኑ ዘልዬዋለው።
ይሄ ዝርዝር ትክክለኛው የጠጪ ሰው የህይወት ዑደት ሲሆን… በአብዛኛው ሰው ቁጥር ሶስት ላይ ይደርስና (ልተው አልተው የሚለው ውዝግብ ጋር ማለት ነው) … በሚገጥሙት ተግዳሮቶች ተወስኖ የቀረውን ዕድሜ ገፊ ነው። ጥቂቶች ቆራጦች ናቸው ቁጥር አራት መተው ላይ የሚደርሱት። ወደ ጉለሌው ሰካራም እንሂድ።


ተመስገን ገብሬ በጉለሌው ሰካራም፣ በተበጀ ውስጥ እነዚህን ዑደቶች… በሚገባ ህይወት ሰ‘ቶ አቅርቧቸዋል። ያውም የቱጋ ምን ማረግ እንዳለበት ተጠንቅቆ። አንዳንድ ምርጫዎቹን እንያቸው… 

 

ተመስገን ገብሬ…  ከሰካራም የመረጠው ባለጠጋ የሆነውን ሰካራም ነው። 

 
**** ተበጀ ሰካራም ነው።
**** ተበጀ ታዋቂ የዶሮ ነጋዴ ነው። (ባለጠጋ ነው!) 

 
ይሄን ያደረገበት ዋነኛው ምክንያቱ… አብዛኛው ሰካራም… የስካር ህይወቱ ምዕራፍ ሶስት ላይ ሲደርስ (ማለትም ልተው አልተው የሚለው ውዝግብ ጋር ሲደርስ ማለት ነው) … ዋነኛ ግብግቡ ከገንዘብ ጋርም ነው። የጤናው ጉዳይ እና የማህበራዊ ህይወቱ ጉዳይ… ለአብዛኛው ጠጪ እዚህ ምዕራፍ ላይ ኢምንት ነው። ስለዚህ ተበጀን ደሃ ጠጪ ቢያደርገው ኖሮ… መጠጥ የሚተውበትን ምክንያት ገንዘብ ይሆንበትና አጠቃላይ ሃሳቡን ሰንካላ ያረግበት ነበር። ስለዚህ ባለፀጋ አድርጎት ምክንያቱን በዋናው ፈሳሹ መጠጥ እና መጠጡ የሚያመጣው ጣጣ ላይ በነፃነት እንዲያተኩር ረድቶታል።


ምሳሌ ስናይ… 


ተበጀ "መጠጥ ለመተው ያሰበበት የመጀመሪያ ጊዜው ይህ ነው" ተብሎ የተገለፀ ክፍል አለ። አብዛኛው ጠጪ ይሄን ጊዜ በደንብ አበጥሮ ያውቀዋል፤ ለሰው ባያወራውም ቅሉ። ተበጀ መጠጥ መተው የፈለገው ቤት ከሰራ በኋላ ነው። "ሰካራም ቤት አይሰራም… ቢሰራም ቶሎ አይገባም" የሚለው ብሂል ላይ ለተበጀ ጉዳይ ሁለተኛው ነው። ቢሰራም ቶሎ አይገባም። መጀመሪያ እንዳነሳሁት ተበጀ በምክንያት ባለፀጋ ነው።


ተበጀ መጀመሪያ አሰበው ተብሎ የተነገረን ስለ አዲስ ቤቱ ክብር ብሎ ነው መጠጥ መተው የፈለገው። ትንሽ ወረድ ብሎ ግን ደራሲው እንዲህ ይለናል…
<<ሰካራምነቱ ጉዳት መሆኑ ተሰምቶት እንደሆን ይናገር እንጂ… ስለቤት ክብር ማለቱ ግን ወደ ዳር ይቆይ። ስለ ቤት ክብር ምን ያውቃል? ዶሮ ነጋዴው ተበጀ፣ ሰካራሙ ተበጀ አይደለምን?…>>
*** አብዛኛው ጠጪ መጠጥ መተው ሲፈልግ አጥርቶ እስኪያወራ ድረስ… መጠጥ ለመተው የሚያቀርባቸው፣ አሳማኝ ያልሆኑ ምክንያቶች አሉ። ዋናው ምክንያት ግን ጠጪው ከውስጥ፣ ከልቡቡቡቡ የሚያውቀው የመጠጥ አስከፊነት ነው። ይህን ማመኑ መጀመሪያ ስለሚከብድ ሌላ ምክንያት መስጠቱ ለጊዜው አሳማኝ ነው። ለዚ ነው ተመስገን የፃፈው ሳይንስም ጭምር ነው የምለው።


የተበጀ ምዕራፍ ሁለት… የስካር ህይወቱ እንዴት ተገለፀ? 


*++ ተበጀ ለመስከር ይጠጣል። ደስ ያለው እንዲመስለው ይጠጣል። ብስጭቱን የሚረሳ መስሎት ይጠጣል። ይህ ነው ተበጀ ++*
==> አብዛኛው ሰካራም ሲጠጣና ሳይጠጣ እንደሚለያይ እሙን ነው። እንደውም ተዳባይ ስብዕና ያለበት እስኪመስል ድረስ የሚቀየርም አለ። (አበሾንም ልብ ይሏል!)
ማለዳ ተበጀ አይናገርም።
በጠርሙስ የከመረውን ከጠጣ በኋላ ሲራገም፣ ሲሳደብ፣ ሲፈክር፣ ሲያቅራራ ድምጡ ከፈረንጅ ውሻ ድምጥ ይወፍራል።
ማታ– ቢያውቀውም ባያውቀውም ላገኘው ሁሉ ሰላምታ ይሰጣል። ቢያውቀውም ባያውቀውም ካገኘው ጋር ይስቃል።


"ከሚያሰክር ሁሉ ትኅርምተኛ ለመሆን ብዙ ጊዜ አስቦ ነበር። ሰክሮ አድሮ ብርሃን ሲሆን "ከእንግዲህ መጠጥ አልቀምስም" ብሎ ምሎ… በነገው የበለጠ ጠጥቶ የባሰ ሰክሯል"
ይህ የአብዛኛው ጠጪ ህይወት ነው። ከዚህ በኋላ አልጠጣም ብሎ መማል የጀመረ ጠጪ… በፊት ከነበረው የበለጠ መጠጣት ይጀምራል። ለምን?
አንደኛ በፊት የሚጠጣውን ሱሰኛ ስለሆነ ይጣዋል…
ሁለተኛ ደሞ የገባውን ቃል ለራሱ መጠበቅ ስላልቻለ ሽንፈቱን ለመሸፈን መጠጥ ይጨምርበታል።
[ ተመስገን ልኳን ሰፍሮ ነው የፃፈው… አያብራራም። ለኛ የፃፈበትን ጥልቀት እንድናይ ይተውልናል]


በሰካራምነቱ ምን አጣ 

 
==> የነፍስ አባቱን አጣ
==> ቤቱ የሚቀጥረው ገረድ አጣ
==> ለጋብቻ የጠየቃቸው ሁሉ በቁሙ ራቁት
==> በሰንበቴ ማህበርተኛ የጠየቃቸው (ነፍሱን) ሳይቀር ንቀዋታል 

 
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ገንዘብ ነበረው። ገንዘብ ስላለው የምጠጣው ስላለኝ ነው በማለት ሊታበይ ሞከረ። በኋላ ወረድ ብሎ ሰክሮ የደረሰበት ተዘረዘረልን 


+++ ሰክሮ አውቶሞቢል በላዩ ላይ ሄዶበታል
+++ ሰክሮ እስር ቤት አድሯል
+++ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ገብቷል
+++ የጎርፍ ውሃ ወስዶታል
+++ ቤቱ መድረስ አቅቶት መንገድ ላይ ተኝቷል


ይሄ ከላይ ያነሳሁት ባለፀጋ መሆኑ የተገለፀበት ጥቅም ነው። የሚጠጣው ደሃ ወይም ሀብታም ስለሆነ ሳይሆን የመጠጥ ሱሰኛ ስለሆነ እንደሚጠጣ እንዲያስተውል ረዳው። የመስከር ስዕሉን ለሱ ብቻ ሳይሆን ለኛም በሚገባ ያሳየናል ደራሲው። ሳያብራራ በተመረጡ ነገሮች። አንድ ሳይንሳዊ ፅሁፍ ላይ እንደተፃፈ የሱሰኛ ህይወት ቁልጭ አርጎ ማየት ያለብንን ያሳየናል። 

 
ሃብት ስላለኝ ነው የምጠጣው የሚለውን ከገጠመው አነፃፅሮ ሲጨርስ እንዲህ ይላል…
"ይህ ሁሉ ውርደት እና ርክሰት ነው እንጂ ክብር ከቶ አይደለም!… እንግዲያውስ ክቡር ደሃ ነው ገንዘብ ስለሌለው ራሱን ይገዛል… ባለፀጋም ሆነ ደሃ ሰው ከራሱ የበለጠ ሊሆን ይገባዋል"
ወደ ነጥቡ ሄደ ማለት ነው። 

 
**** ተመስገን ገብሬ 

 
"ለመስከር ይጠጣል፣ ደስ እንዲለው ይጠጣል፣ ብስጭቱን ለመርሳት ይጠጣል" ቢል ኖሮ፣ በዚች አገላለፁ ብቻ አድናቆቴ ይቀንስ ነበር። እሱ ግን ያለው…
"ለመስከር ይጠጣል። ደስ ያለው እንዲመስለው ይጠጣል። ብስጭቱን የሚረሳ መስሎት ይጠጣል። ይህ ነው ተበጀ"
ለውጡን ለእናንተ ትቼዋለው። እጅግ ጥንቃቄ እና እውቀት የተሞላ ፀሃፊ ነው–ተመስገን ገብሬ።


ማህበረሰቡ እና ተበጀ 


==> ቡን በተፈላ ቁጥር የሰካራም ተረት ሁሉ በተበጀ ይላከካል።
አንዴ ወንዝ ውስጥ ሰው ገባ ተብሎ ተነግሮት… ገብቶ ዋኝቶ ያወጣዋል። በኋላ ግን ይዞት የወጣው ሲታይ አሳማ ነው። መጀመሪያም ሰው ነው ብለው የነገሩት የተሳሳተ ነበር። እዚጋ አገላለጿ ያሳቀቺኝ ክፍል አለች። 

 
<<ጎረቤትህን እንደ ነፍስህ ውደድ ቢባልም እነ እቲላን ነበር እንጂ የእቲላን አሳማዎች አይደለም።>>  ይላል… እቲላ ጎረቤቱ አሳማ አርቢ ነው። ከወንዝ ያወጣው አሳማ የእቲላ ስለሆነ ነው። ነገርዬው ቢያስቅም… ይህ የተበጀን መልካምነት ለማሳየት የቀረበ ብቸኛ ምሳሌ ነው። ማህበረሰቡ ይሄን ሊያይለት እንደማይችል በፅሁፉ ሲገለፅ…
"መልካሙ የሰማዕትነት ስራው ሁሉ ደግሞ እንዲሁ ርካሽ ሆኖ የሚቆጠር የሆነበት ዘወትር የሚሰክር ሆኖ ስለታወቀ ነው። በሞራል (ግብረገብ) መሰረት አደረግሁት የሚለውን ሁሉ ሳያውቀው እንደሚያደርገው ይቆጥሩታል"


አብዛኛው ጠጪ ማህበረሰቡ እንደማይረዳው ያስባል (ደግሞም አይረዳውም)… ማህበረሰቡም ለጠጪው መስመር አበጅቶ ነው የሚረዳው። ይሄን ሁሉ የሚነግረን ፀሃፊው… በልቦለድ ውስጥ መሆኑ አጃኢብ ያሰኘኛል። ያውም እንዲህ እንዲያ እያለ ሳያብራራ።


ከስካር ህይወት ምዕራፍ ሶስት (መተው አለመተው መፈለግ) ወደ ምዕራፍ አራት (ጭራሹኑ መተው) ያለውን ሽግግር እንኳ በሚገባ ነቅሶ ፅፎታል።
ቤቱ ያለውን መጠጥ አውጥቶ መጣል። ያን የጣለውን መጠጥ ፈልጎ መልሶ መጠጣት። ያውም ከበፊቱ ጠንከር አድርጎ። ለዚ ነው ሰውዬው በደንብ አጥንቶ ነው የፃፈው የምለው። ይሄንን ትግል እዛ ምዕራፍ ላይ ያለም ሰው፣ ያለፈውም በደንብ ያውቀዋል። 

 
==> ተበጀ መተው ከፈለገበት ጭሩሱኑ እስኪተው አምስት ወራት ትግል ውስጥ ነበር። ይሄን በመስመር ሳያገን፣ ሳናውቀው ነው የገለፀልን።


የመጨረሻው ምዕራፍ (ጭሩሱኑ መተው) 


ይህን ምዕራፍ ደራሲው የገለፀበት መንገድ በእጅጉ አስገርሞኛል። ሶስት ንዑስ ክፍሎችም አሉት።


የመጀመሪያው ፀፀት ነው… (ወደ ራስ መመለስም ልንለው እንችላለን)
==> በዚ ዕድሜዬ ሁሉ ሚስትም አላገባሁም ልጅም የለኝም አለና አዘነ
==> አመሌ ውሻ ነበረና እንደ ውሻ ስጮህ ነበር ብሎ ራሱን ረገመ። (ትንሽ አገለሰለፁን በራሴ ቀይሬዋለው)


ሁለተኛው ደሞ አምኖ መቀበል ነው… (ከውጪ ሆኖ ማየት መጀመር)
ህይወትን ተቀብሎ መኖር መጀመር። መቀለድ። በተለይ ስለ መጠጥ ያለው አመለካከት ፍፁም ሲለወጥ በቀልዱ እናያለን… 

 
<<ጎጃም የአበባውንና የግራር ማሩን ይጭናል። የተጉለትና የአምቦ ወረዳ ጌሾውን ያቀርባል። የሆላንድ የቢራ ፋብሪካ ቢራውን ያወጣል። የኢጣሊያ ፋብሪካ ወይን ጠጅ (ነቢት) ያፈላል። መደቅሳና ዘቶስ በግሪክ አገር ይጣራል። በስኮትላንድ ውስኪ ይጠመቃል። ይህ ሁሉ የሚሆነው በአራዳ የሚቀመጡትን እንዳይጠማቸው ነው>>
ይህን የሚለው ቀድሞ ጠጪ የነበረ ሰው ነው። ከጠርሙሱ ወጥቶ ስለ ጠርሙሱ ማየት ጀመረ ማለት ነው። አብዛኛው "ከሱስ ሪከቨር" ያደረገ ሰው አመለካከቱ እንደሚለየው ተበጀም በዚ ደረጃ ተለየ።


ሶስተኛው ንዑስ ክፍል የ"ሪላፕስ" ሃሳብ ነው… (ማገርሸት ወይም ምልሰት ይሉታል አማርኛው ቃል ደካማ ስለሆነ ለሱስ… ሪላፕስ የሚለውን ነው የምጠቀመው)
በጣም ያስገረመኝ… የትኛውም ከሱስ የተፋታ ሰው… ቀርባቹ ብትጠይቁት፣ ሱስ የተወበትን ቀን ቀኑን ቆጥሮ ይነግራችኋል። ይሄ በሌላ አቅጣጭ አብዛኛው ሱሰኛ፣ ከሱስ ለመፋታት ታጋይ እና ትግል ውስጥ እንዳለ ማሳያ ነው። 

 
"ተበጀም መጠጥን እርም ካደረገው አንድ አመት ከዘጠኝ ወር ከዘጠኝ ቀን እንደሆነው ጊዜውን ቆጥሮ አወቀው" የሚለው አገላለፅ… የተመስገንን አጭር ልብወለድ፣ ሳይንሳዊም ነው ከምልበት ምክንያት አንዱ ሰበዝ ነው።


ከዛስ ትላንትና ያለ መጠጥ የማይኖረው ሰውዬ እንዲህ ተብሎ ሲገለፅ እናያለን…
"ሰካራሙ ተበጀ ግን ገንዘብ እያለው ውሃ ጣፍጦታል…"
ተመስገን የሚፅፈውን ጠንቅቆ የሚያውቅ የፈጠራ ሰው ነው። ይህ ማሳረጊያው አካባቢ ነው።


ከረዥም ጊዜ በኋላ እንኳ የመጠጥ አምሮት ውል እንደሚል እና ያ ስሜት አስጨናቂ እንደሆነ… ከህልም ጋር አያይዞ ያቀረበበት መንገድ፣ በግሌ ለድርሰቱ ያለኝን አድናቆት ወደር አሳጥቶታል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ አብዛኛው ከሱስ ያገገመ ሰው… የሆነ ወቅት ላይ በህልሙ ወደ ሱሱ ሲመለስ ሊያይ እንደሚችል ይጠቁማሉ። ያንን የሚፈጥረው ሌላ ሳይንሳዊ መላምት አለ። ዋናው ጉዳያችን ግን ተበጀም ከ1 አመት ከዘጠኝ ወር ከዘጠኝ ቀን በኋላ ህልም ያያል።


ያየው ህልም በራሱ ከትዝታ ማህደሩ የተቀዳና ከቢሆንስ ከሚል ፍርሃት የመነጨ መሆኑን… ህልሙን ተርጉሜ አይቼዋለው። ስለ ህልሙ ለብቻ ሌላ ጊዜ ባወራ ደስ ስለሚለኝ አልፈዋለው። የተመስገን ገብሬ ፅሁፍ ግን ሳይንሳዊ ፅሁፍ ነው ለማለት ዋናውን ሚስማር የመታልኝ ህልሙም ነው። እሱ ሲፅፈው እንዲህ ነው እንዲያ ነው አይልም። ትርጉም እየሰጠሁት ያለሁት እኔ ነኝ። አንደኛ አድናቆቴም መጥኖ፣ አርቅቆ፣ ተጨንቆ ስለፃፈው ነው። 


መጨረሻ ለይም ከህይወቱ ለውጥ በኋላ… በቤቱ ገረድ እንደኖረው የገለፀበት መንገድ… ስለ ሱስ ምንም አይነት እውቀት የሌለው ሰው እንኳ… ደራሲው እንዴት እንደሚያወራ፣ እንዴት ነገሮችን እንደሚከስታቸው ይገለፅለታል። እንደተለመደው አፃፃፍ "ህይወቱ ሲቀየር ገረድም ኖረው!" በሚለው አገላለፅ አይሄድም… እኛ እንድናስብ ያረገናል። በማሰባችንም ደስ ይለናል። በቀላሉ ደስታም ይሰጠናል ማለት ነው– ደራሲው ተመስገን ገብሬ።


የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እጭር ልብወለድ ደራሲ ተመስገን ገብሬ!!!!!

iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

1 comment:

  1. ጥሩ ሃያሲ ያላነበብኩትን መፅሃፍ እንዳነበብኩት አድርጎ የሚሄስልኝና መፅሃፉን እንድገዛው የሚያስገድደኝ ነው….. ይሄን ያለው ያንተ ሌላ ፅሁፍ ውስጥ ያነበብኩት ፍሬው ነው። እዚህ ውስጥ ያን አገኘሁት። አመሰግናለሁ።

    ReplyDelete

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement