Advertisement
በላይኛው አውራጃ፣ በታችኛው ቀበሌ፣ በመካከለኛው ቀጠና ተማም የሚባል ባለሱቅ አለ፡፡ ለማሳጠር ብዬ ነው፤ ምድር በምትባለው ፕላኔት፣ አፍሪቃ በሚባል አህጉር ብዬ ያልጀመርኩት፡፡ ባጭሩ ግን ተማም የሰፈራችን ታዋቂ ባለሱቅ ነው፡፡
ያው እንደሚታወቀው ‘crown bird’ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ፣ ዱቤ መጣፊያ ደብተር ነው፡፡ ደሞ እኔ ገንቢ gun-b ነገሮችን ነው በዱቤ የምወስደው፡፡ ታድያ እዚህ ደብተር ላይ ሌሎች ታዋቂ ሰዎችም እንደሰፈሩ አልደብቃቹም፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ መነጋገሪያ የሆነው ‘ድመቷ’ የተሰኘው ድራማ ላይ ድመቷን ሆኖ የሚጫወተው መቻልም አለበት ሃሃሃ…
ታድያ ሰሞኑን ይሄ ተማም የጎልማሶች ትምህርት መማር ከጀመረ ወዲህ፣ አዳዲስ ባህሪ እያመጣ ነው፡፡ ትምህርቱን በጀመረ በሳምንቱ፣ የኔን ስም ያለበትን እያሳደደ በማርከር መንቀሱ፣ የመንደሩ ባለዱቤዎች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቶ ነበር፡፡
ይባስ ብሎ በ15 ቀኑ፣ ‘ተማም ሱቅ’ የሚለው የኮካኮላ ታፔላ ላይ ‘ተማም ሱቅ ዱቤ ነገ እንጂ ዛሬ የለም!’ ብሎ በግብዲያው ሰቅሏል፡፡ እውነት ለመናገር በጎልማሳው ተማም የተፃፈው፣ እንዲህ በቀላሉ አይነበብም ነበር፡፡ እንደምሳሌ እናንሳ ከተባለ ‘ዱቤ’ የሚለው ‘ዳቤ’ ተብሎ ነው የተፃፈው፡፡ እንደአገባቡ ባልተረጉመው ኖሮ… ተማም ዳቤ፣ አነባበሮ፣ ጢቢኛ፣ ሽልጦ ይሸጥ ነበር እንዴ? የሚል ጥያቄ በጭንቅላቴ በመጣ ነበር፡፡
ይህ ማስታወቂያ ታድያ መዘዝ ይዞበት መጣ መሰለኝ፣ አንዳንድ አሉባልተኞች ‘’ብቻውን ማውራት’’ ጀምሯል ሲሉ እየተሰማ ነው፡፡ ላጣራ ብዬ፣ እንደ ፈንጅ ወረዳ በጥንቃቄ እርምጃዬን እየቆጠርኩ፣ በሱቁ በኩል ሳልፍ፣ ቴሌስኮፕ ልቡ ነገረው መሰል፣ በሱቁ አይን አየኝና ጠራኝ፡፡ ላጣራ ብዬ ኪሴ ሊጣራ በመሆኑ እያዘንኩ፣ ሰበቦች እያውጠነጠንኩ ተጠጋሁት፡፡
“በግር በፈረስ ሳስስህ” አለኝ፡፡ “ምነው በሰላም? ደሞ ብለህ ብለህ ፈረስም ገዛህ?” አልኩት:: ሳቀልኝ:: “ባክህ ከዚህ ማስታወቂያ በኋላ ደንበኞቼ ሁሉ የውሃ ሽታ ሆኑ፡፡ ካንዳንድ ተባራሪ ሰዎች በቀር ሱቄ ዝር የሚል ጠፋ እና ይሄን እንድታማክረኝ ነው፡፡ አማካሪ መሆንህን ከሰው ሰምቻለው፡፡” ሲለኝ ‘ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል’ እንዲሉ “ይኧውልህ ተማሜ መማር እኮ ጥሩ ነው…” አላስጨረሰኝም፡፡ ዱቤውን መማር (ምህረት ማረግ) ያልኩ ስለመሰለው እንደጉድ አጓራብኝ፡፡ እስኪጨርስ ታገስኩት፡፡
“ተማሜ ተረጋጋ እንጂ እኔ ኤኮ መማር ያልኩት፣ የምትማረውን የጎልማሶች ትምህርት ነው፡፡ ታዲያ ብዙዎች የሚስቱት ተማርን ብለው እኮ ነው፡፡” ጠላታቹ ስብር ይበል! ልቡ ስበር ብሎ መቅለስለስ ጀመረ፡፡ አሁን ዛሬ የምወስዳቸውን ዱቤዎች እያውጠነጠንኩ ቀጠልኩ፡፡
“እና ተማም ገንዘብ እኮ ከኛ በኋላ የመጣ ነው፡፡ አባባሉም የሚለው ‘ለሰው መዳኒቱ ሰው ነው’ እንጂ ገንዘብ ነው አይደለም፡፡ ሰው ይበልጥብህ ነበር፡፡ አንተ ግን ቸኮልክ፡፡ ዛሬ እንዲህ የበለፀከው በኛ ትከሻ መሆኑን አትርሳ እንጂ፡፡ ቆይ ስትማሩ ስለበለፀጉ ምግቦች ተምራችዋል አደል?” አዎ! አዎ! በሚል ጭንቅላቱን አወዛወዘልኝ፡፡
“በቃ ቀጥሎ ደሞ ስለበለፀጉ አገራት ትማራላቹ፡፡ እና የበለፀጉ አገራት ቢያንስ ባመት አንዴ፣ ለባሰባቸው ታዳጊ ሀገራት የዕዳ ስረዛ ያረጋሉ፡፡ ብራዚልን ታቃት አይድል? የነ ፔሌ ሀገር… እሷ አሁን በቅርቡ እንደዛ አርጋለች፡፡ አየህ ብልህ ነች፤ ትላንቷን አትረሳም፡፡ እንዲህ የምታረገውም ለራሷ ብላ ነው፡፡ ነግ በኔ ነዋ! ስለነገ ማን ያውቃል… በእውነት የሰራኧው ስራ እንዳንተ ከተማረ ሰው አይጠበቅም፡፡ እኔማ ‘ወሄነት የገጉ’ (ደግነት ለራስ ነው) ብለህ ትለጥፋለህ ብዬ ስጠብቅ… አንተ እንዳላዋቂ ሰው… ዱቤ ምናምን ውስጥ ገባህ፡፡” ተማሜ ቅልጥ እያለልኝ ነው፡፡ “አሁን እሺ ምን ላርግ?” አለኝ፡፡
“ጎሽ የተማረ ሰው እንዲህ ነው፡፡ ቶሎ ብሎ ወደ መፍትሄው ነው የሚዞረው፡፡ ታድያ መማር ለመቼ ነው! ምን መሰለህ…”
አሁን ራሴ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ኃይል ላለማባከን፣ ማስታወቂያውን መንቅሮ ማንሳት ዘላቂ መፍትሄ ነው፡፡ ትንሽ ሲታሰብ ደሞ፣ ከዱቤ ከሚለው በፊት ሽምብራ ጨምሮ ‘ተማም ሱቅ ሽምብራ ዱቤ ነገ እንጂ ዛሬ የለም!’ ማረግም ይቻላል፡፡ ሆኖም ይሄን ብለው ተማም ይንቀኛል፡፡ በልቡ ይሄንማ እኔም ማሰብ እችላለው ብሎ ይዘባበትብኛል፡፡ ስለዚህ አላረገውም፡፡
“ይኧውልህ ተምሻ ይሄን እናነሳና በምትኩ ‘ተማም ሱቅ ሁሌም ዱቤ አለ!’ ብለን እንሰቅላለን፡፡ (ልብ አርጉ አሁን እኔም ግብረ አበር ሆኛለው) ደሞ ገና አልደረሳቹበትም እንጂ ሳይኮሎጂ የሚባል ትምህርት አለ፡፡ ያኔ ይገባሃል፡፡ ሰዎች ዱቤ አለ ተብለው፣ ዱቤ መጠየቅ ዉስጣቸው ስለሚተናነቀው፣ በጭራሽ አይጠይቁህም፡፡ ይገርምሃል የሰው ነገር ሁሌም ግራ ነው፡፡ እስኪ ሰፈራችንን ቃኘው… ሰው ሽንቱን የሚሸናው፣ መሽናት ያስነውራል የተባለባቸውን ቦታዎች እያነፈነፈ ነው፡፡” አልኩት፡፡
ከሱቁ ውስጥ ተንጠራርቶ ሲያቅፈኝ ከሚዛን ጋር አጋጨኝ፡፡ ወዲያው ሚዛናዊ ሃሳብ ተከሰተልኝ፡፡ እንዴ ዱቤ አለ ተብሎማ፣ እዚህ ሱቅ በገዛ ገንዘብም ለመግዛት መቆምም፣ ‘ለዱቤ ነው’ ቢሉንስ በሚል ስጋት ከነአካቴው ቢቀሩስ አልኩ፡፡ በዚህ ሃሳቤ ብዙም አልቆየውም፤ የኛን አካባቢ ሰዎች ጠንቅቄ አቃቸዋለው፡፡ የተማም crown bird የቀበሌያችን የነዋሪዎች መመዝገቢያ ማዕደር ነው የሚመስለው፡፡ ስለዚህ ማንም ከማንም ስለማይደበቅ የትም አይሄዱም፡፡ ቢቀሩ ቢቀሩ የሚቀሩት ተባራሪዎቹ ናቸው፡፡ ደሞ ጥቂቶች ቀሩ መጡ፣ ምንም አይጨምሩም፡፡ በሃሳቤ ፀናው፡፡
እንኳን አብሮ ደስ አለን! አሁን በበለፀገው ተማም ዕዳዬ ተሰርዞ፣ አዳዲስ ዱቤዎች ይዤ፣ ወደ ቤቴ እያዘገምኩ ነው፡፡ ሆኖም ውስጤ ከተማም እኩል ቀጣዩን ነገር ለማየት ጓጉቷል፡፡ ተማም ዱቤ ብቻ አይደለም የሰጠኝ፣ ብዙ ሃሳብም መርቆልኛል፡፡ ስንቶች ይሆኑ ዕውቀታቸውን ተገን አርገው፣ በሰዎች ስስ ጎን እየገቡ የሚመዘብሩት??? ስንቶች ይሆኑ ይሆናል ብለው በማስረገጥ የተናገሩትን ነገር፣ ውጤቱን ከሰሚው እኩል ለማየት የሚያደፈጡት??? ቤቱ ይቁጠረው!
ተማም የራሱን ችግር በራሱ መፍታት እንዲችል ማበረታታት ስችል፣ በማይገባው ሳይኮሎጂ አሳቢ ጭንቅቱን ሰለሰለብኩት በራሴ አምርሬ አዘንኩ፡፡ የተማም ከፍታ የኔም ከፍታ ነው፤ ተማም እኔም ነው፡፡ ምናልባት በዱቤ የተተበተበው እኔም፣ ከተማም ጋር አብሮ መዳኒትም ሊያገኝ ይችል ነበር፡፡ ለሆዴ ማሰቤ ለጭንቅላቴ ኪሳራ እንደሆነ የእግር እሳት የሆነ ፀፀቴ አስተምሮኛል፡፡ እውነት እውነት እላችኋለው አይለመደኝም፡፡
አሁን ቀኝ ኋላ ዞሬ ወደ ተማም ሱቅ እያመራው ነው፡፡ ነገር ማሳደር አያስፈልግም፤ ነገ ነገን ይወልዳል፡፡ ተማም በራሱ ማሰብ አለበት፡፡ ነገ ከፍ ብሎም አከፋፋይ እንዲሆን ተመኝቻለው፡፡ የተማም ከፍታ የኔም ከፍታ ነው፤ ተማም እኔም ነው፡፡ ደግነት ለራስ ነው፡፡ ወሄነት የገጉ!!!
ቸር እንሰንብት ቸር ያሰማን ቸር ይሁነን!!!