Komentar baru

Advertisement

የፍቅር ከፍታ!!!

Eriyot Alemu
Dec 21, 2016
Last Updated 2023-01-04T19:36:25Z
Advertisement


ውዴ! መሄድሽን የሰሙ በሙሉ
ተከፍቼ ቢያዩኝ "ጎዳችው" እንዳይሉ
ስምሽ በጥርሳቸው እንዳይገባ ብዬ
ባ‘ደባባይ ፈገግኩ ስብራቴን ችዬ። 

ፍቅሬ! ላንቺ ስም ነው ዛሬም መጨነቄ
በሰው እንዳይታይ የጠቆረው ማቄ
ጸአዳ የመሰለ አዲስ ጨርቅ አጥልቄ
ነጫጭ ዕንባዎቼን የማሳየው ስቄ።


ሆዴ! ጠዋት ሆኖም ወፎች ሲዘምሩ
"ተገለለ" እንዳይሉ ስለሄደች ፍቅሩ
እኔን ካለማየት ወሬም እንዳይፈጥሩ
"ተቀላቀል" ሊለኝ ገርበብ ይላል በሩ።

ግን ውዴ! መሄድሽ የሰጠኝን ሐዘን
ተከርችሟልና በልቤ መጋዘን
አንቺም ብጠይቂኝ አልነግርሽም ከቶ
ለምንስ ያሳቅሽ? አፌ ቃል አውጥቶ።

ግን ከፈለግሽ ደሞ?
ከፀሃይ ውል የለኝ ጨረቃን ጠይቂያት
ሰዎች አስተኝቼ ለሷ ነው ‘ማሳያት።
አራቱ ማዕዘናት ጣሪያና ወለሉ
እነሱው ይንገሩሽ ታዝበናል ካሉ።
ትራሴን ጭመቂው ከወንዝ ዳር ወስደሽ
ቃላት ሳይተነፍስ በመላ ካሳየሽ።
በፊቴ ላይ ነፍሶ፣ በቶሎ ያደረቀው ዕንባዬን በታትኖ
ንፋሱም ያጫውትሽ ስብራቴን ዘግኖ።

ቢሆንም!
ቢሆንም አለሜ!
ሐዘኔ በርትቶም ቢጠናም ህመሜ
ደስ ብሎሽ ማየት ስለነበር ህልሜ
መሄድሽ ግድ ሆኖ ሲያረግሽ ደስተኛ
የጎዳኝን ነገር አረኩት መፅናኛ።

ደሞም…………
ቆይቶ ቆይቶ፣
ሁኔታዬን አይቶ፣
ሳቄን ተመልክቶ
ችሎ ባይታየው ያ‘ዘኔ ድንበሩ
"ድሮም ባይወዳት ነው!" ያለ ቀን ሰፈሩ
ያኔ!
የኔ ስም ጠልሽቶ ያንቺ ስም ሲረሳ
ያኔ
ሌላ አንዳች አልሻም ለሐዘኔ ካሳ።
iklan
Comments
  • Stars Rally to Beat Predators in Winter Classic at Cotton Bowl

Leave Your Comment

Post a Comment

ሱስ ነክ ጉዳዮች

Advertisement