Advertisement
እዚችው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ በአለማየው እሸቴ 'ተማር ልጄ' በሚለው ተግሣፃዊ ዘፈን ተቃኝተው ነው ያደጉት:: 'መማር ያስከብራል ሀገርን ያኮራል' የሚለው ዘፈንንም የልጅነት ላንቃቸው እስኪሠነጠቅ ዘፍነውታል:: ሆኖም ሆኖም......
ሁሉም የመንግስት ሠራተኞች ናቸው፡፡ ግን አሁን የመንግስት ሠራተኛ መሆናቸው ከመደራጀት አላገዳቸውም፡፡በየቀበሌያቸው ሄደውም ከዚህ በፊት ያልተደራጁ መሆኑን የሚገልፅ ደብዳቤ ለማፃፍም ደፋ ቀና አላሉም፡፡ ግን በቃ ራሳቸውን የN -1 በላተኞች ማዕበር በሚል ስም አደራጅተዋል፡፡ ዕድሜ ለመንግስታችን የመደራጀት መብታቸውን አልነፈጋቸውም፡፡
የN-1 በላተኞች ማዕበር አባላት ሁሉም በሀገሪቱ ውስጥ ከሚሰጡ ትምህርቶች በጣም ጥሩ ናቸው; ያበላሉ ከሚባሉት ተርታ ውስጥ ከሚሰለፈው፤ ከአንዱ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፡፡ መተው ነው እነጂ፤ አረ እንደውም ተቀፅላ ስም ሁላ አላቸው፡፡ ግና ያልጠበቁትን፡ያላሰቡትን፡ያልገመቱትን፡በቃ እንዲህ ኑሩ የተባሉትን ኑሮ የሚኖሩ ምስኪን ወጣቶች ናቸው፡፡
መስራት አለባቸው ይሰራሉ፡፡ መብላት አለባቸው ይበላሉም አይበሉምም፡፡ እናም በሀገሪቱ ውስጥ በስፋት የተንሰራፋው ኑሮ ውድነትና መንግስት ለሰራተኞች የሚከፍለው ወርሃዊ ደሞዝ (ወይም በነሱኛ የወር አበባ) ፈፅሞ ባለመመጣጠኑ የተነሳ፤ እናቋቁመው ሳይሉ፤ ማዕበሩም ተቋቁሟል ብለው ጡሩምባ ሳያስነፉ ድንገት ሁሉም በአንድነት የማዕበሩ አባላት ሆነዋል::
የዚህ በላተኛ ማዕበር አንድ መተዳደሪያ ደንብ አለው፡፡ ይኧውም ‘’ሁለት ሆኖ መመገብ አጥብቆ የተከለከለ ነው’’ የሚል፡፡ በትንሹ የማዕበሩ አባላት ሦስት መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከአምስትም መብለጥ እንደሌለባቸው ምንም እንኳ የተፃፈ ህግ ባይኖራቸውም፤ ሁሉም ግን ዘንግተውት አያውቁም፡፡ እናም መብላት ያለባቸው ሰዐት ደርሶ ሦስትም፣ አራትም፣ አምስትም ሆነው ተሰብስበው ሲቀመጡ፤ በመሀከላቸው ከነሱ በአንድ ቁጥር ያነሰ ምግብ ይቀርብላቸዋል:: ይሄ ነው እንግዲህ N-1 ማለት፡፡
እነዚህ ምስጉን የማዕበሩ አባላት አንዴም ቢሆን እንኳ ማንም ለማንም አውርቶት የማያቅ አንድ የተሸሸገ ሐቅ አላቸው፡፡ ባያወሩትም ቁርስ ለነሱ የቅንጦት ምግብ እንደሆነ የሁሉም ልብ ይረዳዋል፡፡ ቁርስ የበላ ቢኖር እንኳ ምሳ ሰዐት ላይ ዓይን ስለሚበዛበትና አበላሉ ስለሚገመገም፣ ማናቸውም ቢሆኑ ቁርስ እንደበሉ አይናገሩም፡፡
እግረ መንገዳችንን ግን ስለ ቁርስ መቅጣት ካነሳን አይቀር፣ አባላቱ ስለሚመኩበትና ትርፍ በትርፍ ስለሚያረጋቸው የፆም ወቅት እናንሳ፡፡ አቤት በዛ ወቅት ያላቸው በራስ መተማመን በፅሁፍ ለመግለፅ ስለማይመች አልፈነዋል፡፡በፆም ወቅት በሁሉም ቦታ የፆም ምግብ እንደልብ ስለሚገኝና ዋጋው ረከስ ስለሚል፤ ነሸጥ ሲያረጋቸው ሁላ ፤N-1+1 ምግብ ሁሉ ሊያዙ ይችላሉ፡፡እናም በዚህ ወቅት ሁሌም ቀጫጭን ሴቶችን ብቻ በመውደድ የሚታወቀውን እና Vegetarian በሚል ቅፅል ስም የሚጠሩትን ጓደኛቸውን በመቀላቀል ሁሉም Vegetarian ይሆናሉ፡፡
ከላይ እንደጠቀስነው እነዚህ የማዕበሩ አባላት፣ አብዛኛውን ጊዜ የተማሩት ትምህርትና የሚሰሩት ስራ ስለማይገናኝላቸው፣ በትርፍ ሰዓታቸው፣ በፊት ት/ቤት እያሉ የቀሰሙአቸውን አንዳንድ ነገሮች፣ እንዳይረሳቸውም እንደመደበሪያም በሌላ ቦታ ላይ እየተገበሯቸው፣ ባይከፈላቸውም ይፅናኑባቸዋል፡፡
እናም ለዚህ ማዕበራቸው የሚጠቀሙበት አንድ የሒሳብ ስሌት አለ፡፡ ይኧውም ‹‹እንበልና…›› ብለው ይጀምራሉ፡፡ ያው ድሮ ሲማሩ፣ ለሚታየውም ለማይታየውም፣ በእንበልና ጀምረው በእንበልና ስለሆነ የጨረሱት፣ እንበልና ሊፋታቸው የማይችል ቋንቋቸው ሆኗል፡፡ አንዳንዴ ግርም የሚለው ደግሞ፣ አስተማሪዎቻቸው ለምዶባቸው ይሁን ባለማስተዋል፣ በእጃቸው ላይ የያዙትን መጣፍ፣ ስርስ ብለው ‹‹እንበልና ይሄ መጣፍ ነው…›› ብለው ይጀምራሉ፡፡
ወደ ሒሳቡ ስንቀጥል ታዲያ፡-
እንበልና የማዕበሩ አባላት 3 ናቸው፡፡ በማስከተል በወር ውስጥ ስንት ጊዜ ሊመገቡ እንደሚችሉ እናስላ፡፡ እንደሚታወቀው አንድ ወር 30 ቀናት አሉት፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው በማዕበሩ አባላት ዘንድ ቁርስ የቅንጦት ምግብ ነው፡፡ ልክ እንደ መክሰስ ዓይነት ነገር፡፡ ስለዚህ ከወዲሁ 30 ቁርሶች ተቀነሱ ማለት ነው፡፡
ወደተቀረው ስሌት ስናመራ ደሞ፡-
እነዚህ 3 አባላት በጋራ ሆነው፣ በተከታታይ አንድ ምሳ፣ አንድ ራት እና በድጋሚ አንድ ምሳ ተመገቡ እንበል፡፡ ማዕበሩ N-1 እንደመሆኑ መጠን፣ በእያንዳንዱ ዙር የሚቀርብላቸው ምግብ ሁለት ሁለት ነው፡፡ በአጠቃላይ በ3ቱ ዙር፣ 6 ምግብ ለ3 ይመገባሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ደሞ፣ በትክክለኛው አካሄድ 9 ምግብ ሊመገቡ ሲገባ 6 በመመገባቸው፣ 3 ምግብ ተቀነሰ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ስሌት ወደ ነጠላ (አንድ ሰው) ስንቀይረው፣ አንድ ሰው በአማካይ በ3 ዙር አንድ ምግብ ያጣል ማለት ነው፡፡ እስካሁን ባለው ከተግባባን በጣም ጥሩ፡፡ እንቀጥል፡-
ታድያ ይሄን ወደ ወር እንለጥጠው፡፡ 3ቱ በላተኞች በወር ወስጥ ምግብ ለመመገብ፣ 60 ጊዜ በጠረጴዛ ዙሪያ ከበው ይቀመጣሉ፡፡ እና አንድ ሰው በ3 ዙር አንድ ምግብ ካጣ፣ በ60 ዙር ደሞ ስንት ምግብ ያጣል? ወደሚለው ስሌት እናምራ፡፡ መቼስ ‘ክሪስ ክሮስን’ የሚዘነጋው የለም፡፡ 3 እኩል ይሆናል 1 ከሆነ፣ 60 እኩል ይሆናል X ነው ብለን እንነሳ፡፤ ክሪስ ክሮስ ስናረገው፣ የX ዋጋ 60 ሲካፈል ለ3 ይሆናል፡፡ X እኩል ይሆናል 20 የሚለው ላይ ደረስን፡፡ እሺ እስካሁንም ላለው፣ እበጥ ብለናል (ስድብ አደለም፤ ነጥቦቹን በመርሳታችን እንጂ እጅግ በጣም ጥሩ ማለታችን ነበር፡፡)
ስለዚህ አንድ ሰው በአማካይ በወር ውስጥ 20 ምግብ ያጣል ማለት ነው፡፡ አሁን ደሞ ይሄንን ስሌት ወደ ቀናት እንለውጠው፡፡ ሆኖም መነሻችን ላይ ቁርስን ሰርዘን፣ አንድ ሰው በቀን 2 ጊዜ ብቻ ይመገባል ብለናል፡፡ እና በወር ውስጥ 20 ጊዜ ምግብ ማጣትን ለ2 ስናካፍለው፣ 10 ቀናት ይመጣል፡፡ አጃኢብ አትሉም፡፡
ሆኖም ስሌቱ ቢያልቅም፣ አባላቱ በዚህ ስሌት ብቻ አይረኩም፡፡ ዘዴ ሁለት ወይንም ‘ሜተድ ቱ’ በሚሉት ያረጋግጡታል፡፡ ስራ እንዳጣ ሞነክሴ ዓይነት ነገር… እንቀጥል፡፡
አንድ ሰው በወር ውስጥ 20 ምግብ ካጣና መመገብ የነበረበት 60 ከነበር፣ በወር 40 ጊዜ ብቻ ተመግቧል ማለት ነው፡፡ በቀን ሲቀየር፣ 40 ለ2 ወደ 20 ቀናት ተመግቧል ወደሚለው ያመራል፡፡ ስለዚህ የማይመገቡበትን ቀናት ለማግኘት፣ ከ30 ቀናት ላይ 20 ቀናት ሲቀነሱ፣ 10 ቀናት እንቅጩ ላይ ይመጣል፡፡ አለቀ በቃ!!!
መልመጃ፡-1
እስካሁን የተማማርነውን ሒሳብ፣ የማዕበሩ አባላት 5 እና 7 ሲሆኑ በድጋሚ አስሉት፡፡
ታዲያ አሁን ‹‹እውነትም የተማረ ወድቆ አይወድቅም፤ በወር 20 ቀናት ብቻ ያውም ቁርስን ፎርሾ እየበላ፣ በተድላና በደስታ ይኖራል፡፡›› አይሉም፡፡
በስተመጨረሻ አንድ በትርፍ ሰዓቱ በሚያነበንብ የማዕበሩ አባል ግጥምና አባባል እንለያይ፡፡ ለነገሩ የትኛው ትርፍ ሰዓት የትኛው ሙሉ ሰዓት እንደሚባል፣ መለየቱን ለናንተ ትተነዋል፡፡
‹‹ሳትማር ሳይኖራት፣ በዱቤ አስተምራ
ብድሯን ልመልስ፣ ስነሳ ለስራ
‹ልስራልሽ› ማለቴን፣ ተርጉማው በሌላ
እሷው ‹ሰራችልኝ›፣ የኔን አብጠልጥላ፡፡
እንዲህ ሆነች ጦቢያ፣ ያሁኗ አገሬ
ማማረር ተረፈኝ፣ ግሬ በመማሬ
አላማው ተረስቶ፣ ቀርቶ መመርመሬ፡፡
‹‹ሀገሬ ሰራችልኝ እንጂ ሰራሁላት አልልም፡፡››
ቀጣዩን እሱ ባይልም፣ እንበልና ቢል ኖሮ ብለን በፈቃዳችን የጨመርነው ነው፡፡ ‹‹ሆኖም እማማ ሁሌም እማማ ነች፤ ችግሩ ከሚቀያየሩት ባልተቤቶቿ እንደሆነ፣ ድሮም ልቤ ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ እና በእናት ቂም አሊ-ዝም፡፡ አሁንም ለእማማ እውነተኛውን ስራ ከመስራት አልቦዝንም፡፡››
አበቃን!!! ቸር ያሰማን ቸር ይግጠመን ቸር ይሁነን!