Komentar baru

Advertisement

ቁርጥራጭ ሃሳቦች ፩

Eriyot Alemu
Jan 22, 2017
Last Updated 2024-04-23T02:15:50Z
Advertisement




አንድ ጓደኛ አለኝ... የሆነ ጊዜ ሲያወራ እንዲህ ሲል ሰማሁት... "በተክለሃይማኖት በኩል ሳልፍ የጃርሶ ኪሩቤል ሞትባይኖርን ገፀ ባህሪይ አስኮ ጌታሁንን ሁሌ አስበዋለሁ!" ... እኔም ከዛ በኋላ በዛ በኩል ሳልፍ ይሄ ጓደኛዬ ትዝ ይለኛል፡፡


እኔም በኢትዮጵያ ሆቴል ሳልፍም ከሀራምቤ ሆቴል እስከ ስታድየም በተዘረጋው መንገድ ላይ ሳገድም የአዳም ረታው ገፀባህሪይ ጢቦ ትዝ ይለኛል፡፡ ጋንዲ ጋር ቁጭ ብዬ የአድቬንቲስት ቤተክርስቲያንን አሻግሬ እያየሁ... አዳም ረታ "ጉርድ ቀሚስ የመሰለው የአድቬንቲስት ቤተክርስቲያን..." የሚለውን አገላለፁን እያሰብኩ ፈገግ እላለሁ፡፡ 


ዛሬ ግን መፅሃፍ ላይ ሳይሆን፣ እውኑ ዓለም ላይ የሚገኙ ሁለት ግለሰቦችን ለማንሳት ነው አመጣጤ...

1) በክቡ ባንክ እና በኢቢሲ መካከል ባለች መንገድ ላይ ብዙ ጊዜ የማይጠፋ አንድ ሰው አለ፡፡ አንዲት ውሻም አለችው ስሩ የማጠፋ፡፡ ሁሌ የክቡ ባንክን አጥር ተደግፎ ይቆምና... የሆነ ሰው በመንገድ ሲያልፍ፣ ሮጥ ይልና አንድ ዙር ክብ ይዞረዋል፡፡ መልሶ ግንቡን ተደግፎ ይቆማል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሄ የሚገጥመው እጅግ እንደሚደነግጥ አልጠራጠርም፡፡ በተለይ ለአይን ያዝ ሲያረግ ከሆነ ድርጊቱ የገጠመው ድንጋጤው በዛው ልክ ከፍ ማለቱ አይቀርም፡፡ ከዛም ብዙ ነገር ማሰቡ አይቀርም፡፡ ብቻ የሚገርም ሰው ነው፡፡


2) ከጦርሃይሎች ወደ ቶታል በሚወስደው መንገድ ምናዬ ሕንፃ፣ የቀለበት ድልድይ ስር፣ ዘወትር በስርሃቱ ጫቱን ይዞ የሚቀመጥ አንድ ሰው አለ፡፡ የድሮ ፈላስፋዎችን የሚመስል፡፡ መሃሉ መላጣ ዳር ዳሩ ድሬድ የሆነ፡፡ (የድሮ ፈላስፎች እንደዛ ስለሚመስሉኝ ነው) ...የዚህ ሰው ፊት ላይ የሚታይ እርጋታ ከባህር ይጠልቃል፡፡ አንድ ቀን ነው ልብሱን አውልቆ በራቁቱ ሲሄድ ያየሁት፡፡ ያን ቀንም ፍፁም ሰላማዊ ነበር– ለሌላው ሰው፡፡ ዘወትር ጫቱን እና ሲጋራውን ይዞ እዛች ቦታ ላይ በርጋታ ይቀመጣል፡፡ ክረምት ሲሆን እሳት በብዛት ያቀጣጥላል፡፡ በዙሪያው ነጋዴዎች አሉ፡፡ 


እናም እነዚህን ሁለት እውነተኛ ሰዎች እያዩ በማሰብና… ከላይ የተጠቀሱትን 2 ገፀ ባህሪያት እያነበቡ በማሰብ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው እላለሁ፡፡ ይሄ ይገርመኛል፡፡

እነዚህ ሰዎች የአዲስ አበባ ታሪክ አካሎች ናቸው። በምን አይነት መልኩ ነው ታሪካቸው መቅረት ያለበትም? እላለሁ፡፡ ታሪካቸውን መማማሪያ ለማድረግ እውነታቸውን የሚረዳ ማነውስ? እላለሁም፡፡ ሁሉ ፈጠራ ፈብራኪ አይደለምን? ... 

ብሄራዊ ጋር ስለሚቆመው ሰው እንኳ ሁለት የተለያዩ ታሪኮች ሰምቼ አውቃለሁ፡፡ "የባንክ ቤት ሰራተኛ ነበር እና ጥቁር አንበሳ የምትሰራ ዶክተር አፍቅሮ ነው" የሚል... ሌላ ሰው ባዳምጥ ሌላ ይነግረኛል፡፡


ብቻ ይገርመኛል፡፡ አንዳንዴ ልቦለድ አንዳንዴ ደሞ የማየውም እውነት ይገርመኛል፡፡ ሲደላኝ "ምንድነው ልቦለድ?" እላለሁ... ሲደብረኝ ደሞ "ይሄ ነው ልቦለድ!'' እላለሁ፡፡

ብቻ ይገርመኛል።
iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

Leave Your Comment

Post a Comment

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement