Advertisement
መኩሪያ እባላለሁ። በጣም ሲሪየስ ሰው ነኝ። ነበርኩ ወይንም አላቅም። ስሜ እንደሚያመለክተው ቤተሰቦቼ ሲጀምር መኩሪያ ብለው ጠርተውኛል። አስተውሎ ላየው ትልቅ ጫና ያለው ስም ነው። ማስጠንቀቂያም ያዘለ ይመስላል። ይሄን ‘ኮራ’ የሚለውን ቃል ይዘው ሁለት ነገር ማለት ይችሉ ነበር። ‘ኮራንብህ’:— ለራሳቸው አድልተው እኔን ስም መንሳት ይሆንባቸው ነበር። ‘ኩራባቸው’:— ብለውም ሊመክሩኝ ይችሉ ነበር። ግን ቤተሰቦቼ እንደዛ አላደረጉም። ዝም ብለው መኩሪያ ብለው አላፊነት አስታጠቁኝ። ደሞም መኩሪያቸው ነኝ። በስሜም እጅግ እኮራለሁ። እንደውም መኩሪያ የሆነ ስም ነው ያለኝ።
ከልጅነት እስከ ዕውቀት ህይወቴን የመራሁት ቀጥ ባለ መንገድ ነው። በፊት የቤተሰቦቼ ህግ ነበረኝ። ሳድግ የራሴም ሆኖ አደገ። ቀጥሎ የማህበረሰቡም ተጨማመረና… ሳላውቀው የራሴም አርጌ አመንኩት። ከማምንበት ነገር ዝንፍ የማልል ግን ያመንኩበትን ለምን እንዳመንኩት የማላውቅም የማልጠይቅም ግትር ሰው ነኝ። አሁን አሁን ነው እንደዚህ ብዬ እንኳን ራሴን መግለፅ የጀመርኩት። በፊትማ ሲጀምር መች አስቤው አውቅና ነው። ብቻ እድሜ ለሱ።
በዕቅድ መመራት ጥሩ ነው። ምንም ክፋት የለውም። እናም በዕቅዴ የማሰፍራቸውን አብዛኛዎቹን ነገሮች እያሳካሁ ነው እዚህ የደረስኩት። ግን ቁጭ ብዬ ሳስበው የአንዱም ግትርነቴ መገለጫ ይሄ ይመስለኛል። የኔን ብቻ መኖር። ለሰዎች አለመኖር ራስ ወዳድነቴን የወለደው የማያወላዳው እቅዴ እንደሆነ እየተሰማኝ ነው። ማመጣጠን የሚባል ነገር እንዳለ ያወኩት ዘግይቼ ነው። በራሴው እቅድ ራሴን እስረኛ አርጌ ብዙ አመት ከኖርኩ በኋላ። ብቻ እድሜ ለሱ።
ሁሉ ነገሬ ቅርፅ አለው። አለባበሴ እንኳን ወጥ ነው። የስራውን አለም ከተቀላቀልኩ ጀምሮ ያለፉትን ስምንት አመታት ሁሌም የምለብሰው ሱፍ ብቻ ነው። 8 ዓመት ሙሉ በከረባት መታነቅ ከባድ ይመስለኛል። አሁን ነው ይሄ የተገለጠልኝ። እድሜ ለታፈሰ እሱ ነው አይኔን የገለጠው።
ታፈሰ አብሮ አደጌ ነው። የልጅነት ጓደኛዬ ስለሆነና አሁንም ሰፈራችን አንድ ስለሆነ እንጂ ታፈሰ ባሁን ማንነቴ ጓደኛዬ ሊሆን የሚችል ሰው አልነበረም። ታፌ ሲበዛ ግዴለሽ ሰው ነው። ወይንም ይመስለኝ ነበር። ዝም ብሎ የሚኖር ለምንም ነገር የማይጨነቅ ሰው ነው፣ ከሩቅ ሳየው። ግን ልጅ እያለንም ቅርፁ ይለያይ እንጂ ኑሮው ይኸው ነበር። ታድያ የሚገርመኝ ደስተኛም ብቻ ሳይሆን ስኬታማም ነበር።
ብዙ ጊዜ ከመሸና ሰፈር አካባቢ ካልሆነ በቀር እሱን ማግኘት አልፈልግም። በቃ አለባበሱ ከኔ ጋር አይሄድም። በርግጥ ልብሱ ሁሌም ንፁህ ነው። ግን ግድየለሽ ሰው መሆኑን በሚገባ ያሳብቃል። እውነት ለመናገር በአለባበሱ አፍር ነበር። ደሞም እነግረዋለሁ። ስቆ ዝም ይለኛል። አንድ ቀን <<ምንህም እኮ የተማረ ሰው አይመስልም>> ስለው እየሳቀ <<የሚመሰለው እኮ ያልሆኑትን ነው። ስለዚህ እኔ የሆንኩትን መምሰል አልፈልግም። ደሞ ብላቹ ብላቹ ለተማረም አለባበስ ፎርሙላ አወጣቹለት?>> ብሎኝ ጥሎኝ ሄደ። ተቀይሞኝ አልነበረም። አንድ ጉዳይ ካልጣመው ዝምብሎ ጥሎ ይሄዳል። ከልጅነቱ ጀምሮ የማልወድለት ባህሪው ነው።
ከወር በፊት ጠዋት ወደስራ ስሄድ (በነሱ በር ጋር ነው የማልፈው) በራቸው ላይ ድንጋይ ላይ ቁጭ ብሏል። ሳየው ተሸማቀኩ። ለሱ እኔ አፈርኩ። ስራውን እንደለቀቀ ከሰማው እጅግ ቆይቼ ነበር። እንዳላየው ላልፍ ስል ያጣመረውን እግሩን ፈታና አንድ እግር ነጠላ ጫማውን ይዞ ተነሳ።
"ሱፉን ግጥም አርጎ ፀጉሩን ተከርክሞ" አለና ሳቀ። ሳቁ ይጋባል። አብሬው ፈገግ አልኩ። ላለፉት ስምንት አመታት ብዙ አልተገናኘንም ነበር። እውነት ለመናገር በውስጤ ስንቀው ኖሬያለሁ። ያን ቀን ግን የማላውቀው ስሜት ተሰማኝ። ከኔ ይልቅ ታፈሰ ልክ ነው የሚል ስሜት ተሰማኝ። እዛው የቆምኩበት ስቀየር ታወቀኝ። ወደ ውስጤ አዲስ ነገር ሲገባ አሁንም ድረስ ስሜቱ ይሰማኛል። ከመኪናዬ ወረድኩና በደንብ አቅፌ ሰላም አልኩት። ለመጀመሪያ ጊዜ እሱ ቆሞ እያለ፣ተቀምጦበት የነበረው ድንጋይ ላይ ሄጄ ዘፍ ማለት አማረኝ።
ለምን እንደሆነ በውል ሳይገባኝ ጆሮዬንም ልቤንም ልሰጠው ፈለኩ። ብዙ ጊዜ የሚያወራው ቀልድ እና ቧልት ነው። ሆኖም ምንም ቢያወራ ልሰማው ፈቀድኩ። በተለይ አልፎ አልፎ እየሳቀ የሚያወራቸውን ነገሮች ከኔ ሁሌ ከምኮሳተረው ቁምነገር ያዘሉ መሰለኝ። ደስ ሲለኝ ታወቀኝ። ልጅ እያለን ከሱ ጋር ሆንኩ ማለት ሁሉ ነገሬ ሳቀ ማለት ነበር። አሁንም ያ ስሜት ተሰማኝ። ከረዥም አመታት በኋላ…
<<ምን እያረክ ነው በጠዋቱ?>> አልኩት። ፈገግ እንዳልኩ ነበር።
<<ፀሃይ እየሞኩ… ህፃን እያለን ቤተሰቦቻችን እያገላበጡ ፀሃይ ያስመቱን ነበር። ትልቅ ስንሆን ግን ፀሃይ እንደማያስፈልገን ይሰማናል መሰለኝ… እንደውም ሳንሸሽ ሁሉ አንቀርም። ብቻ እንደእኔ ስራ ፈት የሆነና ጠዋት ከእንቅልፉ ፀሃይ ለመሞቅ የሚነሳ ሰው ነው የፀሃይ ጥቅም የሚገባው። ወደ ስራ ነው?>> አለኝና መልሶ ድንጋዩ ላይ ቁጭ አለ።
ወዲያውም <<አዲስ ሱፍ ነው?>> ብሎ ጠየቀኝ።
<<አዎ>> ብዬው ቀጣዩን መጠባበቅ ጀመርኩ።
<<አይሰለችህም ግን? ዝምብዬ ሳስበው ሱፍ አበባው ራሱ የሚያወራበት አፍ አጥቶ እንጂ ሁሌ ሱፍ መሆን የሚደብረው ይመስለኛል። እንደውም በሰሊጥና በኑግ እንደሚቀና በሚስጥር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ አሉ … ትንሽ ብቻ ‘ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ’ መባሉ ይከነክነዋል እንጂ… በል ንካው ይረፍድብሃል። አለቃህ እንዳይቆጣህ>> ሲለኝ ምን እንደሆነ ባላቅም በጣም ጮክ ብዬ ሳኩ። አሁን ሳስበው ቀድሜ መሳቅ ፈልጌ እንደነበር እገምታለሁ።
<<ብቻ ዛሬ ላገኝህ አፈልጋለው። ዛሬህን ለማንም እንዳታሲዘው!>> ስለው በጣም ሳቅ።
<<አረ ሁሌዬንም ከፈለከው ለማንም አላሲዘውም!>> ሲለኝ አገላለፄ እንዳሳቀው ገባኝ። እኔ እንደዚህ ነኝ። የሰው ጊዜ ማባከን ከመስረቅ ለይቼ አላየውም። አወራሬ ግን ሁሌም ፎርማል ነገር እንዳለው ይገባኛል።
<<ማለቴ… ያው ምንድነው ዛሬ ፕሮግራምህ ብዬ ነው>>
ከኋላው ኪሱ ወረቀት አወጣና አሳየኝ። ነጭ ወረቀት ነው።
<<አየህ ምንም አልተፃፈበትም። ዛሬ ቀኑን እንደቀኑ ነው የምኖረው። አዋዋሌ ተፈጥሮአዊ ነው። ሰዋዊ ፕሮግራም የለኝም። በፈለከኝ ሰዓት እነሆኝ ጓደኛህ!>> አለና ተነስቶ ቲያትር እንደሚሰሩ ሰዎች እግሩን አጣምሮ አጎነበሰና እየሳቀ ቁጭ አለ።
ትንሽ ስለ ለውጥ ምን አንደሚያስብ አወራሁትና መሄድ ስለነበረብኝ ተሰናብቼው ተንቀሳቀስኩ። መሃል ላይ ያለው ነገር ግን ከአዕምሮዬ አልጠፋም። ምንድነው ተፈጥሮአዊ አዋዋል? ሰዋዊውስ? … በመጨራሻም ስለለውጥ ያለኝም አዕምሮዬ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መከሰቱ ገረመኝ።
<<ሰዎች አይለወጡም በሚለው ድምዳሜ አላምንም። ሰዎች ግን ለመለወጥ በጣም ይቸገራሉ። ባይ ዲፎልት ‘እኔ ጭንቅላቴ ነኝ’ ብለው ነው የሚያምኑት። ይሄ ደሞ ከልጅነት እስከ ዕውቀት በግል ቴፓቸው ውስጥ ሲቀዱ የነበረውን ነገር መልሶ መላልሶ ከማዳመጥ ውጪ ለሌላ እውነት ዝግጁ አያረጋቸውም። ያለም አይመስላቸው። ጥቂቶች ‘እኔ መንፈሴ ነኝ’ ብለው ያመኑ ናቸው ተለውጠው አለማችንንም እየለወጡ ያሉት። እና መለወጥ ከፈለክ ከልብህ ከሆነ ትለወጣለህ>> ነበር ያለኝ።
ይሄንን እያሰብኩ ነው ቢሮዬ የደረስኩት። እውነት ነው ኑሮዬ ሰልችቶኛል። መሰልቸቱን ያወኩት ደስታ እየሰጠኝ ስላልሆነ ነው። ደስታን ፍለጋ ያላረኩት ነገር የለም። በገንዘብ የሚገዛ ደስታዬ ጣሪያውን ስላለፈ ደስታ እየሰጠኝ አይደለም። እኔ በቃ በተበጀልኝና ባበጀሁት ቦይ ዝምብዬ የምፈስ ሰው ነኝ። ለውጥ እፈልጋለሁ። ደስታ ምን እንደሆነ እንዲገባኝ እፈልጋለሁ። ከዛ እንዴት እንደሚገኝ ለማወቅ እታትራለሁ። ለዚህም ታፈሰ ያስፈልገኛል። ታፌ አብሮ አደጌ!!!
★★★ ታፈሰ ★★★
ታፈሰ። ስሜ አይገርምም? ከየት ነው ግን ያፈሱኝ? ይመቻቸው በቃ እንግዲህ ዝም ብሎ መታፈስ ነው። ለማንኛውም ስም መጠሪያ ነው… በቅርብ ሆኖ እንትና፣ አባቱ፣ ወንድም፣ እከሌ ላለኝ ሁሉ ብዞርም እንደታፈሰ ግን አልደነግጥም።
ስለራሴ ማውራት አልወድም። ግን አንድ መኩሪያ የሚባል ሱሪ ሳያረግ ጀምሮ የማቀው አብሮ አደግ ጓደኛ አለኝ። እሱ ነው የተጫነኝ። መኩ በድሮ ሂሳብ ጓደኛዬ ሆነ እንጂ ባሁን ማንነቱ ጭራሽ ለጓደኝነት አይደለም ለማወቅ እንኳ የማልሻው ሰው ነው። ብቻ ገጣጠመኝ አንዴ አገናኝቶናልና እስካሁን አለን።
አለባበሱ፣ ድርጊቱ ሁሉ ነገሩ ፎርሙላ አለው። እኔ ደሞ ፍፁም ተቃራኒው ነኝ። ለምሳሌ ማህበረሰቡ ድንገት እኔን ሱፍ ለብሼ ቢያየኝ <<ታፌ ጆባ ሆንክ እንዴ?>> ብሎኝ ይስቃል። ከዛ እኔም አብሬው እስቃለሁ። ፋይል ይዘጋል። የፈለኩትን ነገር የማረግ መብቴን ማንም አይነፍገኝምም አይገርመውምም። ይሄ እንዲሆን እንግዲህ ብዙ ዋጋ ከፍያለሁ። ሆኖም ህብረተሰቡ እግዜር ይስጠው የልፋቴን እየከፈለኝ ነው።
ለመኩሪያ ግን ይሄ አይሰራም። ለምሳሌ መኩን ያለ ሱፍ ስራ ሲሄድ ብናየው፣ መጀመሪያ ራሳችንን የምንጠይቀው ጤንነቱን ነው። ይሄን ያህል ውስጣችን ተቀርፅዋል። የመኩዬን ህይወት እሱም እኛም ስለለመድነው <ሊቀያየር የማይችል> በሚል አሳትመነዋል። ድንገት ሳት ብሎት ጥቃቅን ለውጦች እንኳ ካሳየ፣ ወደቀደመው ማንነቱ እንዲመለስ በፍቅር እንጫነዋለን። እሱም ታዛዥ ነው። መኩ እንደ አርቲስቶቻችን የሕዝብ ነው። የራሱ አይደለም።
ድንገት ማታ ቤት መጣና አስጠራኝ። ቀደም ብሎ እፈልግሃለሁ ምናምን ብሎኝ ነበር…
<<ምን እያረክ ነው?>> አለኝ። ድራማ እያየሁ ነበር፣ ነገርኩት። ከዚህ በፊት ከሱ የማልገምተው አይነት ጠረን ለአፍንጫዬ ደረሰኝ። እኔ እኮ በልጅነታችን ዘመን እንደዘፈንለት አውሮፕላን ነጂ ነበር የሚመስለኝ። ያ እንደውም…
"አውሮፕላን ነጂ አይጠጣም ሲጃራ…አይጠጣም ሲጃራ
አፉ የሚሸተው ሜንታ ከረሜላ… ሜንታ ከረሜላ"
ብለን በሚያስደምም ዜማ ያንጎራጎርንለት… እሱ አውሮፕላን ነጂ ግን አለ ይሆን?……… ብቻ መኩነት ዛሬ አሁን አፉ ሜንት ሜንት ሸተተኝ። የሲጋራውም ሽታ የቄንጠኛ ሰው ነው የሚመስለው… ጨዋ ሰው ሲበላሽ ቅራሪ የለውም ብዬ ልገስጠው ነበር ተውኩት።
<<በናትህ በህይወቴ ምንም ትርጉም የሌለው ስራ መስራት አስቤያለሁ… አስተምረኝ!!!>> ሲለኝ ድንገት የሳኩት ሳቅ ብዙ የተኙ ሰዎችን ቀስቅሶ ይሆናል። እየተሰደብኩ የምስቅ ብቸኛ ሰው ሳልሆን አልቀርም። እንደውም ደስ ነው ያለኝ። ሌሎች በሩቁ የሚሉኝን እሱ በቅርቡ ነው ያረዳኝ። ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል፤ አፈነዳው እኮ!
<<በህይወትህ ትርጉም ያለው ጥያቄ የጠየከው እንደውም ዛሬ ይመስለኛል>> ስለው ተንፈስ አለ። እሱም ሳቄ አስደንግጦት ነበር።
<<ሊሆን ይችላል! አሁን ቤት መግባት አለብኝ። ከቻልክ ግን የአንድ ቀን ዉሎህ ምን እንደሚመስል መዝግበህ ስጠኝ>> ብሎኝ እብስ አለ። ዛሬ ምን ቢጠጣ ነው እያልኩ ወደቤቴ ገባው። ድራማውን ስላስመለጠኝ አልተቀየምኩትም። የሚደገምበትን ቀን አቀዋለሁ።
★★★
በማግስቱ ግን ከእንቅልፌ ስነቃ የሆነ ሸክም አሸክሞኝ እንደሄደ ተረዳሁ። ሰዓቴን አየሁት 4 ከ 10 ይላል። ሌላ ጊዜ ሶስትም አራትም ሰባት ሰዓትም ሲል ልነቃ እችላለው። ባይሎጂካል ክሎኬ ሳይበላሽ አይቀርም። ቆይ ሴኮ ሰዓት የሚሰሩ ጋር እወስደዋለሁ ብዬ ራሴን ፎገርኩት። ራሴን ስፎግረው ደስ ይለኛል። ከአልጋዬ ፈንጠር ብዬ ተነሳሁ።
ቁርሴን በላሁና ወንበር ይዤ ፀሃይ ልሞቅ ወጣሁ። ብርድ ብርድ ተሰምቶኝ ነበርና ብዬ አልፎግርም። የምሄድበት ከሌለኝ ሁሌም እንዲሁ ነው የማደርገው። አንዴ ጠብሻት የነበረች ልጅ <<እኔ እኮ እንዳንተ ከእንቅልፌ ፀሃይ ልሞቅ አልነሳም… ብዙ ስራ ያለብኝ ሰው ነኝ!>> ብላ አጥንት የሚሰብር ንግግር ተናግራኝ ነው የተፋታነው። ሰንጋተራ አካባቢ ግሩም መረቅ ቤት ነበር፣ በዛ ነው አጥንቴን የጠገንኩት።
ፀሃይ የምሞቅበት ቦታ ላይ አንድ እድሜ ጠገብ መፋቂያ አለ። እና ሌሎች ጠዋት ተነስተው እንደሚያረጉት እኔም ጥርሴን እፍቃለሁ። አንድ ደራሲ "ጥርሴ ልብስ አይደለምና በሳሙና አላጥበውም… አርፌ በእንጨት መፋቂያ ነው የምሸከሽከው!" ብሎ ፅፏል። እኔ ክርክር ስለማልወድ ስለ ሳሙናዎች አያገባኝም… ሆኖም እኔም በእንጨት ነው የምሸከሽከው። በዛውም ንቦች፣ ተርቦች እያዜሙ መፋቂያው ጫፍ ላይ ያሉ ነጫጭ አበባዎች ላይ ሲሻፍዱ በአግራሞት እቃኛለሁ። የተፈጥሮ ነገሮችን ሳይ ውስጤን አንዳች ነገር ያሞቀዋል። ትርጉም ያለው ነገር የሰራው የሚመስለኝ ያኔ ያኔ ነው። ይቺ እጅግግግ ጥንጧ ወፍ መታ መፋቂያው ጫፍ ላይ ለአበባው ስትደንስ ካየሁማ… አበቃ ቀኔ ሰመረ ማለት ነው። ብዙ ጊዜ ግን አትገጥመኝም።
ፀሃይ እየሞኩ፣ ጥርሴን እየፋኩ፣ መፋቂያውን ንቦችን ተርቦችን እያየሁ በውስጤ መኩሪያ ስላነሳቸው አንዳንድ ሃሳቦች እያሰላሰልኩ ቆየሁ… ለምሳሌ መኩሪያ <<አንተ ልክ ሳትሆን አትቀርም>> ያለኝ ነገር ልክ አይደለም። እኔ ከምን አንፃር ነው ልክ የሆንኩት? ሰዎች ለምን ህይወታቸውን በሰው ህይወት ልክ እንደሚያርሙ አይገባኝም! … እኔ ተሰርቼ ያላለኩ፣ ብዙ ስህተት ያለብኝ ሰው ነኝ። የኔ የጎደለኝን በራሴ እያሻሻልኩ፣ ከመኩሪያም ልክ ነው ብዬ የማስበውን ራሴን እያየሁበትም እየቀየርኩበትም እኖራለሁ እንጂ… ቁጭ ተብሎ በደፈናው እንትና ልክ እኔ ስህተት እንዴት ይባላል?… ማንም ሙሉ ልክ ማንም ሙሉ ስህተት የለም። በርግጥ በብዙ ልክ የሆነ ሊኖር ይችላል…
ይሄን መሰል ሃሳቦች አወጣሁ አወረድኩና ሲበቃኝ ወንበሬን ይዤ ወደቤት ገባሁ። ከሰአት ቀውጢ ሽቀላ አለብኝ። ብዙ ጊዜ ስራ ስለማልሰራ የምሰራው ስራ ሁሉ በጥራት ነው። ለዛም የምጠይቀውም ዋጋ ውድ ነው። ጥራቴ ማስታወቂያዬ ስለሆነ ስራ ፈልጎኝ ቤቴ መጥቶ ተሰርቶ ይመለሳል። አንድ ስድስት ዙር ወጥሬ ከሰራሁ ድሮ ተቀጥሬ ስሰራ የማገኘውን የአመት ደሞዝ እዘጋለሁ። በመጠን እና በስሱ ስለምኖር ሁሌም በትርፍ ነው የምኖረው። ያም ሌላውን ህይወቴን ለመኖር በቂ ጊዜ ሰጥቶኛል። በጊዜዬ ቀልጄ አላውቅም። ስሜ ግን በሌሎች ዘንድ ስራ ፈቱ ነው። ይሄ ደሞ ያስቀኛል።
ከሽቀላ ስመለስ የጎረቤታችን ጋሽ ሃሰን ዲሽ ተበላሽቷል… እሱን አስተካክዬ የምወደውን ምርቃት እጄን ዘርግቼ አፋፍሳለሁ። እንግዲህ የዛሬ አንዱ ቀን ውሎዬ ይሄን መሳይ ነው። ለመኩሪያ ያጥግበው አያጥግበው አላውቅም። ነገ ደግሞ ሌላ ቀን ነው። የነገንም ቀጥል ካለኝ ምን አደርጋለሁ… እንዳመጣብኝ ማስታወሻ ደብተር ገዝቼ "ዲር መኩሪያ… " ብዬ መጀመሬ ነው።