Komentar baru

Advertisement

ንገሪኝ

Eriyot Alemu
Jan 3, 2017
Last Updated 2023-08-21T23:52:05Z
Advertisement




ስበትን ድል ነስተው፣ አየሩንም ቀዝፈው
ተንሳፈው ሊያንሳፉሽ፣ ያለሙት እግሮችሽ
ድንገት!
ብርክርክ እያሉ
እንኳን ከሰዉ ጋር ከመሬት ቢጣሉ
ንገሪኛ ፍቅር
ምን ታረጊ ነበር?
ከመውደቅሽ በቀር…


ንገሪኝ!
እንደ ንስር ዓይኖች ደመናን ተጭነው
ዝናብ ቁልቁል ሲወርድ ለማየት አልመው
የተሰናዱ ዓይኖች
በነዛ ሰዓቶች
ካዘናቸው ብዛት በዕንባ ሲጋረዱ
ባልፈለጉት መንገድ በመሪ ሲነዱ
ንገሪኛ ፍቅር
ምን ታረጊ ነበር?
ከመነዳት በቀር…



ንገሪኝ!
የወፎች ዝማሬን
የነፋሱን ድምፀት፣ ከፊቱ በጥልቀት
ለመስማት ያለሙት ጆሮዎችሽ ድንገት
ውስጣዊ ጩኧትሽ ከውጪው አይሎ
አላሰማ ቢልሽ መስሚያሽን ከልሎ
ንገሪኛ ፍቅር
ምን ታረጊ ነበር?
ከመደፈን በቀር…


ንገሪኝ!
የዲዳ አፍ ፈቺው፣ ጤፍ ቆይው ምላስሽ
እንደ ዲሞጥሮስ አፍ ድንገት ኮልትፎብሽ
ለዛሽን አባሮ፣ አልብሶሽ እሮሮ
ብቻውን ሲዳክር ያለ ሰሚ ጆሮ
ንገሪኛ ፍቅር
ምን ታረጊ ነበር?
ከዝምሽ በስተቀር…


ንገሪኝ!
ሁሉን ሲያቅፍ የኖረው ጠፈርን ወክሎ
እጅሽ ሲተጣጠፍ ምፅሀት ተመስሎ
ሲደረደርብሽ የስቃይ ሀተታ
አንድ ባንድ እያሉ የነጎዱ ለታ
ብቻሽን ስትቀሪ ከውድቀትሽ ቦታ
ንገሪኛ ፍቅር
ምን ታረጊ ነበር?
ከማቀርቀር በቀር…


ንገሪኝ!
ከአበቦች መዓዛ እስከ ናርዱስ ሽቱ
የተወራረደ ሁሉን ለማሽተቱ
አፍንጫሽ…..
ራሱን ከጣለ
ከጭሳጭስ ሌላ አልጥመው እያለ
የንብ አፍንጫ ሆኖ ዝንቦች ጋር ከዋለ
ንገሪኛ ፍቅር
ምን ታረጊ ነበር?
ከማሽተትስ በቀር…


ንገሪኝ!
ስሜት አልባ ህዋሳት፣ በድን አካል ታቅፈሽ
እስከ መኖርሽም በፍፁም ዘንግተሸ
እፍ ባለው ያኔ እስትንፋስሽ ብቻ
ብትወዛወዢም ሆነሽ ለሰው አቻ
ከዕፅዋት ከፍ ያልሽ፣ ከእንስሳት ግን ያነሽ
ለፍጥረታት ዓለም አዲስ ግኝት ሆነሽ
የማይመሹ ቀናት፣ የማይነጉ ሌቶች
በደመነፍስሽ ውስጥ በመጡ ስሌቶች
መሸ-ነጋ ኑሮ ሳታውቂው ምትገፊ
‘’ከፍጥረታት ጎራ አንዷ ተሰላፊ”
ተብለሽ የተቆጠርሽ
ብቸኛ ሰው ሆነሽ
እያለሽ!…..


ንገሪኝ!
እኔ ተመችቶኝ፣ በራፌን ከፍቼ
በሙሉ ልብ ሆኜ፣ እጆቼን ዘርግቼ
በጠበኩሽ ሰዓት 
ታቅፈሽ ይሄን መአት
ትመጪ ነበረ???
ንገሪኝ እስኪ ኧረ!!!


ልንገርሽ!???
ይህን ሁሉ አልፌ የመጣሁኝ ጊዜ
“የት ነበርክ?” ስትይኝ ያኔ አፌን መያዜ
ጥፋቴ ተገልጦ ታይቶኝም አይደለ
ማስታወስ ባይሻ ነው አፌ ልጉም ያለ፡፡
“ስላልነበርኩ ነው ያልመጣሁት ያኔ”
ብልም አይገባትም ብሎ ነው ልሳኔ፡፡


ልንገርሽ!???
ያልነበርኩበትን ህይወቴን ሰርዤ
ልክ ካቆምኩበት ያለን ፍቅር ይዤ
እንቀጥለው ልልሽ
ብቆም ከደጃፍሽ
ገርሞት ባይታይሽ የያኔው ሀዘኔ
ዝሙን ብቻ ታቅፎ ፈዞ እያየሽ ዓይኔ
“ለካ ፊታችን ላይ ያለፍንበት መንገድ
ተፅፎ አይታይም ይዩም ብለን ብንፈቅድ፡፡”
እያለ ሲያስብ ነው ከቆምንበት ቦታ…
መሄድሽ ትዝ ያለኝ የማታ የማታ
እስኪ ልጠይቅሽ ልስማሽ በዝምታ
ምን ታረጊ ነበር? ብትሆኝ በኔ ቦታ…

ንገሪኝ?????

iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

Leave Your Comment

Post a Comment

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement